ትውልዷና እድገቷ በውቢቷ ባህርዳር ከተማ ነው። የፊደልን ሀሁ የቆጠረችው እዚያው ባህርዳር በሚገኘው በባህርዳር አካዳሚ ሲሆን፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም በባህርዳር አካዳሚ ተከታትላለች። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሴቶች ድካምና ዘርፈ ብዙ የሆኑ ጫናዎችን እያየች አድጋለች። ጊዜ ዑደቱን ጠብቆ ቢነጉድም የልጅነት አእምሯዋ መዝግቦ የያዘውን የእናቶችን ችግር፣ ድካምና እንግልት ቸል ማለት አልሆነላትም።
በአእምሯዋ ጓዳ የሚያንጎዳጎደው የእናቶችና የሴቶች ድካም እንዲሁም እንግልት እንዴት ማቅለል ይቻል ይሆን በማለት አውጥታለች አውርዳለች። ለጥያቄዋ ምላሽ እስክታገኝ ድረስ በውስጧ ማብሰልሰል አላቋረጠችም። ሀሳቧ ከሀሳብነት ተሻግሮ እውን እስኪሆን እረፍት ያልነበራት በመሆኑ ዛሬ እናቶችንና ሴቶችን ያግዛል ባለችው ተግባር እርምጃዋን አንድ ብላ ጀምራለች።
የእናቶችንና የሴቶችን ድካም እንዲሁም እንግልት ለመቀነስ ቴክኖሎጂን አጋዥ በማድረግ ‹‹ሞግዚት ዶት ኮም›› የተሰኘ መተግበሪያ በመፍጠር ‹‹ሀ›› ብላ ወደ ሥራ የገባችው እንግዳችን ወጣት ሳምራዊት ታረቀኝ ትባላለች። የወጣቷን የሥራ ፈጠራ፣ የሕይወት ልምድና ተሞክሮ የሴቶች ቀን በሚከበርበት በዛሬው ዕለት ያቀረብነው ለብዙ ሴቶች ተምሳሌት መሆን እንደምትችል በማሰብ ነው። መልካም ንባብ።
የእናቶችንና የሴቶችን ድካም ለማቅለል ቆርጣ የተነሳችው እንግዳችን ወጣት ሳምራዊት፤ ከአምስት ሴት እህቶችና ከአንድ ወንድሟ ጋር አብራ አድጋለች። ከአስተዳደጓ ጀምሮ በቅርበት የምታየው ነገር ሁሉ ለሴት ትልቅ ትኩረት እንዲኖራት አድርጓል። እናቷ ጠንካራ ሠራተኛ ስለነበረች የሥራ ትጋትና ብዙ ነገሮች ከሷ ተምራለች። ሆኖም ግን በአካባቢዋ የምታያቸው ሥራ ለመሥራት የሚወጡ እናቶች ልጅ ሲወልዱ ከልጅ የሚበልጥ ነገር የለም በሚል ሥራ ትተው ወደ ቤት ሲመለሱ አስተውላለች። ይህ ደግሞ ስለጉዳዩ አብዝታ እንድታስብበት አድርጓታል።
በአእምሯ ለሚመላለሰው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ጠንክራ መማር እንዳለባት የገባት ሳምራዊት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አቀናች። የመጀመሪያ ዲግሪዋን በኤሌክትሪካል እና ኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ ትምህርት ተመርቃ በዩኒቨርሲቲ ለሁለት ዓመታት በረዳት መምህርነት አገልግላለች። ሁለተኛ ዲግሪዋን ለመማር ወደ ሕንድ ሀገር ባቀናችበት ቅጽበት ታዲያ የልጅነት አእምሯ የመዘገበው በውስጧ የተጸነሰው ሀሳብ ሊወለድ የሚችልበት አጋጣሚ ተፈጥረላት።
በሕንድ አገር በትምህርት ላይ በነበረችበት ጊዜ ሰዎች ቴክኖሎጂ ተጠቅመው በቀላሉ ሕይወታቸውን እንዴት መምራት እንደሚችሉ መመልከቷ መንፈሳዊ ቅናት እንዳሳደረባት ትናገራለች። የሰው ልጆች ሕይወት ቀላል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ውለው ብዙ ነገሮች ሲሰሩ ስትመለከት በእጅጉ ተገረመች። በዙሪያ ያሉ ወደ ውስጧ ያስገባቻቸው እናቶችን ውል አሉባት። ቁጭት ውስጧ ገብቶ ያንገበግባት ጀመር።
በሀገሯ ያሉ ብዙ ጠንካራ መሥራት እንዲሁም መማር የሚፈልጉ እናቶች በወሊድ ምክንያት የሚያግዛቸው ሰው በማጣት ሥራቸውን ሲለቁ በቅርበት እያየች ያደገችው ሳምራዊት፤ ይቺ እናት የሚያግዛት ብታገኝ ሥራዋን አትለቅም ነበር ትላለች። እናቶች ሠርተው የተሻለ ነገር መፍጠር ሲችሉ በዚህ መልኩ መገደባቸው በእጅጉ የሚቆጫት መሆኑን ትናገራለች።
‹‹ቴክኖሎጂ መሠረት ያደረገ አንድ የሆነ ዘዴ (ሲስተም) ቢፈጠር እናቶች ከሥራ ውጭ አይሆኑም፣ ድርጅታቸውንም አይለቁም፤ ትምህርታቸውንም አያቋርጡም፣ ከህልማቸውም አይነጣጠሉም›› የምትለው ሳምራዊት፤ እሷን መርዳት ቢቻል ልጇቿን በአግባቡ ታሳድጋለች፤ ቤተሰቦቿንም ትረዳለች። ሥራዋን በአግባብ ትሰራለች፤ ሕልሟንም ትኖራለች የሚል ቁጭት አሳድሮባታል።
ሕንድ ሀገር ያየችው ዲጅታል ሲስተም በጣም አስደሳች እንደሆነ የምትናገረው ሳምራዊት፤ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ እንዲህ እንደአሁኑ በዲጅታል ሲስተም የሚሰሩ ሥራዎች እምብዛም እንዳልነበሩ ታስታውሳለች። በሕንድ ቆይታዋ የመጀመሪያው ቴክኖሎጂ ምን ያህል የሰዎችን ሕይወት ቀላል እንዳደረገላቸው ማስተዋል ችላለች። ሁለተኛው ደግሞ ሲስተሙ በራሱ እምነትን መፍጠር መቻሉን ተመልክታለች።
በዚያ ያጋጠማትን አጋጣሚም አጫውታናለች። ‹‹እኔ የልብስ ብራንድ ለመስራት ፈልጌ ሎጎውን ዲዛይን አድርጌ የምፈልገው ልብስ በኦንላይን አዘዘኩ›› የምትለው ሳምራዊት፣ ትዕዛዙን ስፈጽም እከፍላቸዋለሁ በሚል ያዘዘችው ትዕዛዙ በታዘዘው መስፈርት መሠረት ተሰርቶ ያለችበት መምጣቱ አግራሞት ፈጥሮባታል። ‹‹ይህንን ትዕዛዝ ስልኬን ባላነሳ ወይም አልፈልግም ብላቸው ለሌላ ሰው የሚሸጡት ነገር አይደለም›› የምትለው ሳምራዊት፤ ይህ የሚያሳየው እምነት የተሞላበት በቀላል መንገድ መገበያየት የሚያስችል ስርዓት መፍጠር በመቻላቸው ነው ትላለች።
በአገር ውስጥም እንዲህ ያለ ስርዓት መፍጠር ባለመቻሉ ነገሮች መራዘማቸው፣ አድካሚና አሰልቺ መሆናቸውን ታነሳለች። ሳምራዊት፤ ለቴክኖሎጂ ቅርብ በመሆኗ ይህንን ሲስተም ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ብዙም አልከበዳትም። ሕንድ አገር እያለች በንድፈ ሀሳቡን (በፕሮፖዛል) አዘጋጅታለች። ወደ ሀገሯ ስትመለስም ሀሳቧን እውን ለማድረግ ቴክኖሎጂና ሙያውን አንድ ላይ ማስኬድ የሚያስችል ዘዴ ለመፈለግ ጥናት ማድረጓን ታወሳለች። እነዚህን ሁለቱን ሲስተሞች በአንድ የያዘ ፤ በደንብ ያልተነካ እና ብዙ ሰው ያላየው ዘርፍ የልጆች እንክብካቤ ሆኖ አግኝታዋለች። ያን ጊዜ ነበር በሀሳብ የነበረው ‹‹ሞግዚት ዶት ኮም›› መወለድ የቻለው።
ሳምራዊት የፈጠራ ሀሳቧን እውን ለማድረግ በምታደርገው ጥረት ብዙ መሰናክሎችን ማለፍ የግድ ሆኖባታል። ‹‹የቴክኖሎጂ እውቀቱ ቢኖረኝም የቢዝነስ እውቀት አልነበረኝም›› የምትለው ሳምራዊት፤ ለዚህም ስለቢዝነስ የሚያስለጥኑ አካላት መፈለግ የመጀመሪያ ሥራዋ ነበር። ያኔ ነበር በልጆች እንክብካቤ መሥራት እንደምትፈልግ በማሳወቅ ሀሳቧን ይዛ ‹‹ቡሉሙን ኢትዮጵያ›› የተሰኘ የቴክኖሎጂ ተቋም የተቀላቀለችው። በዚያም ለስድስት ወራት ቆይታ ካደረገች በኋላ በሀሳብ ያደገው ‹‹ሞግዚት ዶት ኮም›› 2014 ዓ.ም ተመሠረተ።
‹‹ሞግዚት ዶት ኮም›› ወላጆችን ከሞግዚት ጋር የሚያገናኝ የልጆች እንክብካቤ ላይ የሚሰራ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ሥራውን ሲጀምር ትልቁ ተግዳሮት የነበረው በቂ የሆኑና የሰለጠኑ ሞግዚቶች ማግኘት አለመቻል ነው። ይህ ደግሞ ድርጅቱ ሞግዚቶችን ከማገናኘት ባሻገር ሞግዚቶችን ማስልጠን ላይ ትኩረት እንዲያደርግ አስችሎታል። ከተለያዩ ስልጠና ተቋማት ጋር በአጋርነት በመስራት ለበርካታ ሞግዚቶች ስልጠና መስጠት ተችሏል። ስልጠናውም ለብዙ እናቶች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል።
ሳምራዊት እንደምትለው ‹‹በአንድ በኩል ብዙ ሥራ የሚፈልጉ ሴቶች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ልጆቻቸውን የሚንከባከቡላቸው ሞግዚት ፈላጊ ብዙ ሠራተኛ እናቶች አሉ›› እነዚህ ሁለቱን የማገናኘት ተመጋጋቢ ሥራዎች ናቸው። ሠራተኛ የሆኑ እናቶች የሚፈልጉት የሰለጠነች፣ ሥራውን የምታከብር እና ታማኝ ልጅ ተንከባካቤ ሞግዚት ነው። ለሞግዚቶችም የሥራ እድል በመፈጠሩ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩበት እና ለእናቶች ደግሞ ሥራቸውን ከመተው ሙሉ እምነታቸውን የሚጥሉባቸው ሞግዚቶች ሰጥተው እንዲሰሩ ማድረግ ተችሏል ትላለች።
‹‹በአገር ውስጥ ተሞክሮ ብዙ ስልጠናዎች ቢሰጡም ሥራ መፍጠር ላይ ግን ችግር አለ›› የምትለው ሳምራዊት፤ አንዲት ሞግዚት ሦስት ወይም አራት ሰርተፊኬት ሊኖራት ይችላል። ድርጅቱ ሥራ መፍጠር ላይ ያለውን ክፍተት እየሞላ መሆኑን ትናገራለች። ስልጠና የተሰጣቸው ሞግዚቶች ከወረዳ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ተመልምለው የሚመጡት እናቶች ናቸው። የስድስት ወር፣ የሦስት ወርና የአርባ አምስት ቀናት ስልጠናዎች ያለምንም ክፍያ በነጻ እንዲወሰዱ መደረጉን ተናግራለች።
ሞግዚት ዶት ኮም በ20 ሞግዚቶች ሥራ መጀመሩን ያነሳችው ሳምራዊት፤ አሁን ላይ 600 መቶ ሞግዚቶች በፕላት/ፎርሙ ላይ ተመዝግበዋል። ከእነዚህ ውስጥ 300 ለሚሆኑ ሞግዚቶች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። በአንድ አመት ጉዞ ውስጥም እጅግ አስደሳች ሥራዎችን ሰርቷል ትላለች። ድርጅቱ በርካታ ተግዳሮቶችን በማለፍ ለእናቶች እፎይታ መሆን እንዲሁም ለሞግዚቶች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ትናገራለች።
ሞግዚት ዶት ኮም የሚሰጠው አገልግሎት ዘርፍ ብዙ ሲሆን የመጀመሪያው 80 በመቶ የሚሆነው አገልግሎት በተመላላሽነት የሚሰሩ ሞግዚቶችን ማገናኘት ነው። ሁለተኛው በቋሚነት ቤተሰቦች ውስጥ የሚኖሩ ሞግዚቶችን ማገናኘት ነው። ሦስተኛው የአዛውንት እንክብካቤ አገልግሎት ሲሆን፤ አራተኛው ደግሞ አስታማሚነት የሚሰጡ አገልግሎቶች ናቸው። አምስተኛ አራሶችን እንክብካቤ (ምትኬ የተባለ) አገልግሎቶች ያሉት ነው።
ድርጅቱ ዓላማ አድርጎ የተነሳው ሲሰተም አስተማማኝ የሆነ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ነው። አሁንም ለብዙ ወላጆች ተደራሽ ለመሆን ብዙ ሞግዚቶች በመቅጠር አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ዋና ዋና ከተሞችን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
ወደዚህ ሥራ ስትገባ የከበዳት ለሥራ ያለው አመለካከትና ለሥራ የሚሰጠው ክብደት እንደሆነ የተናገረችው ሳምራዊት፤ እኛ የምናስበው የሚከፈለንን እንጂ ከእኔ ምን ይጠበቃል የሚለው አናስብም ትላለች። አሁን ላይ ያሉን የሥራ ባህሪያት እንደሀገር ትልቁ ተግዳሮቶቻችን ናቸው። ሥራውን ለማገናኘት በሚደረገው ጥረት ወላጆች ወይም ሥራውን ፈላጊዋ ሞግዚት በተቀጠሩበት ሰዓትና ጊዜ አንዳቸው ላይገኙ እንደሚችሉ ትናገራለች። በዚህ የተነሳ ድርጅቱ የራሱን የሥራ ባህል መፍጠር ችሏል። የድርጅቱ ሠራተኞችም ሆኑ ተቀጣሪዎችም በእኔነት ሰሜት ሥራዎችን እንዲሰሩ ሆኗል።
ድርጅቱ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ 10 ሺ ለሚሆኑ እናቶችና ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅዶ እየሰራ ነው የምትለው ሳምራዊት፤ ሞግዚት ዶት ኮም የቴክኖሎጂ ድርጅት ብቻ ሳይሆን የስልጠና ተቋም እንዲሆን ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን ትናገራለች። በዩኒቨርሲቲ እና በኮሌጅም ያሉ ተማሪዎች ጭምር ስልጠናዎች እንዲወሰዱ በማድረግ በትርፍ ጊዜያቸው መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ ይመቻቻል ብላለች።
አሁን ላይ በዌብ ሳይት ብቻ የነበረው አገልግሎት የሞባይል መተግበሪያ እና የጥሪ ማዕከላት እንዲኖሩት ለማድረግም እየተሰራ እንደሆነ ያነሳችው ሳምራዊት፤ ድርጅቱ በአፍሪካ ቴክኖሎጂውንም ሆነ ሥነ ምግባርን የያዘ ጠንካራ የሆነ የእንክብካቤ ተቋም ለመፍጠር ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነው የተናገረችው።
ሥራ በማጣት የተንገላቱ ወጣት ሴቶች ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ማሰብ አለባቸው የምትለው ሳምራዊት፤ የራስን ሕልም ለመኖር በርካታ ውጣ ውረዶችን ለማለፍ መገደድም እንዳለ ማወቅ ይገባል ትላለች። አንድ ደረጃ ሳይረገጥ አስረኛው ደረጃ ላይ አይደረስምና ፤ እራስ ላይ ኢንቪስት በማድረግ ዘመኑ የሚጠይቀውን እውቀት በመያዝ በሁሉም ቦታ ተፈላጊ መሆን ይቻላል ትላለች። አሁን መሥራት የማንፈልገው ነገር መሥራት ነገ የምንፈልገው ሕልማችን ላይ ለመድረስ እንደመሰላል ነው የምትለው ሳምራዊት፤ በራስ ተስፋ አለመቁረጥ፣ ችግሮች በሚደራረቡበት ጊዜ መጨረሻ ናቸው ብሎ አለማሰብ እና ወጣትነት በማሰብ በጣም ብዙ እድልና ተስፋ ከፊታችን እንዳለ በጥልቀት ማሰብ ይገባል ትላለች።
‹‹ሥራው ባልጀምረው ኖሮ ውስጤ ያለው ኃይል እኔን ይበላኝ ነበር›› የምትለው ሳምራዊት፣ ብዙ ልምዱ ሳይኖራት የራሷን ሥራ መጀመሯ በጣም እንዳስፈራትም አልሸሸገችም። ‹‹ዛሬ በወጣትነቴ ይህንን ኃላፊነት ካልወሰድኩ መቼም አልወሰድም በሚል ጽኑ መንፈስ መነሳቷን ትናገራለች። ዛሬ በሕይወት አድርገዋለሁ የምለው ነገር ዛሬ ካላደረግኩ መቼም አላደርገውም፤ ስለዚህ ማድረግ አለብኝ፤ ማየት ያለብኝ ማየት አለብኝ ብዬ ወሰንኩ ካልተሳካ እማርበታለሁ። እግዚአብሔር ይረዳኛል፤ መወጣት እችላለሁ›› በሚል በድፍረት እንደገባችበት ትናገራለች።
በዚህም ያጋጥሙኛል ብላ ያልጠበቀችው ብዙ እድሎች እንዳጋጠሟት የምትናገረው ሳምራዊት፤ አንድን ሥራ ለመጀመር መወሰን፣ ማየትና መጀመር በጣም አስፈላጊ ነገሮች እንደሆኑ ትናገራለች። በዚያ መንገድ ውስጥ ደግሞ ሌሎች በሮች ይከፈታሉ፤ የተወሰነ ጭላንጭል ብርሃን ሲታይ ያንን እየተከተሉ መሄድ ያስፈልጋል ትላለች።
‹‹የመጀመሪያ ሴት ፕሮፌሰር፣ የመጀመሪያ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመሳሰሉት የመጀመሪያ የሚባለው ስሞች እስኪቀየሩ ድረስ መስራት አለብን›› የምትለው ሳምራዊት፤ ሁላችንም ሴቶች በተሰማራንበት የሥራ መስክ ጎልተን በመውጣት ለሚቀጥለው ትውልድ ነገሮች ቀላል ማድረግ እንችላለን ትላለች። በመጨረሻም ሴት ሆይ በርቺ! ስትል በአጽንኦት በመስጠት መልዕክቷን አስተላልፋለች።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም