ክፍል አንድ
የዛሬው ‹‹የፍረዱኝ አምድ›› ዝግጅታችን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀድሞው መጠሪያ ስሙ ወረዳ 19 ቀበሌ 57 በአሁኑ መጠሪያው ደግሞ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በተለምዶ አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ እየተባለ ወደሚጠራው ሰፈር ይወስደናል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በተለምዶ አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ ከ65 በላይ የሚሆኑ አባወራዎች «በራሳችን ወጪ እና መሬት ላይ የሠራነውን እንዲሁም ከ60 ዓመት በላይ የኖርንበት ቤት ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ ቤቱ የመንግሥት ስለሆነ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ጋር የቀበሌ ቤት ኪራይ ውል ተዋዋሉ ተብለን ተገደናል። በራሳችን መሬት እና ወጭ ሠርተን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የኖርንበትን ቤት፤ ሕግ ባለበት ሀገር እንዴት ከአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ጋር የኪራይ ውል ተዋዋሉ እንባላለን? የኢትዮጵያ ሕዝብም መንግሥት ማኅበረሰቡን እንዲያገለግሉ ባስቀመጣቸው ሹመኞች እየደረሰብን ያለውን በደል ተመልክቶ ይፍረደን » ሲሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቤት ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ሕዝብም ግራና ቀኙን አይቶ ይፈርድ ዘንድ ዝግጅት ክፍሉ ስለጉዳዩ ከሰዎች እና ሰነድ ያገኛቸውን መረጃዎች እና ማስረጃዎች በጥልቀት መርምሮ የደረሰበትን የክፍል አንድ ዝግጅት እነሆ ብሏል። ቀሪ የምርመራ ዘገባዎችን በቀጣይ ሳምንት ለሕዝብ የምናደርስ ይሆናል። መልካምን ንባብ ።
የፋብሪካው አመሠራረት እና ውዝግቡ መነሻ
ፋብሪካው በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በአርመናዊያን እንደተመሠረተ ከሰዎች እና ከሰነድ ያገኘናቸው ማስረጃዎች ያመላክታሉ። ፋብሪካው ሲመሠረትም በአካባቢው አቶ ተሰማ ወልደማሪያም እና ወይዘሮ ይፍቱ ሥራ አብዩ የተባሉ አባወራ ብቻ ይኖሩ እንደነበር ከአካባቢው ሰዎች የተገኙ ማስረጃዎች ያሳያሉ። አርመናውያኑም ፋብሪካውን ለመትከል ከእኝህ አባወራ በአስራ ሁለት ብር እንደገዙት ያካባቢው ሰዎች እና ለፋብሪካው መሬቱን የሸጡት ቤተሰቦች ያስረዳሉ።
ፋብሪካው ወደ ሥራ ሲገባም 65 የሚደርሱ ሠራተኞችን እንደቀጠረ የተለያዩ ማስረጃዎች ያሳያሉ። ይህን ተከትሎ በፋብሪካው ለሥራ የተቀጠሩ ሰዎች ለሥራ ቦታቸው ቅርብ ሰፈር በመምረጥ ግማሾቹ በአነስተኛ ብር ለፋብሪካው መሬት ከሸጡት አባወራ መሬት ገዝተው ቤት ሠሩ። ግማሾቹ ደግሞ ከወቅቱ የእርስት ቢሮ በምሪት መሬት አገኙ። ይሁን እንጂ እነኝህ 65 የሚደርሱ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሠራተኞች የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ አልበራቸውም ፡።
ቀን ቀን ሲወልደው የንጉሙ ዘመን አለቀና የወታ ደራዊ ደርግ መንግሥት ተተካ። ይህን ተከትሎ የ47/67 አዋጅ ታወጀ። በዚህም በአርመናውያን ስር ይተዳደር የነበረው ፋብሪካ በመንግሥት ተወረሰ።
በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ ቤት ሠርተው ይኖሩ የነበሩ ሠራተኞችም የሠሩት ቤት ተጠብቆላቸው በራሳቸው ሲያስተዳድሩት ኖሩ። አሁን ላይ እነኝህ ሠራተኞች በቤታቸው እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ ተዋልደው በየመኖሪያ ቤታቸው እየኖሩ ይገኛሉ።
ይሁንና በ2002 ዓ.ም ምክንያቱ በውል ባልታወቀ አግባብ ቤቶቹ ሰነድ አልባ ስለሆኑ ብቻ በወቅቱ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የቤቶች አስተዳደር ኃላፊ በነበሩት ግለሰብ የ65ቱን አባወራ ቤቶች ባለቤት የአልባ የሚባል መታወቂያ ለጠፉባቸው። ይህን ተከትሎ ‹‹በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የቤቶች አስተዳደር ኃላፊ ያለምንም ምክንያት ከመሬት ተነስቶ ቤቶቹ የመንግሥት ስለሆኑ የቀበሌ ቤት ኪራይ ውል መዋዋል
አለባችሁ›› ሲሉ አሁን ላይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አቤቱታ ያቀረቡትን ሰዎች አስገደዱ። ይህን ተከትሎ በወረዳ 6 ቤቶች አስተዳዳሪ እና በነዋሪዎቹ መካከል ውዝግብ ተነሳ።
ከአቤቱታ አቅራቢዎች አንደበት
የተሰማው ቅሬታ
አቤቱታ አቅራቢዎቹ በርካታ ቢሆኑም ስለተፈ ጠረው ውዝግብ በአግባቡ ሊያስረዱ ይችላሉ የተባሉ የተወሰኑ ሰዎችን በቃለ መጠየቅ አካተናል። ከእነኝህ መካከል አቶ አሥራት አራርሶ አንዱ ናቸው ።
አቶ አሥራት አራርሶ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የቤት ቁጥር 160 ነዋሪ ናቸው። እድሜአቸው በሃምሳዎቹ አጋማሽ ላይ እንደሚገኝ ያስረዱት አቶ አሥራት፤ ውዝግብ በተነሳበት ቤት ውስጥ ተወልደው ማደጋቸውን እና አሁን ላይም በቤቱ ልጅም ወልደው እየኖሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
እንደ አቶ አሥራት ገለጻ ፤ በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ዙሪያ የራሳቸውን ቤት ሠርተው የሚኖሩ 65 የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሠራተኞች ነበሩ። እነኝህ ሠራተኞች ምንም እንኳን በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ተቀጥረው የሚሠሩ ቢሆንም ይኖሩበት የነበረውን ቤት በራሳቸው ገንዘብ እና ጉልበት የሠሩት ስለነበር ፋብሪካው በደርግ ዘመነ መንግሥት በአዋጅ 47/67 ሲወረስ የፋብሪካው ተቀጣሪ ሠራተኞች ቤቶች ግን አልተወረሱም ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ የነበረው አስተዳደር ቤቶቹ በሠራተኞች ገንዘብ እና ጉልበት የተሠሩ መሆናቸውን አረጋግጦ ስለነበረ።
በወቅቱ የነበረው መንግሥት ሁሉን አቀፍ ማጣራት አድርጎ ቤቶች የሠራተኞች የግላቸው መሆኑን ተረድቶ ያልወረሳቸው ቢሆንም በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ግን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የቦታ እና ዲዛይን ኃላፊ ሆነው የተሾሙት ግለሰብ በ24/12/2002 ዓ.ም በክፍለ ከተማው እና በወረዳው የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ለአንዳቸውም ሳያማክር በራሱ ተነሳሽነት ከ60 ዓመት በላይ የኖሩበትን ቤት ባለቤት አልባ በማለትና ለክፍለ ከተማ በማስተላለፍ እንዲሁም ክፍለ ከተማ ደግሞ ለአዲስ አበባ ቤቶች በማስተላለፉ ሳቢያ የወረዳው ቤቶች ልማት አስተዳደር ነዋሪዎችን የቀበሌ ቤት ኪራይ ውል እንዲዋዋሉ የሚል ማስታወቂያ ለነዋሪዎቹ መላካቸውን ይናገራሉ።
ይህን ተከትሎ በወቅቱ በነበሩት ኃላፊ የተወሰነው ውሳኔ እውነታን ያላገናዘበ እና መነሻው ምን እንደሆነ ስለማይታወቅ በራሳችን ገንዘብ እና ጉልበት በሠራነው ቤት የኪራይ ውል ሊዋዋሉ እንደማይችሉ እና አንድ ግለሰብ ከመሬት ተነስቶ ይህን መሰል ውሳኔ እንዴት በግሉ ሊወስን ይችላል? ሲሉ ለክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደር አቤት ማለታቸውን ያስረዳሉ።
አቤቱታውን ተከትሎ የክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደርም ስለእነዚህ ቤቶች የሚያውቀው ነገር እንደሌለ እና ግለሰቡ ከመሬት ተነስቶ በግሉ ይህን የመሰለ ውሳኔ መወሰኑ አግባብ ባለመሆኑ ቅሬታቸውን ለክፍለ ከተማው ሥራ አስፈጻሚ እንዲያመለክቱ ተደረገ። ይህን ተከትሎ አቤቱታ አቅራቢዎቹም ለክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ማመልከታቸውን ይናገራሉ።
በወቅቱ የነበሩት የክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ኃላፊም ስለጉዳዩ ለማጣራት በጣም ቀላል ዘዴዎች መኖራቸውን ገልጸው ፤ ቤቶቹ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ መሆናቸውን እና አለመሆናቸውን ለማጣራት ለፕራይ ቬታይዜሽን ኤጄንሲ፣ የባለደራ ምክር ቤት እና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት ማኔጅመንት ስለቤቶች የሚያውቁትን ነገር አጣርተው እንዲያሳውቁ የሚል ደብዳቤ እንደሚጽፉ እና እነኝህ መሥሪያ ቤቶች ውዝግብ ያስነሱትን ቤቶች አናውቅም ካሉ በእውነትም ግለሰቡ ሐሰተኛ እና ትክከል ያልሆነ በመሆኑ ይህንን ቦታ ለአቤቱታ አቅራቢዎች እንመልሳለን በማለት ከላይ ለተገለጹት መሥሪያ ቤቶች ደብዳቤ መጻፉን ይናገራሉ።
ይህን ተከትሎ የፕራይቬታዜሽን ኤጀንሲ ስለቤቱ ምንም የምናውቀው ነገር የለም የሚል ምላሽ ሲሰጥ፤ የባላደራ ምክር ቤት ደግሞ ቤቱ ቀድሞ የቤቶች አስተዳደር ቢሆን ኖሮ ቤቱን ድርጅቱ ለእነሱ ያስረክባቸው እንደነበር ነገር ግን አሁን ላይ ቤቶቹን እነሱ እንደማያውቋቸው የሚገልጽ ምላሸ ሰጡ ።
ሌላው ስለጉዳዩ እንዲያብራራ የተጠየቀው ደግሞ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት ማኔጅመንት ነበር። የክፍለ ከተማው መሬት ማኔጅመንትም ስለቤቶቹ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ በደብዳቤ ለክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደር አሳወቀ።
ከዚህ በተጨማሪ የቀድሞው አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ የአሁኑ ኢትዮጵያ ሌዘር ስለጉዳዩ ተጠይቆ ለሠራተኞች የመብራት እና የውሃ ክፍያ ከመክፈል ውጭ ስለቤቶቹ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ በደብዳቤ ምላሽ ተሰጠ።
የክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደርም እነኝህን ደብዳቤዎች ካሰባሰቡ በኋላ ከደብዳቤዎቹ የተገኙ ቀን እና ቁጥሮችን በመጥቀስ «ይህ ቤት የመንግሥት ነው ተብሏል። ስለዚህ ጥያቄአችሁ በቂ መልስ የሚያሰጥ ሆኖ አላገኘንም» ሲሉ እንደመለሱላቸው አቤቱታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ።
ይህን ተከትሎ ጉዳዩን በይግባኝ በ2006 ዓ.ም ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቅሬታ ሰሚ አቀረቡ። ይሁን እንጂ የክፍለ ከተማው ቅሬታ ሰሚ ይህን ቅሬታ አልቀበልም ይላሉ። ምክንያቱም ቅሬታ ሰሚ ኃላፊ የነበሩት ሰው ቀደም ሲል ችግሩን ከፈጠረው የወረዳ 6 ቤቶች አስተዳደር ጋር በአንድ ቦታ ይሠሩ ስለነበር መሆኑን አመላክተዋል። ይህን ተከትሎ ቅሬታ ሰሚ ቢሮ ቅሬታቸውን ሊቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑን ጠቅሰው ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቤት አሉ።በክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስገዳጅነት ክፍለ ከተማው ቅሬታ ሰሚ ጽሕፈት ቤት በግድ አቤቱታቸውን እንዲቀበል ሆነ።
ይሁን እንጂ የአቤቱታውን ምላሽ ቀጥታ ለቅሬታ አቅራቢዎቹ መስጠት ሲገባቸው ጉዳዩን ወደ አዲስ አበባ ከተማ ቅሬታ ሰሚ እንዲላክ አደረገ።ይህም የአሠራር ሂደቱን ያልተከተለ ከመሆኑም ባሻገር ሆነ ተብሎ ጉዳዩን ለማወሳሰብ የተደረገ ተግባር መሆኑን አቤቱታ አቅራቢው ያስረዳሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅሬታ ሰሚ የነበሩትም በወቅቱ አጣሪ ኮሚቴ አደራጅተን ስለጉዳዩ ምርመራ እንጀምራለን ብለው እንቅስቃሴ ከጀመሩ በኋላ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ አግባብ የጀመሩትን ምርመራውን አቁመው የደረሰበትን የመጨረሻ ምላሽ ነው በማለት ወረዳው ላይ የነበረውን ምላሽ ሳይጨምሩ እና ሳይቀንሱ እንደወረደ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ምላሽ እንደሰጧቸው ይገልጻሉ።
ቅሬታ አቅራቢዎችም እውነታን ይዘን እያለ በአንድ ግለሰብ በተፈጠረ የክፋት አካሄድ ስለምን እንዲህ ያለ መልስ እንሰጣለን ? ሲሉ መጠየቃቸውን እና ከተማ አስተዳደሩ ቅሬታ ሰሚም ‹‹መንግሥት ከሚቀየመን እናንተ ብትቀየሙ ይሻላል ፤ ሲደክማችሁ ትተውታላችሁ›› የሚል በማስፈራራት እና ማንጓጠጥ በተቀላቀለበት አግብብ ትክክለኛ እና ተገቢ ያልሆነ ምላሽ እንደሰጣቸው ያስረዳሉ።
ይህንን የደረሰባቸውን አስተዳደራዊ በድል እንዲ ፈታላቸው እስከዛሬዋ ቀን ድረስ የተለያዩ የመንግሥት ቢሮዎችን ቢያንኳኩም ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ይናገራሉ።
እነኝህን ክርክሮች መከራከር ከጀመሩ አንስቶ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ከአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ቤቶች አስተዳደር ጋር ምንም አይነት የኪራይ ውል አልገቡም። ምንም የተጣራ ነገር በሌለበት እያንዳንዱ አባወራ የኪራይ ውል መግባት አለባችሁ በማለት እና በማስፈራራት ቢሞክሩም እስከዛሬ ማንም ሊቀበለው ያልቻለ ነገር ነው።ቤቱ የግላቸው ስለሆነ በምንም አይነት አግባብ የኪራይ ውል ሊገቡ እንደማይችሉ አመላክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቤቱ የቀበሌ ሳይሆን የራሳችን ነው ብለው አቤቱታ አቅርበው ሲከራከሩ ከነበሩ ሰዎች መካከል ምክንያቱ በውል ባልተገለጸ አኳኋን መሬቱን በሰነድ አልባ ተፈቅዶላቸው ግማሾቹ ከክፍለ ከተማው ሕጋዊ ካርታ ሲሰጣቸው፤ የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ የአፈር ግብር እንዲከፍሉ በማድረግ ክፍለ ከተማው ስለሰዎቹ ሕጋዊነት እውቅና እንዲኖረው መደረጉን አመላክተዋል።
ለአብነት ያህል እነ ተስፋዬ ዘውዴ 101 የቤት ቁጥር ካርታ የተሰጣቸው ፣ የቤት ቁጥር 102 በላይነህ ጥላሁን የአፈር ግብር የሚከፍሉ፣ የቤት ቁጥር 103 ጋዲሴ ሙለታ ካርታ የተሰጣት እና ግብር እየከፈለች ያለች ፣ የቤት ቁጥር 141 የአፈር ግብር የሚከፍሉ ፣ የቤት ቁጥር 144 የአፈር ግብር የሚከፍሉ ፣ የቤት ቁጥር 145 የአፈር ግብር የሚከፍሉ ፣ የቤት ቁጥር 149 «ለ» የአፈር ግብር የሚከፍሉ፣ የቤት ቁጥር 154 እና 165 የአፈር ግብር የሚከፍሉ ሲሆን ፤ በፕሮስ ካውንስል ጉዳያቸው እየታየላቸው እና በሰነድ አልባ በወጣው መመሪያ መሠረት የቤት ካርታ ሊሰጣቸው በሂደት ላይ የሚገኙ ናቸው ።
እነኝህ ሰዎች ከአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሠራተኞች ጋር ቤታችሁ የመንግሥት ስለሆነ አዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ጋር የኪራይ ውል እንዲዋዋሉ ተጠይቀው የነበር ነገር ግን አሁን የእነሱ ብቻ ተመርጦ ካርታ ለማሠራት በሂደት ላይ የሚገኙ ናቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ሰነዶች ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቅርበዋል ።
ይህን ተከትሎ «እነኝህ ሰዎች እና እኛ በንጉሡ ዘመን መሬቱን የያዝንበት አግባብ አንድ ሆኖ ሳለ በምን ምክንያት እነሱ ሕጋዊ እውቅና አግኝተው የተቀረው አቤቱታ አቅራቢ ደግሞ እንዴት ሕጋዊ እውቅና ሳይሰጥ ቀረ?» ብለው ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት መጠየቃቸውን ይገልጻሉ፡።
ነገር ግን ጉዳዩ የሚመለከታቸው ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ ያሉ አካላት ምንም አይነት ምላሽ ሊሰጡ ፈቃደኛ አለመሆቸውን አብራርተዋል። ምላሽ በማጣታቸውም እስካሁን ድረስ ከፍተኛ እንግልት ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በልዩነት ካርታ የተሰጣቸው ሰዎች እና የቅሬታ አቅራቢዎቹ የጂአይኤስ እና የሲአይ ኤስ መረጃ ምን ይመስላል? ተብለው በአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል የተጠየቁት አቤቱታ አቅራቢው፤ ሁላቸውም በንጉሡ ዘመን በተመሳሳይ ሁኔታ መሬቱን እንዳገኙት እና በ1988ቱም የአየር ካርታ ላይ እንደሚታዩ ማረጋገጫ ከክፍለ ከተማውም የኮፒ ግልባጭ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ፡።
በመጀመሪያ ደረጃ ቤቶች ባለቤት አልባ መባሉ አግባብነት የለውም የሚሉት ቅሬታ አቅራቢው በቤቱ በየስማችን የቤት ቁጥር ፋይል ወጥቶልን በማንኛው ነገር ላይ የምንስተናገድ ሆኖ ሳለ ባለቤት አልባ ቤቶች መሰኘቱ በራሱ ትክክል አለመሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ፡።
በድርጅቱ የተቀጠሩ ሰዎች በወቅቱ በየቤታቸው የራሳቸው ውሃ እና መብራት እንዳልበራቸው ነገር ግን ከሰፈሩ አንድ በአቅም ሻል የሚል ሰው ካለ ለተቀሩት ሰፈር ሰዎች ውሀና መብራት በትውስት ይሰጥ እንደነበር ያስረዳሉ።ነገሮች እየዋሉ እያደሩ ሲመጡ ግን ሁሉም ሰው በስሙ መብራት እና ውሃ ማስገባቱን ይገልጻሉ።
ድርጅቱ ወደ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ከተላለፈ ጀምሮ ሁሉም የሰፈሩ ነዋሪዎች በየራሳቸው ውሃ እና መብራት ማስገባታቸውን ይገልጻሉ። ሁሉም ሰው የድርጅቱ ሠራተኛ ስለነበር ድርጅቱ ለሠራተኞቹ እንደ ትብብር ውሃ በአጥር ውስጥ እያሾለከ ይሰጥ ነበር። ከሠራተኞች ደመወዝ የሚቆረጥ የመብራት ክፍያም የሚከፍለው ድርጅቱ እንደነበር ያስረዳሉ።
ለሠራተኞቹ የመብራት ክፍያ መክፈል እና ሠራተኞቹ ውሃ ባልነበራቸው ጊዜ በአጥር አሾልከው ውሃ መቅዳታቸው ደግሞ ውዝግብ ያስነሱት ቤቶች የፋብሪካው ናቸው ሊያስብ የሚችል መሠረት እንደሌለው እና የሠራተኞችንም የቤት ባለቤትነት መብት የሚያሳጣ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡።
እስከዛሬ ድረስ ጉዳዩን ሰምቶ እና አጣርቶ መልስ የሰጠን አንድም አካል የለም የሚሉት አቶ አሥራት ፤ በአንድ ግለሰብ ማንአለብኝነት በተጻፈ ደብዳቤ ይህ ሁሉ አባወራ ለበርካታ ዓመታት መሰቃየቱ በወረዳቸው ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ይገልጻሉ።
ሌላኛው አቤቱታ አቅራቢ አቶ ሳምሶን ይልማ ይባላሉ። በአዋሽ ቆዳ አካባቢ የቤት ቁጥር 146 ነዋሪ ናቸው። እንደ አቶ ሳምሶን ገለጻ ፤ ጉዳዩን እየተከታተሉ ለረጅም ጊዜያት ቆይተዋል። ይህ ችግራቸው እንዲፈታ ለበርካታ ዓመታት ያልገቡበት የመንግሥት ቢሮ የለም። ይሁንና በወረዳቸው ብሎም በክፍለ ከተማቸው ከፍተኛ የሆኑ አስተዳደር ችግሮች በመኖራቸው ሳቢያ የተፈጸመባቸው ግፍ የሚፈታው አካል አልተገኘም።
ይህ ጉዳይ ግልጽ እና የሚታይ ነገር ነው የሚሉት አቶ ሳምሶን ፤ ጉዳዩን እስከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ድረስ እንደወሰዱት ይገልጻሉ።ይሁን እንጂ የከንቲባ ጽሕፈት ቤትም ጉዳዩን መልሶ ችግር ወደ ፈጠረው ወደታችው የአስተዳደር እርከን መመለሱን ያስረዳሉ፡።
አሁን ላይ የቤታቸው ጣራ ቢፈርስ የቤቱን ጣራ ማስተካከል እንደማይችሉና መጸዳጃ ቤታቸውም ቢፈ ርስ ለማስገንባት ፈቃድ አናገኝም ያሉት አቶ ሳምሶን ፤ በመሆኑም የአካባቢው ማኅበረሰብ ለከፋ ችግር ተጋልጦ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
እናት እና አባታቸው ከ60 ዓመት በላይ የኖሩበት ቤት በሰነድ አልባ ተመዝግቦ ካርታ የሚያገኙበት መብት ሊፈጠርላቸው ሲገባ የመንግሥት ሹመኞች በሚፈጥሩት አግባብ ያልሆነ ምክንያት ጉዳዩ እስከዛሬ ድረስ ሊፈታ አልቻለም። በዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ ይናገራሉ።
‹‹እኛ ቤት ብትመጣ በቤቱ መኖር ከጀመርን አራተኛ ትውልድ ደርሷል›› የሚሉት አቶ ሳምሶን ፤ መኖሪያ ቤታቸውም የጂአይሴ እና የሲኤ ኤስ ማስረጃዎችም በእጃቸው እንደሚገኙ አመላክተዋል። ይሁን እንጂ የአየር ካርታውን እና የሲአይ ኤስ መረጃ ለወረዳው እና ለክፍለ ከተማው ቢያሳዩም መልስ ሊሰጣቸው የቻለ አካል አለመኖሩን ይገልጻሉ።
እንደ አቶ ሳምሶን ገለጻ ፤ አሁን ላይ እየተንገላቱ ያሉት ሰዎች ከአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሠራተኞች ውጭ በአካባቢው ሌላ ሰዎች መኖር ሳይጀምሩ የነበሩ የአካባቢው ነባር ሰዎች ናቸው። ከነባር ሰዎች በኋላ በሕገ ወጥ መንገድ መጥተው መሬት የያዙ ሰዎች በሰነድ አልባ ታቅፈው መብት ተፈጥሮላቸው ባለይዞታ ሲደረጉ ነባር ነዋሪዎቹ ግን መብታው ተነፍጎ እንዲሁ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
አሁን ላይ በራሳቸው ቤት እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ ቀድመው ቢያውቁ ኖሮ በአካባቢው በጣም ብዙ ባዶ ቦታዎች ስለነበሩ ሌሎች እንዳደረጉት በሕገ ወጥ መንገድ ባዶ ቦታዎችን በመያዝ በሰነድ አልባ መብት ሊፈጠርላቸው እንደሚችል ያስረዳሉ። ይህ ሁሉ ችግር የተፈጠረው በአንድ ግለሰብ ውሳኔ በመሆኑ እየደረሰብን ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይወቅልን ሲሉ ተናግረዋል።
ከአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ አቻ የሆነው አቃቂ ጨርቃ ጨርቅ በፋብሪካው ዙሪያ በሚገኝ ቦታ ላይ ከ47/67 ዐዋጅ በፊት ለሠራተኞቹ መኖሪያ ሠርቶ ነበር። ሠራተኞችም ሲኖሩበት ነበር። ይህ ማለት ቤቶቹ የፋብሪካው ነበሩ። በመሆኑም መንግሥት በ47/67 አዋጅ ትርፍ ቤቶቹን ሲወርስ ለፋብሪካው ሠራተኞች መኖሪያ የተሠሩት ቤቶች ጭምር ተወረሱ። አሁንም ድርጅቱን ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ሲረከብ የተረከበው ፋብሪካውን ብቻ ሳይሆን ለፋብሪካው ለሠራተኞች የተሠሩ ቤቶች ጭምር ነው።
የአዋሽ ፋብሪካ ሠራተኞች ቤቶች ግን በሠራተኞች በራሳቸው የገንዘብ እና ጉልበት ወጭ የተሠሩ ስለነበሩ በአዋጅ 47/67ም አልተወረሱም፤ ፋብሪካውን ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ሲረከብ ቤቶችን አልተ ረከበም። ምክንያቱም ቤቶቹ የግለሰቦቹ እንጂ የመን ግሥት ስላልሆኑ።
በወቅቱ የአዋሽ ፋብሪካ ቤቶች የነበሩ ሦስት ቤቶች ንብረትነታቸው ከፋብሪካው ስለነበሩ በአዋጅ 47/67 ድርጅቱ ሲወረስ ቤቶችም አብረው መወረሳቸውን ይገልጻሉ። የአዲስ ዘመን ጋዜጣም ይህንኑ በቦታው ተገኝቶ ለማረጋገጥ ችሏል፡።
እነኝህ ሦስት ቤቶች በወቅቱ የመኖሪያ ቤቶች የነበሩ። ነገር ግን የፋብሪካው ንብረት ስለነበሩ በአዋጅ 47/67 ሊወረሱ ችለዋል የሚሉት አቶ ሳምሶን ፤ የ65ቱ አባወራ መኖሪያ ቤቶች የእውነት የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ቢሆኑ ኖሮ በወቅቱ የነበረውን መንግሥት ከመውረስ ማን እና ምን ይከለክለው ነበር? ሲሉ ይጠይቃሉ። ቤቶቹ በአዋጁ ያልተወሰዱትም የሠራተኞቹ ስለነበሩ መሆኑን ያስረዳሉ።
በወቅቱ ትርፍ ቤት የነበራቸው ነገር ግን የአዋሽ ቆዳ ሠራተኛ ሆነው በፋብሪካው ዙሪያ ቤት ሠርተው ይኖሩ የነበሩ በርካታ ሰዎች በሌላ ቦታ ይገኝ የነበረው ቤታቸው በ47/67 ዓዋጅ እንደተወረሱ ያስረዳሉ።
የአባወራዎቹ ቁጥር መጀመሪያ በነበሩት ሠራተኞች 65 ይባል እንጂ አሁን ላይ በቤቶቹ የሚገኙ ልጅ እና የልጅ ልጅ ጋር ተዳምሮ ከ250 በላይ አባወራዎች በሰፈሩ እየኖሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡።
ሌላኛዋ አቤቱታ አቅራቢዋ ወይዘሮ ጥሩነሽ ወርቁ ይባላሉ። እንደ ወይዘሮ ጥሩነሽ ገለጻ ፤ አሁን ላይ ውዝግብ በተነሳበት ቦታ ላይ ከአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ መኖር እንደጀመሩ እና አራት ያህል መንግሥታት ሲፈራረቁም እርሳቸው በዚሁ ቤት እንደነበሩ ያስረዳሉ።
የወረዳ እና ክፍለ ከተማ አካላት ቤቱ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ነበር ይላሉ። ቤቶቹም በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ባለቤትነት የተሠሩ መሆናቸውን ይናገራሉ። እዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው? ስንል ጠይቀናቸው ነበር። ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ወይዘሮ ጥሩነሽ ባለቤታቸው በአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ተቀጥረው ይሠሩ እንደነበር ገልጸው ፤ የባለቤታቸው ሥራ ሌሊት ሌሊት ስለነበር ለሥራቸው ቅርበት እና ለችግር እንዳይጋለጡ በመስጋት አሁን የሚኖሩበትን ቦታ ከአቶ ተሰማ ወልደማሪያም ገዝተው ቤት እንደሠሩበት ይጠቅሳሉ።
በገዙት ቦታ ላይ ቤት ለመሥራት አቅም ባጠራቸው ጊዜ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ በብድር ቤት ሠራላቸው። ይህ የሆነው ለበርካታ ሠራተኞች መሆኑ ይናገራሉ። ሠራተኛውም ቤቶቹን ድርጅቱ በብድር ሠርቶላቸው ስለነበር ድርጅቱ የከፈለላቸውን ገንዘብ በየወሩ ከደመዛቸው እየተቆረጠ ለድርጅቱ ገቢ ይደረግ ነበር። ድርጅቱ የከፈላቸውን ገንዘብ ከወር ደመወዛቸው ከፍለው ሲጨርሱ ቤቱን የራሳቸው ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡
ነገር ግን አንዱ ሲሾም አንዱ ሲሻር የቤታቸውን ጉዳይ አንዱም ሳይፈጽምላቸው እዚህ መድረሳቸውን ይገልጸሉ።
ሌላው አቤቱታ አቅራቢ የ84 አመት አዛውንቱ አቶ አሰፋ አላብሴ ናቸው። እንደ አቶ አሰፋ ገለጻ ፤ በዚህ ቤት መኖር የጀመሩት በ1950ዎቹ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሲመሠረት ጀምሮ ነው። በዚህ ቤትም ከ60 ዓመታት በላይ ኖረዋል። አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሲቀጠሩ ወርሐዊ ደመወዛቸው 75 ሳንቲም ነበር። አሁን ላይ በጡረታ የሚገኙ ሲሆን ወርሐዊ የጡረታ ገንዘባቸውም 95 ብር ደርሷል። አሁን ውዝግብ በተነሳበት ቤት 10 ልጆች እና ሰባት የልጅ ልጆች አሳድገው ለወግ ለማዕረግ አድርሰዋል።
አቶ አሰፋ አላብሴን ቤቱን ማን እንደሠራው ያውቃሉ? የወረዳ እና የክፍለ ከተማ አካላት ቤቱን የሠራው አዋሽ ቆዳ ፋብሪካ እንደሆነ ይናገራሉ። እዚህ ላይ የእርስዎ ሃሳብ ምንድን ነው ? ስንል ጠይቀናቸው ነበር። ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ አሰፋ እንዳሉት ፤ሌሎች ቤቶች እንደኔ ፋብሪካው ሲመሠረት በነበሩ ባዶ ቦታዎች ላይ ሠራተኛው በራሱ ገንዘብ እና ጉልበት የሠራቸው ናቸው። ቤቶቹ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ቢሆኑማ ኖሮ በአዋጅ 47/67 ይወረሱ ነበር።ነገር ግን ቤቶቹ የሠራተኛው ስለነበሩ በአዋጁም አልተወረሱም።
ውሃ እና መብራት ጋር ተያይዞ ለበርካታ ዓመታት ከፋብሪካው ይጠቀሙ እንደነበር ያስታውሳሉ። ለመብራት እና ለውሃ የሚከፈለው ክፍያ ደግሞ ከደመ ወዛቸው የሚቆረጥ መሆኑን ጠቁመዋል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መብራቱ እና ውሃው ለግለሰብ ቤት ሳይሆን ለፋብሪካው ማምረቻ ነው በመባሉ ከፋብሪካው ስበው ይጠቀሙበት የነበረው መብራት እና ውሃ ተቆረጠ። በዚህም ምክንያት መብራት እና ውሃ በማጣታቸው መብራት እና ውሃ ይሰጠን ሲሉ ለቀበሌ አመለከቱ። የሰፈሩን ችግር የተረዳውም ቀበሌ በሠራተኞች ወጭ ፤ በስማቸው መብራት እና ውሃ ተሰጣቸው።
ሌላኛዋ አቤቱታ አቅራቢ ወይዘሮ ወይንሸት ለማ ይባላሉ። እኝህ ግለሰብ የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሲመሠረት የፋብሪካው ባለቤቶች በቦታው ፋብሪካውን ለማቋቋም በፈለጉ ጊዜ ፋብሪካው የተሠራበትን ቦታ የሸጡት አባወራ የአቶ ተሰማ ወልደማሪያም እና የወይዘሮ ይፍቱ ስራ አብዩ የልጅ ልጅ ናቸው።
እንደ ወይዘሮ ወይንሸት ገለጻ ፤ የአባታቸውን ስም የማታስታውሰው ነገርግን በልጅነት ልቦናቸው ስማቸውን ያረሷቸው «ካችክ» እና «ማንድሮስ» የተባሉ አርመናውያን የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካን ባለቤቶች ፋብሪካውን ለመገንባት ባዶ ቦታ ከእርሳቸው ቤተሰቦች እንደገዙ ያስታውሳሉ። ቦታው የተሸጠውም ሃያ ብር በማይሞላ ገንዘብ ነው። ያንንም ገንዘብ ለአርመናውያኑ አጠናቀው እንዳልከፈሉ ይናገራሉ።
የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ሠራተኞች በፋብሪካው ዙሪያ ሲሰፍሩ የተወሰኑት ሠራተኞች ከእርሳቸው ቤተሰቦች በትንሽ ብር ቦታ ገዝተው ቤት የሠሩ ሲሆን አብዛኛዎቹ ሠራተኞች ግን ከቤተሰቦቻቸው በነጻ መሬት ተሰጥቷቸው ቤት የሠሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
አሁን ላይ የወረዳ 6 ቤቶች አስተዳደር ‹‹ቤቶች የኔ ናቸው ማለቱ ከእውነት የራቀ›› ነው ሲሉ ይናገራሉ፡።
ውድ አንባቢያን በክፍል ሁለት ዝግጅታችን ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎችን ፣ ጉዳዩ የሚመ ለከታቸውን የወረዳ እና የክፍለ ከተማ አመራሮች ምላሽ እንዲሁም የጋዜጠኛውን ትዝብት ይዘን የምንቀርብ ይሆናል። እስከዚያው ቸር እንሰንብት ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም