የዓለም አትሌቲክስ በተያዘው 2023 የውድድር አመት ከፆታ እኩልነት ጋር በተያያዘ በርካታ ርምጃዎችን በመውሰድ የተለያዩ ለውጦችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ገልጿል። ከነዚህ ርምጃዎች መካከል የዓለም አትሌቲክስ ምክር ቤት ውስጥ ሴቶች አርባ በመቶ መቀመጫ እንዲኖራቸው ማድረግ አንዱ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም ቢያንስ አንድ ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲኖር ይደረጋል ተብሏል።
በዓለም አትሌቲክስ ምክር ቤት ሴቶች አርባ በመቶ መቀመጫ እንዲኖራቸው ለተጀመረው ጥረትም ስፖርቱን ይመራሉ ተብለው ለሚጠበቁ ሴቶች ከወዲሁ የተለያዩ አስተዳደራዊ ስልጠናዎች በበይነ መረብ እየተሰጠ ይገኛል። ይህንንም የዓለም አትሌቲክስ 214 አባል አገራት 2023 መጨረሻ ድረስ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተቀምጧል።
የዓለም አትሌቲክስ በስፖርቱ የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እወስዳለሁ ያለውን ርምጃ በይፋ የገለጸው ትናንት የተከበረውን ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አስመልክቶ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱ ሴባስቲያን ኮ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት ” የዓለም አትሌቲክስ በስፖርቱ የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ቀዳሚ ሆኖ የተለያዩ ርምጃዎችን እንደሚወስድ ይፋ ማድረጉን ስገልፅ ኩራት ይሰማኛል” ያሉ ሲሆን ይህ ርምጃ የዓለም አትሌቲክስ እኤአ በ2016 ተቋማዊ ሪፎርም ለማድረግ ካስቀመጣቸው ግቦች አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኮ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለፁት፣ በዓለም አትሌቲክስ ምክር ቤት በአሁኑ ወቅት ሴቶች ስምንት ውክልና ብቻ ነው ያላቸው። ይህንን ቁጥር በ2023 ነሐሴ ላይ በሚካሄደው ምርጫ ላይ ወደ አስር ለማሳደግ የታሰበ ሲሆን አንድ ሴት ምክትል ፕሬዝዳንትም እንዲኖር ይደረጋል። ይህም በምክር ቤቱ የሴቶችን ቁጥር አርባ በመቶ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል። የዓለም አትሌቲክስ ሴቶች በአስተዳደራዊ ስልጣን ሃምሳ በመቶ ቦታ እንዲኖራቸውም እኤአ እስከ 2027 ጥረቱ እንደሚቀጥል የፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ ይጠቁማል።
ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ባሻገርም ዓለም አቀፉ ተቋም ከፆታ እኩልነት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ርምጃዎችን የሚወስድ ሲሆን የሴት አሰልጣኞች ጉዳይ አንዱ ነው። በዚህም በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች የሴት አሰልጣኞችን ቁጥር ቢያንስ ሃያ በመቶ እንዲደርስ ታስቧል። ይህም እኤአ በ2025 የቶኪዮ የዓለም ቻምፒዮና ተግባራዊ ለማድረግ የታሰበ ሲሆን አባል አገራትም ተግባራዊ እንዲያደርጉ ዓለም አቀፉ ተቋም የተለያዩ ማበረታቻዎችንና ድጋፎችን እንደሚያደርግ አሳውቋል። ለዚህም የዓለም አትሌቲክስ ከተባበሩት መንግስታትና የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በመተባበር የሴት አሰልጣኞችን ቁጥር ወደ አርባ በመቶ የማሳደግ ግብ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ሴት አትሌቶች በተለይም በጎዳና ላይ ውድድሮች የተሻለ እድልና እኩል የሽልማት መጠን እንዲያገኙም ከተለያዩ የውድድር አዘጋጆች ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ኮ፣ ሴት የውድድር ዳኞችን የተመለከተ በርካታ ስራ እንደሚሰራም አብራርተዋል።
በተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ከአትሌቲክስ ጋር በተገናኘ ሴት አትሌቶች ውክልና እንዲኖራቸው ዓለም አቀፉ ተቋም ጥናቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተጠቁሟል።
“በምንኖርባት ዓለም ለሴቶች እኩል እድልን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት በቂ አይደለም፣ እኛ ይህን እኩልነት ቀዳሚ ሆነን ለማረጋገጥ የግድ ጥረት ማድረግ አለብን፣ እውነተኛ እኩልነትን በስፖርታችን እውን ማድረግ አለብን፣ ሴት አትሌቶቻችን፣ አሰልጣኞቻችን፣ ዳኞቻችንና አመራሮቻችን በሁሉም መስክ እኩል ሆነው ራሳቸውን የሚያሳዩባቸው የተመቻቹ ሁኔታዎችን ልንፈጥርላቸው ይገባል፣ ለሌሎች የስፖርት ተቋማትም በዚህ ተግባር ምሳሌ መሆን እንችላለን” ያሉት ኮ፣ ሴት አትሌቶችንና ባለሙያዎችን በተለይም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከሚደርስባቸው ጥቃት ለመጠበቅ ዓለም አቀፉ ተቋም የሚዘረጋቸው አሰራሮች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።
ኔልሰን የተባለ ተቋም በሰራው ጥናት መሰረት ሰባ አራት በመቶ የሚሆኑ የአትሌቲክስ ደጋፊዎች የዓለምን አትሌቲክስ በበላይነት የሚመራው ተቋም የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኛና ተጨባጭ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ያምናሉ። በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን የገለፁት ኮ፣ የዓለም አትሌቲክስ ከፆታ እኩልነት ጋር በተያያዘ እየወሰደ የሚገኘውን እርምጃዎች ከግብ ለማድረስ ሁሉም የአትሌቲክስ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም