ዘመናዊ ስፖርቶች ከመስፋፋታቸውና ዛሬ ላይ ያላቸውን ቅርፅ ከመያዛቸው አስቀድሞ እንደየአካባቢው ባህላዊ የስፖርት ጨዋታዎችንና ውድድሮች ይካሄዱ ነበር። አንዳንድ ጥናቶችም ለበርካቶቹ ዘመናዊ ስፖርቶች የባህል ስፖርቶች መነሻ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። የበርካታ ባህሎች ባለቤት በሆነችው ኢትዮጵያ የራሷ የሆኑ በርካታ ባህላዊ ስፖርቶች በተለያዩ አካባቢዎች ይከወናሉ፣ እየተከወኑም ይገኛሉ። እነዚህ ባህላዊ የስፖርት እንቅስቃሴዎች ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ተዘውታሪነታቸው እየቀነሰ ሄዶ በገጠር አካባቢዎች ቢገደብም፤ በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ተሰጥቷቸው በፌዴሬሽን እየተመሩ በየዓመቱ የባህል ፌስቴቫል እና ውድድር መድረኮች ይዘጋጃሉ።
በመጠናቀቅ ላይ ከሚገኘው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶም አገር አቀፍ የባህል ስፖርት ውድድር ለ20ኛ ጊዜ እንዲሁም የባህል ፌስቲቫል ለ16ተኛ ጊዜ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት በቤንች ሸኮ ዞን በሚዛን አማን ከተማ ሲካሄድ ቆይቷል። የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከባህል ስፖርቶች ፌደሬሽን እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ይህ ውድድርም ‹‹የባህል ስፖርታችንና ፌስቲቫላችን ለአንድነታችን ለሰላማችን›› በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ ቆይቶ ወደ ማጠቃለያው ተቃርቧል። 9 ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊ በሆኑበት ውድድርም፤ በ11 የባህል ስፖርቶች 884 ስፖርተኞች ተካፋይ መሆናቸው ታውቋል።
ተሳታፊዎች ከስፖርታዊ ውድድሮች ባለፈም የመጡበትን አካባቢ የሚገልጽ የጎዳና ላይ ባህላዊ ልብስ፣ ዘፈንና ውዝዋዜ በማሳየትም ውድድሩን አድምቀዋል።
የባህል ስፖርትና ጨዋታዎች ላይ ትኩረት ያደረጉና፤ የባህል ስፖርትና ጨዋታዎች ምንነት፣ አስፈላጊነት፣ ተግዳሮቶች እንዲሁም ስፖርቱን እንዴት ማሳደግ ይቻላል የሚሉ ዋና ዋና ሀሳቦች የተካተቱባቸው ጥናታዊ ጽሁፎችም ቀርበዋል።
እንደ ገና ጨዋታ ያሉ የባህል ስፖርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተለመደው የሆኪ ስፖርት ጋር ያላቸው ተመሳሳይነት በአገር ውስጥ ከመወሰን አልፎ በኦሊምፒክ እስከመሳተፍ የሚያደርስ መሆኑ ተጠቁሟል። የቀስት ውርወራና የፈረስ ጉግስም ቢሰራበት ጥሩ ውጤት ማምጣት እንደሚችልበት ይታመናል። በእነዚህ ስፖርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሳታፊ ለመሆን እቅድ ተይዞ ጥናቶችም ተጠንተው ወደ ትግበራ በመግባት ስፖርቱን ለማሳደግ መታቀዱን የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጠቁሟል።
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ በቀለ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዓላማ አድርጎ የተቋቋመው የማህበረሰብ ስፖርትን ማስፋፋትና የስፖርት እንቅስቃሴን ማሳደግ መሆኑን ገልፀው፣ የማህበረስብ የስፖርት እንቅስቃሴ ከሚባሉት የስፖርት ለሁሉም እንቅስቃሴዎች ጋር የባህል ስፖርትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማካተት ህብረተሰቡ በሚኖርበትና በሚሰራበት አካባቢ ጤንነቱን እንዲጠብቅ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ያብራራሉ።
በ1970 ዓ.ም በተደረገ ጥናት በኢትዮጵያ ያሉ የባህል ስፖርቶች 293 እንደሚደርሱ ይታወቃል። አሁን ግን ወጥ የሆነ ህግ ተረቆላቸው ውድድር የሚካሄድባቸው 11 ብቻ ናቸው። በቀጣይ ግን በየክልሉ ጥናት ተደርጎ ሁሉም ክልል በመረጠው የስፖርት ዓይነት ተሳታፊ እንደሚሆንም አቶ ተስፋዬ ይናገራሉ። እንደ ገና ያሉ ጨዋታዎችንም ከባህላዊ ስፖርትነታቸው ባሻገር ወደ ዘመናዊ ስፖርት ለማሳደግ ጥረት በመደረግ ላይ ነው። ውድድሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና በኦሊምፒክ ከሚደረጉ ውድድሮች ጋር ተመሳሳይነት ስላለው ኢትዮጵያን በስፖርቱ ለመወከል ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል። ይህንን ለማሳካት ግን አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አስቀድሞ መስራት ተገቢ መሆኑን አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል። ለአብነት ያህል የገና ጨዋታ (ሆኪ) ከአስራ አንድ በላይ ተጫዋችና የውድድር ቁሳቁሶች የሚፈልግ ውድድር በመሆኑ ብዙ ስራ ይፈልጋል።
ተወዳዳሪዎቹን ጨምሮ የማዘውተሪያ ስፍራውንና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች ሲታከሉም ውድ ከሆኑ ስፖርቶች መካከል እንዲመደብ ያደርገዋል። ለዚህም መፍትሄ እንዲሆን የታሰበው ዓለም አቀፍ ስፖንሰሮችን ማፈላለግ እንደሆነም ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል። ለዚህም በስፖርቱ ጥሩ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ሀገራት የሙያና ቁሳቁስ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል። በተጨማሪም ስፖርቱን የሚያስተዋውቁ አሰልጣኞችንም ለማሰልጠን ዝግጅት እንደተጀመረ ተገልጿል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም