ፈገግታ የዘወትር ስንቋ የውስጣዊ ሰላሟ ነፀብራቅ ነው:: በራስ መተማመኗ የአንድን ትልቅ አገር ህዝብ በንግስና ዙፋኗ ላይ ሆና የምታስተዳድር ንግስት እንጂ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ የተቀመጠች መሆኗን ያስረሳል:: ለዓለም ሁነቶችና ፈተናዎች ያላት በጎ አመለካከት እና ምላሽ ተኝቼ ስነሳ እሷን ሆኜ በነቃሁ ያስብላል::
አካል ጉዳተኛ መሆኗ ዳግም እንድትፈጠር እንድትወለድ አደረጋት እንጂ ከወደቀችበት ከቲቢያ እንድትቀር አላደረጋትም:: በተሽከርካሪ ወንበር ላይ መቀመጥ መቻልና ፈተናን አሸንፎ መኖርን በብዙ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ እንድትቀርፅ አደረጋት እንጂ መራመድ አለመቻሏን እንድታስብ አላደረጋትም:: ሚሊዮኖችን ባነቃቃችበት አንድ ንግግሯ የህይወትን ጎምዛዛ ገፈት የተጎነጨችበትን ግን ደግሞ ለዛሬ ማንነቷና ለገነባችው ጥንካሬ መሰረት የሆነን ክስተት ትተርካለች:: ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጣ ለአዳራሽ ሙሉ ህዝብ በወደቁበት ሳይቀሩ ይበልጥ ጎልቶና ጎልብቶ አንፀባርቆ የመነሳት ስነልቦናዊ ጥንካሬን ታጋራለች:: ሙኒባ ማዛሪ ፓኪስታናዊቷ ብረቷ እመቤት!
“እነሱ አካል ጉዳተኝነቴን ነው የሚመለከቱት፤ እኔ ደግሞ መቻሌን ነው የማየው፤ በህይወታችሁ ውስጥ የሚያጋጥሙ አንዳንድ ክስተቶች አሉ:: እነዚህ ክስተቶች ሊሰብሯችሁ ይችላሉ፤ ቅርፀ ቢስ ሊያደርጓችሁም ይችላሉ ግን በተሻለ አቅጣጫ ይቀርጿችኋል” ትላለች:: በሷም የሆነው ይህ ነው፤ ባል ስታገባ ገና የ18 ዓመት ወጣት ነበረች:: የትዳሯ መነሻም አባቷ ነበር:: አባቷ እንድታገባ ያለውን ፅኑ ፍላጎት የተመለከተችው ሙኒባ ‹‹የኔ ማግባት አባቴን የሚያስደስተው ከሆነ ይሁን›› በማለት የትዳርን ዓለም ተቀላቀለች:: ነገር ግን እንዳሰበችው ትዳሯ አባቷን አስደስታ እሷም ደስታን የምታገኝበት አልሆነላትም::
ካገባች ከሁለት ዓመት በኋላ ከፍተኛ የሆነ የመኪና አደጋ ደረሰባት:: “በአንደኛው በኩል ባለቤቴ ተኝቶ ነበር፤ መኪናዋ ወደ ገደል ተገለበጠች:: ባለቤቴ ከመኪናዋ ውስጥ ዘሎ በመውጣት እራሱን አዳነ:: በዚያ ደግሞ ደስተኛ ነኝ:: እኔ ግን መኪናዋ ውስጥ ቀረሁ” ትላለች ስለአደጋው ስታስረዳ:: በአደጋው ብዙ የሰውነቷ ክፍል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባት:: ወገቧ ተሰበረ፣ ትከሻዋ ውልቃት ገጠመው፣ ደረቷም ከፉኛ ተጎዳ፣ ሳንባዋና ኩላሊቷ አደጋ አገኛቸው:: መተንፈስ አቃታት፤ እናም ሆስፒታል ገባች:: ለሁለት ወር ተኩል ያህል ጊዜ የሆስፒታሉ አንድ ክፍል ውስጥ ተኛች፤ በርካታ ቀዶ ጥገናም ተደረገላት:: ያች ቀን ቀሪ ህይወቷን በሙሉ ፓራላይዝ እንድትሆንና በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆና እንድትንቀሳቀስ ምክንያት ሆነች::
ሆስፒታል በነበረችበት ባንዱ ቀን ዶክተሩ ወደሷ በመሄድ፤ “አርቲስት መሆን እንደምትፈልጊ ሰማሁ ነገር ግን መጥፎ ዜና ይዤልሽ ነው የመጣሁት” አላት:: “ከዚህ በኋላ ስዕል መሳል አትችይም ምክንያቱም ወገብሽ እና እጅሽ ክፉኛ ተጎድቷል” በማለት አረዳት:: በቀጣዩ ቀን ዶክተሩ አከርካሪዋ ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድ መሆኑንና ከዚህ በኋላ መራመድ እንደማትችል ነገራት:: ከዚህ ሁሉ የከፋውና የሙኒባ ማዛሪን ስነልቦና የጎዳው “ከዚህ ጉዳትሽ የተነሳ ከዚህ በኋላ መውለድ አትችይም” የሚለው የዶክተሩ ቃል ነበር:: “ያን ቀን ሙሉ ለሙሉ ጠፋሁ፤ እናቴን ‹‹ለምን በኔ?›› ብዬ ጠየኳት:: ያን ቀን ስለህልውናዋና ስለመኖሯ ትርጉም መጠየቅ ጀመረች::
“ይህም ያልፋል፤ ፈጣሪ ላንቺ ትልቅ እቅድ አለው” የሚለው የእናቷ ቃል የዳግም መፈጠሯ፤ ከወደቀችበት የመነሳቷ መሰረት ሆነ:: ከሁለት ወር በኋላ ከሆስፒታል ወጣች፤ ሁለት ዓመት በቤት ውስጥ ከአልጋ ሳትነሳ በመስኮቷ በኩል ውጪ ውጪውን አሻግራ እየተመለከተች በአንድ ክፍል ውስጥ ተወስና ቆየች:: የወፎቹን ድምፅ ብቻ እየሰማች የአልጋ ቁራኛ ሆና ከረመች:: በተኛችበት ክፍል ሆና አንድ ቀን እሷም ከቤተሰቦቿ ጋር ሆና ወደ ውጭ እንደምትወጣ፣ የዓለምን ውብ ተፈጥሮ እንደምታደንቅና ዳገት ቁልቁለቱን እንደምታይ አሰበች:: የዚህን ጊዜ ነበር ሰዎች ምን ያህል እድለኛ እንደሆኑ የተረዳችው::
የሙኒባ ቀጣይ ተግባር ፍርሃቷን መዋጋት ነበር እናም ሁሉንም ፍርሃቶቿን ማሸነፍ እንዳለባት ወሰነች:: “ትልቁ ፍርሃቴ ፍቺ ነበር፤ ከኔ ጋር ኪዚያ በላይ መቆየት የማይፈልግ ሰው ላይ የሙጥኝ ብዬ ነበር:: ፍርሃቴን ሳሸንፍ በቃ አልኩኝ:: ስለፈራሁ ነው እንጂ ምንም ማለት አይደለም አልኩኝ:: እሱን ለቅቄ ራሴን ነፃ አወጣሁ:: እናም እራሴን የጠንካራ ስሜት ባለቤት አደረኩ:: ሌላ ማግባቱን የሰማሁ ቀን የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት ላኩለት ዛሬም እንደምፀልይለት ያውቃል” ስትል እንዴት ፍርሃቷን ማሸነፍ እንደጀመረች ታብራራለች::
ሌላኛውና ትልቁ ፍርሃቷ እናት መሆን አለመቻሏ ነበር:: ይህ ለሷ ለመቀበል የሚከብድና በትልቁ ቅስሟን የሚሰብር ነበር:: ግን በጥሞና አሰበች፤ ዓለም ላይ የሚቀበላቸው የሚፈልጉ ብዙ ህፃናት አሉ፤ ስለዚህ በምንም መልኩ ማልቀስ አያስፈልግም በማለት ወደ ህፃናት ማሳደጊያ ሄዳ አንዱን ህፃን በማደጎ ወሰደች፤ ልጅ አገኘች እንደምትመኘውም እናት ሆነች::
በተለያየ የዓለም ጥግ የሚኖሩ ሰዎች በሌሎች ሰዎች ዘንድ ተቀባይነትን አናገኝም ብለው ያስባሉ ምክንያቱም ፍፁም በሆነች ዓለም ፍፁም ያልሆኑ እነሱ እየኖሩ ይመስላቸዋል:: ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን መጥቀም የሚችሉ ነገር ግን በሌሎች ፊት የሚኖራቸውን ተቀባይነት በማሰብ በቤታቸው የተቀመጡ ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ፀጋ የሚያባክኑ በርካቶች ናቸው:: ሙኒባ ግን ይህ እንዲሆን አልፈቀደችም ራሷን በደንብ ብትገልፅ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ተስፋ መሆን እንደምትችል አሰበች:: ወደ አደባባይ በመውጣት መንቀሳቀስ ጀመረች፤ ከልቧ የምትወደውንና ሃኪሟ ከዚህ በኋላ ማድረግ አትችይም ያላትን ስዕል መሳል ጀመረች:: በዚህ ብቻም አላበቃችም በፓኪስታን ቴሌቪዥን ጣቢያ በመግባት ዜና አንባቢ በመሆን መስራት ቻለች:: ባለፉት ሶስት ዓመታት በርካታ የቴሌቪዥን ሾዎችን አዘጋጅታለች::
ሙኒባ ስኬታማነቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቀጠለ፤ ለፓኪስታን ዩን ውሜን የመልካም አርአያ አምባሳደር በመሆን ተመረጠች:: ለሴቶችና ለህፃናት መብት ትናገራለች፤ ድምፅ ላጡ እህቶቿ ድምፅ በመሆን አጋርነቷን ታሳያለች:: ሁሌም ወደ አደባባይ ስትወጣ ፊቷ ላይ ትልቅ ፈገግታ አለ፤ ሰዎች የዚህ ፈገግታዋ ምንጭ ምንድነው? በማለት ይጠይቋታል:: ሙኒባ ግን ሁሌም መልሷ፤ “ስላጣኋቸው ነገሮች መጨነቅ ስላቆምኩ፤ ስላጣሁት ጤና፣ ሰው መጨነቅ ስላቆምኩ ነው” በማለት ምላሽ ትሰጣለች::
‹‹አንዳንዴ ከህይወታችሁ አንዳንድ ነገሮች ሲቀነሱ የተሻለ ሰው ሊያደርጓችሁ ይችላሉ:: ሁሌም ሁሉም ነገር የሚሆነው ለበጎ ነው:: ሙሉ ህይወታችሁን ኑሩ ፤ ራሳችሁን ተቀበሉት ለራሳችሁ ፍቅርን ስጡ፤ ራሳችሁን ውደዱ ያኔ ነው ሌላ ሰው የምትወዱት ህይወት ከባድና አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፤ እነዚያ ሁሁ ነገሮች ግን እናንተን ነው ጠንካራ የሚያደርጉት:: ራሳችሁን ስትቀበሉት ዓለምም እውቅና ይሰጣቹኋል፤ ሀሉም የሚጀምረው ከራስ ነው” በማለትም ሙኒባ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ለሰዎች መልዕክቷን ታስተላልፋለች::
ሙኒባ ማዛሪ ከ15 ዓመት በፊት በወጣትነቷ በደረሰባት የመኪና አደጋ ዘመኗን ሙሉ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ የምትቀመጥ አካል ጉዳተኛ ሆናለች:: የእናቷ ቃላት ግን ቃላት ብቻ ሆነው አልቀሩም፤ ሙኒባ ማዛሪ ዛሬ በመላው ፓኪስታን የምትወደድ አርቲስት ለመሆንዋ እርሾ ሆንዋታል:: የመጀመሪያዋ ተሽከርካሪ ወንበር ላይ የተቀመጠች ሞዴልም ተብላለች:: በርካታ የቴሌቪዥን ሾዎችን አዘጋጅታለች፤ ከዚያም ባሻገር በፓኪስታን ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዜና አንባቢ ሆናም ትሰራለች:: አነቃቂ ንግግር እንድታደርግ በየመድረኩ ትጋበዛለች:: ሙኒባ አሁን ሁሉም ሊሰማት እና የሷን ጥንካሬና ተስፋ ያለመቁረጥ ፅናት ለመጋራት የሚሻማባት በአነቃቂ ንግግር የሰዎችን የመኖር ፍላጎት ከፍ የምታደርግ የፓኪስታን እንቁ፤ ፈተና እንደወርቅ በእሳት የፈተናት የዓለም መሰናክል ያልበገራት የማትፈርስ አለት ናት::
እ.ኤ.አ 2015 ዓ.ም ቢቢሲ ከመቶ አነቃቂ ሰዎች አንዷ ሲል መርጧታል:: የፓኪስታን ብሄራዊ ዩን ውሜን አምባሳደር ተብላ ተሰይማለች:: በ2016 ፎርቢስ ከ30 ዓመት በታች ያሉ 30 የዓለማችን ምርጦች በሚለው ዘርፍ አንዷ አደረጋት:: በ2019 ዓ.ም የያኔው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሚር አንከሃን የፓኪስታን ብሄራዊ የወጣቶች ምክር ቤት አካል አደረጓት:: እ.ኤ.አ2017 ዓ.ም በሰርቢያ የካሪክ ወንድማማቾች ሽልማት ተቀበለች:: ይህንን ሁሉ ስኬት የተጎናፀፈችው በደረሰባት አደጋ አካል ጉዳተኛ ሆና ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ለመቀመጥ ከተገደደች በኋላ ነው:: ዛር ሙኒባ ማዛሪ ሚሊዮኖች የሷን ንግግር ለመስማት የሚሰለፉ ሊያይዋትና ሊያደንቋት የሚሹ የ35 ዓመት ሴት ሆናለች::
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም