በአፍሪካ ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ የሆነውና ተወዳጁ የአፍሪካ ዋንጫ ለ34ኛ ጊዜ በተያዘው ዓመት መጨረሻ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ኮትዲቯር አዘጋጅነት ይካሄዳል። በዚህ ውድድር ተካፋይ ከሚሆኑት 24 ሃገራት መካከል ለመካተትም 44 ብሔራዊ ቡድኖች በ12 ምድቦች ተደልድለው ካለፈው ዓመት ጀምሮ የማጣሪያ ፍልሚያቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በማጣሪያ ውድድሩ ላይ እየተካፈሉ ከሚገኙት ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም በምድብ አራት ከግብጽ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር ተደልድላ በመወዳደር ላይ እንደምትገኝ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) የምድቡን ወሳኝ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታዎችም ከቀናት በኋላ የምታደርግ ይሆናል። መጋቢት 15 እና 18/2015 ዓም ከጊኒ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለሚካሄደው ጨዋታም የዋሊያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከቀናት በፊት የቡድናቸውን 23 ተሰላፊዎች ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው። ጥሪ የተደረገላው የቡድኑ አባላትም ከትናንት አንስቶ ወደ ዝግጅት መግባታቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የስታዲየሞች ዝቅተኛ መስፈርትን ባለማሟላቷ የትኛውንም አህጉር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ውድድሮች በሃገሯ እንዳታስተናግድ የታገደችው ኢትዮጵያ ይህንንም ጨዋታ በሰው ሃገር በውሰት ሜዳ ላይ ታከናውናለች። ከደጋፊውና ከሜዳው ከሦስት ዓመታት በላይ ርቆ ለመጫወት የተገደደውና ‹‹ስደተኛው›› የሚል ቅጽል የተሰጠው ብሔራዊ ቡድኑ (ዋሊያዎቹ) ከጊኒ አቻው ጋር ያለበትን ጨዋታ በሞሮኮ ካዛብላንካ የሚያደርግ ይሆናል። ከሦስት ቀናት በኋላ ደግሞ ሁለቱ ሃገራት ራባት ላይ የመልስ ጨዋታቸውን በልዑል ሞላይ አብዱላህ ስታዲየም ያከናውናሉ።
ዋሊያዎቹ ላለባቸው ግጥሚያ የሚሆናቸውን የዝግጅት ጨዋታም ከሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር እንደሚያደርጉ ታውቋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በያዘው መርሐ ግብር መሠረትም የአቋም መለኪያ ጨዋታው በመጪው እሁድ መጋቢት 10/2015 ዓም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚከናወን ይሆናል። በማጣሪያ ውድድሩ ላይ ሩዋንዳ በምድብ 12 ከሴኔጋል፣ ሞዛምቢክ እና ቤኒን ጋር የተደለደለች ሲሆን፤ ከሞዛምቢክ ጋር አቻ በመውጣት እንዲሁም በሴኔጋል ሽንፈትን አስተናግዳ በአንድ ነጥብ ከምድቡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በዚህ የማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያ ከማላዊ ጋር በነበራት የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ 68ኛው ደቂቃ ላይ ያገኘውን ቅጣት ምት በመጠቀም የመጀመሪያዋን ግብ ለሃገሩ ያስቆጠረው ወጣቱ አጥቂ አቡበከር ናስር በቅዳሜው የወዳጅነት ጨዋታ ላይ እንደማይሰለፍ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። ለደቡብ አፍሪካው ታላቅ ቡድን ማሜሎዲ ሰንዳውስ በመጫወት ላይ የሚገኘው የ23 ዓመቱ አቡበከር በዚህ ጨዋታ ላይ የማይሰለፈው በገጠመው ጉዳት ምክንያት ነው። ተጫዋቹ ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ አገግሞ ከቀናት በኋላ በሞሮኮ ከጊኒ ጋር ለሚካሄደው ግጥሚያ እንደማይደርስም ተረጋግጧል። በመሆኑም በተጫዋቹ ምትክ በፕሪሚየር ሊጉን ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድን አጥቂ የሆነውና በቻን ውድድር ላይ የብሄራዊ ቡድን አባል የነበረው ኪቲካ ጀማ ዋሊያዎቹን በመቀላቀል በሞሮኮ የሚካሄዱት ቀጣይ ጨዋታዎች ላይ የሚካፈል ይሆናል።
ዋሊያዎቹ የማጣሪያ ጨዋታቸውን በማላዊ የ2ለ1 ሽንፈት የጀመሩ ቢሆንም፤ ከቀናት በኋላ እዚያው ማላዊ ላይ ግብጽን በማስተናገድ የ2 ለምንም ጣፋጭ ድል ማስመዝገባቸው የሚታወስ ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ከሁለት ጨዋታ 3 ነጥብ እና 1 የግብ ልዩነት በመያዝ ምድቡን በመምራት ላይ ትገኛለ ች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም