በ2015 በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ17ኛ ሳምንት መርሃግብር ሊካሄዱ የነበሩ ቀሪ ጨዋታዎች ለሌላ ተስተካካይ መርሃ ግብር መዘዋወራቸው ይታወቃል። በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 በ17ኛ ሳምንት በድሬዳዋ ስታዲየም ቅዳሜ መጋቢት 02/2015 ዓ.ም የመጀመሪያ ጨዋታ በ10:00 ሰዓት ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ያገናኘ ሲሆን ጨዋታው ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
በመርሃ ግብሩ መሠረት ቀጣይ የሳምንቱ ጨዋታዎችን ለማድረግ ግን በድሬዳዋ ከተማ በጣለው ያልተጠበቀ ዝናብ ሜዳው በመበላሸቱና በቀላሉ ሊያገግም ባለመቻሉ አወዳዳሪው አካል ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በማየት ቀሪ የከተማው የመጨረሻ ጨዋታዎች መሰረዛቸው ይታወሳል።
በዚህም መሠረት ውድድሩ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ተቋርጦ በተመረጠ ቦታ መካሄዱ ሲቀጥል ከ18ኛው ሳምንት በኋላ ባለው ወቅት በተስተካካይ መርሃ ግብር የሚካሄዱ ይሆናል። ለዚህም የሊጉ የበላይ አካል በሦስት ከተሞች የሚገኙ ስታዲየሞችን ከቀናት በፊት ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ከ18ኛው ሳምንት ጀምሮ የሚደረጉ የሊጉ ጨዋታዎችን ማከናወኛ ስታዲየም ለመወሰን የሊግ ካምፓኒው የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እና ሥራ አስኪያጁ ክፍሌ ሰይፈ ወደ አዳማ አምርተው ከከተማው ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተው የዩኒቨርሲቲውን ሜዳ ተዟዙረው ተመልክተዋል።
በሌላ በኩል የሊግ ካምፓኒው የውድድር እና ሥነ ሥርዓት ሰብሳቢው ዶክተር ወገኔ ዋልተንጉስ ወደ ሀዋሳ አምርተው በተመሳሳይ ከከተማው ኃላፊዎች ጋር በመሆን የዩኒቨርሲቲውን ሜዳ የተመለከቱ ሲሆን ከመጫወቻ ሜዳው ባለፈም የልምምድ እና የሆቴል አቅርቦት በበቂ ሁኔታ መዘጋጀቱን እና በስታዲየሙ ላይ ተጨማሪ መብራቶች ዙሪያውን መገጠሙን በመቃኘት ውይይት ማከናወናቸው ተጠቁሟል።
የሊግ ካምፓኒው የቦርድ አባል አቶ አሰፋ ሆሲሶ፣ አቶ መንግሥቱ ሳሳሞ እና አንበሴ መገርሳ ባህርዳር ከተማ አምርተው ምልከታ አድርገዋል። ልዑኩ የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በግንባታ ላይ በመሆኑ የዩኒቨርሲቲውን ስታዲየም ቃኝቷል።
ሦስቱን ሜዳዎች የተመለከቱት የካምፓኒው አባላት ውይይቶችን ካደረጉ በኋላ በቀጣይ ውድድሮቹን የሚያስተናግዱ ሁለት ሜዳዎችን ትናንት ይፋ አድርገዋል። በዚህም መሠረት ከ18ኛው ሳምንት አንስቶ ያሉት የመጀመሪያዎቹ አምስት ጨዋታዎች (እስከ 22ኛው ሳምንት) በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ላይ እንዲከናወኑ ተወስኗል። ቀሪዎቹ ከ23ኛው እስከ 27ኛው ሳምንት መርሃግብር ያሉት ጨዋታዎች ደግሞ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ላይ እንዲካሄዱ መወሰኑ ታውቋል። በዚህ ሂደት ውስጥ በሁለቱም ሜዳዎች በ17ኛው ሳምንት ያልተካሄዱት ጨዋታዎችም በየጣልቃው በተስተካካይ መርሃግብር ይካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከ28ኛው እስከ 30ኛው ያሉት የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ጨዋታዎች የት ይካሄዳሉ? የሚለው ጉዳይ ግን አልታወቀም፡፡
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 እስከ 17ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ድረስ በድሬዳዋ ስታዲየም የተደረገ ሲሆን፣ የ17ኛው ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎችና ከ18ኛ ሳምንት በኋላ ያሉ ጨዋታዎች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ መልስ የሚደረግ ይሆናል። ቀሪ ዝርዝር ጉዳዮችንም የሊግ ካምፓኒው ወደ ፊት እንደሚገልፅ ጠቁሟል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2015 ዓ.ም