ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በውሃ ዋና ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚዳኙ አምስት ዳኞችን አስመረጠች። ዓለም አቀፉ ውሃ ስፖርቶች ማህበር (ዎርልድ አኳቲክስ) በዓለም አቀፍ ደረጃ በፈረንጆቹ ከ2023 እስከ 2026 ድረስ ውሃ ዋና ውድድርን የሚዳኙ ዳኞችን ስም ዝርዝር ይፋ ሲያደርግ አምስት ኢትዮጵያውያን የውሃ ዋና ዳኞችን ማካተቱን የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ገልጿል። ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በውሃ ዋና ስፖርት ውድድሮችን የሚዳኙ ዳኞችን ስታስመርጥ በታሪክ የመጀመሪያው መሆኑ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዲመሩ የተመረጡት አምስት ዳኞች በእውቀት አሳዬ፣ ጌታነህ ገብረስላሴ፣ በላቸው መላክ፣ ልደታ ገብረስላሴና አደባባይ ዘውዱ መሆናቸውን የዓለም አቀፉ ውሃ ስፖርቶች ማህበር ይፋ ካደረገው ዝርዝር መረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሠረት ደምሱ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ዳኞቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውድድሮችን እንዲዳኙ ያገኙት እድል ዓለም አቀፉ የውሃ ስፖርቶች ማህበር ለአባል አገሮቹ የተሰጠውን እድል በመጠቀም ነው።
ይህም “የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ከመገንባት ባለፈ ኢትዮጵያውያን ጠንክረን ከሰራን እና የሚገኙ መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ ከተጠቀምን በየትኛውም ደረጃ መስራት እንደምንችልና ብቁ ባለሙያዎች እንዳሉን ማሳያ ከመሆኑ ባሻገር በውሃ ዋና ስፖርቶች ጠንክረን እንድንሰራም የሚያደርግ ነው” በማለት ፕሬዘዳንቷ ተናግረዋል።
ፌዴሬሽኑ በውሃ ስፖርት የሀገራቸውን ስም የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን እና ባለሙያዎችን ለማፍራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራና የጀመራቸውን አበረታች ስራዎችም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ወይዘሮ መሰረት አክለዋል።
ፌዴሬሽኑ ባለሙያዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁ እንዲሆኑ ከማገዝ ባሻገር የውሃ ስፖርቶችን ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት የጀመረውን ከዓለም አቀፉ ውሃ ስፖርቶች ማህበር ጋር በቅርበት በመስራት ፕሮጀክት ቀርፆ የሚያገኘውን የገንዘብ ድጋፍ በየክልሉ የሚገኙ የውሃ ዋና የታዳጊ ፕሮጀክቶችን በሥልጠና ቁሳቁስ የማጠናከር ስራ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል።
በዚህም በዘንድሮ በጀት ዓመት ለክልሎችና ከተማ አስተዳደር የሚያደርገውን የቁሳቁስ ስርጭት ድጋፍ መጀመሩን ወይዘሮ መሰረት ጠቁመዋል።
ፌዴሬሽኑ ከቀናት በፊት ለአዲስ አበባ ከተማ ውሃ ዋና ፌዴሬሽን የስፖርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ ከሃያ ዘጠኝ ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ የፑል ቦይ እና የኪክ ቦርድ የስፖርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።
ወይዘሮ መሰረት ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ውሃ ዋና ፌዴሬሽን በተለይ በታዳጊና ወጣቶች ላይ እየሰራ የሚገኘው ስራ የሚያበረታታና ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት በመሆኑ የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽንም የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።
በድጋፍ እርክክቡ ወቅት የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በላይ ደጀን በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ላደረገው ድጋፍ አመስግነው “ለከተማችን ብሎም ለሀገራችን የውሃ ዋና ስፖርት ሁለንተናዊ እድገት ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ እንሰራለን” ብለዋል።
የስፖርት ቁሳቁሶችን የተረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ ውሃ ዋና ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ዳዊት እምሩ እንደተናገሩትም፣ በኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን የተደረገላቸው ድጋፍ ታዳጊ ወጣቶችን ለማሰልጠን የሚረዳና ተተኪዎችን ለማፍራት ፌዴሬሽኑ እያደረገ ላለው ጥረት አጋዥ ይሆናል። የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ትናንትናና ከትናንት በስቲያም ለክልሎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠል ወደ ጋምቤላ ማቅናቱ ታውቋል።
ፌዴሬሽኑ በውሃ ዋና ስፖርት ተተኪና ውጤታማ ስፖርተኞችን ለማፍራት በታዳጊዎች ላይ መስራት የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ በተግባር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የገለጸ ሲሆን፣ በፈረንጆቹ ከህዳር 16 እስከ 20 ታንዛንያ ዳሬሰላም በተካሄደው የዞን 3 የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ዋና ቻምፒዮና ላይ በሁለት ታዳጊ ዋናተኞች መሳተፉ ይታወሳል። በቀጣይም አውስትራሊያ በሚካሄደው የዓለም የውሃ ዋና ቻምፒዮና ላይ በታዳጊዎች ለመሳተፍ እየሰራ ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም