ሴትነት ሲነሳ ጥበብ የተሞላበት ድል አድራጊነት እንደሆነ ለመረዳት አያስቸግርም፡፡ ከትላንት ታሪካችን ጀምሮ ዛሬም ድረስ በታላላቅ የስልጣን ደረጃ ተቀምጠው ኃላፊነታቸውን በትጋት የሚወጡ እልፍ ሴቶች ስለመኖራቸው ህያው ሥራቸው ምስክር ነው።
ሀገር ሚዛንዋን ጠብቃ እንድትቆም የሴቶች ሚና ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ ወደ ትላንትና ታሪካችን መለስ ብለን ስንቃኝ ለሁሉም ነገር መነሻ የሆነው ሐሳብ ነው፤ ከሐሳብም የተመረጠና ድል የሚያጎናፅፍ ጥበብ የተሞላበት ሐሳብ በማመንጨት ታሪክ የሚዘክራቸው ዝነኛዋ እቴጌ ጣይቱ በመቀሌ ጦርነት ላይ ያቀረቡት የጦር ስልት ዋነኛው ጉዳይ ነው፡፡
እቴጌ ጣይቱ ከተለመደው የጦር ስልት ወጣ በማለት በጣልያኖች አጠገብ የነበረው የውኃ ኩሬ (ምንጭ) በቁጥጥር ስር እንዲውል በማዘዝ ጣልያኖች በውኃ ጥም ምክንያት እንዲማረኩና እንዲሸነፉ ማድረግ ችለዋል፡፡
ከእቴጌ ጣይቱ ጋር የዘመቱ በርካታ ሴቶች ለጦር ምግብ ከማቅረብ አልፈው የጦር መሳሪያ ያቀርቡ ነበር፤ በዚያ ጊዜ ታዲያ ሴቶች ‹‹ልብ ሳይቀር ያቀርቡ ነበር›› ሲል ፀሐፊ በእውቀቱ ስዩም ከአሜን ባሻገር በሚለው መፅሐፉ ላይ ይጠቅሳል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታላላቅ ገድል ከፈፀሙት ከእቴጌ ጣይቱ በተጨማሪ በወቅቱ አብረዋቸው የዘመቱ በርካታ እህቶች፣ ሚስቶችና እናቶች ስለመኖራቸው ታሪክ ይነግረናል። ከእነዚህም መካከል በኪነጥበቡ ዘርፍ ብዙ ያልተነገረላቸው አዝማሪ ጻዲቄ ለዓድዋ ድል ባበረከቱት አስተዋጽኦ ድርሻቸው ከፍ ያለ ቢሆንም አልተዘመረላቸውም፡፡
ከዘማች አዝማሪዎች መካከል አንፀባራቂ የነበረችው አዝማሪ ጻዲቄ ዛሬ ተረስታለች፡፡ አዝማሪዋ በጦር ሜዳ የጀግኖች ልብ ትቆሰቁሳለች። የመቀሌ ውጊያ ላይ ጣልያኖች እርቅ ሲያስቡ እንዲህ ስትል ትችት አቅርባ ነበር፡፡
“አውድማው ይለቅለቅ፤ በሮችም አይለቁ
ቀድሞም ያልሆነ ነው፤ ውትፍትፍ ነው እርቁ”
አብዛኛው ዘማች ገበሬ ስለነበረ ጻዲቄ ጦርሜዳውን ባውድማ፤ አርበኞችን በበሬ መስላ መግጠሟ ነበር፡፡
ዋልተር ፕለውደን የተባለ በዘመነ መሳፍንት ዘመን ኢትዮጵያን የጎበኘ የውጭ ዜጋ እንደመዘገበው፤ የወሎ ኦሮሞ ሴቶች ጦር ሜዳ ላይ ከወገን ጦር ጀርባ በመሆን ወኔ የሚቀሰቅሱ ዘፈኖችን ይዘፍናሉ፤ የጀግንነት ቅኔዎች ይቀኛሉ፤ የሚሸሽ ወታደር ሲያዩ ፊቱን ወደ ጠላቶቹ እንዲያዞር ይገስፃሉ፤ ይህ በወሎ ብቻ የተወሰነ አይደለም በሁሉም አቅጣጫ እንጂ፡፡
ዘመናዊ አዋጊ መኮንን ጠላቶቹ ወደፊት እንዲሄዱለት ሲፈልግ ከኋላ እየተከተለ ባቀባበለው ሽጉጥ እያስፈራራ ይገፋቸዋል፤ ሲሸሽ በተገኘ ወታደር የሞት ፍርድ የሚፈረድበት አጋጣሚም ነበረ፡፡ ይህ እንዳይሆን ቀላሉ መንገድ ሴቶች ከወንዶች ጀርባ እንዲሰለፉ ማድረግ ነው፡፡ ወታደር በሚስት ወይም በእህት እየታየ እንደሆነ ሲገባው የቆጠባትን ጉልበት ከለገመም ይበረታል፡፡
በወቅቱ እቴጌ ጣይቱ ከሴት ሰራዊቷ ጋር ሆና ጥቁር ጃንጥላ አስይዛ፤ በባዶ እግሯ እየተራመደች ከሰራዊት ጀርባ ትከተላለች፤ ድንገት ሰራዊቱ የጠላት ጦር ተጭኖት እንደ መሸሽ ሲል እቴጌ፤ አይዞህ አንተ ምን ሆነሃል ‹‹ድሉ የኛ ነው በለው›› ሲሉት ሰውየው የሰማው ቃልና እቴጌ ባያቸው ጊዜ ፀጥ ብሎ ይዋጋል፡፡ ወኔ እንደ ሰውነት ክፍላችን በተፈጥሮ ይዘነው አንወለድም፤ ጀግንነት የማህበራዊ ግኑኝነት ውጤት ነው፡፡
በዓድዋ ድል ማግስት ከተገጠሙ ግጥሞች መካከል የትኞቹ አዝማሪ ጻዲቄ እንደሆኑ ባይታወቁም ብዙ ቀስቃሽ ግጥሞችን በመግጠም ትታወቃለች፡፡ ከግጥሟ የተነሳም ሃኪም መሬብ የተባለ ፈረንሳዊ ጎብኚ ከዝነኛው የስፓርታ የጦር ሜዳ ገጣሚ ጋር አወዳድሯታል፡፡ አዝማሪዋ በዓድዋ ጦርነት ላይ ባደረገችው አስተዋፅኦ ሽልማትና የወይዘሮነት ማዕረግ ተቀዳጅታለች፡፡
በአጠቃላይ የሀገር ነፃነትና ፍትህ ለማስፈን እስከ ዛሬ ድረስ የሴቶች ሚና ትልቅ ቢሆንም እንደ ሰሩት ገድል እና ብዙ ልፋት የሚገባቸው ክብር መስጠት ላይ የሚቀር ብዙ ነገር አለ። ለአብነትም አሁን በከፍተኛ ስልጣን ሆነው ሀገር የሚመሩ ሴቶች ላይ አላስፈላጊ ትችቶች ይሰነዘራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ‹‹አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ›› እንደሚባለው የማህበረሰቡ ግማሽ አካል የሆኑትንና ትልቅ ድርሻ ያላቸውን ሴቶች ማግለል በመሆኑ እንደ አገር ወደ ኋላ ያስቀረናልና ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ሄርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም