በረከት የበጎነት፣ የመልካምነት ፍሬ ማሳያ ነው። የበረከት እሴቶች በምድር ጸጋዎች፣ በድንቅ ተፈጥሮዎች ይመሰላሉ። ይህ እውነት ከስም በላይ ግብር ሆኖ ሲታይ ደግሞ የቃሉን ትርጉም ይበልጥ ያገዝፋል።
‹‹ሥምን መልአክ ያወጣዋል›› እንዲሉ ወላጆቿ ‹‹በረከት›› ይሉትን ስም የቸሯት በምክንያት ነበር። ውሎ አድሮ ሀሳባቸው እውን ሆነ። እነሆ ! ስሟ ትርጉሙን ለበሰ። የእነሱም ትንቢት ከቀኑ ደርሶ ፍሬያቸው አሸተ። በረከት እንደ ልባቸው ሀሳብ ሆና ጸጋዋን አበዛች። የህልማቸውን ትርጉም ፈታች።
አንዳንዴ አንዳንዶች ከነፍስ ጥሪያቸው ይናበባሉ። ከመክሊታቸው ጫፍ ይገኛሉ። እንዲህ በሆነ ጊዜ በረከታቸው ከእነሱ አልፎ ለሌሎች ይተርፋል። ፍሬያቸው ለብዙሀን፣ ዘራቸው ለበርካቶች ይዋረሳል።
‹‹ገበሬ›› ይሉት የወል ስም፤ ልክ እንደ ማዕረግ ስም ሁሉ ከስሟ በፊት ቀድሞ ይጠራል። ይህኔ የሚሰማት ክብር ላቅ ያለ ነው። ከግብርና ስራ ጋር ያላት ቁርኝት ከልጅነቷ የጀመረ ነውና ወደመሬት ተጥሎ ለሚያድግና ለሚያፈራ ሁሉ ልዩ ፍቅር አላት። እሷ የፍሬውን መጨረሻ እስክታይ ድረስ እንክብካቤዋ ልክ ለእንቦቀቅላ ልጅ የሚደረግ ጥንቃቄ አይነት ነው – ገበሬዋ በረከት ወርቁ።
በረከት፣ ትውልዷም ሆነ እድገቷ በውቢቷ ሐዋሳ ከተማ ነው። ፊደል ቆጥራ እስከ 12ኛ ክፍል የተማረችው በሐዋሳ ነው። አባቷ መምህር፤ እናቷ ደግሞ የኤች.አይ.ቪ እና ስነ ተዋልዶ መማክርት ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት ይሰሩ ነበር። እናት በበጎፈቃድ ያለ ወርሃዊ ደመወዝ መስራታቸው የእነ በረከትን ቤት አላጎደለውም። የኑሯቸው ሁኔታ እንደአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ቤተሰብ ቢሆንም ልጆቻቸውን ከመማር የሚያናጥባቸው አልሆነም።
አባት የቤተሰባቸው ብዛት ስድስት በመሆኑ በእርሳቸው ብቻ ይመጣ የነበረው የአስተማሪ ደመወዝ በቂ ነው ብሎ መቀመጥ አልወደዱም፤ ከመምህርነቱ ስራ ጎን ለጎን ተጨማሪ ስራ መስራት ግድ ብሏቸው እንደነበር ገበሬዋ በረከት ትናገራለች። ስለዚህም የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ምሩቁ የሆኑት አባቷ ተጨማሪ ስራ ፍለጋ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልጋቸው ባላቸው ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኝ ማፍላቱን ተያያዙት።
ይህ ብቻ አይደለም ዶሮ ማርባቱንም ስለጀመሩ ኑሯቸውን መደጎም ቻሉ። በግቢያቸው ከችግኝ ማፍላቱና ከዶሮ ማርባቱ በተጨማሪ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶች ስለነበሩ የጓዳውን ጎዶሎ በቀላሉ ማስተካከል ቻለ። አባታቸው የልጆቻቸውን የትምህርት ወጪም ሆነ የቤት አስቤዛ ይጠቀሙ የነበረው በግቢያቸው ካበቀሉት አትክልት ላይ በመሸጥ ነበር።
የግብርና ጅማሬው ምስጢር
እንደሚታወቀው በክረምት ትምህርት ቤት ይዘጋል። በዚህ ወቅት የገበሬዋ በረከት አባት ቤተሰቡን ይዘው ወደትውልድ ቀያቸው ሱሉልታ ያመራሉ። ወደስፍራው ሲያመሩ በዓላማ ነው። የግብርና ስራ ዋንኛ እቅዳቸው ይሆናል። ይህ አጋጣሚ ነበር በረከት ‹‹ገበሬ ›› የሚለውን ስያሜ እንድታገኝ ምክንያት የሆናት። በረከት ገበሬነትን ከስሟ አስቀድማ የማዕረግ ስም ለማድረግ የክረምቱ ጊዜ መነሻዋ ሆነ። የግብርና ፍቅርም ውስጣዊ ሚስጥሯን ገለጠ። ውሎ አድሮ ግብርናውን በፍቅር የምትወደው፣ የምታከብረው ሙያ አደረገችው። በክረምት በሚሰራው የግብርና ስራ ከመመሰጥ አልፋ እያንዳንዱን ሒደት በትኩረት ትከታተል ጀመር። ከሌሎቹ እህት ወንድሞቿ በተለየ መልኩ ስራውን ትወደው ታከብረው ያዘች። ይሁንና የምትወደውን የግብርና ስራ ከምትወደው አባቷ ጋር በመሆን ረጅም ጊዜ ለመስራት አልታደለችም። ወላጅ አባቷን ሞት ነጠቃት። ይህኔ በእጅጉ ተፈተነች፣፡ እርሳቸው በሕይወት በነበሩ ጊዜ እንደምታደርገው አልሆነችም። ነፍስያዋ በሀዘን ተሸፍና ሕይወትን አከበደችባት። ችግሩ የእሷ ብቻ አልሆነም። በቤተሰቡ ላይ ጫናው አየለ።
እናትነት በልጅነት – በስነ ልቦና ጫና
ብዙ ጊዜ በተማሪነት ያለጋብቻ መውለድ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ፍጹም ነውር ነው፤ ከጋብቻ በፊት በቤተሰብ ቁጥጥር ስር እያለች የምትወልድ ሴት የሚደርስባት ውግዘትም ከበድ ይላል። ከጎረቤት ጀምሮ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በሚያስብል ሁኔታ ልጅቱን ለማግለል የማንንም ምክክር አይጠብቁም። ገበሬዋ በረከትም በልጅነቷ የልጅ እናት ሆና ነበር።ይሁን እንጂ እሷን ብዘዎች የሚያጋጥማቸው ጫና አላገኛትም። የስነ ልቡና ተጽዕኖ ሳይበረታባት ቤተሰቦቿ ሊያጋጥማት ከሚችል አካባቢያዊ ጫና ነጻ ሊያወጧት ችለዋል።
በተለይ አባቷ እንደሌሎች አባቶች አልነበሩም። አንዴ ለተከሰተ ነገር ብዙ እንዳትጨነቅ መከሯት። ልቧ እንዳይሰበር፣ ውስጧ እንዳይጎዳ ‹‹አለሁሽ›› ልጄ አሏት። የዛኔ በሰዎች ጫና ልጃቸውን እንዳያጧት በብዙ ተጠንቅቀውላታል። በዙሪያዋ የሚፈትኗት፣ የሚያነውሯት ቢበዙም በአባቷ አይዞሽ ባይነት በርትታ ጠንክራ ቆይታለች።
በረከት በወቅቱ እሷን ያሳቅቁ የነበሩ አባባሎች ውስጧን የሚፈታተኑ ነበሩ። አባባሎቹ ዛሬም ቢሆን ትውስ ይሏታል።
‹‹ቆመሽ ቀረሽ፣ የሴት ልጅ መጨረሻ ይኸው ነው፣ እንዲህ ሆነሽ ቀረሽ፣ የት ይደርሳል የተባለው ዛፍ ቀበሌ ቆረጠው›› በሚል እንድትሳቀቅ መሳለቅ ደርሶባታል። አባቷ ግን ከእነዚህ ሰባሪ አባባሎች በላይ ገዝፎ የሚሰማትን የሞራል ድጋፍ ያደርጉላት ነበር። በረከት የእሳቸው በጎ አባባል ዛሬ የዓይምሮዋ ደማቅ ማህተም ሆኗል። ‹‹አይዞሽ የእኔ ጀግና፤ አንቺ አሁንም ቆንጆና ጠንካራ ልጄ ነሽ፤ አንቺ ልብስ ቀርቶ ጆንያ ለብሰሽ ብትሄጂ እንኳ ዛሬም ያምርብሻል›› እያሉ ያበረቷት፣ ያጀግኗት ነበር።
አዎ! ድንቅ አባቷ እነዚያን የስነ ልቦና እሾሆች ለመንቀል ጠንካራ እጆች ሆነዋታል። በእሷ ጫና ለመፍጠር የሚወረወሩ ክፉ ማህበረሰባዊ ቃላትን አሽመድምደው ጥለውላታል። ይህ የአባቷ አጽናኝ ሐሳብ ሞራሏን ቢደግፍ ውስጧ በረታ። ትምህርቷን ሳታቋርጥ በታሰበችው መንገድ እንዳትገኝ ምክንያት ሆነ።
ስራን በባህር ማዶ
በረከት፣ በመጀመሪያ አገር ለቅቃ ያቀናቸው ወደ ደቡብ ሱዳን ነበር። ጥቂት ቆይታ ዑጋንዳ፤ ከዛም ኬንያ ተጓዘች። ይህ ብቻ አልበቃትም ታንዛኒያ ብሎም ሞዛምቢክ ተጓዘች። ከአፍሪካ አህጉር ወጣ ብላ ደግሞ ወደቻይና ጣሊያን እያለች ወደተለያዩ አገራት ካመራች በኋላ የትዳር አጋሯ የትውልድ አገር ወደሆነችው ‹‹አየርላንድ ደብሊን›› አቀናች። በዚያ ለተወሰነ ጊዜ ተረጋግታ ተቀመጠች።
የአገር ናፍቆት
አሁን በረከት ባለትዳርና የሶስት ልጆች እናት ናት። ባለቤቷ ጆናታን ፒን፣ አየርላንዳዊ ሲሆን፣ የሶስት ድርጅቶች ባለቤትም ነው። እርሱ ገበሬዋ በረከት ለኢትዮጵያ ያላትን ጽኑ ፍቅር ጠንቅቆ ያውቃል። አገሯን መውደድ ብቻ ሳይሆን መኖር የምትፈልገውም በአገሯ ሰማይ ስር እንደሆነም ይረዳል። እንደ እርሷ እምነትም ሁሉም ሰው መኖር ያለበት በአገሩ ምድር ነው። ወደ ውጭ መሄድ የፈለገ ቢኖር ለተጨማሪ ትምህርት አሊያም ለመዝናናት መሆን ይኖርበታል። ኑሮን በዘለቄታው በሰው አገር ማድረግ ተገቢ አይደለም ባይ ነች።
የሰው አገር እንደሚያሳቅቅ ሁሉ በአገር መኖር የልብ ልብ ይሰጣል። በአገሬ ሆኜ ባጠፋ ‹‹ግፋ ቢል ቢያስሩኝ ነው እንጂ ወደመጣሽበት ሂጂ ተብዬ አልመለስም›› የሚል ጽኑ እምነት አላት፤ አገሯ ከሆነ ወደመጣችበት አገር እንድትመለስ አትደረግም። እንደሌላ አገር ተወላጅ ፓስፖርት አትነጠቀም፤ በተገኘባት ጥቃቅን እንከን ሁሉ ለእስር አትዳረግም።
ኢትዮጵያዊ ቁጭት
ገበሬዋ በረከት፣ ከኢትዮጵያ በቆዳ ስፋትና በሕዝብ ብዛት የማይወዳደሩ፣ ሚዛን የማይደፉ አገራት ኢትዮጵያን ሲረዱ ስታይ በእጅጉ ትበሳጫለች። ኢትዮጵያ ያሏት ወንዞች እንኳን ለራሷ ለሌላው የሚተርፉ ናቸው። ከአየር ንብረቷ ጀምሮ የትኛውንም አይነት ምርት የሚያሳፍስ ለም መሬት አለን። ክረምቱ፣ በጋው፣ በልጉ ሁሉ ተስማሚ የአየር ንብረት እንጂ እንደሌላው ዓለም በረዶ የሚያዘንብ፣ በከባድ ሙቀት የሚያሰቃይ አይደለም።
በረከት እንደምትለው ‹‹እኛ እንጂ ያልሰራንበት እግዚአብሔር ያልሰጠን መልካም ነገር የለም። ያለንን ብናውቅ ኖሮ የሌለን ነገር እንደሌለ ይገባንና ለ40 ካሬ የጋራ መኖሪያ ቤት አንገዳደለም ነበር›› እሷ ይህን እውነት በአዕምሮዋ ስታስብ ቆይታ በመጨረሻም ወደአገሯ ለመመለስ ወስናለች። ወደ አገሯ መመለስ ብቻ አይደለም። ቁጭቷን በስራ ለመወጣት ጭምር አንጂ። ወስና አልቀረችም፤ አደረገችው፣ ወደ እናት ምድሯ ኢትዮጵያ ጓዟን ጠቅላላ ገባች። የሀሳቧ ሞላ፣ የልቧ ደረሰ።
ህይወት በአገር ምድር – ኢትዮጵያ
ወደእናት ምድሯ ኢትዮጵያ የመመለሷ ምስጢር ሰርታ ለበርካቶች በጎ አርዓያ ለመሆን ነው። እርሷ መስራት የምትፈልገው ደግሞ የአገሪቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በሆነው የግብርና ዘርፍ ላይ ነው። በረከት ወደመረጠችው የግብርና ዘርፍ ለመግባት ጉዞ ጀመረች። መንገዶች ግን አልጋ በአልጋ አልሆኑም።
የመጀመሪያውን ዕቅድ ዕውን ለማድረግ ባሰበች ጊዜ መሬት ለማግኘት አራት ዓመታትን መጠበቅ ግድ ብሏታል። እንዲያም ሆኖ የተሰጣት መሬት አነስተኛ ነበር። ይሁን እንጂ ከአርሶ አደሮች ጋር በአብሮነት በመስራት፣ መሬት እየተከራየች ስራዋን ማጣደፍ ጀመረች። የበረከት ዋንኛ መርህ ጠንክሮ በመስራት መለወጥ እንደሚቻል
ማመን ነው። እሷም የበኩሏን አድርጋ አገሯን መለወጥ ትሻለች።
ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰች በኋላ መጀመሪያ ላይ ኦሮሚያ ክልል፣ አርሲ ዞን መሬት አግኝታ አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት ቀጠለች። ባገኘችው 40 ሔክታር መሬት ላይ በትጋት እየሰራች ሳለ በአን ድ ወቅት በኦሮሚያ አካባቢ ተከስቶ ከነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ የአትክልትና ፍራፍሬ እርሻዋ ሙሉ በሙሉ ወደመባት። በወቅቱ ብታዝንም ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጠችም።
በአገር ተስፋ አለመቁረጥ
ገበሬዋ በረከት ‹‹በአገር ተስፋ አይቆረጥም›› በሚል መርህ በትጋት መንቀሳቀሷን ቀጠለች። ‹‹ ያለችኝ አገር አንድ ናት፤ እርሷም ኢትዮጵያ ናት›› በሚል ቁርጠኝነት ተነሳች። በአገሯ ተስፋ መቁረጥ ማለት በራሷም ተስፋ እንደመቁረጥ መሆኑን አምና ዳግም ስራውን ለመቀጠል ተወተረተረች። ትጋቷን ዕለት በዕለት ከፍ በማድረግ በትጋት ሰራች። አልወደቀችም። በእጅጉ ተሳካላት። በአሁኑ ጊዜ በ840 ሔክታር መሬት፣ በፈለገችው መጠንና ልክ የግብርና ስራዋን እየከወነች ትገኛለች።
በዚህ ስራ ውስጥ መውደቅ እንዳለ ሁሉ መነሳት እንዳለ ታምናለች። ቢሮክራሲው በዛው ልክ ፈታኝ ነው። በዘርፉ ተግዳሮት የሚሆኑ አካላት ቢኖሩም ‹‹እነርሱ ትልቋን ኢትዮጵያ ሊወክሉ አይችሉም›› በሚል ጠንካራ ጽናት አገሯን ብቻ በማሰብ ከስራዋ እንዳትስተጓጎል ትጥራለች።
በስራ እንቅስቃሴ የሚያጋጥሟት በርካታ ነገሮች ናቸው። በባህሪዋ ሰዎች ለሙስና ሲሰናዱ ስታይ እንደ የአገሯ ደመኛ ትቆጥራቸዋለች። የኢትዮጵያ ጠላት ጦር የሰበቀ ብቻ ሳይሆን ሙሰኛም ጠላት እንደሆነ ነው የምታምነው። በሌላ በኩል ሴቶች ስራቸውን ሳያስተጓጉሉ እንዳይሰሩ የሚተነኩሷቸውን ሁሉ እንደ አገር ጠላት ትቆጥራቸዋለች። ስለዚህም በእርሷ ዘንድ ጠላትን መዋጋት እንጂ አሳልፎ ለጠላት አገርን መተው ክልክል ነው።
ስለዚህ እንዲህ አይነቱን የአገር ጠላት በመፋለም ለቀጣዩ ትውልድ ከጠላት የጸዳች አገርን ማስረከብ ፍላጎቷ ነው። ከሙስናው ጋር በተያያዘ እኛ ጤነኛ የሆነች ኢትዮጵያን እንዳልተረከብን የምትናገረው በረከት፣ ጤነኛ የሆነች ኢትዮጵያን እኛ ለትውልድ ማስተላለፍ ግዴታ አለብን በሚለው ሐሳብ ታምናለች። አሁን ድህነትንም ሙስናንም በመዋጋቱ ረገድ ግብግብ ገጥማለች፤ በዚህም ብዙ ለውጥ እያመጣች ስለመሆኗ ነው የምትገልጸው።
የእርሻ ስራ አጀማመሯ
በረከት ወርቁ ኢንተግሬትድ አግሮ ኢንዱስትሪ ባለቤት የሆነችው ጠንካራዋ ገበሬ፣ ወደእርሻ ስራዋ ስትገባ የስምንት ወር ህጻን ልጇን አዝላ ነበር። አካባቢው ሞቃት እንደመሆኑ በአካባቢው ዘንዶው እባቡ እንዲሁም ከሌላውም የዱር አራዊት ጋር መጋፈጡ ከስራው ባህሪ እንደ አንዱ የሚቆጠር ነበር። እንዲያም ሆኖ ፍርሃት ይሉት ነገር አልበገራትም። በዚህ ሁሉ ውስጥ ‹‹እመጫት ነኝና እንክብካቤ እፈልጋለሁ›› ሳትል ሕጻን ልጇን መኪናዋ ውስጥ አስቀምጣት ተመላልሳ እያጠባች ስራውን ሳታጓድል ስትሰራ ቆይታለች።
የእርሻ ሥራን ያህል ተግባር ታከናውን የነበረው ልጇን አቅፋ፤ ባስ ሲልም አዝላ ነው። ‹‹ልጅ ታቅፌ እንዴት መስራት እችላለሁ›› ለሚሉ ሴቶች መስራት እንደሚቻል የገለጸችው በንግግር አይደለም። በረሃ ወርዶ በተግባር በመስራት ነው። እውነት ለመናገር የእርሻ ስራ ፈታኝ የሚባል ነው፤ ነገር ግን ፈታኝ ነው ብላ አልተወችውም፤ ልጇን አቅፋ፣ ስራውን በገሀድ ተጋፈጠችው እንጂ።
በረከት ‹‹ሕጻንም አዝለን መስራት እንችላለንና የሚያግድ ነገር ምንም የለም›› ትላለች። እንዲያውም ልጅ ይዞ ስራ ብርታት የሚሰጥ ተግባር እንደሆነ ነው የምትናገረው። ለዚህ ምክንያቷ ደግሞ አንድ የምንኖርለት ዓላማም ተስፋ በመኖሩ ነው ስትል ትናገራለች። ‹‹እኔ እንዲያውም ልንገርሽና አለችኝ ‹‹ወደስራ ታጥቄ የመግባቴ ምስጢር ይህቺን አገር ወደከፍታ ማማ ለማውጣትና ወንዶች ሞክረው ስላቃታቸው እኛ ሴቶች ደግሞ መሞከር ሳይሆን እንቀይራታለን በሚል ተነሳሽነት ነው››።
የማዕረግ መጠሪያዋ ቃል ‹‹ ገበሬ››
ቀደም ሲል የግብርና ሙያን የስራ ዘርፌ ነው ብሎ ለመናገር አብዛኛው ሰው ፍላጎት አልነበረውም። ሌላው ቀርቶ በሰፋፊ እርሻዎች ኢንቨስትመንት እያካሄዱ ከዘርፉ በሚገባ በመጠቀም ላይ ያሉ ባለሀብቶች ሳይቀሩ የስራ መስካቸውን ‹‹ግብርና›› ብሎ ከመጥራት አስመጪና ላኪ ወደሚለው እንደሚያመዝኑ ይታወቃል። በዚህ ዘመን ግን በረከት ግብርናንና ገበሬነትን የስሟ መጠሪያ ይሆን ዘንድ ከስሟ በፊት አስቀድማዋለች። የማዕረግ ስሟ ይሆን ዘንድም ፈቅዳለች። ግብርና የተዋረደ ስራ አይደለም፤ ይልቁንም ሰዎች ቀና ብለው እንዲሄዱ የሚያስችል የተከበረ የስራ መስክ ነው ትላለች። ግብርና ከምግብ እስከ መድኃኒት የሚገኝበት የሰው ልጅ የጀርባ አጥንት በሆነው ዘርፍ መሳተፏ ከምንም በላይ እርካታን ይሰጣታል። ስለዚህም ነው በየደረሰችበት ራሷን ስታስተዋውቅ ‹‹ገበሬዋ በረከት›› በማለት በልበ ሙሉነት ራሷን የምትገልጸው። በዛ ስም በመጠራቷም ትልቅ ክብር ይሰማታል።
እርሷ በምታለማበት አካባቢ በአሁኑ ወቅት ከ11 በላይ ባለሀብቶች መሬት ወስደው በማልማት ላይ ይገኛሉ። እርሷ በዛ ቦታ ከገባች በኋላ ለብዙዎች ብርታት ሆናለች። ከምንም በላይ ደግሞ ሴቶች ለአምስትም ለስድስትም በመሆን በረከት የሰራችው የግብርና ዘርፍ እኛም ብንገባበት ውጤታማ የማንሆንበት ነገር የለም በሚል መንፈስ ዘርፉን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ። ምክር ሲፈልጉ ሁሉ ከመምከር ጀምሮ መንገድ እስከማሳየት ትደግፋቸዋለች።
እርሷ እንደምትለው ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ጋር በመሆን አብሮ ማደግ ከሌለ ድካም ሁሉ የቁልቁለት ጉዞ ይሆናል። አገር በድህነት ውስጥ ሆና ውስን ዜጎቿ ብቻ ሀብታም ቢሆኑ ትርጉም አይሰጥም ትላለች። ሀብታሙ ራሱ መጠሪያ ስሙ የሚሆነው የዚያች የድሃዋ አገር ሰው ነው እንጂ ክብር ይሉት ነገር አይታሰብም ባይ ነች።
ኅብረተሰብን የሚደግፍ ተግባር
እስካሁን ለልማት ስራ በተሰማራችበት አካባቢ የተለያዩ የድጋፍ ስራ ስታከናውን ቆይታለች፤ ለአብነትም ትምህርት ቤት በመገንባት አቅም ያጡ የማኅበረሰቡን ልጆች እንዲማሩ አድርጋለች። በቋሚነት‹‹ ቢሻን ጉራቻ›› ላይ የምታስተምራቸውም 400 ያህል ተማሪዎች አሏት። ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል በአባቷ ‹‹ወርቁ አደራ ቡታ›› ስም በገነባቸው በዚሁ ትምህርት ቤት ሙሉ ለሙሉ የተማሪዎቹን የ ትምህርት ቁሳቁስ በማሟላት በማስተማር ላይ ትገኛለች። በትምህርት ቤቱ የሚማሩ 400ውም ተማሪዎች የምግብ አገልግሎት ጭምር ያገኛሉ።
ትምህርት ቤቱ ስራውን በዚህ ዓመት የጀመረ ነው። ትምህርት ቤት የተገነባላቸው ልጆች በሐዋሳ ሐይቅ መሙላት ምክንያት የተፈናቀሉና ከሱማሌ ክልል ለመጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው። እነዚህ ልጆች ትምህርት ለመማር የአምስት ኪሎ ሜትር መንገድ ለመጓዝ ይገደዱ ነበር፤ አለፍ ሲልም ሐዋሳ ድረስ ይሄዱ ነበር፤ ስለዚህ መፍትሔ ይሆን ዘንድ በማሰብ የተገነባ ትምህርት ቤት ነው ትላለች።
ከዚህ ጎን ለጎን የእርሻ ስራውን በምታከናውንበት አካባቢ ደግሞ ማዋለጃና የላቦራቶሪ ሙሉ ቁስ ያለው ክሊኒክ ዲዛይኑ ጸድቆ የግንባታ ስራው ተጀምሯል። ለዚህ ዋና ምክንያቷ የእርሻ ስራ በምታከናውንበት አካባቢ በ25 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ምንም አይነት የጤና ኬላ ባለመኖሩ ነው። ሴቶች በተለይም ወላዶች እንዳይቸገሩ በቅርቡ አገልግሎቱን ያገኙ ዘንድ ዕድል ፈጥራለች።
በክሊኒኩ የሚሰጠው ሕክምና ከክፍያ ነጻ የሚሆን ነው። ይህ አገልግሎት የተሟላ እንዲሆንም ከክፍያ ነጻ የሆነ የአምቡላንስ አገልግሎትም እንደሚኖር በረከት ትናገራለች። ክሊኒኩ የሚሰራበት አካባቢ ያለው የኅብረተሰብ ብዛት ወደ አስር ሺ የሚጠጋ ሲሆን፣ የበረከት እርሻ የሚገኘውም በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ኦቢቻ ወረዳ ውስጥ ነው።
በኮሮና ወቅት ለአገር መከላከያ ሰራዊት አስር ሺ የፊት ጭንብል እስከ 900 ሺ በላይ ብር በማውጣት እንዲሁም የወላይታ ፖሊስ የሚጠቀምበትን ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ (ዘመናዊ የመገናኛ ሬዲዮ) ከ400 ሺ ብር በላይ በማውጣት ገዝታላቸዋለች፤ ለየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በኮሮና ወቅት ልክ እንደ አገር መከላከያ ሁሉ አስፈላጊዎቹን የኮቪድ 19 መከላከያ ቁሳቁስ ከአንድ መቶ ሺ ብር በላይ በማውጣት ገዝታ አበርክታለች። ለፍቼ ዞን አስተዳደር እንዲሁ የ200 ሺ ብር ድጋፍ ለኮሮና መከላከል ስራ አድርጋለች።
በፍቼ ስር ባለች ዱበር አካባቢ በተለይ ተፈናቃዮች ባሉበት አካባቢ ትምህርት ቤት ለመገንባት ቦታ ወስዳ በመንቀሳቀስ ላይ ናት። አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ዘንድሮ ከክሊኒኩ ቀጥሎ የሚጀመር ይሆናል።
የእርሻ ስራዋን የምታከናውንበት አንዱ በሆነው አርሲ ዞን፣ ዝዋይ ዱግዳ ወረዳ አንዶዴ ቀበሌ የሚገኙ ለ680 ተማሪዎች በሙሉ ወደ ስምንት ሺ ደብተር፣ አንድ ሺ እስክሪብቶና አንድ ሺ እርሳስ ገዝታ የሰጠች ሲሆን፣ የትምህርት ቁሳቁስ በመትረፉም ለጎረቤት ቀበሌዎች ሊሰጥ ችሏል።
አካባቢ ጥበቃ
የእርሻን ስራ በፍቅር የምታከናውነው ገበሬዋ በረከት፣ አካባቢን ለመጠበቅና የአየር ንብረቱ መልካም ይሆን ዘንድ ለአፍታም ቢሆን ተዘናግታ አታውቅም። ከ300 ሺ በላይ ችግኝ ተክላ እርሱኑ በመንከባከብ ላይ ትገኛለች። ችግኞቹን በቀን ከ30 እና 40 ሊትር በላይ ናፍጣ በመመደብ እንዳይደርቁባት ታጠጣለች። ችግኙን ብቻ በቋሚነት ወራዊ ደመወዝ እየተከፈላቸው የሚንከባከቡ 12 ሰራተኞች አሏት። እነዚህ ሰራተኞች የምግብ ወጪያቸው ሙሉ በሙሉ ተችሏቸው የሚሰሩ ናቸው።
የሴቶች ተሳትፎ
እርሻ ስራዋ ላይ የምታሳትፈው አብዛኛውን ጊዜ ሴቶችን ነው፤ በረከት ሴት ከወንድ ይልቅ አትክልት የመንከባከብ ዝንባሌ አላት ትላለች። በእርግጥ በእርሻ ስራዋ ላይ ወንዶችም የሚሳተፉ ቢሆንም ብዙን ጊዜ ወደሱስ ስለሚያመዝኑ ሱሳቸውን ለማስታገስ የሚባክነው ጊዜ እንደሚበልጥ ታምናለች።
ሴቶች ብዙዉን ጊዜ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ደካማ ይቆጠራሉ። ይህ የማኅበረሰቡ አስተሳሰብ የመጣው ዛሬ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ ነው። በትምህርት ቤት ደረጃ እንኳ የሴቷ ውጤት ላቅ ብሎ ከታየ ‹‹ሴት ሆና ሳለ ያመጣችውን ውጤት አያችሁ!!!›› ነው የሚባለው እንጂ ሴት ከፍ ያለ ውጤት እንኳ ታመጣለች ተብሎ ከፍ ያለ ሙገሳ አይሰጥም። በብዙዎች አዕምሮም ያለው የሴት ደካማነትን ጎልቶ ማሳየት ብቻ ነው፤ ገበሬዋ በረከት ግን ፈጽሞ እንዲህ አታስብም፤ ልክ እንደ ወንዱ ሁሉ ሴት የመስራት አቅም አላት ስትል በአርግጠኝነት ትናገራለች።
ሁሌ የትዳር አጋሯን የምትጠብቅን ሴት ብቻ ማየት የለብንም። እንኳን ራሷንና ቤተሰቧንም ጭምር ከጥቃት የመጠበቅ አቅም አላትም ባይ ናት።
በረከት ለዚህ ሁሉ አባባል ራሷን በአብነት ታስቀምጣለች። እርሷ የቻለችውን ‹‹ሌላዋ ሴት የማትችልበት ምንም ምክንያት የለም›› ስትል የሴቷ ጥንካሬ ከሰፈር እስከ አገር መለወጥ የሚያስችል ብርታት ነው። ሴቶች ጠንካራ ሲሆኑ በርካታ ነገር የመቀየር አቅም አላቸው ስትልም ታክላለች። የምንችለውም የማንለውጠውም ነገር የለም ስትል በራስ መተማመኗ ከፍ ያለ መሆኑን ትገልጻለች።
‹‹እኔ የለማ እርሻ ውስጥ ዘው ብዬ ያልገባሁት ለምቶ ስለተሰጣት ነው የሚለው እሳቤ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ እንዳይንገዋለል በማሰብ ነው። ምክንያቱም ሴትም ከምንም ነገር ከባዶ ተነስታ ቦታውን ምርታማ ማድረግ የሚችል አቅም እንዳላት ማሳየቷ ትልሟ ነውና›› ይህም ስኬታማ ሆኖ መታየት ጀምሯል ባይ ነች። ‹‹እኛ ሴቶች ከዜሮ መነሳት እንደምንችል ማስገንዘብ እፈልጋለሁ›› ትላለች። እንደሚቻል በማሳየቷም ሌሎቹ ሴቶች እንደሚከተሏትና እየተከተሏትም እንደሆነ ትረዳለች።
ሴትነትና ተግዳሮት
በአገራችን ጾታዊ ጥቃት መኖሩ አይካድም፤ በረከትም ገና ወደ ኢንቨስትመንቱ ከመግባቷ ጀምሮ አሁንም ድረስ እንዲህ አይነቱ መሰናክሎች ያጋጥማታል። ይሁንና የገጠሟትን እና እየገጠሟት ያሉ ፈተናዎች ሁሉ ካሰበችው ግብ ለአፍታም አላስተጓጎሏትም። ፈተናው ከሙሰኛው ጀምሮ ሴትነትን የሚያንኳስስን ይጨምራል፤ ነገር ግን እነዚህ ተግዳሮቶች ይበልጥ አበረታቷት እንጂ ከመንገዷ አደናቅፈው አልጣሏትም።
እሷ ችግሮች ጠንከር ብለው ሲመጡባት ልትሸሸግበት የምትችለው ዘመድ ወይም ሊያስጥላት የሚችል ወገን የላትም። አቅሟን ከበቂ በላይ የሚፈታተናት ጉዳይ ሲገጥማት አሳልፋ የምትሰጠው ለአምላኳ ‹‹ለእግዚአብሔር›› ነው። የክፉ ቀኔ ብላ ለክፉ ቀን ከጎኗ ያስቀመጠችው አንድ ፈጣሪዋን ብቻ ነው። ብርቱዋ ገበሬ በረከት ወርቁ።
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን
“እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ!”
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም