በሰው ዘር ብቻ ሳይሆን በእንስሳቱ ዓለም ላይም እናትነት ባለ ከባድ ሚዛን ነው። በምድር ያሉ ሁሉ ሲሆኑት የሚገባቸው በመኖር የሚረዱት የህይወት ትልቁ መሰጠት ነው። የመኖር ጽዋ መሙያ የለጋስነት በአት የጥሩነት ዋሻ። እኔ ለእኔ ብቻ ባይነት በበረታበት ዘመን ግለኝነት ባስቸገረበት ስፍራ ልጄን የሚያስብል። እኔን ከሚሉት ቀንሶ ለራስ ሰው መልካም የሚሆንበት የገራሞች መንገድ ነው።
ክፉ የትዳር አጋር ጥፊው፣ የህይወት ብርቱ ክንድ ግፊው፣ የርሀብ ጥማቱ መበርታት ፣የችግሩ መደራረብ በእናትነት ውስጥ ትንሹ የሚቻል መከራ ነው። የፈጣሪ ጥልቅ ፍቅርና መቻል በእናትነት ውስጥ በብዙ ይገለጣል። የእናቶቻቸውን ያህል የሚሳሳ ወዳጅ ያጡ ብዙ ሰዎች አሉ። እናትነት ለሁሉም ጠሊቅ ቢሆንም ኢትዮጵያውያኑ እናቶች ጋር ሲደርስ ግን እናትነት በእልፍ መስዋዕትነት ተኩሎ ይሞሸራል። እናትነት ለኢትዮጵያውያን ከወለዱት ምንም ሳይጠብቁ ራስን እንደ ሻማ አቅልጦ ለልጅ ብርሀን የሚሰጥበት ህይወት ነው። ከማድጋው ውሀ ሲጠፋ እኔ አሁን ጠጣሁ የሚሉበት ከሌማቱ እንጀራ ሲታጣ ጠግቤያለሁ እያሉ ሆድን ባዶ ማሳደር እናቶች በየቤቱ ቢያንስ አንዴ የሚሏት ቃል ናት።
እናትነት ውስጥ አለመቻል በመሆን ሲረታ ራስ ወዳድነት በልጅ ፍቅር ሲበለጥ ማየት እንዳዘቦቱ ቀን ብዙ ነው። እናቶች በነጣ ፊታቸው ለልጆቻቸው ወዝ ይሆናሉ። የራሳቸውን የተጣበቀ አንጀት በብጣሽ ጨርቅ ሸፍነው ለልጆቻቸው ልባሽ ለመግዛት ለክፉ ቀን ያስቀመጧትን ጌጣቸውን ይሸጣሉ።
እናት ለልጇ አንድ ፈገግታ ስትል ልትከፍለው የምትችል እልፍ ዋጋ አላት። ለዚህም ይመስላል በተለምዶ እንኳን የእናትን ውለታ ይቅርና አንድ ቀን ልጇ ሲወድቅ እኔን ይድፋኝ ስትል የምትደነግጠውን ድንጋጤ ለመመለስ ራሱ የልጅ የእድሜ ልክ ምላሽ አይበቃም የሚባለው።
ዛሬ ስለ አንዲት ልጅን ለማሳደግ ሲሉ ብዙ የሆኑ እናትን ታሪክ ልናወጋችሁ ወደናል። ወይዘሮ ሽታዬ ወንድሙ ይባላሉ፤ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውሰጥ በጥበቃ ሰራተኝነት ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። የአሁኑን ድርጅት የመጠበቅ ስራ ከመስራታቸው በፊት እልፍ የህይወት ዳገትና ቁልቁለቶች በእራሳቸው ወጥተው ወርደዋል። ከልጅነት ህይወታቸው ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስራን ሳይንቁ በመስራት ነው ያሳለፉት። ህይወት ምጣድ ላይ እንዳረረ ቂጣ ያላገለባበጠቻቸው ጊዜ የለም። የህይወትን መክፋትና መግፋት በበረታ ክንድ ነው ወርደው የወጡት።
ሌብነትና ባዕድ አምላኪነት አይሁን እንጂ ስራ ከተባለ ምንም ሳይንቁ ይሰራሉ። በረጀሙ ዞማው ጸጉራቸው ላይ በኩራት የተጀቦነው ሽበታቸው ሺህ ውበት ሆኖላቸዋል። በባለሞያ ሴት እጆች ደርበብ ብሎ የተቆላ ቡና የሚመስለው ጠይም የሰውነት ከለራቸው እንደ በረድ ከነጻው ፀጉራቸው ጋር አብሮ ሲታይ ልብ ይማርካል። አተኩሮ ላያቸው ሰው እናት ይህች ናት ተብለው በየሁሉም ቤት ሊሰቀል የሚገባው ምስል ባለቤት ናቸው። አይናቸው አወራራቸው አካሄድ አነሳሳቸው ሁሉ የእናትነት ነፋስ አለበት።
በኦሮሚያ ክልል ኖኖ ወረዳ ተወለዱ። ስፍራው የህይወታቸው አራት ዓመታት ብቻ የተኖረበት ነው። 1962 ዓ.ም በአራት ዓመታቸው በአጎታቸው አማካኝነት አዲስ አበባን ተዋወቁ። የእስከዛሬው ህይወታቸው ቀሪ ጊዜም በመዲናይቱ ቀጠለ። ከቄስ ትምህርት ቤት ዘልቀው ስድስት ወራትን ተማሩ። ቀጥለውም ከዜሮ ክፍል ጀምሮ እስከ አምስተኛ ተማሩ፤
በንጉሱ ዘመን በነበረው መፈንቅለ መንግስት ምክንያት ትምህርታቸውን አቋረጡ። ትምህርት እንደተቋረጠባቸው በአስራ አራት ዓመታቸው ህይወታቸው አጋር አገኘች። ተስፋዬ ውብሸት ከተባሉ ሰው ዘንድ ትዳር መሠረቱ። ለምለሙ ማህጸናቸው አራት ልጆችን አፍርቶላቸዋል። ልጆቻቸውን ለማኖር እርሳቸው ከመሞት ውጪ ሁሉንም ሆነው ኖሩ።
በዚሁ ጊዜ ሁመራ ሄደው ሰሊጥ አራሚ አጫጅ ሆነው ሰሩ። ከዚያ መልስም ህንዶች ቤት በጽዳት ለስድስት ዓመታት ሰሩ። ህንዶቹ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ሁርሶ በምድር ጦር ውስጥ ሁለት ዓመት ተቀመጡ። ብዙም አልቆዩ አባት ታመው ነበርና ተመልሰው ወደ አባታቸው ማስታመም ዘለቁ።
ያኔም በሰላምና መረጋጋት ተመርጠው ቀበሌ ሁለት ዓመት በመሳርያ ህዝብ የመጠበቅ ስራ ለአራት አመት ደግሞ የቀበሌ መስተዳድር ጸሀፊ በመሆን አገለገሉ።
ቤት የሚያስታምምላቸው ሰው ባለመኖሩ ምክንያት ስራውን አቆሙ፤ ያለአጋዥ ያስታመሟቸው አባት ከአራት ዓመታት በኋላ አረፉ። ከአባት ሞት በኋላ ህይወት ከባድ ሆነባቸው። መልክና ሁኔታን በቀያየረችባቸው ህይወት በብዙ ተሰቃዩ። ልጆቻቸውን ለማሳደግ ጥጥ እየፈተሉ መሸጥ ጀመሩ። ከዚያም መልስ ንግድ ምክርቤት ሁለት ዓመት ስራ ከሰሩ በኋላ አሁን ወዳሉበት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተቀጠሩ። በዚህ መስሪያ ቤት ዓለም አየሁ የልፋቴ ተከፈለኝ አሉ። በእድሜ ጀንበር ብዙ ቢያዩም ወጥተው ቢወርዱም ካለፈው ያለው ይሻላል እያሉ ለልጆቻቸው አባትም እናትም ሆነው አሉ።
በዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም