እ.አ.አ. በ1908 በአሜሪካዋ ኒውዮርክ ከተማ 15 ሺህ ሴቶች ወደ አደባባይ ወጡ። ሴቶች መምረጥ እንዲፈቀድላቸው እንዲሁም ከስራ ጋር የተያያዙ ጥቅሞቻቸው እንዲከበሩላቸው ጠየቁ። ከዘጠኝ አመታት በኋላ ደግሞ እ.አ.አ. ማርች 8 ቀን 1917 የሩሲያ ሴቶች በሞስኮና ፒተስበርግ ከተሞች አደባባዮችን አጥለቀለቁ። ለአራት ቀናት የዘለቀ አመጽ አቀጣጥለው የመምረጥ መብታቸውን አስከበሩ። ዛሬ ድረስ ለምንዘክረው የሴቶች ቀን መሰረት የሆኑት ሁለቱ አመጾች በወንዶች ለወንዶች በተበጀው ኢፍታዊ ስርዓት ላይ እንጂ ወንዶች ላይ የተካሄዱ አልነበሩም። የእንቅስቃሴዎቹ መገለጫም እምቢተኝነት እንጂ ሞገደኝነት አይደለም።
የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ያዘጋጀው “አማርኛ መዝገበ ቃላት” ሞገደኛ የሚለውን ቃል ሃይለኛ፣ እልኸኛ፣ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ባይ ሲል ይበይነዋል። እምቢተኝነትን ደግሞ አልቀበልም፣ አላደርግም፣ አልታዘዝም ብሎ ይፈታዋል። ካምብሪጅ ዲክሽነሪ (Cambridge Dictionary) በተመሳሳይ መልኩ ለአማርኛው እምቢተኝነት አቻ የሆነውን “REFUSAL” ሲደፈይነው “the act of refusing to do or accept something» ይለዋል። ከሁለቱ ቃላት ሴቶች የበታችነትን አንቀበልም በማለት ለዘመናት ያደረጉትን ትግል የሚገልጸው “እምቢተኝነት” ነው።
በቆይታ ግን አንዳንድ ፌሚኒስቶች ዕለቱን የአመጸ ቀን (በወንዶች ላይ የሚካሄድ) አድርጎ የመቁጥር ዝንባሌ ተጠናወታቸው። «ፌሚኒስት» እየተባሉ የሚጠሩት የወንዶች የበላይነት በነገሰበት ዓለም ባዩት፣ በሰሙት እና በደረሰባቸው በደል በወንዶች ላይ ከፍ ያለ ቁጣና ቅያሜ ያደረባቸው፣ ይህንንም በግለቱ ልክ ለመግለጽ ፍም ሆኖ መቆየትን የመረጡ ሴቶች ናቸው። እንዲህ ያለ ቁመና ላይ ጽንፈኝነት ሲታከልበት ሞገደኝነት ይወለዳል። መምህር ሄኖክ ኃይሌ ሞገደኞቹን ጽንፈኛ ፊሜኒስቶች ሲገልጻቸው፣ አባታችን ሆይ ተብሎ ጸሎት ሲደረግ ለምን እናታችን ሆይ አይባልም ብለው አምባጓሮ የሚያስነሱ ናቸው ይላቸዋል።
ከዚህ ቀደም ለአንድ ጽሁፌ ማዋዣ አድርጌ የተጠቀምኩትን አጋጣሚ ልጨምር። የሴቶች ቀንን ለማክበር በተሰናዳ መድረክ ላይ ንግግር ያደረገች አንድ ሴት በተከታዩ ንግግር ታዳሚውን አስደመመች። “እኛ ሴቶች ባደረግነው እልህ አስጨራሽ ትግል በትምህርቱ ዓለም ከዚህ በፊት በቋንቋ አጠቃቀም ረገድ ለወንዶች ብቻ ሲቀርቡ የነበሩ ትዕዛዛት ለሁለቱም ጾታዎች እንዲሆኑ ተደርገው መቅረብ ጀምረዋል። ለምሳሌ ‘ምረጥ’ ይል የነበረው ትዕዛዝ ‘እዝባር’ እና ‘ጭ’ ተጨምረውበት፣ ምረጥ/ጭ እንዲል ተደርጓል። ሆኖም አሁንም ይቀረዋል። ‘ጥ’ እንድትቀድም እና ‘ጭ’ እንድትከተል መደረጉ የወንዶችን የበላይነት ጠብቆ ለማቆየት የተወጠነ ሴራ ነው” እንግዲህ ሞገደኞቹ ፌሚኒስቶች እንዲህ ናቸው። መቼም መሰል የብሽሽቅና ጽንፍ የመያዝ አካሄዶች እንዲሰፍን የምንፈልገውን እኩልነትና ፍታዊነት ለማምጣት አያግዙም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እየተስተዋለ ያለው የሴቶች ቀን አከባበር ማርች ኤት ወዴት? የሚያሰኝ እየሆነ ነው። በዓሉ ከላይ ባነሳኋቸው ሞገደኛ ፌሚኒስቶች ተጠልፎ በቁጥጥራቸው ስር የዋለ ይመስላል። ወንዶች የሴቶች ቀን ወደሚከበርበት አዳራሽ ዝር እንዳይሉ አድርገው፣ ሴቶች ብቻቸውን የሴቶች ቀንን እንዲያከብሩ የሚያደርጉ ተቋማት እየተበራከቱ መጥተዋል። ማርች ኤት በሚከበርበት አዳራሽ ግድግዳ ላይ “ያለ ሴቶች ተሳትፎ ልማት አይረጋገጥም” እንደሚለው ሁሉ “ያለወንዶች ተሳትፎ የሴቶች መብት አይከበርም” የሚል መፈክር መታየት ነበረበት። እየሆነ ያለው ግን ሌላ ነው፡፡
እዚህች ጋ ኃይለጊዮርጊስ ማሞ ዊል ዱራንት የተባለ ጸሐፊ “The History of Philosophy” በሚል ርዕስ የጻፈውን መጽሐፍ ጠቅሶ ግሪክ ውስጥ በባርነት ይኖር ስለነበረ ኤፒኪተተስ ስለተባለ ሰው ያሰፈረውን ታሪክ ብጠቅስ ሸጋ ነው። አንድ ዕለት ኤፒኪተተስ በማይመች ሁኔተ የራሱ እግር ላይ እንዲቀመጥ በጌታው ይታዘዛል። ኤፒኪተተስ እየተጨነቀ ትዕዛዙን ሲፈጽም ጌታው እየተመለከተው ይዝናናል። ኤፒኪተተስ ጌታዬ ሆይ ከእግሮቼ ላይ እንድነሳ ካልፈቀድክልኝ እግሮቼ ይሰበራሉ ብሎ ተማጸነው። ጌታው ግን ይበልጥ በአገልጋዩ ጭንቀት መዝናናት ያዘ። ከሰዓታት በኋላ የኤፒኪተተስ እግሮች ተሰበሩ። ኤፒኪተተስም ጌታውን “እግሮቼ ይሰበራሉ ብዬ ስነግርህ እንደ አላዋቂ ገምተኸኝ ነበር። እንደምታየው አሁን እግሮቼ ተሰብረዋልና አዋቂነቴን ተረዳህ?” ሲል ጠየቀው።
ጸሐፊው ዊል ዱራንት ኤፒኪተተስ ለጌታው ባቀረበው በዚህ ጥያቄ ውስጥ የሚያስተላልፈው መልዕክት አለ ይላል። ይህ መልዕክት በሥጋ የሚያሸንፍህን በእውቀት እንደማሸነፍ ታላቅ ነገር የለም። በሚደርስብህ ስቃይ ብትጮኽ ትርፉ የሚያሰቃይህን ሰው ማስደሰት ብቻ ነው። የስቃይህ ምንጭ ግን አላዋቂነቱ መሆኑን ለሚያሰቃይህ ሰው ብትነግረው አንተ እንደ ክርስቶስ ትሆናለህ የሚል ነው። ምሳሌ ከሚመሰልለት ነገር ያንሳል ይባላልና የኤፒኪተተስን ታሪክ እዚህ የጠቀስኩት ሴቶች በወንዶች የሚደርስባቸውን በደል አሜን ብለው እንዲቀበሉ አይደለም። በደል የሚያደርስባቸውን አሰራር፣ ባህልና ሥርዓት አብረዋቸው እንዲታገሉ፣ ወንዶችን ማቅረብ እንጂ ማራቅ የለባቸውም ለማለት ነው። ማርች ኤትን በመሰሉ ቀናት ወንዶች የበዓሉ አካል እንዲሆኑ ማድረግ በሴቶች ላይ የሚፈጽሟቸው በደሎች የሚያስከትሏቸውን ግለሰባዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ህብረተሰባዊ ብሎም አገራዊ መዘዞች እንዲረዱና እንዲከለከሉ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ።
እንደ ማርች ኤት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና ባይሰጠውም 80 አገራት የወንዶች ቀንን ያከብራሉ። እለቱ የሚከበረው ወንዶች በዓለም ላይ ያመጧቸው በጎ እሴቶች እየተወሱ፤ አርዓያ የሚሆኑ ወንዶች ለቤተሰባቸውና ለማኅበረሰባቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ እውቅና እየተሰጠ ነው። በአንጻሩ የሴቶች ቀን የሚከበረው ሴቶች የደረሰባቸውን ጭቆናን ተቋቁመው ያገኙትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት በማሰብና ዛሬም ድረስ የቀጠለውን ተጋድሏቸውን ይበልጥ ማቀጣጠል የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ ነው። ሁለቱ ቀናት የሚከበሩበት መንፈስ የሰማይና የምድር ያህል መራራቁ ግልጽ ነው። የሞገደኛ ፌሚኒስቶች አያያዝ ግን የወንዶችን አጋርነትና ስልታዊ ትግል የሚጠይቀውን ይህን ኢፍታዊነትን የመታገል ረጅም ጉዞ ከግምት ያስገባ አይመስልም።
የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ፉምዚሌ ምላምቦ ንጉካ ከሁለት አመታት በፊት የሴቶች ቀንን አስመልከቶ ባደረጉት ንግግግር “በሚቀጥለው ክፍለ ዘመን እንኳን የሥርዓተ ፆታ ኃይል መዛባትን ማስተካከል አንችልም። እዚህ ያለነው ሁላችንም አይደለም መጪዎቹ ልጆቻችን እንኳን ኢፍትሃዊ የሆነው የሥርዓተ ፆታ ተስተካክሎ ሊያዩት አይችሉም” ብለዋል። ይህ ንግግር ከተመጣው መንገድ በላይ የሚቀረው እንደሚረዝም የሚያሳይ ነው። ይህ ጉዞ የሚወስደውን ጊዜ ሴቶች ከወንዶች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ሊያሳጥሩት ይገባል።
በተለይ ኢትዮጵያን በመሰሉ የሦስተኛው ዓለም አገራት ሴቶች የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ለቁጥር የሚታክቱ ናቸው። እነዚህን ጫናዎች ወንዶችን ባገለለ ሁኔታ ለመቅረፍ መንቀሳቀስ ስራውን ይበልጥ ያከብደዋል። በአመት አንድ ቀን በሚደረግ ዘመቻ ብቻም ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት አይቻልም። የሴቶች መብት በሚገባ ይከበርባታል እየተባለ በሚነገርላት አሜሪካ እንኳን ሙሉ መጋቢት (ማርች) ወር “የሴቶች ታሪክ ወር” የሚል ዕውቅና ተሰጥቶት፣ በእያንዳንዷ ቀን የአሜሪካ ሴቶች አስተዋፅኦ ይዘከራል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሴቶች ቀን መሪ መልዕክት ማዘጋጀት የጀመረው እ.አ.አ. ከ1996 ጀምሮ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው መሪ መልዕክት “የኋላውን ማክበር፤ የወደፊቱን ማቀድ” የሚል ነበር። ዛሬም ይህ መሪ መልዕክት ይሰራል። ከኋላ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማጣጣም፣ ወንዶችን ባቀፈ መልኩ የወደፊቱን በማቀድ ከጾታዊ መድሎ የጸዳ ዓለም ለመፈጠር የሚደረገው ትግል ይቀጥላል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም