እትመት አሰፋ ትባላለች። ከአስመራ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሰብሳቢ ዳኛነት የተደረገ የስኬት ጉዞ ባለቤት ናት። እሷና ባልደረቦቿ የሰጡት ውሳኔ የአገሪቷ ህግ ሆኖ ይጸናል።
መጠቃት ሞቷ ነው። ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረችበት ጊዜ ነበር ከዚህች ዓለም ጋር የተዋወቀችው፤ ጓዳ ጎድጓዳዋ በአስመራ መንደሮች መሀል ተደብቋል። የእውቁ ደራሲ የበዓሉ ግርማ ገጸ ባህሪ የሆነችው የፌያሜታ ጊላይ መብቀያ የድምጸ መረዋዎቹ ጸሀይቱ ባራኪ እና የየማነ ባርያው ሀገር ኤርትራ መዲና አስመራ የእትብቷ መቀበርያ ስፍራ ነው። የመኖር ጅማሬ መነሻዋ ምድርን መቀላቀያ ስፍራዋ አስመራ ናት። ዳኛዋ እትመት ከፍተኛ የሆነ የራስ መተማመን ያላት እና ያመነችበትን ነገር በግልጽ የምትናገር ቀለል ያለች ሴት ነች።
መብትን ለማስከበር መነሳት ለሰዎችም ለራስም ፍትህ ዘብ መቆም መለያዋ ነው፤ ሁሉም ሰው በስነ ስርዓት መመራት ህግም መከበር አለበት ባይ ናት። ዳኛ እትመት አሰፋ በሀገሪቱ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ የህግ ሰውነት ያለው ተቋም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሰብሳቢ ዳኛ ናት። በእጇ የጨበጠችው የፍትህ መዶሻ የእልፍ ‹‹ከኔ በላይ ማን አለ›› ባዮች ትዕቢትን አዶልዱሟል። የፍትህ በትሯ ለብዙ ባለ እምባዎች መታበስ ሆኗል።
የልጅነት ሕይወት፡-
ልጅነቷ ጥሩ የሚባል አይነት መልክ ነበረው። የተገኘችው መተዳደሪያ ገቢያቸው መካከለኛ ከሆነ ቤተሰብ ነው። የአባቷ ሻለቃ አሰፋ አሳምሬ ወታደራዊ ስርዓት የእርሷንና የእህት ወንድሞቿን ሕይወት በቀና መንገድ መርቷል። ወላጅ እናቷ ወይዘሮ ከበደች ደመቀም ቢሆኑ ሳይማሩ በርካታ ኃላፊነቶችን በመወጣት ለልጆቻቸው ዛሬ መድረስ ትልቁን ስፍራ ይይዛሉ።
የአሁኗ ህግ ተርጓሚ በብላቴንነት ዘመኗ እልኸኛ እና ተደባዳቢ ነበረች። ጥቃት አትወድም፤ ለታናናሽ እህትና ወንድሞቿ ተቆርቋሪ ናት፤ አቻ ጓደኞቿ ከተደበደቡ የደበደባቸውን ሰው ለወዳጆቿ ተደርባ ትደበድብ ነበር። የቤት ውስጥ ስራ መስራት አትወድም፤ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቦርቃ ተጫውታ ለቤተሰብ ታዛ አድጋለች።
የአባቷ ወታደር መሆን እሷና እህቶቿን በጥብቅ ስነ ስርዓት ማሳደግ ችሏል። ጥልቅ የሙያ ፍቅር፤ ሐገር ወዳድነት፤ ሕዝብን ታምኖ በሀቀኝነት ማገልገል እና ለእውነት መታገልን ከአባቷ ወርሳለች። ከእናቷም ቢሆን የትዬለሌ ጉዳዮች ተጋብተውባታል። እናቷ ወይዘሮ ከበደች ደመቀ ባይማሩም የትምህርትን ጥቅም ከዘመናቸው ቀድመው ያወቁ ታታሪ ሴት ነበሩ፤ ባለመማራቸው ምክንያት የደረሰባቸውን ተጽእኖ መሠረት በማድረግ ልጆቻቸው ተግተው እንዲማሩ ማድረግ ችለዋል። ሴቶች መብቶቻቸውን የሚያረጋግጡት በትምህርት ብቻ መሆኑን አምነው በመቀበልም ልጆቻቸውንም አሳምነዋል። ከተማሩ ደግሞ ለከፍተኛ ውጤት መሆን እንደሚገባቸው ሁሌም ይመክሯቸውም ነበር።
ዳኛዋ እስከ ዓለም ጥግ ብትኳትን ለእርሷ የእናቷን ያህል የራሱን ሕይወት ትቶ ለእርሷ ዋጋ የከፈለ አንዳች ፍጥረት የለም። በልቧ ሰሌዳ በትልቁ የተፃፈው የወላጅ እናቷ መልካም አድራጊነት ነው። እናቷ ሙሉ ጊዜያቸውን ለልጆቻቸው በመስጠት በአግባቡ አሳድገው አስተምረዋቸዋል፤ እንደውም ለዛሬ ደረጃ እንድትደርስ ትልቁን ድርሻ የወሰዱት እናቷ ናቸው፤ ለዳኛዋ እትመት እናቷ በእጅጉ ዋጋ በመክፈላቸው ሳይማሩ ላስተማሯት እናቷ ምስጋናዋ የበዛ ነው። ባሉበት በሰማዩ ዓለም ‹‹ደግ ይግጠምሽ፤ አፈሩ ይቅለልሽ›› ብላም በሞት ለተለዩአት እናቷ ደግ ደጉን ተመኝታለች።
የሕይወት መርኋ ሕሊና ምን ይላል የሚለው ነው። በእንግሊዝኛው / morale value / ጥሏም ንግግሯም ከህሊናዋ ነውና ለምትሰራቸው ስራዎች ብቸኛ ዳኛ አድርጋ የምትሾመው ህሊናዋን ነው።
ትምህርትና እትመት
ዳኛ እትመት አሰፋ ከወደ አስኳላው ዓለምም ተሸላሚ ነበረች። ጥልቅ የሆነ የንባብ ልምድ ባለቤት ናት። ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ የማንበብ ልምድን አዳብራለች። የዛሬ ዳኝነቷን ያወቀች ይመስል የትላንቱ የልጅነት ልቧ ለወንጀል ታሪኮች ይማረክ ነበር። በዚሁ ጊዜም ልብ ወለድ፣ ከወንጀል ምርመራ እና ከስለላ ጋር የተገናኙ እንዲሁም የታሪክ መጽሐፍቶችን የማንበብ ልምድ ነበራት። አብዛኛዎቹ የሀገራችን እውቅ ደራሲያን የጻፏቸውን መጽሐፍቶች አንብባለች። እነኚህ መጽሐፎች አሁን ላላት ባሕርይ እና አመለካከት ትልቁን ሚናም ተጫውተዋል።
በትውልድ ስፍራዋ አስመራ በወቅቱ የትምህርት አሰጣጡ ጥሩ በተባለለት ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርቷን ተከታትላለች። ካደገች በኋላም ሙሉ የትምህርት ዝግጅቷ በሀገሪቷ አንጋፋ የትምህርት ተቋም ውስጥ ያለፈ ነበር።
ከሀገሪቷ ትልቁ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በሕግ ማግኘት ችላለች። ሁለተኛ ዲግሪዋን በሰብዓዊ መብት: በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የ ‘ Gender studies ‘ ማስተርስ ዲግሪ ተማሪ ስትሆን የመመረቂያ ጽሑፍ በማዘጋጀት ላይ ናት።
እትመትና የስራ ሕይወት
የዳኛ እትመት አሰፋ የስራ ዓለም ጉዞዋ በቀድሞ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት አሀዱ ብሎ ተጀመረ። በዚሁ መስሪያ ቤትም ከ1995 ዓ.ም እስከ 2000 ዓም ድረስ ለአምስት ዓመታት በነገረ ፈጅነት አገልግላለች፤ በቀጣይም የጥብቅና ፈቃድ ለማውጣት ቻለች። ከ2000 ዓ.ም እስከ 2006 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በፌዴራል ማናቸውም ፍርድ ቤት ጠበቃ በመሆን ለተጨማሪ አምስት ዓመታት ሰርታለች። ቀጣይ የስራ ታሪኮቿ ከዳኝነት የሚያስተዋውቁና ከስራውም በጥልቅ ፍቅር ያስተሳሰሯት ሆኑ። ከ2006 ዓ.ም መጨረሻ እስከ 2008 ዓም መጨረሻ ድረስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን ሠራች። ከ2008 ዓ.ም መጨረሻ እስከ አሁን ድረስ ደግሞ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን በማገልገል ላይ ትገኛለች። በአሁኑ ሰዓት የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት 3ኛ ሰበር ሰሚ ችሎት ሰብሳቢ ዳኛ ናት።
የዳኝነት በጣም የምትወደው ሙያ ነው፤ ‹‹እግዚአብሔር እስከፈቀደበት ጊዜ ድረስ በከፍተኛ የሙያ ፍቅር ሥራውን እሰራለሁ ብዬ አምናለሁ›› ትላለች ለሙያው ያላትን ጥልቅ ፍቅር ስትገልጽ። የሀገሪቱ የመጨረሻ ፍርድ ቤት በሆነው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውስጥ መስራት ለዳኛ እትመት ትልቅ ስኬት ነው። ከሌሎች ለመማር ዝግጁ ናት። በየጊዜው ራሷን ለማሳደግ የተለያዩ መጽሀፍትን ታነባለች። ከጊዜው ጋር ራሷን በማዘመን ወቅቱ ባመጣው ቴክኖሎጂ ትሳተፋለች። የማሕበራዊ ትስስር ገጾችን ለበጎ ዓላማም ትገለገልባቸዋለች። ራሷን ለማሳደግ እና አዳዲስ መረጃ ለማግኘትም ትጥራለች።
እትመትና ዳኝነት
ዳኝነት በተቃራኒ ጎራ የተሰለፉ ሁለት ተፋላሚዎች በሚፋለሙበት የክርክር ሜዳ ላይ የሚከወነውን ውጊያ መምራት ነው። ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ እና ጥብቅ ተጠያቂነት ያለበት ሙያም ጭምር ነው። ይህን በመሰለ ሙያ ውስጥ በጥብቅ ስነምግባር በላቀ ትጋት እና በከፍተኛ የሙያ ፍቅር ትሰራለች። ለዚህ ሁሉ ብርታቷ የጀርባ አጥንት የምትለውና በዚህ ጥንካሬ ልክ እንድትሰራ ያስቻላት የወላጆቿ አስተዳደግ እና ሴትነት ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል የሚል እምነትም አላት።
በዳኝነት ሕይወት ሴት መሆኗ ጠቅሟታል። የሀገሪቱ የመጨረሻ ፍርድ ቤት የሆነው የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሰብሳቢ ዳኛ ብትሆንም አሁንም ካለችበት በላይ ሩቅ ታልማለች፤ ሕልሟን እንደምታሳካም በራስ መተማመን አላት። ዳኝነት ልዩ መሰጠትን እና ከፍተኛ ኃላፊነትን ጠያቂ ነው። በላቀ ስነምግባር የሚከወን ሙያም ጭምር። ዳኝነት የልጆችን፤ የትዳርን እና የቤተሰብን ጊዜ የሚሻማ በአብዛኛው ከማሕበራዊ ሕይወት መገለልን የሚጠይቅ ሙያም ነው።
ሴትነትና እትመት
ሴትነት ለእትመት ብዙ የእድል በሮችን ከፍቶላታል። ሴት በመሆን ውስጥ ያለውን ጸጋ አንጠፍጥፋ ተጠቅማለች። ሴትነት ውስጥ ባለው ጥንካሬ፣ ታጋሽነት፣ ውጤታማነት፣ አስተዋይነት፣ ስክነት፣ አቃፊነት፣ ደፋርነት ፣ ጀግንነት፣ ፍትሐዊነት እንዲሁም ውሳኔ ሰጭነት ዳኝነቷ የሰመረ ሆኗል።
የዚህ ሁሉ ጸጋ ባለቤቶች የሆኑ በተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የራሳቸውን ስራ የፈጠሩ፣ በንግድ የሚሳተፉ፣ የቤት እመቤት የሆኑ፣ ከታችኛው እስከ ላይኛው እርከን ድረስ በርካታ ብርቅዬ ሴቶች አሉ። እነኚህ ሴቶችም የሀገር ብርሃን ናቸው። ብርቅዬ የሆኑ ሴቶች እንዳይታዩ ወደፊት እንዳይመጡ የሚያደርጉ ማነቆዎች አሉና መንግስት እና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እነኚህን ማነቆዎች በማስወገድ የሀገር ብርሃን የሆኑ ውድ ሴቶችን ሊጠቀሙባቸው እንዲሁም ድጋፍ ለሚፈልጉትም ተገቢውን ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል የሚል መልእክቷንም አስተላልፋለች።
‹‹የሴቶች ነባራዊ ሁኔታ፤ ማሕበራዊ፤ ታሪካዊ፤ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ተጽእኖዎች ሴቶች መብታችን እንዳይረጋገጥ ተግዳሮቶች ናቸው፤ ሆኖም ዋነኛው መፍትሔ ያለው በሴቶች ላይ ነው፤ ሴቶች መብቶቻችን እንዲረጋገጥ ተግተን ልንጥር ራሳችንን ልናበቃ እና ባልተመቻቸ ሁኔታም ቢሆን ተግዳሮቶችን እየተቋቋምን ልንወጣ ይገባል። በግሌ ተግዳሮቶችን እንደዕድል ፈንታ በመውሰድ ሁሌም ራሴን ለማብቃት እና ለማሳደግ እጥራለሁ፤ ይህን በማድረጌም ውጤታማ ሆኛለሁ። እኔ ማሕበራዊ እና ቤተሰባዊ ጫናዎችን አሸንፌ ወጥቻለሁ፤ የቤት ውስጥም ሆነ የስራ ኃላፊነቴንም በአግባቡ በመወጣት ላይ እገኛለሁ ይህን በማድረግ ላይ ያሉ ብዙ ሴቶች አሉ።” ብላለች።
ሁሉንም እንደየአመጣጡ የመመለስ ፀጋ ተችሯታል። ቤት ስትሆን ለልጆች እናት፣ በችሎት አደባባይ ደግሞ ውሳኔ አሳላፊ ዳኛ ነች። በመአልት በውጭ መዶሻዋን ይዛ ለመዝገቦች ውሳኔ ስትሰጥ ትውላለች፤ በሌሊት በቤቷ ውስጥ ደግሞ ሻሿን ሸብ አድርጋ ምግብ አብስላ ቤቷን አሰናድታ ልጆቿን ትንከባከባለች። የችሎቱ ዳኛ ለመሆን እልፍ በጥንካሬ የተፈተነችባቸው ትላንቶችን አሳልፋለች።
የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናት። በዚህ ወንዶች ፈላጭ ቆራጭ በሆኑበት ዓለም ለሴት ልጅ ክብር ያላቸውና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች እንዲሆኑ አድርጋ ቀርጻ ነው ያሳደገቻቸው። የማንም እምባና ሀዘን ምክንያት እንዳይሆኑ በንፅህና አሳድጋቸዋለች። ለነገ የተሻለ ዓለም ዛሬ ትውልድ ላይ መስራት አቻ የሌለው መፍትሔ ነው ትላለች። ራሷን የለውጡ ሀዋሪያ በማድረግ ለሴት ምቹ የሆነ ነገ መፍጠር ላይም ተሳታፊ ናት።
በዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም