እንዳለፉት በርካታ ሳምንታት ሁሉ ያለፈው እሁድ በተለያዩ የዓለም ከተሞች በርካታ የጎዳና ላይ ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በትልልቅ ውድድሮች ድል አድርገዋል። ከነዚህ ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነውና ከዓለም ታላላቅ የጎዳና ላይ ውድድሮች የሚጠቀሰው የ2023 የስፔን የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ነው። በዚህ ውድድር ወጣቱ ኦሊምፒያን አትሌት በሪሁ አረጋዊ ድልን ተቀዳጅቷል።
ከሦስት ሳምንት በፊት በአውስትራሊያ ባትረስ በተካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ካሸነፈ በኋላ ፊቱን ወደ ጎዳና ላይ ውድድር ያዞረው አትሌት በሪሁ በስፔን ቪላ ዲ ላሬዶ ከትላንት በስቲያ በተካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የዓለማችንን ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ነው ማሸነፍ የቻለው። አትሌቱ ውድድሩን በፍጹም የበላይነትና ተፎካካሪዎቹን በሰፊ ርቀት መርቶ ሊያሸንፍ ችሏል።
ተጠባቂ በነበረው ፉክክር አትሌት በሪሁ ተፎካካሪዎቹን በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት በመቅደም 26፡33 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል። የርቀቱ ዓለም ፈጣን ሰዓት ተመዝግቦ የሚገኘው ሪሆኔክስ ኪፕሩቶስ በተባለ አትሌት ሲሆን የተመዘገበውም ከሦስት ዓመታት በፊት በስፔን ቫሌንስያ በተደረገ ውድድር ነበር።
በወቅቱም የተመዘገበው 26፡24 ሰዓት ነው። የ22 ዓመቱ ወጣት አትሌት በሪሁ የዚህን ርቀት ሁለተኛ ሰዓት ከማስመዝገቡ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ፈጣን ሰዓት በ23 ሰከንድ በማሻሻል አዲስ ታሪክ መሥራት ችሏል። እሱን በመከተል ለአየርላንድ የሚሮጠው ኤፍሬም ግደይ በ28፡17 ሰዓት ሲገባ፣ ቶማስ ሞርቲመር ሦስተኛ ሆኖ አጠናቋል።
አትሌት በሪሁ “ውድድሩ ትልቅ በመሆኑ ስሜቴ የተደበላለቀ ነበር፤ ነገርግን የዓለም ክብረወሰንን ለመስበር ግብ አስቀምጬ ነበርም” ሲል ከውድድሩ በኋላ አስተያየቱን ሰጥቷል። “ውድድሩ በሙሉ ማለት ይቻላል ብቻዬን መሮጥ ቀላል አልነበረም፣ ነገር ግን ለኔ አስቸጋሪ የነበረው ነገር መንገዱ ጭቃማ መሆኑና ጠባቦቹ የመንገዱ መታጠፊያና ማቋረጫዎች ላይ እንዳልወድቅ ፈርቼ ነበር፣ ለማንኛውም በእውነት በጣም ረክቻለሁ” ሲልም ባለ ድሉ ተናግሯል።
አትሌት በሪሁ በቶኪዮ ኦሊምፒክ በ10ሺ ሜትር አራተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል። እአአ ታኅሣሥ 2021 በባርሴሎና በተካሄደው የ5ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድርም የምንጊዜውም ፈጣን ሰዓት ባለቤት የሆነበትን ድል ማስመዝገቡ ይታወቃል።
ሌላኛው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ያደረጉበት ውድድር በፖርቹጋል ሊዝበን የተደረገ የግማሽ ማራቶን ውድድር ሲሆን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶች አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል። በሴቶች ደግሞ አንደኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ጨርሰዋል።
በወንዶች መካከል በተካሄደው ውድድር አትሌት ንብረት መላክ 59፡06 በሆነ ሰዓት 1ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት በተመሳሳይ 59፡07 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ በመሆን አጠናቋል። ሐጎስን በመከተል ቪኒሰንት ነግቲች ከኬንያ በ59፡10 ሦስተኛ ሆኖ ውድድሩን ጨርሷል።
በተመሳሳይ በሴቶች መካከል በተካሄደው ውድድር አትሌት አልማዝ አያና 1፡05፡30 በሆነ ሰዓት አሸንፋለች። የሪዮ 2016 ኦሊምፒክ የ10 ሺ ሜትር ባለ ድሏ አልማዝ ለረጅም ጊዜ በጉዳት ከውድድር ርቃ ከቆየች በኋላ ከመም ውድድሮች ሙሉ በሙሉ ወጥታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የጎዳና ላይ ውድድሮች ትኩረት አድርጋለች።
ከወራት በፊትም አምስተርዳም ላይ የመጀመሪያ የማራቶን ድሏን ያጣጣመች ሲሆን ተደጋጋሚ የግማሽ ማራቶን ውድድሮችን አድርጋ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች። ባለፈው እሁድ ፖርቹጋል ላይ ስታሸንፍ ያስመዘገበችው ሰዓትም በግማሽ ማራቶን ታሪክ ሃያ አምስተኛው የዓለም ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦላታል። አልማዝን በመከተል ማርጋሬት ቸሊሞ ከኬንያ ሁለተኛ ስትሆን ግርማዊት ገብረእግዚያብሔር በ1፡06፡28 ሦስተኛ በመሆን ውድድሯን አጠናቃለች።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2015 ዓ.ም