የኑሮን ነገር “ኑሮ ንሯል” የሚለው አይገልፀውም። አይደለም ኑሮ ንሯል፣ “ኑሮ ጦዟል”ም የሚገልፀው ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በዐይን ጭፍን-ክፍት ፍጥነት ተለዋዋጭ የመሆኑ ጉዳይ ሲሆን፤ ገበያው ከገበያ ሥርዓት ማፈንገጡም ሌላው ነው።
እንኳን ዘንቦብሽ . . . እንዲሉ፣ ድሮም ባልጠና ኢኮኖሚ ላይ የገበያ አሻጥር ተሠርቶበት፣ በአሻጥሩም ውስጥ አሻጥረኛ ተሰግስጎበት፣ የንግድ ሥርዓቱ በደላላ ተዘውሮ፣ ጎማው በኪራይ ሰብሳቢ ተሽከርክሮ . . . ይቅርና፣ እንኳን . . . እንዲሁም አልቅስ አልቅስ ይለኛል እንደሚባለው፣ ድሮውንም በከፍ-ዝቅታ የታጀበ ኢኮኖሚ እንዲህ እንደ አሁኑ ዓይነት ፈተና ሲገጥመው የሸማቹ የመግዛት አቅም “ወገቤን” ቢል የሚፈረድበት አይሆንም።
አሁን ባለው ሁኔታ ገበያና ግብይት ከሸማች ዜጎች ቁጥጥር ውጭ ሆነዋል። የጠዋቱ ለማታ፣ የማታው ለጠዋት . . . ባለበት አይገኝም። ገንዘቡ “የመግዛት አቅሜን ተነጥቄያለሁ” ካለ ቆየ። ሁኔታው ሁሉ አስደንጋጭ ነው። ጀግና ካልመለሰው መሸምጠጡ ነው። እንደ አንዳንድ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሀገራት፣ ሳሙና ለመግዛት ብር በጆንያ ሞልተን በጋሪ እየገፋን ላለመሄዳችን ምንም ዋስትና የለንም። በዋናነት የዚህ ሁሉ ምክንያት ደግሞ ገበያው ባለቤት ማጣቱ ሲሆን፤ ገሳጭም ገልማጭም የለውም። በመሆኑም እንዳሻው ሲፈነጭ ውሎ፣ እንዳሻው ሲፈነጭ ያድራል። (የቤት ኪራይ በሚያስደነግጥ ሁኔታ እየጨመረ ስለ መሄዱም ይኸው የገበያው እብደት ያመጣው ጦስ መሆኑንም ልብ ይሏል።)
የውጭ ምንዛሪ፣ የነዳጅ ዋጋ መናር፣ ጥቁር ገበያ፣ የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም፣ የቁጥጥር መላላት (ወይም አለመኖር)፣ በንግዱ ዓለም የተሠማራው ባለ ሀብት ይሉኝታ ማጣትና ማን አለብኝነት፣ ደላላ-መር የገበያ ሥርዓት መንሰራፋት፣ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ፣ ሕገወጥ ንግድ፣ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት . . . ወዘተ ሁሉ በአንድ ተሰልፈው በምክንያትነት ቢቀርቡ አሁን ላይ እየተስተዋለ ላለው የዋጋ መናር መልስ ሊሆኑ ከቶም አይቻላቸውም። ይህ የአንድ ሰው ድምፅ ሳይሆን ወደ ገበያ የወጣ ሸማች ሁሉ የሚያጋጥመው ነው። እያንዳንዱ ዜጋ እየኖረው ያለ ኑሮ ሆኗል። እስኪ አንድ ሳሙና 60 ብር፣ አንድ ኪሎ ጤፍ መቶ ብር፣ የአንድ ኪሎ ቃሪያን ዋጋ 114 ብር መግባትን ምን ይሏል?
አሁን እንደምናየው መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ግብረ ኃይላት ሲቋቋሙ ነው ። ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን አድርጌያለሁ እያለ ነው። ሃገራዊ የሆነውን የኑሮ ውድነት ችግር በዘላቂነት ለመከላከል ሸማቹም የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ሲያጋጥመው ግዥ ባለመፈጸምና ጥቆማ ከማድረግ ጀምሮ መረጃ በመስጠት ግብረ ኃይሉን በመደገፍ ለመብቱ መቆም እንዳለበት ነው የሚገለጸው። ግን እስካሁን ምን ተገኘ? ከተባለ መልሱ ”ምንም” ይመስላል። ለዚህ ደግሞ ከላይ እንዳልነው አይን ተጨፍኖ በተገለጠ ቁጥር ዋጋዎች ሰማየ ሰማያት ደርሰው መገኘታቸው ነው። ከሦስት ቀን በፊት በ79 ብር ይገኝ የነበረ አንድ (መቀመጫው ወገቡ ላይ የደረሰ) ብርጭቆ ጭማቂ በሦስተኛው ቀን በኋላ ሲሄዱ 100 ብር ሆኖ ሲያገኙት ምን ይላሉ? ወደ 4 ኪሎ ብቅ ካሉ ይሄ ሆነ “በቃ፣ ከዛሬ ጀምሮ ጁስ መጠጣት አቆምን ማለት ነው?” ያለችውን ወጣት አስተያየት ጨምሮ ያለውን) እውነት ያረጋግጣሉና ገበያው አብዷል በሚያስብል ደረጃ ላይ ደርሷል።
የብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፤ “አሁንም በኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ፈተና እየገጠመን ያለው ከዋጋ ግሽበት ጋር በተገናኘ ሲሆን፥ ከአምናው የሚያዚያ ወር ጋር ሲነጻጸር የዋጋ ግሽበቱ 36 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል። ነገሩን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተመዘገበ ያለው የምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ መሆኑ ነው፡፡” በማለት መግለፃቸው ይህንኑ እያልን ያልነውን ከማረጋገጥ በላይ የሚለው የለውም።
ይህንን የገበያ ሁኔታ ለማረጋገጥ በተለያዩ ስፍራዎች በመዘዋወርና ሸማቾችን በማነጋገር ሁኔታዎችን ለማረጋገጥ የተሞከረ ሲሆን፣ ቀዳሚ ያደረግነው ወደ አቅራቢያችን ወደሚገኘውና ከገበያው ጋር ያላሰለሰ ትስስር ወዳለው አንድ ክበብ ነው።
በጉዳዩ ላይ የክበቡ ሥራ ኃላፊ የሆነችውን፣ ወይዘሪት ሃና ኪዳኔን አግኝተን አነጋገርናት። በ“ያው እንደምታውቀው ነው” አይነት አሳሳቅ ነበር የተቀበለችን።
እንደ ሥራ ኃላፊዋ ሃና አገላለፅ፣ ምንም ነገር ባለበት ሁኔታ ለሳምንት አይቆይም። ሁሉም ነገር ከአቅም በላይ እየሆነ ነው። ፓስታ (በኪሎ) 65 ብር፣ ካሮት 60፣ ቀይ ስር 35፣ ጥቅል ጎመን 35፣ ድንች 30፣ ደረቅ እንጀራ 15 (ባለ 20ም አለ)፣ ያልተቆላ አተር 90፣ ባለ5 ሊትር ዘይት 900፣ ፉርኖ ዱቄት 80፣ ጥቁር ጤፍ 86፣ ነጭ (አንደኛው) 100 ብር . . . ነው እየተሸመተ ያለው። ይህ እስካነጋገርናት ቅዳሜ እለት ድረስ ያለ ገበያ ነው።
ወደ 6 ኪሎ – መነን አካባቢ አቅንተንም የሚመለከታቸውን ሰዎች ያነጋግረን ሲሆን፤ አንዷም የናሆም ምግብ ቤት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ እቴነሽ ናቸው።
ወይዘሮ እቴነሽ እንደሚሉት ፤ገበያው ወይዘሪት ሃና ካለችው የተለየ አይደለም። እንደውም እንቁላል፣ ቅቤ . . . እና የመሳሰሉት ሲጨማመሩ ገበያው አናት ያዞራል ባይ ናቸው። “አብዶ አሳበደን። የምግብ ዋጋ ተመን ለማውጣት እንኳን እስኪያቅተን ድረስ ነው እያሻቀበ ያለው።” ሲሉም ነው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ የሚገልፁት።
የገንዘቡስ ጉዳይ ብለናቸውም፣ “የቱ ብር፣ ምን ብር አለና፤ ዝም ብለን ተሸክመን እኮ ነው የምንዞረው፣ ምንም የሚገዛው ነገር የለም።” የሚለው ነበር መልሳቸው።
ጉዳዩን የበለጠ ለመረዳት ከነጋዴው በተሻለ ለሸማቹ ያቀርባሉ የተባሉትን፣ የእሁድ ገበያ ተራዎችንም ለመጎብኘት ሞክረናል።
ባደረግነው ሙከራ መሠረት የተመለከትነው (ሁሉም በኪሎ ነው) ቲማቲም 25፣ ፓፓያ 40፣ ሽንኩርት 30፣ ቀይ ስር 40፣ ድንች 28፣ ቃሪያ 114፣ ምስር 135 መሆኑን ሲሆን፣ ሌሎች ምርቶችም ከሌሎች መደብሮች ብዙም የተለዩ ሆነው አላገኘናቸውም።
ይህ ዘንድሮ ብቻ ሳይሆን ባለፈው ዓመትም ሸማቹን ኅብረተሰብ ለስቃይና ለሸመታ አቅም መዳከም የዳረገ የግብይት ሥርዓት ሲሆን፣ እንደ ማሳያም “ባለፈው ዓመት (ግንቦት 2014 ዓ.ም) በፍጆታ ምርቶች ላይ እየጨመረ የመጣውን የገበያ ዋጋና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት መንግሥት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።” በሚል በዜና እወጃ መልክ የቀረበውን የክልሎች ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል።
ይህም ሆነ ሌሎች ዜናዎች አየር ላይ ሲውሉ፣ መንግሥት የሕዝቡን ድምፅ ይሰማል፤ ችግሩም በዛው ይቀረፋል በሚል ብዙዎች ተስፋ ቢያደርጉም፣ ሁኔታው ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ እዚህ ደርሷል። እዚህ መድረስ ብቻም ሳይሆን፤«የኑሮ ውድነት ጉዳይ የእኛ ኃላፊነት አይደለም» የሚል አስተያየት ከወደ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በተሠራ ዜና አማካኝነት ብቅ ብሏል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ በላይነሽ ረጋሳ ባለፈው ሐሙስ መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ ዘመን ለንባብ አብቅቶት በነበረው ዜና አጠቃላይ የኑሮ ውድነቱን በተመለከተ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንደማይመለከተው፤ እንዲሁም፣ ዋጋ ባልወጣበት ነገር ላይ መሥሪያ ቤታቸው ኃላፊነት መውሰድ እንደማይችል ገልጸዋል። ይህ ያስኬዳል? ወደ ፊት የምናየው ይሆናል።
ይህንን የተፈጠረውን ከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ ወይም የኑሮ ውድነት አስመልክተን የተለያዩ ምሑራንን ለማነጋገር ጥረት ያደረግን ሲሆን፣ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ ፍቃደኛ የሆኑት በቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር፤ አቶ ኤርሚያስ ብርሀን የሚከተለውን አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
መምህር እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሥራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ከፍተኛ የጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ሰዓት ምንም አይነት ጥናትም ሆነ ምርምር በማያስፈልገው መልኩ ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ውድነት ይታያል።
ጉዳዩን ከኢኮኖሚክስ ሕግ አኳያ እንየው ከተባለ የዋጋ ንረት፣ ወይም የኑሮ ውድነት ባለ ድርሻ አካላቱ ብዙ ናቸው። የእነዚህ ባለ ድርሻ አካላት እንቅስቃሴና ተግባር በገበያው ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። አሁን ባለው ሁኔታ እየታየ ያለው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እና የኑሮ ውድነት ስለሆነ ከእሱ አኳያ እንነጋገር የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው “ምክንያቶች” የሚሏቸውንም እንደሚከተለው ገልጸዋቸዋል።
ለዋጋ ንረት ምክንያቶች በርካታ ሲሆን፣ ቀዳሚው የፍላጎትና ምርት አለመጣጣም፣ ማለትም ፍላጎት ከፍ ሲልና ምርት ሲያንስ እውነተኛ የዋጋ ጭማሪ ሊሆን ይችላል። የአንድ ሀገር ፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ሰላም ሁኔታ፣ ስጋት (በተለይ በሸማቹ በኩል ነገ የባሰ ሊወደድ ይችላል፣ ላይገኝም ይችላል ከሚል የሚመጣ ስጋት)፤ ግሽበት፤ሕገወጥ ክምችት መፍጠርና መደበቅ) በተለይ በአንዳንድ ሕገወጥ ነጋዴዎች በኩል ሊታይ የሚችል ሁኔታ ሲሆን፣ እሱም “ምርቱ ነገ ላይገባ ስለሚችል በውድ ልሸጠው እችላለሁ” ከሚል የሚመጣ የግለኝነት ስሜት፤ እጥረት ይኖራል ከሚል የሚመጣ ያልተገባ ሽሚያ፣ የሕግ መላላት፣ የቁጥጥር ማነስ፣ የሕግ ክፍተቶች መኖር ወዘተ ለእንደዚህ አይነቱ የግብይት ሥርዓት (ዋጋ ንረት) ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው።
መምህር፣ የኢኮኖሚ ባለሙያና ተመራማሪው አቶ ኤርሚያስን ስለ መፍትሔዎቹም አንስተንባቸው ነበር። እንደ ባለሙያው ከሆነ መፍትሔውም፣ ልክ ከላይ እንደ ተጠቀሰው ሁሉ፣ በርካታ ባለ ድርሻ አካላት አሉት።
የመጀመሪያውና ትልቁ ሚና የመንግሥት ሲሆን፣ እሱም ሀብት (ሪሶርስ)ን ማከፋፈል ላይ መሥራትን፣ ሰላምና የፖለቲካ መረጋጋትን መፍጠር፣ (እንደ ዘላቂ መፍትሔ) ምርት የሚጨምርበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ መካከለኛና ከፍተኛ ማኑፋክቸሪንግ ሴክተሮችን በማስፋት፣ የሕግና ቁጥጥር ሥርዓትን ማጥበቅና ከሕግ ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ማስተካከል እና የመሳሰሉትን ተግባራት ማከናወንን ይመለከታል።
ከኅብረተሰብ የተደበቀ ምንም ነገር የለምና ከማንም በላይ ሸማቹ ሁሉንም ነገር በቅርብ ያውቃል። በሰፈር፣ በመደብር በአካባቢ፣ … ያውቃል። ከነጋዴው ጋር አብሮ ነው የሚኖረው። በመሆኑም፣ ሕጋዊውን ሕጋዊ ካልሆነው በመለየት በኩል ሊጫወተው የሚችለው ሚና ከፍተኛ ነው። በመሆኑም፣ ላልተፈለገ የዋጋ ንረትና ጭማሪ ከመጋለጡ በፊት የግብይት ሥርዓቱ ሥርዓት እንዲኖረው የማድረግ ድርሻውን መወጣት ይገባዋል። ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው ከመንግሥት ጋር በመሆን ስለሆነ በዚሁ አግባብ መሥራትን ይጠይቃል ይላሉ አቶ ኤርሚያስ። ሸማቹም እንደ አንድ ባለ ድርሻ አካል ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት መሆኑንም ይናገራሉ። በዚህ ደግሞ ተጠቃሚው ማንም ሳይሆን ራሱ ሸማቹ ነው።ስለዚህ ለሕገወጥ ተግባር ተባባሪ ባለመሆን ኃላፊነቱን መወጣት አለበት።
አቶ ኤርሚያስ በነጋዴው ማኅበረሰብ በኩል ያለውንም አንስተዋል። እንደ እሳቸው ሙያዊ አስተያየት ጉዳዩ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፎ በኃላፊነት አብሮ የመሄድ ጉዳይ ነው። ነጋዴው ለሸማቹ አስፈላጊው እንደሆነው ሁሉ፤ ሸማቹ ለነጋዴው አስፈላጊ ባለድርሻ አካል መሆኑን በሚገባ ማወቅ አለበት። በመሆኑም ደንበኛው የሚጎዳበትን መንገድ በፍፁም መፈለግ የለበትም። የሚያስፈልገውና ገበያውን ጤናማ የሚያደርገው የሁለቱ ተደጋግፎ መሄድ ነውና ነጋዴው ለዚህ መርሕ መገዛት ይገባዋል። ተገቢ ያልሆነ ትርፍን መሻት የለበትም፤ ሕገ ወጥ በሆነ ንግድ ላይ መሠማራት የለበትም፤ አላስፈላጊና ምስጢራዊ ክምችትን በመፍጠር የግብይት ሥርዓቱን በግል ጥቅም በመለወጥ አላስፈላጊ መጨናነቅንና ትርምስን በሀገር ላይ መፍጠር አይገባውም። ይህ ሄዶ ሄዶ ራሱን፣ የንግዱን ማኅበረሰብ ነው የሚጎዳው። በርካታ ነገሮችንም ያሳጣል። በመሆኑም፣ ከእንደዚህ አይነቶቹ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ራሱን በማፅዳት ለግብይት ሥርዓቱ ሥርዓታማነት የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት። በዚህ ደግሞ የመጀመሪያው ተጠቃሚ ራሱ ነጋዴው ነው።
ባለፈው ዓመት የነበረውን የዋጋ ንረት ሁኔታ በተመለከተ በርካታ ሥራዎች ተሠርተው የነበረ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ። ከእነዚህም መካከል፤
የገንዘብ ሚኒስቴር በጥቅምት እና ኅዳር 2014 ዓ.ም 4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ እና 12.5 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት መግዛቱ፤ እርምጃውም የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ያለመ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የአዲስ አበባ መስተዳድር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ለመርዳት በማሰብ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ለማቅረብና የእህል የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት እስከ 500 ሚሊዮን ብር ብድር ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ መሠረታዊ ሸቀጦችን በመደጎም ያቀደውን የዋጋ ግሽበት ከሁለት አኃዝ ወደ አንድ አኃዝ ለመቀነስ አቅዶ ሲንቀሳቀስ የነበረ መሆኑ፤
የዚሁ የኑሮ ውድነቱን ችግር ለመቅረፍ፣ በተለይ ሕገወጡን ክፍል ሥርዓት ለማስያዝ የተቋቋመው ግብረ ኃይል “ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ ያለው ግብረ ኃይል ለኢንዱስትሪና ለግብርና ፍጆታ የሚውል ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር የዋጋ ጭማሪ በማድረግ በኅብረተሰቡ ላይ ለከፋ ችግር በሚዳርጉ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ እርምጃ ሲወስድ” የነበረ መሆኑ የሚጠቀሱ ናቸው። ጥያቄው፣ “ዘንድሮስ?” የሚል ነው።
በመጨረሻም፣ ገበያውን ሥርዓት በማስያዝ በኩል መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ የሚያከራክር አይደለም። ለዚህ ማስረጃው ደግሞ ከላይ የጠቀስናቸውና የተከናወኑ ተግባራት ናቸው። አሁንም፣ ሰሞኑን አንድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊ እንደሰጡት፣ ሕገወጥ ንግዱን የሚያበረታታና የ“አይመለከተንም” መግለጫ ሳይሆን መንግሥት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ወገቡን አስሮ ሊሠራና የዜጎችን ኑሮ የተረጋጋ ሊያደርግ ይገባል። የኑሮ ውድነትን በማርገብ ረገድ ትልቁ ድርሻ የመንግሥት ነው። የሀገርን ሰላምና ፖለቲካዊ ሁኔታዎን ማስተካከል፤ አርተፊሻል የኑሮ ግሽበት እንዲፈጠር በሚያደርጉ አካላት ላይ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ተግባራት መሆኑን በመፍትሔነት አንስተዋል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2015 ዓ.ም