ኢትዮጵያ የብዝሃ ቱሪዝም መገኛ ነች። ለአገር ገፅታ ግንባታ፣ ለምጣኔ ሀብት መጎልበት፣ ለጋራ እሴት መገለጫ ከፍተኛ አበርክቶ ያላቸው የባህል፣ የተፈጥሮ፣ የታሪክ የመካነ ቅርስ እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም ሀብቶችን በዚህች “ምድረ ቀደምት” የሚል ስያሜ በተሰጣት አገር ላይ እንደ ልብ ማግኘት ይቻላል፡፡ እነዚህን ሁሉ በረከቶች ትርጉም ወዳለው ጠቀሜታ መቀየር፣ ለቀሪው ዓለምም ሆነ ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች ማስተዋወቅ፣ አገርና ትውልድን በሚጠቅም መልኩ ምጣኔ ሀብቱን እንዲደግፍ ፈር ማስያዝ ላይ ግን ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ ባለሙያዎች ይናገራሉ። መረጃዎችና ጥናቶችም ኢትዮጵያ በተሰጣት የቱሪዝም በረከት ልክ ተጠቃሚ እንዳልሆነች ያመለክታሉ።
የአገራችን የቱሪዝም ሀብቶች በሚፈለገው ልክ ለምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች ጥቅሞች እንዳይውሉ ካደረጉት መካከል ቀዳሚ የሆነው ምክንያት ሀብቶቹ በዓለም መድረክ ላይ እንዲተዋወቁ፣ እውቅና እንዲያገኙና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚካሄደው የገበያና ፕሮሞሽን ስራ በቂ አለመሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ። ዓለም አቀፍ መድረኮችን አቅም በፈቀደ መልኩ መጠቀምና ለዚያም ሀብቶቹን የሚታዩበትን እድል (visible) ማስፋት እንደሚያስፈልግ ይገለፃሉ።
የቱሪዝም ዘርፉን በቀዳሚነት የሚመራው የቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይህንን ችግር በመለየት መፍትሄ ለመስጠት እየሰራ እንደሆነ ይገለፃል። በተለይ መንግሥት መስኩን ከዋና ዋና የኢኮኖሚ አመንጪ ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ በመውሰድ በትኩረት ለመስራት መሰናዳቱን አስታውቆ እየሰራ ይገኛል። በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የቱሪዝም የመስህብ ሀብቶችን የማስተዋወቅ እና የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸውን የሚያሳዩ ጥረቶችም እንዲሁ ይስተዋላሉ።
ሰሞኑንም የቱሪዝም ሚኒስቴር አመራሮች በተለያዩ አህጉርና ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ሁነቶች ላይ ተሳትፈዋል፤ በዚህም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች አስተዋውቀዋል፤ ልምድ ተለዋውጠዋል፡፡ ከእነዚህ አመራሮች መካከል የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ይገኙበታል። እርሳቸው በደቡብ አፍሪካ “የቱሪዝም ልምድ ልውውጥና ቀጣናዊ ትስስር”ን ማጠናከርን ታሳቢ ባደረገና 13 አገራትን ባሳተፈ መድረክ ላይ ተገኝተው የኢትዮጵያን ተሞክሮ ከማጋራታቸው ባሻገር ከደቡብ አፍሪካ ጋርም የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በበርሊን የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የተሳተፉበት የአይቲቢ ኤግዚቢሽንና በሳውዲ አረቢያ ኢትዮጵያ በጮቄ ተራራና ሙሉ ኢኮ ሎጅ መልከዓ ምድር የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ በሚል ሽልማት የተቀበለችበት መድረክን አስመልክተን ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰላማዊት ዳዊትን አነጋግረን የሚከተለውን ዳሰሳ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት፤ 13 አገራት የተሳተፉበት የደቡብ አፍሪካ ኬፕታውኑ መድረክ ዓላማ በዋናነት አገራት ያላቸውን የቱሪዝም አቅምና አፈፃፀም የሚያቀርቡበትና ልምድ የሚለዋወጡበት ነው፤ ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ በማቅረብም ለዚያ የተቀመጠውን መፍትሄ ሌሎች አገራትም እንዲወስዱት ታሳቢ ያደረገም ነው።
በተለይ የኮቪድ ወረርሽኝን ተከትሎ ብዙ የአፍሪካ አገራት መጎዳታቸውን የሚናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ መድረኩ ሀገሮች ይህንን ችግር በምን መልኩ እንዳለፉና ምርጥ ተሞክሮዎችን የተለዋወጡበት እንደሆነም ገልፀዋል። በቱሪዝም ዘርፉ ያለው የኢኮኖሚ መነቃቃት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝም የተወያዩበት መሆኑን ያስረዳሉ።
በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከተማም ሆነ በገጠር ያሳካቻቸውን የቱሪዝም ልማት ስራዎችና የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን የማልማት (የገበታ ለሃገር፣ ገበታ ለሸገር፣ እና የገበታ ለትውልድ) ስኬት በመድረኩ ላይ እንደ ምርጥ ተሞክሮ ለተሳታፊ አገራት ማካፈሏን ተናግረዋል። በተለይ የልማት ስራዎችን የሚደግፍ መዋእለ ነዋይ ከግል ዘርፉ፣ ከማህበረሰቡ እንዲሁም አቅም ካላቸው አካላት የተሰባሰበበትን መንገድ፣ በማህበረሰብ አቀፍ ሎጅ መልከዓምድራቸውንና ያላቸውን የመስህብ ስራዎች በባህላዊ ሥርዓት ጠብቀው ለቱሪዝም መስህብነት ተመራጭ ያደረጉ እንደ ወንጪ ደንዲና ጮቄ ተራራ አይነት ስፍራዎችን እና ሌሎችም የዘርፉ ስኬቶችን እንደ ልምድ ማጋራት እንደተቻለ ገልፀዋል። መንግሥት የቱሪዝም ዘርፍን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ዋና የምጣኔ ሀብት መስክ ቆጥሮ ልዩ ትኩረት እንደሰጠው ማስረዳታቸውንም አስረድተዋለ።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፏ በኩል መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች በመድረኩ አንስታለች፡፡ ከተሳተፉት 13 አገራት የፀጥታና ሰላም ችግር ያለባቸው ቢኖሩም፣ የአገር ውስጥ ሆነ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን የሚያስተናግዱ መሆናቸውና ዘርፉ እክል እንዳልገጠመው ከመድረኩ መገንዘባቸው ተችሏል።
ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ውስጥ ቱሪዝሙን ተጠቅሞ እዚህም እዚያም የሚነሱ የፀጥታ ስጋቶችን መቀነስና ለጎብኚዎች ምቹ የሆነ ከባቢያዊ ሁኔታ መፍጠር የሚቻልበትን ልምድ ከአገራቱ ማግኘት የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
“በልምድ ልውውጡ ላይ ምርጥ ተሞክሮን ከመለዋወጥና ከመማማር ባሻገር ከደቡብ አፍሪካ ጋር ተጨማሪ ውይይቶችንና ስምምነቶችን የማድረግ ፍላጎት ነበረን” የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በዋናነት በቱሪዝም ዘርፍ ከአገሪቱ ጋር በቅንጅት ለመስራት ፍላጎት እንዳለም ይገልፃሉ። ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በደቡብ አፍሪካ በነበራቸው ይፋዊ ጉብኝት ላይም በቀዳሚነት ከተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ውስጥ “በቱሪዝም ዘርፍ በጋራና በትብብር እንሰራለን” የሚል ሃሳብ እንደሰፈረበት ጠቅሰው፣ ይህንን ወደ ተግባር በመለወጡ ስራ ላይ ከልምድ ልውውጥ መድረኩ ጎን ለጎን ውይይት መደረጉን ይናገራሉ።
በዚህም ሁለቱ አገራት እርስ በእርስ የሚማማሩበትና የተለያዩ ድጋፎችን የሚለዋወጡበት ማእቀፍ ወደ ስራ ለማስገባት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸው፣ መድረኩንም ለዚህ ተጨማሪ ዓላማ ለማዋል እንደተጠቀሙበት ተናግረዋል። በተለይ ሁለቱም አገራት የቱሪዝም መስህቦቻቸውን በጋራ የሚያስተዋውቁበት እድል ለመፍጠር እንደሚሰሩ፤ ደቡብ አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ እንዲሁም ባላት የመገናኛ ብዙሃን አቅም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች ተደራሽ እንዲሆን ለማስቻል ከሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ዳይሬክተር ጀነራል ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አሳውቀዋል።
ከዳይሬክተር ጀነራሉ ጋር ከዚህ ቀደም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋዊ ጉብኝት የተደረሰውን የመግባቢያ ስምምነት መሬት ላይ ለማውረድ የቴክኒክ ኮሚቴ በጋራ አቋቁሞ ወደ ስራ ለመግባት መጋቢት 23 ጀምሮ የልኡክ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ገልጸዋል።
“እንደ አገር ሁለት ዓላማዎችን ይዘን ነው በመድረኩ ላይ የተገኘነው” ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታዋ የመጀመሪያው ልምድ መለዋወጥ ሲሆን ሁለተኛው፣ ከአዘጋጅ አገሯ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት መፈፀም መሆኑን ተናግረው ሁለቱንም ማሳካት እንደተቻለ ይናገራሉ።
“በቱሪዝም ዘርፍ ቀጣናዊ ትስስር መፍጠር በአገራቱ መካከል በሚኖረው ውድድር ላይ ምን አይነት ተፅእኖ ሊያሳድር ይችላል” የሚል ጥያቄ የዝግጅት ክፍላችን አንስቶ ሚኒስትር ዴኤታዋ ሲመልሱ፤ ሁሉም ሀገሮች በዘርፉ የተሰጣቸው ፀጋና የቱሪዝም ሀብት የተለያየ መሆኑን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች፣ መልከዓምድር፣ ባህላዊና አርኪዮሎጂካል ሀብቶች ከደቡብ አፍሪካም ይሁን ከሌሎች አገራት የተለየ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የገበያ ሽሚያም ሆነ በጋራ ለመስራት እንቅፋት የሚሆን ሁኔታ እንደሌለ ገልፀዋል። ሌሎች አገራት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሃብት ለዜጎቻቸው ቢያስተዋውቁም ሆነ ተመሳሳዩን ኢትዮጵያ ብታደርግ የተሻለ ውጤት በመስኩ ላይ ከማስመዝገብ ውጪ ምንም አይነት ጉዳት እንደማይኖረው ይገልፃሉ።
በዘርፉ በተለይ ቀጣናዊና ትስስር ከጎረቤት አገሮች ጋር ማድረግ አያሌ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ለምሳሌ ያህል ጅቡቲን ለመጎብኘት የሚመጣ የቀሪው ዓለም ቱሪስት እግረ መንገዱን አፋር ላይ ያሉትን የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲመለከት በጋራ ቢሰራና እድሉ ቢመቻች ለሁለቱም አገራት የተሻለ አማራጭና ገበያ የሚከፍት እንደሆነ ይናገራሉ። ይህንን መሰል ልምድ በኬንያም፣ በኤርትራም ሆነ በሌሎች የቀጣናው አገራት ማስፋትና በጋራ አህጉሪቱን አስተዋውቆ ከዚያ እድል ተጠቃሚ መሆን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በደቡብ አፍሪካ ከተካሄደው የቱሪዝም ምርጥ ተሞክሮ መድረክ ባሻገር የቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባላቸው ሁለት ተጨማሪ መድረኮች ላይ መካፈሉን የሚናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ የመጀመሪያው በሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ አማካኝነት “አይ ቲቢ” አውደ ርእይ ሲሆን ሁለተኛው የጮቄ ተራራና ሙሉ ኢኮ ሎጅ “የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር” ተብሎ መሸለሙን አስመልክቶ በሳውዲአረቢያ የተካሄደ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከ30 በላይ ባለድርሻ አካላትን (የቱር ኦፕሬተሮች፣ የተወሰኑ ክልሎችን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን፣ ኢንተርናሽናል ሆቴሎችን) ይዛ በጀርመን በርሊን በተካሄደው የአይ ቲቢ ኤግዚቢሽን ተካፍላለች፡፡ መድረኩ በጀርመን በየዓመቱ የሚካሄድና የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችንና ምርቶችን ለማስተዋወቅ ዓላማ ያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። በርካታ ካምፓኒዎችና ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ዘርፍ አንቀሳቃሾች የኢትዮጵያ አቅም ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመድረኩ ከመመልከታቸውም ባሻገር አብረው የሚሰሩበት ስምምነት ላይ የተደረሰበት መልካም አጋጣሚ መፈጠሩንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ይገልፃሉ።
በበርሊኑ አውደ ርእይ በሚኒስትሯ መሪነት የተሳተፈው ልኡክ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ግጭትና የኮቪድ ተፅእኖዎችን ኢትዮጵያ እንደተሻገረቻቸውና ሁሉም መዳረሻዎች ለጎብኚዎች ክፍት መሆናቸውን ለማስተዋወቅ እድል ያገኙበት እንደነበር ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልፀዋል። ቦታው ላይ በተንቀሳቃሽ ምስል፣ በቡና አፈላል ዝግጅት፣ በፅሁፍና በልዩ ልዩ የግንኙነት አግባቦች ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ስኬት የተገኘበትና ውጤታማ መድረክ እንደነበር አስረድተዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፤ የሳውዲ አረቢያው መድረክ የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ‘UNWTO’ ያዘጋጀው ነው፡፡ መድረኩ በየዓመቱ የሚደረግ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም አባል አገር እንደመሆኗ በመድረኩ ተሳትፋለች።
ድርጅቱ የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መድረክ እንደሚያወዳድርና እንደሚሸልም ገልፀው፣ ኢትዮጵያ በተንቀሳቃሽ ምስል የጮቄ ተራራ መልከአምድርና ሙሉ የማህበረሰብ አቀፍ ኢኮ ሎጅን ጨምሮ ሶስት የቱሪዝም መዳረሻ መንደሮችን ዶክመንት በማዘጋጀት ከመድረኩ ቀደም ብሎ መላኳን ተናግረዋል። የጮቄ ተራራና ማህበረሰብ አቀፍ ሎጂ ሽልማቱን ማሸነፉን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ በመድረኩ ላይ ሽልማቱን መቀበሏን ተናግረዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ልኡኩን የወከሉት አመራሮች ከሳውዲ አረቢያ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታዎች ጋራ በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ምክክር መደረጉን ገልፀውልናል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሰለማዊት ዳዊት ሶስቱን ዓለም አቀፍ መድረኮች ጨምሮ መሰል መድረኮችን አሟጦ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ሁሉም ጋ ለመገኘትና ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በበጎ መልኩ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ የመዋለንዋይ አቅም እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፣ በተቻለ አቅም ያሉትን አጋጣሚዎች ሁሉ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ማዋል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ.ም