ባደጉት አገራት የታሪክ አዛቢነት እና በራሳችንም ቸልተኝነት ጥሩ እና ጠቃሚ የሆኑ ባህሎችን ፤ ፖሊሲዎች ፤ አመለካከቶችን፤ የኪነ ህንጻ ጥበቦች እንደው በአጠቃላይ የጀብዱ ታሪኮች ሁሉ ከነጮች እንደቀዳን ተደርጎ ይቀርባሉ።
ለአብትነት ያህል የተወሰኑትን ላንሳና ወደ ዛሬው ቁም ነገሬ እገባለሁ። የጢስ አባይን መነሻ አገኘ ተብሎ የሚነገርው ከወደ ምእራቡ የመጣ ሰው ነው፤ ጣና ላይ ሲኖር የነበረውስ ያገሬ ገበሬ ? እሱማ ሲኖርበት የቆየው ከአባቶቹ የወረሰው ፤ በመኖር ያገኘው እውቀት ነውና አገኘሁ ብሎ ስላላወራ ያገኘው ምእራባዊው እንደሆነ ይነገራል።
ልክ እንደዚሁ ሁሉ የጤፋችንም ታሪክ አስገራሚ ነው ። ኢትዮጵያ ስትፈጠር ጀምሮ ስንበላው የቆየነውን ጤፍ ምእራባዊቷ አገር አዲስ ያገኘሁት ግኝት ነው ስትል ለዓለም አስታወቀች። ልጁ ቀማኛ አባቱ ዳኛ ነውና ነገሩ እኛ ብንጮህ ማን ሰምቶን።
ላሊበላና ሌሎች ጥንታዊ ቅርሶቻችን ሁሉ በነሱ የተገነቡ ለማስመሰል ለሊት እና ቀን ሲታትሩ ማየት የተለመደ ነው። ለልጆቻቸውም በመማሪያ መጽሀፍቶቻቸው ሳይቀር የትምህርት ስርዓት አድርገው ሲያስጠኑበት ማየት እንግዳ ነገር አይደለም።
የዚህ ሁሉ ነገር ግን አላማው አንድ ነው፤ ስልጣኔ ከኛ ነው የተቀዳው፤ ከዚህ በኋላም ከኛ ፈቃድ እና እውቅና ውጭ ከእናንተ የሚመጣና እኛ የምንኮርጀው ምንም እውቀት፤ ባህልና ትውፊት የላችሁም ነው አሽሙሩ። እኔስ ኢትዮጵያዊ አይደለሁ አሽሙር እና ነገር ቶሎ ይገባኛል ።
ለማንኛውም ወደዛሬው ርዕሰ ጉዳዬ ልግባ። ደግሞ እንዲህ ስል እስካሁን ስለ ርዕሰ ጉዳይሽ ማውራት አልጀመርሽም ለምትሉኝ እሱ መግቢያ ነው እላችኋለሁ።
እንደ ታሪክ ባለሙያዎች ገለጻ፣ በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ ውስጥ የሴቶች መብት እና እኩልነት እንዲከበር የሚያደርግ ንቅናቄ እንደተጀመረ ይነገራል። ንቅናቄውም የሴቶች መብት የነጻነት ንቅናቄ በመባልም ይታወቃል። አላማውም ለሴቶች የበለጠ የግል ነፃነት እና የእኩል ዕድል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ነው። መሰረቱም ከወደ ምእራባዊቷ አገር አሜሪካ ነው ይሉናል። ታሪክ አዋቂ ነን ባዮች ።
እኔ ግን በዚህ አልስማማም። አለመስማማቴ ደግሞ ምክንያታዊ ይሁን እንጂ መብቴ ነው።
እኛ ዲሞክራሲንም ሆነ የሴትን መብት ለማክበር ምእራባውያንን ምሳሌ ማድረግ የለብንም። አባት አያቶቻችን ያቆዩልን ያልተበረዘ እና እኛን የሚመስል ባህል አለን ።
ሁላችንም እንደምናውቀው ቻይና አሜሪካንን እውቀት ቀድታ (ኮፒ) አድርጋ ነው ዛሬ ላይ ለደረሰችበት የኢኮኖሚ ማማ የደረሰችው። አንኮርጅ እንልም ምክንያቱም ሁሉንም አናውቅምና ነገር ግን መኮረጅ ብቻ ሳይሆን ሌላው ዓለም ከኛ ሊቀዳው የሚችል እውቀት፤ ባህል እና ማንነት እንቀዳለን ያለንን በማክበር እና በማሳየት ለዓለም ማሳወቅ አለብን ባይ ነኝ ።
ኢትዮጵያ ከምእራባውያን ንቅናቄ በፊት የተለየ የሴቶችን መብት የሚያከብር ጥንታዊ ባህል ያላት አገር ነች። ነገሩ እንግዲ እንዲህ ነው ፡- በኦሮሚያ ገዳ ስርአት የሴቶች መብት ማስከበር የሚችል ባህል ከ2000 ዓመታት በፊት ጀምሮ መከበር ጀምሯል። የሴቶችን መብት የሚያስከብረው የ”ሲንቄ” ስርአት ይባላል።
በአፋን ኦሮሞ “ሲንቄ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ሴቶች ከጋብቻ በኋላ የሚይዙትን ቀጭን ዱላ ነው። የመዋለድ፣ የምርታማነት እና የሀብት ምልክትም ነው። “ሲንቄ” በገዳ ሥርዓት ውስጥ ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ተጽእኖም አለው።
“ሲንቄ” ከጥሩ መዓዛ ካለው ዛፍ ላይ ተቆርጦ በጥበብ ይዘጋጃል። በአብዛኛው “ሲንቄ” ለማዘጋጀት የበለጠ ተመራጭ የሆኑት ዛፎች በአገሬው ቋንቋ ‘ዋዴሳ’ ፣ ‘ሃሮርሳ’ ፣ ‘ልማና’ እና ‘ኡርጌሳ’ ከሚባሉ ዛፎች ነው።
በባለ ትዳር ሴት የምትይዘው ይህ ”ሲንቄ” ከሃሮሬሳ እንጨት እንዲዘጋጅ የሚደረገው ጠንካራ ስለሆነ በቀላሉ ስለማይሰበር ነው። ”ሲንቄውን” ለማዘጋጀት ለሴቲቷ ቁመት በሚስማማ መልኩ ይቆረጣል።
“ሲንቄ” የያዘች ማንኛዋም ወይዘሮ “ሲንቄውን” እንደ ማንኛውም እንጨት መጠቀም አትችልም። እንስሳትን አትመታበትም፤ ሰዎችንም መሳሪያ አድርጋ ለማጥቃት አትጠቀምበትም።
ማህበረሰቡ “ሲንቄ” የሴቶች መሳሪያ ነው ይላሉ፤ ምክንያቱም ሴቶች “ሲንቄ” ን በመያዝ በቡድን ብዙ ማህበራዊ እና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ይፈጽማሉ።
የገዳ ስርዓት ተብሎ የሚታወቀው የአስተዳደር መዋቅር ሴቶች መብታቸውን እንዲያስጠብቁ፤ የባሎችን የበላይነት እና ጫና እንዲያስወግዱ ያስችላቸዋል።
ሴቶች ልጆች ሲጋቡ እናቶቻቸው መብታቸውን የሚያስጠብቁበትን “ሲንቄ “ ይሰጡዋቸዋል።
የ”ሲንቄ” ህግጋት የሚገለፀው በቀጭኗ ዱላ ነው።
የሙሽራዋ እናት ለልጇ ስንቄ፣ ቦራቲ እና ባሬን ታዘጋጃለች። “ሲንቄ” የ’ቢርማድዱማ’ (የተፈጥሮ ነፃነት) ምልክት ነው። ከእንጨት ተቀርጾ በሃር የተጌጠ ‘ቦርቲ’ የእናትነት ምልክት ነው ለልጇ ትሰጣታለች። በጮጮ ውስጥም ወተት አዘጋጅታ ትሰጣታለች። የወተቱ በጮጮ ውስጥ መሆኑ የሀብት ምልክት ነው።
ሰርግ ላይ ሙሽራው ሙሽራዋን ሊያመጣ ሲነሳ የሙሽሪት እናት ከበሩ ፊት ለፊት “ሲንቄ” ፣ ቦራቲ እና ባሬ ይዛ ትቀመጣለች። የሙሽራዋ እናት “ሆ ባሬ፣ ሆ ባርሴ” ብላ እየዘፈነች ቦራቲውን እና ባሬውን ትሰጣታለች። ይህ ስርአትም ልጃቸውን ለወደፊቱ ባሏ ማስረከባቸውን የሚያሳይ ነው።
“ሲንቄ” ያላት ሴት በማህበረሰቡ ውስጥ በጣም የተከበረች ነች። “ሲንቄ” የያዘችን ሴት በመንገዷ ወንዝ ቢኖርና ማለፍ ቢያቅታት ማንም ወንድ ቀድሟት አይሻገርም። ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አድርጎ ያሻግራታል እንጂ።
ማንም ሰው “ሲንቄ” የያዘችን ሴት አልፏት መሄድ አይችልም እርሷ ካልፈቀደችለት በስተቀር።
የ”ሲንቄ” ተከታዮች አቴቴ ወይም ገንያ በመባል ይታወቃሉ። ሴቶቹ ከ”ብዩማ” (ከሰፈራቸው) ሲወጡ “ሲንቄያቸውን” በመያዝ እየዘፈኑ አንድ ወይም ብዙ ሰዎች ሽማግሌዎች ሳይቀሩ ከፈረሳቸው ወርደው ተቀምጠው እርጥብ ሳርን እያጨዱ “ኢልቴኒናአ” ይላሉ። ሴቶቹም ሳሩን እየቆረጡ ሰላምታ ያቀርቡላቸዋል። ሴቶቹ የስርአቱን ህግ ሳይከተሉ የሚቀሩትን ተከታትለው ይቀጣሉ።
በገዳ ስርአት ለኦሮሞ ሴቶች በስንቄ ህግ ከተሰጣቸው የመብት መገለጫዎች መሀል በቡድን በመሆን አንዲት ሴት በባሏ ብትደበደብ ለሴቲቱ ፍትህ ማስከበር ነው።
የተደበደበችው ሴት ካለችበት ቦታ ድምፅ ካሰማች፤ ድምጹን የሰማች ሴት በሙሉ ሮጣ ትወጣለች። ስታጠባ የነበረች ልጇን ጥላ፣ላም ስታልብ ነበረች “ኦኮቴዋን” ጥላ በእጇ ያለውን ስራ ሁሉ አስቀምጣ ወደ ውጭ መውጣት አለባት። ከዚያም ”በገዳ” ህግ መሰረትም ጥቃት ለደረሰባት ሴት ዳኝነት ይሰጣታል።
የ”ሲንቄ” ን ሥርዓት ለመፈጸም በቡድን የሚሄዱት ሴቶች ባሏ የደበደበባትን ሴት ቤት የሚሄዱት የ”ሲንቄ” መዝሙር እየዘመሩ ነው። መጀመሪያ የመጡት ሴቶች ልጅቱን ይዙና ከቤት ያወጧታል።
ሚስቱ በዚህ በሲንቄው ቡድን ውስጥ ያለች እያንዳንዱ ሰው ሚስቱን የደበደበውን ሰው ጨምሮ ሊያገኛቸው አይፈቀድለትም። በዚህ ሁሉ መካከል ቤቶች ሚስቶች የሌሉባቸው ኦና በረዶ ይሆናሉ። ህፃናት እናቶቻቸውን ማግኘት ስለማይችሉ ያለቅሳሉ። በዚህም ምክንያት ሌሎች አባወራዎች ተባብረው ሁሉም አጥፊውን ለፍርድ ለማቅረብ ይሞክራሉ፤ ቤት ያለ ሴት አይደምቅም እና ሚስቶቻቸው ሁሉ ከቤት የኮበለሉባቸው ባሎች አጥፊው ላይ ፍርድ ለማሰጠት ይፈጥናሉ።
ሴቶቹም ለተደበደበችው ሴት ፍርድ ሳይሰጥ አንዳቸውም ወደቤታቸው አይገቡም። ፍርዱ እስኪሰጥ ድረስ ሴቶቹ፣ የተጎዳችውን አባላቸውን ከበው፣ ጭቆናውን በዝማሬያቸው በመቃወም፣ በገዳ ሕጎች ውስጥ ለጨፌ / ለገዳ ምክር ቤት (ለአካባቢው ሽማግሌዎች) ይግባኝ ይጠይቃሉ።
ሴቶቹ ጉዳያቸውን ወደ “ጨፌ /ገዳ” ሲያመጡ ቁጢጥ ብለው ነው ጥያቄያቸውን የሚያቀርቡት። ይኸውም ለስርአቱ ያላቸውን ክብር ለማሳየት ነው።
ጉዳያቸውን ለመስማት የተቀመጠው እና የሴቶችን ክብር (ዋይዮማ) በሕግ ያስቀመጠው አካል የገዳ ስርአት ነው። በሌላ አነጋገር በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ደንቦች መፈጸማቸውን ያረጋግጣሉ፤ የህግ ጥሰት ደረጃዎችን ያዘጋጃሉ።
ከዚያም ሴቶቹን እንዲህ ሲሉ ይጠይቋቸዋል፡- “የኛ ሴት ልጆች ምን አጋጥሟችሁ ነው?” “በምንድነው የተበደላችሁት?” ብለው ይጠይቃሉ።
ቡድኑን የምትመራዋም ሴት የተደበደበችውን ሴት ከፊት ለፊቷ ይዛ ለጨፌው ተሰብሳቢ ምን እንደተፈጠረ ታስረዳለች። የሕግ አስከባሪዎች (የጨፌው ዳኞች) በደል ያደረሰውን በመለየት ጉዳዩን ያጣራሉ።
በመጨረሻም ጨፌው የደረሰውን ጉዳት ገምግሞ ውሳኔ ያሳልፋል። ይህ ውሳኔውም ካሳ የሚሆን በከብት ማረድን ሊያካትት ይችላል።
የ”ሲንቄው” አባላትም ይህንን ውሳኔ ያስፈጽማሉ። በመቀጠልም የታረደውን ስጋ ለጉባኤው ሰጥተው ዘፈናቸውን ይዘምራሉ እና ፍርድ ያገኘችውም ሴት ወደ ቤቷ ትመለሳለች።
እንዲህ ያለው ስርአት የሚተገበረውም በፊቷ ላይ ጠባሳ ላለባት ሴት ወይም ከስድስት ወር በፊት ለወለደች ሴት እንጂ በባሏ ለተደበደበች ሴት ሁሉ አይደለም የሚሉም አሉ። ነገር ግን ስርአቱ እንደየ አካባቢው ይለያያል።
ከሽማግሌዎች እንደሰማነው የገዳ ስርዓት ከመዳከሙ በፊት እንዲህ አይነት እርዳታ ለሁሉም ሴቶች ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል። ከዚህ ሁሉ በተለየ አዋላጅ የሆነችን ሴት መደብደብ ደግሞ ቅጣቱ ትልቅ ነው።
የሲንቄ አባላትም በጦርነት ወይም በግጭት ጊዜ አስጣራቂና ተሰሚም ጭምር ናቸው። በኦሮሞ ጎሳዎች መካከል ግጭት ሲፈጠር ወይም ትልቅ ጦርነት ሲከፈት አንዱ ሌላውን የሚጎዳ ከሆነ፤ የጦርነቱን ዜና ቀድማ የሰማች ሴት በመንደሯ ያሉትን ሴቶች ታስተባብራለች። የጦርነቱን ዜና የደረሳቸው የሴቶች ቡድን ወዲያው ከ”ሲንቄዎቻቸው” ጋር ይሰበሰባሉ።
የ”ሲንቄ” ን መዝሙር እየዘመሩ ወደ ጦር ሜዳም ይሄዳሉ። ይህን ኃይል ለ”ሲንቄ” የሰጠህ አምላክ ተመስገን እያሉም ያመሰግኑታል። ወደ ጦርነቱ ሲቃረቡ ጦርነቱ እንዲያበቃ በእግዚአብሔር ስም ይጸልያሉ። ጦርነቱም ጋር ሲደርሱም ዘፈናቸውን እየዘፈኑ ጦርነቱ እንዲቆሙ ጸበኞቹን ይጠይቃሉ፤ ለማቆም ፈቃደኛ ካልሆኑ ጣልቃ ይገባሉ። ጦርነቱ የቱንም ያህል የከፋ ቢሆን ከዚህ ህግ በላይ አይሆንም። ወዲያውኑ ይቆማል። በዚህ ሰአት “ሲንቄ” የማስታረቂያ መሳሪያ ሆኖ ይገለጣል ።
በተፈጥሮ ልጅ መውለድ የማይችሉ ሴቶች ወይም መካን የሆኑ ቤተሰቦች ከዘመድ ወይም ከሌላ ሰው ልጅን በጉዲፈቻ መውሰድ ይችላሉ። ልጅ የሌላት እና በጉዲፈቻ ህግ ልጅን ማደጎ ለመውሰድ የምትፈልግ ሴት ሲንቄ, ወተት እና ጭኮ ይዛ ወደ ህጸኑ ወላጆች ዘንድ ትሄዳለች። ጉዲፈቻ ለመውሰድ የሚመረጡት ወላጆች ብዙ ልጆች ሊኖራቸው ይገባል። እንደነዚህ ያሉት ወላጆች ልጆቻቸውን የሲንቄ ዱላ ይዛ ወደ እነርሱ ቤት የመጣችን ሴት በክብር እንዲቀበሉ እና እንዲያስተናግዷት ይገደዳሉ። ሄዳ ልጃቸውን ለማደጎ የጠየቀች ሴት አሳፍረው መላክ አይችሉም።
”ሲንቄ” ይዛ ለምትማጸናቸው ሴት ልጃቸውን እንድታሳድግ የመስጠት ግዴታ አለባቸው። በምትኩም እሷም ልጁን እንደልጇ የማሳደግ ኃላፊነት አለባት።
ይህ ነገር የሴቲቱን ሞራል እና ባለመውለዷ የሚደርስባትን ጫና ለመቀነስ ታልሞ የሚደረግ ባህል ነው። እንግዲ ወዳጆቼ ያሉንን ጠቃሚ ባህሎች አዘምነን እና በሰፊው ጽፈንላቸው ለዓለም ሁሉ አርአያ የምንሆንበትን ቀን ያምጣው እያልኩ ለዛሬው ጨረስኩ።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም