ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዚያት ከተለያዩ አገራት ጋር ጦርነት አድርጋ አሸንፋለች:: በቅርቡም የዓድዋን እና የሶማሊያን ወረራ ያከሸፈችበት የካራማራ ድሎች ተከብረዋል:: እነሆ በመጋቢት ወር መጀመሪያ ደግሞ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አጼ ዮሐንስ 4ኛ ሕይወታቸውን ያጡበትን የመተማ ጦርነት እናስታውሳለን::
እነሆ ከ134 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት አንድ እና መጋቢት ሁለት የመተማ ጦርነት እና የአጼ ዮሐንስ 4ኛ ሞት በኢትዮጵያ ውስጥ ተከሰቱ:: ‹‹ደርቡሽ›› በመባል የሚታወቁት የሱዳን መሀዲስቶች የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው ጦርነት ከፈቱ:: ይህም ጦርነት በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ለነበሩት ለአጼ ዮሐንስ አራተኛ መሰዋት ምክንያት የሆነው የመተማው ጦርነት ተባለ፤ ታሪኩም በዚህ ሳምንት መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም የተከሰተ ነበር:: በነጋታው መጋቢት 2 ቀን 1881 ዓ.ም ደግሞ መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም በተካሄደው የመተማ ጦርነት በጽኑ ቆስለው የነበሩት ንጉሰ ነገሥት አጼ ዮሐንስ 4ኛ አረፉ::
በመጀመሪያ ‹‹አጼ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት›› የተሰኘውን የተክለጻድቅ መኩሪያ መጽሐፍ ዋቢ አድርገን ታሪኩን በአጭሩ እናስታውስ::
ከጣሊያን ጋር ጦርነት ላይ የነበሩት አጼ ዮሐንስ አራተኛ ደርቡሾች ኢትዮጵያ ላይ ያደረሱትን ጥፋት ለመበቀልና የአገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር የደርቡሾችን ጦር ለሚመራው ዘኪ ቱማል ‹‹መጣሁ ጠብቀኝ! እንደ ሌባ አዘናግቶ ወጋኝ እንዳትል!›› የሚል መልዕክት ላኩበት:: አጼ ዮሐንስ አራተኛ ይህን መልዕክት ልከው ጦራቸውን ይዘው ወደ መተማ ሄዱ::
በዕለተ ቅዳሜ መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም ረፋድ አካባቢ ጦርነቱ ተጀመረ:: አጼ ዮሐንስ ልክ እንደ ተራው ወታደር መሐል ገብተው ሲዋጉ ዋሉ:: ኢትዮጵያውያን ጠንክረው እየተዋጉና ምርኮኛ እየያዙ ሳሉ አንዲት ተባራሪ ጥይት የንጉሠ ነገሥቱ አጼ ዮሐንስ አራተኛ ደረት ላይ አረፈች:: የንጉሡን መቁሰል ያየው ሠራዊታቸውም መደናገጥና መሸሽ ጀመረ::
በጽኑ ቆስለው የነበሩት አጼ ዮሐንስ አራተኛ በማግስቱ መጋቢት 2 ቀን 1881 ዓ.ም አረፉ:: ደርቡሾችም እየተከታተሉ የአጼ ዮሐንስ አራተኛን አስክሬን ይዘው፤ አትባራ ወንዝ ላይ የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ጥቃት አድርሰው፣ መጋቢት 3 ቀን 1881 ዓ.ም የአጼ ዮሐንስ አራተኛን ጭንቅላት ወሰዱ::
የአጼ ዮሐንስ አራተኛ መልዕክት፤ ለዘኪ ቱማል እንደደረሰ በደርቡሾች ዘንድ ሽብር ተፈጥሮ ነበር:: ዘኪ ቱልማ ወታደሮቹን ሰብስቦ ‹‹ምን ይሻለናል? ውጭ ወጥተን ሜዳ ላይ እንጠብቃቸው ወይስ እዚህ በቅጽሩ ውስጥ ምሽግ ውስጥ እንጠብቃቸው?›› ብሎ ሲጠይቅ፤ አህመድ አሊ የሚባለው (የእስላሞች ቃዲ ይሉታል የታሪክ ጸሐፊው ተክለጻድቅ መኩሪያ) ‹‹አይ! ሜዳ ላይ ከወጣን አበሾች ፈረሰኞች ናቸው፤ በፈረስ አጎዳ ይጥሉናል፣ ስለዚህ እዚሁ አጥራችን ውስጥ ሆነን ብንጠብቃቸው ይሻለናል›› ብሎ እንደነበር የታሪክ መጻሕፍት ይናገራሉ::
ደጃዝማች ካሣ ምርጫ (አባ በዝብዝ ካሳ) አጼ ተክለጊዮርጊስን ድል ካደረጉ በኋላ ‹‹ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ግርማዊ ዮሐንስ ራብዓዊ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ፅዮን ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም ነገሱ::
አጼ ዮሐንስ 4ኛ የተንቤንና የእንደርታ ባላባቶች ከነበሩት ወላጆቻቸው ሐምሌ 5 ቀን 1825 ዓ.ም ማይ በሀ (ተምቤን) በሚባል ሥፍራ ነው የተወለዱ። ከመንገሣቸው በፊትም ‹‹ርዕሰ መኳንንት ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ›› በመባል ይታወቁ ነበር። በወቅቱም በትግራይ መኳንንት እግር ተተክተው የአካባቢው ገዢ ሆነው ቆይተዋል።
በሰሜን በኩል በወደቡ አቅራቢያ መገኘታቸውም ከአውሮፓውያን ቆንሲሎች ጋር ወዳጅነት እየመሰረቱ መጠነኛ የትጥቅ ድጋፍ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል:: ደጃዝማች ካሳ ምርጫ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት እንደሚሆኑ እርግጠኛ ስለነበሩ ‹‹ደጃዝማች›› ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ራሳቸውን ለውጭ አገራት መንግስታት በደብዳቤ ያስተዋውቁ ነበር።
ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ከሞቱ በኋላ ለሦስት ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩት አፄ ተክለጊዮርጊሥ፣ ደጃዝማች ካሳን ሊያስፈራሩ አንድ ስልቻ ጤፍ አስቋጥረው ‹‹የሰራዊቴ ቁጥር እንደዚህ የበዛ ነውና አትችለኝም፤ ስለዚህ ገብር!›› ብለው ላኩባቸው:: ደጃዝማች ካሳ ደግሞ በምላሹ የተላከውን ጤፍ አስቆልተው ‹‹የእኔ ሰራዊት ደግሞ ያንተን ሰራዊት እንደዚህ ይቆላዋል›› ብለው ላኩላቸው:: የተናገሩት አልቀረም፤ ደጃዝማች ካሣ አፄ ተክለ ጊዮርጊስን ዓድዋ አካባቢ አሰም በሚባል ሥፍራ ላይ ሐምሌ 5 ቀን 1863 ዓ.ም ወግተው ድል አደረጓቸው::
ከድሉ በኋላም ለበዓለ ንግስናቸው የሚያስፈልገውን ሁሉ ሲያደራጁ ቆይተው ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም በእለተ እሁድ በአክሱም ፅዮን ቤተ ክርስትያን በጳጳሱ አቡነ አትናቴዎስ እጅ ተቀብተው ‹‹ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ግርማዊ ዮሐንስ ራብዓዊ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ፅዮን ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ነው የነገሡ።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ለአገራቸውና ለሃይማኖታቸው ባላቸው ቀናኢነት የሚታወቁት አጼ ዮሐንስ 4ኛ፣ አንዲት ጠንካራ አገር እውን እንድትሆን ያለ ዕረፍት ሲተጉ ኖረዋል። በተለያዩ አቅጣጫዎች አገር ለመውረር ከመጡት ከግብጾች፣ ከቱርኮች፣ ከጣሊያኖችና ከደርቡሾች (መሐዲስቶች) እና ከሌሎች የውጭ ኃይሎች ጋር ተደጋጋሚ ጦርነቶችን አድርገው ነፃ አገርን ለቀጣዩ ትውልድ ያስረከቡ ትጉህ ንጉሥ እንደሆኑ የታሪክ ሰነዶች ያሳያሉ::
አጼ ዮሐንስ አራተኛን በብዙዎች ዘንድ እንዲታወቁ ያደረጋቸው ይሄው በዚህ ሳምንት የምናስተውሰው የመተማው ጦርነት ነው::
አጼ ዮሐንስ 4ኛ ገላባትን፣ ብሎም አምድሩማንንና ካርቱምን በመያዝ የደርቡሽን መንግሥት ለመገርሰስ ዝግጅት መጀመራቸው ሱዳን ውስጥ ጭምጭምታ እንደተሰማ፤ አጼ ዮሐንስ በዋነኞቹ የጦር መሪዎች በእነ ራስ አርአያ ድምፁ፣ ራስ ሚካኤል (መሐመድ አሊ)፣ ራስ ኃይለማርያም ጉግሳ፣ ራስ አሉላ፣ ስልሕ ሻንቆ እና ሌሎችም ታላላቅ የጦር አዛዦች የሚንቀሳቀሱ ክፍለ ሠራዊቶችን በመምራት በቅድሚያ ገላባትን ለመያዝ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸው ጭምር በደርቡሽ ዘንድ ተሰማ።
የገላባቱ ምሽግ ዋና አዛዥ ሸክ በኪ ጡማል በመምጣት ላይ ያለውን ጠላት ከምሽግ ውስጥ ሆኖ መዋጋት ወይስ ገና ከመንገድ ላይ መቁረጥ የትኛው እንደሚሻል አማካሪዎቹን አወያየ። ካለምንም ማወላወል ምሽጋቸውን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ዘዴ መሆኑ እርግጥ ነበር። እንደማዕበል የሚነጉደውን የኢትዮጵያ ሠራዊት ከምሽግ ወጥቶ መመካት የማይታሰብም የማይሞከርም ነበር።
አጼ ዮሐንስን ለመግጠም የተመደበው የዘኪ ጥምር ጦር 80 ሺህ ደርሷል። ከቁጥሩ በላይ ጦሩ ምሽጉን አጥብቆ በመያዝ የመጣበትን ጦር ለመመከት ቁርጠኛ ነበር። አዋጅ ነጋሪዎች በገጠር በከተማው እየዞሩ ሱዳናዊ ሁሉ የዕለት ተግባሩን ትቶ ጠብመንጃውን አንግቶ፣ ጎራዴውን ታጥቆ አገሩን እንዲከላከል የመሪያቸውን ትዕዛዝ አሰሙ። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የዘመቻ ዝግጅት ከተነገረው በላይ ተጠናክሮ መቀጠሉን የደርቡሽ ወታደራዊ ምንጮች ገለፁ። እነዚህ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት መረጃዎችን ያሰባሰቡ የነበሩ ሰላዮች የኢትዮጵያን ሠራዊት እንቅስቃሴ በሚከተለው መልክ አቀረቡት።
‹‹የሀበሻ ሠራዊት እንደሰማይ ከዋክብት እንደባህር አሸዋ ህልቆ መስፈርት የለውም። ሠራዊቱ ሲርመሰመስ ለዓይን እይታ የሚታክት፣ መጨረሻው ከአድማስ ባሻገር የሆነ፣ የዘመቻው ንቅናቄ በሚያስነሳው ምድራዊ ደመና ጸሐይን ያጠቆረ አስፈሪ ኃይል ነው››
ይህ ደማቅ ወታደራዊ ዘገባ የደርቡሾች ዋና ከተማ የነበረችውን አምድሩማንን ከወዲህ ወዲያ በሽብር አናወጣት። ከዕለታት አንድ ቀን ሱዳን በሀበሻ እንደምትተፋ፣ የንጉሡ ፈረስም ኮቴው በፈሰሰው ደም ተውጦ፣ እንደ ወሬ ነጋሪ ከጥፋት በተረፈችው አንዲት ዛፍ ጥግ ታስሮ እንደሚታይ እንደ ትንቢት የሚነገረው አፈ ታሪክ ጊዜው መድረሱና ትንቢት የተነገረለት የሀበሻ ንጉሥ ዮሐንስ እንደሆነ ትንቢት ተናጋሪዎች አስረዱ።
በ1881 ዓ.ም ወርሃ የካቲት መጨረሻ ላይ ንጉሠ ነገሥቱ አጼ ዮሐንስ 4ኛ ጎንደር ከተማን ለቅቀው በመውጣት ሕዝብን ለማጥፋት የተነሳውን ቁርጠኛ ጠላት ለመደምሰስ ሠራዊታቸውን በረድፍ በረድፍ አስከትለው ወደ ገላባት ተመሙ። ከከተማዋ አቅራቢያ እንደደረሱ አጼ ዮሐንስ እንዲህ አሉ::
‹‹እንደ ሌባ ተሽሎክልኮ መጣ እንዳትለኝ፤ ለፍልሚያው ተነስቻለሁና ተነስ!›› ብለው ለደርቡሹ አዋጊና የጦር አዛዥ መልዕክት ሰደዱለት:: ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ከወንዶቹ ሌላ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወይዛዝርት አብረው ተሰልፈዋል። እነዚህ ሴት ዘማቾች የትዳር ጓደኞቻቸውን፣ የእጮኞቻቸውን፣ የወንድሞቻቸውንና የአባቶቻቸውን የሞትና የመከራ ጽዋ ለመቅመስ ኑሯቸውን በትነው፣ ጎጇቸውን ዘግተው ወደ ጦር ሜዳ የዘመቱ ናቸው።
አጼ ዮሐንስ በቀጥታ ወደ ውጊያው ሲገቡ፤ ሠራዊታቸው መሪውን እየተከተለ ከምሽጉ ውስጥ በፉከራና በቀረርቶ እየዘለለ ገባ። ከጦር አውድማው የሚነሳውን አቧራ አውሎ ነፋሱ ሲያነሳው እሽክርክሪት እየሰራ በውጊያው መሀል ሰይጣናዊ ጭፈራውን አቀለጠው። ከወዲያም ከወዲህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለዘመን ፍጻሜ የሚዋደቁ የሚመስሉ ወታደሮች አንዱ ሌላውን ለመለየት በማይቻልበት ሁኔታ የሞትና ሽረት ትግሉ የቀኑን ብርሃን ጽልመት አለበሰው።
ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሐንስ ጦርነቱ መሐል ገብተው ሲዋጉ ያየው የኢትዮጵያ ወታደር መንፈሱ በአንዳች ወኔ እየተፈነቀለ ግስጋሴውን ቀጠለ። የደርቡሾች ጠንካራ ምሽግ መላላትና መሳሳት ጀመረ።
ከደርቡሾች ሰይፍና የጥይት አረር ይልቅ የኢትዮጵያ ጦር የከበደው ነገር በአገር ምድሩ የበቀለው እሾህማ ጥቅጥቅ የቆላ ግራር ነበር። ለደርቡሾች ተደራቢ ምሽግ ሆነላቸው። ሀበሾቹ ግራሩን ግራ ቀኝ ረግጠው እየዘለሉ፣ አንዳንድ ጊዜም እያቃጠሉ ወደ ዋናው የደርቡሽ ማዘዣ ጣቢያ ዘልቀው ለመግባት ሲዋጉ የደርቡሽ ሠራዊት አጋጣሚውን በመጠቀም ጥይቱን አርከፈከፈው። በዚህ የትንቅንቅ ሰዓት ነበር ከማህዲ ሰፈር አምልጠው ለኢትዮጵያ ሠራዊት እጃቸውን የሰጡ ትኹሪሮች (ደቡብ ሱዳናውያን) ጠቃሚ መረጃ የሰጡት።
በደርቡሾች የጦር ሰፈር ደካማው የውጊያ ግንባር ያለበትን ምርኮኞቹ ተናገሩ። የኢትዮጵያ ሠራዊት ለመጨረሻው የሞት ሽረት ድል ወጊያውን አፋፋመ::
በሁለቱም ወገን ከተከፈለ ከባድ የሕይወት መስዋዕትነት በኋላ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንደ ውቅያኖስ ማዕበል እያስገመገመ ከፊት ለፊቱ የቆመውን ሁሉ እየደመሰሰ የደርቡሾችን ወታደራዊ እምብርት ዘልቆ በመግባት የበላይነቱን ተቀዳጀ። ድልን ጨብጦ በመገስገስ ላይ የነበረውን ኃይል በተመለከቱ ጊዜ ከኋላ ሆነው ግፋ በለው እያሉ እልል ሲሉ የዋሉት በሺዎች የሚቆጠሩ የደርቡሽ ሴቶች ልብ የሚነካ እዬዬና ዋይታ ያሰሙ ጀመር።
የኢትዮጵያ ጦር አሁንም ማጥቃቱን በመቀጠልና ያገኘውን ድል በማጠናከር የደርቡሾችን ምሽግ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ። ይህ ግስጋሴ ሀበሾችን ወደ ፍፁም ድል በር የሚያደርሰው ወሳኝ እርምጃ ነበር።
የገላባት (መተማ) ጦርነት ከዚያም ከዚህም የሰው ልጅ እንደ ቅጠል ቢረግፍበትም ድል ፊቷን ወደ ዮሐንስ ማዞሯ አጠራጣሪ አልነበረም። ሐበሾች የደርቡሽን የትጥቅና የስንቅ ማከፋፈያ ማዕከልን ተቆጣጠሩ። የጦር አዛዡ አቡ አንጋ ጦርነቱን ይመራ የነበረው ከዚሁ ሠፈር ሆኖ ነበርና የዮሐንስ ወታደሮች የማዘዣ ጣቢያው መደምሰስን ተከትሎ የደርቡሾችን የሬሳና የቁስለኛ ክምር በማገላበጥ የራሱን የአቡ አንጋን አስክሬን ለማግኘት ፍለጋ ጀመሩ።
ከማዘዣ ጣቢያቸው ሙሉ በሙሉ መደምሰስና ትጥቅና ስንቃቸው በኢትዮጵያ ሰራዊት መማረክ በኋላ የደርቡሾች ወኔ ሟሸሸ። የደርቡሽ ጦር በእጁ የያዘው ጥይትና ሌላ አስፈላጊ የውጊያ መሣሪያ አልቆ መዋጋት በማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ የዮሐንስ ዘማች ኃይል አሸናፊነት እርግጥ ሆነ።
ደርቡሾች ተሸንፈው እግሬ አውጭኝ እያሉ በሚሸሹበት ሰዓት ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሐንስ በአንዲት ጥይት ተመትተው መውደቃቸው በኢትዮጵያውያን ሰፈር ተሰማ። ወሬው እየተቀጣጠለ ጦሩን ግራ አጋባው:: በደርቡሽ ቆራጥነት ያልተፈቱት ሀበሾች በድል አፋፍ ላይ ቆመው የደርቡሽን ሽሽት አሻግረው በሚመለከቱበት ሰዓት በንጉሠ ነገሥታቸው መመታት ድንጋጤ ጥርጣሬና ተስፋ መቁረጥ ወረራቸው። ከድል በኋላ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ በተተኮሰችው ጥይት ምክንያት የኢትዮጵያውያኑ ሠፈር ተስፋ መቁረጥና ትካዜ ገባበት። ካለ መሪ ካለ አስተባባሪ የቀረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ፊቱን ወደ አገሩ በማዞር ጉዞ ጀመረ። ድል ፊቷን ወደ ኢትዮጵያውያን ብታዞርም እንደገና ወደ ደርቡሽ ዞረች::
የተበታተኑት የደርቡሽ ሠራዊቶች እየተሰበሰቡ ወደ ተደመሰሰው ምሽጋቸው መመለስ ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ ድል የቀናው የደርቡሽ ሠራዊት የአጼ ዮሐንስ አራተኛን ራስ ቆርጦ ለመውሰድ ዕድል አገኘ::
የአፄ ዮሐንስ ራስ በአምድሩማን አደባባይ ለዕይታ ቀርቦ እንደበቃ በቆዳ ተለብዶ ወደ ደንጎላ (ዳርፉር ግዛት) ከዚያም አልፎ እስከ ግብጽ ድንበር ድረስ በግመል ተጭኖ እንዲወሰድ ተደርጓል:: እነሆ ዛሬ ድረስ ይህ ታሪክ በጠላትም ሆነ በወዳጅ ወገን ይነገራል::
አጼ ዮሐንስ 4ኛ ከነገሥታቱ ለየት የሚያደርጋቸውም ይህ ታሪካቸው ነው:: ንጉሥ ሆነው ልክ እንደ ተራ ወታደር ሲዋጉ ነው የሞቱት:: እንደ አገር ባላቸው ታሪክ ደግሞ ኢትዮጵያ አገራቸውን የማያስደፍሩ ጀግኖች አገር መሆኗን አሳይተዋል:: የጀግኖችን ታሪክ የምናስታውሰውም ለዚህ ነው::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም