ወላጅ አባቷን በህፃንነት እድሜዋ አጥታለች። በዚህም እናቷ ከጉሊት ንግድ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት ነበር እርሷንና ሌሎች ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት። ይህም ሆኖ እናቷ ቀን በሥራ ውለው የማታ ትምህርት በመማር ከልጆቻቸው እኩል ክፍል እየቆጠሩ ለከፍተኛ ውጤት በቅተዋል። ይህ ደግሞ ልጆቻቸውን በማሳደጉ በኩል የተሻሉ አድርጓቸዋል፡፡ ከስድስት ልጆች መካከል የመጨረሻዋ ልጅ ነበረች መቅደስ ገብረወልድ። “እናቴ አርአያዬ ነች” የምትለው መቅደስ ለእያንዳንዱ እርምጃዋ እናቷ ትልቁ መሰረቷ ናቸው፡፡ የስኬት መንገድ ልክ ብሎም ከፍታን አይታባቸዋለችና፡፡
እናቷ ከመንገድ ላይ የጉሊት ንግድ ተነስተው ሕይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ በኢ.ሲ.ኤ ሰራተኝነት አገልግለዋል። ለትምህርት ከፍተኛ ግምት የነበራቸው እኚህ እናት ልጆቻቸው በትምህርት ለውጥ እንደሚያመጡ በማመን ሌት ከቀን ይለፋሉ፡፡ በዚህም ልጆቻቸው በሙሉ በትምህርት የተሳካላቸው ሆነዋል።
በታላላቆቿ መካከል ማደጓ ቤት ውስጥ ያሉ ችግሮች እንዳይታወቃት ያደረጋት መሆኑን የምትናገረው መቅደስ፤ እናታቸው “የሴት ልጅ እንዳትባሉ” በማለት በስነ ምግባር እንዲመሩ አድርገዋቸዋልና ለዛሬ ስኬት በቅታለች፡፡ የመጀመሪያም ሁለተኛም ደረጃ ትምህርት ላይ ውጤታማ ከነበሩት ተማሪዎች መካከል መቅደስ ተጠቃሽ ሆናለችም።
የመቅደስ ጭንቀት የጀመረው የስኬት መሰረቷ የሆኑት እናቷ ገና ዩኒቨርሲቲ ስትገባ በጉበት ካንሰር ሲታመሙ ጀምሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እናት ይህንን ህመማቸውን አብራ ውላ አብራ የምታድረውን የመጨረሻ ልጃቸው ማሳየት አይፈልጉም፡፡ እንዳትጨነቅ ህመማቸው ምንም እንኳን ከባድ ቢሆንም ቻል ያደርጉት ነበርም፡፡ ሆኖም እስከመጨረሻው ህመማቸውን ማፈን አልቻሉም። ‹‹የፈሩት ይደርሳል…›› እንደሚባለው ሆነና ላይመለሱ አሸለቡ፡፡
ይህ ጊዜ ለትንሿ መቅደስ እጅግ ከባዱ ነበር፡፡ ምክንያቱም የእናቷን ሃዘን በቀላሉ መቋቋም አልቻለችም፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ ህመም ውስጥም ገብታ እንደነበረና ለሁለት ዓመታት በከባድ ስቃይ ውስጥ ቆይታ ከሁለት ዓመት በኋላ እንደገና ለመኖር ትግል መጀመሯን ታስታውሳለች፡፡
መቅደስ ዳግም እራሷን አረጋግታ እናቷ ይሏት የነበሩትን ተግባራት ለመከወን ትጥርም ጀመር፡፡ አንዱ “የሴት ልጅ እንዳታስብሉኝ…” የሚለው ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን ስድብ የሚመስል አባባል እርሷ ሕይወትና ኑሮ እንዲሁም ስኬት አድርጋው ለሌሎች አርአያ ለመሆንም ታተረች፡፡ ለእናቷ ነፍስ ማረፍም ስኬቷን አማራጭ አደረገች፡፡ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በጥሩ ውጤት ያዘችም።
ከዲግሪው በኋላ ኮተቤ አካባቢ በሚገኝ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በማስተማር የሥራ ዓለምን አንድ ብላ ጀመረች። በመቀጠል ሌላ ፒያሳ አካባቢ የሚገኝ አንድ የመንግስት ትምህርት ቤት አንድ ዓመት አስተማረች፡፡ ይህ ቦታ ግን ለእርሷ ሌላ ትምህርት የሰጣት ነው፡፡ ምክንያቱም የምትሰማቸው የድህነት ታሪኮች እጅግ ልብ የሚሰብሩ ናቸው፡፡ መቋቋም የሚችሉት አይነትም አይደለም፡፡
በአንድ ጎኑ የማታውቀውን የሕይወት ውጣውረድ ብታይበትም በአንድ በኩል ግን በየቀኑ የምታዝንበትን ነገር እንዲገጥማት አድርጓታል፡፡ ስለዚህም ከዚያ ወጥታ ሌላ የመንግስት ትምህርት ቤት ለመቀየር ወሰነች፤ አደረገችውም፡፡ ነገር ግን እዚያም ቢሆን የተለየ ታሪክ አልገጠማትም፡፡ የችግሩ መጠን መልኩን ቀይሮ አገኘችው እንጂ።
አዲሱ ትምህርት ቤቷ አንድ የእርዳታ ድርጅት የሚያግዛቸው ኤች አይቪ ፖዘቲቭ የሆኑ ህፃናት ያሉበት ነው፡፡ ስቃያቸው ከባድ ነበር፡፡ እጅግ በጣም ያሳዝናሉ፡፡ ሁሌም በእንባ ታጀባ ታናግራቸዋለች። ግን ይህ መፍትሄ እንዳልሆነ ታውቃለች፡፡ እናም የማህበረሰቡ ችግር እጅግ ሰፊ መሆኑንን ተረድታ አባይን በጭልፋ ቢሆንባትም ነገሩ የራሷን አሻራ ለማሳረፍ ወሰነች፡፡
አንድ አራት ኪሎ አካባቢ ያለ ህፃናት ላይ የሚሰራ ገብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ የማህበራዊ አገልግሎት ሰራተኛ በመሆንም መስራት ጀመረች። በዚያም ልጆቹን ቤት ለቤት በመሄድ መመልከት ብሎም ከወላጆቻቸው ጋር የሚያገናኝ አይነት ሥራ መከወኗን ቀጠለች። ድርጅቱ አዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ የነበረ በመሆኑ አራት ኪሎ ላይ ያለውን የድህነት ጥግ ማየት፤ ልጆች ያለባቸውን ችግሮች የመመለከት እድል ሰጣት።
መቅደስ በዚህ ሥራዋ ሌላም ገጽታ ያለው ችግርን ተመልክታለች፡፡ ከሁሉ በላይ የሚያሳዝናት ልቧን ያደማው ግን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሆነው ማታ ማታ ገቢ ለማግኘት በሴተኛ አዳሪነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ልጆች ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ በተለያዩ በሥራና በሕይወት ልምድ የተመለከተችው ነገር የሕይወት አቅጣጫዋን ወደ አንድ መስመር እንዲያመራ ይቃኘው ጀመር።
‹‹ሲሲ ኤፍ ካናዳ›› የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ በመቀጠር በመላው ኢትዮጵያ በመዞር የሚሰሩ ሥራዎችን የመመልከት እድል አገኘች። በዚህም ከአዲስ አበባ የበለጠ ፍፁም ድህነት የሚታይባት አንድም የኢትዮጵያ ክፍል አለመኖሩን ተመለከተች፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ድህነት በዚህ ልክ ከሆነ የሀገራችን ሀብታሞች ምን እያደረጉ ነው፤ ይህ ሁሉ ህብረተሰብ በድህነት የሚማቅቀው የሚለውን የወስጧን ጥያቄ ለመመለስ የሀብታሞች መወያያ ነው ወዳለችው አንድ በአዲስ አበባ ውስጥ ያለ ትልቅ ሆቴል ተቀጠረች።
በሆቴሉም ለዘጠኝ ወራት በነበራት ቆይታ ያለ ምንም መሳሳት በአንደ ቀን እስከ 100 ሺህ ብር የሚከፍሉ ሀብታሞች መቶ ብር አጥተው መንገድ ላይ ከሚንጠራወዙት ድሆች ጋር ማነፃፀር ከአዕምሮ በላይ ሆኖባት፡፡ ሌላ የሥራ አማራጭ መፈለግ ጀመረች። ይህም በኤዩ ስር ያለ የጉድ ገቨርነንስ ዲፓርትመንት የሚመራ ድርጀት ላይ ጣላት፡፡
የአፍሪካ 2063 አጀንዳ እንዴት ተግባራዊ ሆኖ ሀገርን መቀየር ይቻላል በማለትም ማሰብ ጀመረች። በዚህም ሀገሪቱ በርካታ ወጣቶች በተለይም ሴቶች የሞሉባት ሀገር በመሆኗ እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች ለማገዝና እነርሱ ላይ ሰርቶ ለውጥ ለማምጣት ብዙ የሚያዳግቱ ነገሮች እንደሌሉ አምናም ሥራ ጀመረች፡፡
በዚህ መካከል በእንግሊዝ ሀገር ሁለተኛ ዲግሪዋን ሊዲንግ ኢኖቬሽን ኤንድ ቼንጅ በሚል ትምህርት መስክ የያዘችው መቅደስ፤ ትምህርቱን ለመማር ያነሳሳት የኢትዮጵያዊን ችግር ምን ላይ እንደሆነ በመመልከት፤ የተቋማት ባህልን፤ የስራ ባህልን፤ በአጠቃላይ ያለውን የባህል ለውጥ በማጥናት “አሻጋሪ” የሚባል ድርጅት በማቋቋም ለመስራትም ነው፡፡ በዚህም ሀሳቧ ተፀንሶ “አሻጋሪ” የሚባል ተቋም ተወለደ፡፡
ትውልድን ከአንዱ ወደ አንዱ በመለወጥ ሀገርን የማሻገር ሀሳብ ያለው ነው፡፡ ትወልዱ የሚሻገር አስተሳሰብ እንዲያመጣ የአቅም ግንባታ ላይ ይሰራልም። በድርጅቱም የተለያዩ አይነት ትምህርቶችን ለመሪዎች መሰጠት ጀመረች። “መሪነት ሲባል ራስን መርሳት ማለት ነው ለሕዝብ መኖር ማለት ነው›› ብሎ የሚያምን ዜጋ መፍጠር ነው፡፡ እኔ መሪ የሆንኩት ለምድነው? ለመሪነት በመጣሁበት መንገድ ልክ ነው ወይ? ሕዝቡን እያገለገልኩ ያለሁበት መንገድስ በሕዝብ ዓይን እንዴት ይታያል? የሚለውን ጥያቄ የሚመለስ መሪን እንዲሁ ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡ በዚህም በርካቶችን የማሰልጠን ሥራ ሰርቷል ትላለች መቅደስ።
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፐብሊክ ሰርቪሰና የሰው ሀብት አስተዳደር ቢሮ ጋር በመሆን ወደ 50ሺህ ሰዎችን ለማሰልጠን የቻለው ድርጅቱ፤ በስልጠናውም የመንግስት ሰራተኞችን ችግር በመፍታት ውጤታማ አገልጋዮችን ለመፍጠር እስካሁን ድረስ ስምንት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ለመድረስ እንደቻሉ ታብራራለች።
“‹እናቴ ለልጆቼ እዳ ጥዬ አልሄድም› በማለት ቤት ለመስራት እንኳን ዓመታትን ጠብቃለች። እኛም ለትውልደ እዳ ጥለን እንዳንሄድ በየተሰማራንበት ዘርፍ በቂ ስራን መስራት ይኖርብናል” ብላ የምታምነው መቅደስ፤ አሁን ሦስተኛ ዲግሪዋን በሚዲየሸንና ኮንፍሊክት ሪዞልሽን የትምህርት መስክ እየተማረች ትገኛለች፡፡ እስካሁን መሪዎችን በማሰለጠን ብትቆይም አሁን ላይ ማህበረሰብ ለማህበረሰብ፣ ቤተሰብ ለቤተሰብ እንዴት ተግባብቶ መኖር እንዳለበት ግራ የተጋባበት ዘመን ላይ ያለን በመሆኑ ይህን ችግር መፍታት ትፈልጋለች፡፡
ሌላው ዲፕሎማሲ በሚባል ትምህርት በዩናየትድ ኔሽን በተሰጣት የትምህርት እድል ጀኔቫ ላይ እየተማረች መሆኑንና ዘንድሮ እንደምትጨርስ፤ እስከ ዛሬ 135 ሺህ ሰዎች በላይ ስልጠና እንደሰጠችና ለ146 ሴቶች የስራ እድልን እንደፈጠረች የነገረችን መቅደስ፤ የእራሳችን የሆነ እሴትን በመጠቀም ችግሮቹን ተነጋግሮ የሚፈታበት መንገድን ማስተማር፤ ወጣቱ ላይም የተለያዩ አጋጣሚዎችን ተጠቀሞ ማን እንደሆነ ማሳየት፤ ባህሉን ወጉን ሳይረሳ የዘመኑ ጀግና የሚሆንበት አካሄድ እንዲከተል ማነቃቃት ላይ የተለያዩ ሀሳቦች በማንሳት ለወጣቱ ለመድረስ እየሞከረች ነውም፡፡
መቅደስ እንደምትለው፤ ስልጠናዎቹ እንደ ሰልጣኞቹ ሁኔታ ይወሰናል፡፡ ለምሳሌ፡- መሪዎች ሲሰለጥኑ እንዴት የሚመሩትን ተቋም መምራት እንዳለባቸው፤ እንዴት ሰራተኞችን ማስተናገድ እንደሚችሉ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ‹‹ኮቺንግ›› የተባለ ስልጠና ነው የሚወስዱት፡፡ ከዚያ ውጭ ወጣቶች ጋር ሲሄዱ ደግሞ ምን መሆን እንደሚፈልጉ፤ ምን መስራት እንደሚሹ ስለማያውቁ ያንን መምራት፤ ዓይን የሚከፍቱ ፕሮግራሞችን በማካተት እንዲሰለጥኑ ይደረጋል።
በወጣቶች ስልጠና ላይ ደግሞ ሕይወትን እንዴት መምራት እንደሚችሉ፤ ራስን ማክበር ላይ፤ ጓደኝነትን መምረጥ ላይ፤ የተለያዩ ጥያቄዎቻቸውን መመለስ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሀሳቦች ይነሳሉ። አሁን ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመፈራረም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ ዜጎች በስነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ፤ ራሱን የሚያውቅ ትውልድ እንዲያፈራ እየተሰራ ይገኛል።
ሴቶች ላይ የሴቶች ዋጋን በአግባቡ ተረድተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ማስቻል ላይም እንደሚሰሩ የገለጸችው መቅደስ፤ ከሴቶች ጋር የስራ እድል ፈጠራን ለሴቶች ብቻ እየተሰጣቸው ቤተሰብን የሚመሩ ሴቶችን የማፍራት ሰፊ ተግባርም በአሻጋሪ ድርጅቱ አማካኝነት እየተከናወነ እንደሆነም ነግራናለች፡፡ አሁን ላይ በድርጅቱ ትኩረት ተሰጥቶት ከሚሰራው ስራ መካከል መልካም ወላጅነት ምን ይመሰላል የሚል ሀሳብ ያለው ስራ ነው።
“ትውልድ የሚሰራው ከቤት ነው። ለእያንዳንዱ ትውልድ መንሻፈፍ ተጠያቂው ደግሞ ቤተሰብ ነው። የአሁን ጊዜ ወላጅ ስለ አበላ ስለ አጠጣ ምንም ስላላጓደለ ልጁን ያሳደገ ይመስለዋል። ልጅ ዝም ብሎ ቤት ቁጭ ሰላለ ጨዋ አይደለም። በዚህ በቴክኖሎጂ ዘመን ሁሉን ነገር እጃቸው ላይ ያገኙታል” የምትለው መቅደስ፤ ልጆችን ለማሳደግ መልካም አስተሳሰብ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ወላጅ ሊረዳው ይገባል። ልጅ የተዘራበትን ነው የሚያበቀለው፤ ምንም ያልተዘራበት ልጅ ወጥቶ ምንም አይሰራም።፡ ስለዚህ ቤተሰብ ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ መስራት እንዳለበት ትመክራለች፡፡
ድርጅታቸው ለታዳጊዎችም ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ሲሆን፤ ይህም ከአስራ ሶሰት ዓመት በላይ የሆኑ ልጆችን የሚያካትት ነው፡፡ ቅዳሜ ቅዳሜ የሚሰለጥኑበት ሁኔታ ተመቻችቷል። ሌላው በኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በኩል መምህራንን በማሰልጠን ተማሪዎቻቸው ጋር እንዲደርሱ የማድረግ ስራ እየሰሩ ነው፡፡
“ትውልዱ በጣም ከመፍጠኑ የተነሳ ያውቃል ተብሎ የማይታሰበውን ነገር በቀደመ እድሜ ሊያወቅ ችሏል። ልጆች በእውቀት፣ በማንነት መሰራት የሚገባቸው እድሜ ላይ የሌሎች ባህል ተፅእኖዎች ስር ወድቀዋል። ይህንን የማስተካከል ሀላፊነት ደግሞ የወላጅ ነው” ትላለች መቅደስ፡፡
እኛ ቤተሰቦቻችን የመከሩንን የመሩንን መንገድ ተከትለናል፡፡ ልጆቻችንም የእኛን ፈለግ መከተል ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዘመኑ የሚመጥነውን የእድገት ደረጃ ማሳየት ያለብን እኛ ነን፡፡ በጥበብና በማስተዋል ልናሳድጋቸው ያስፈልጋል፡፡ ከአንድ ዓመት እስከ አስር ዓመት ድረስ ያለው እድሜያቸው ደግሞ ለዚህ ስኬታችን ጥሩ አማራጭ ነው፡፡ ስለዚህም በመመከር ሳይሆን አርአያ ሆነን በማሳየት ማሳደግ አለብን ባይ ናት።
ልጆች ከ12 ዓመታቸው በኋላ ምክር ይሰለቻቸዋል። ከዚያ ይልቅ የሚፈልጉት መሞከርን ነው፡፡ ወላጅን መስማት ትተው ጓደኞቻቸውን ማዳመጥ ይጀምራሉ። እናም በቀላሉ ለመመለስ እንቸገራለንና በእድሜያቸው ልክ እናሳድጋቸው፡፡ ወላጅ መናገርን አቁሞ ማዳመጥና እንደ ጓደኛ ነገሮችን የማስረዳት ጊዜ ላይ መድረስ አለበት ትላለች።
ይህ ጊዜ ለልጆች ሀሳባቸውን የሚከፋፍል ነገር የሚበዛበት ነው፡፡ እናም በትምህርታቸው ዝቅ የሚሉበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ስለዚህም ይህንን በመረዳት የጥበበኛ ወላጅ ሚናን መወጣት ይገባናልም ስትል መልዕክቷን ታስተላልፋለች፡፡
ልጆች 16 ዓመታቸው ላይ ሲደርሱ በችኮላ ሁሉንም ነገር ማግኘት ይፈልጋሉ፤ ቶሎ ያስቡበት ላይ መድረስን ይሻሉ። ስለሆነም ከቤተሰባቸው ልዩ ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እናም በትኩረት ሁኔታቸውን እየተመለከቱ መከታተልና መምራት ተገቢ ይሆናል በማለት ታስረዳለች።
ወላጅነት ማልበስ ማስተማር ብቻ ሳይሆን ልጆችን አዳምጦ በትክከለኛው መንገድ መምራት ግዴታው ነው። ትውልድ ሳያመልጥ ለመመለስ የሚያስችለውን እያንዳንዱን ተግባር ማከናወን አለበት፡፡ ለስኬትም ሆነ ለውድቀቱ ዋናው የወላጅ ተግባር ነውና ከወለዱ በኋላ የልጅን ፍላጎት በመከተል ማስተካከል ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ ይገባዋል የማሳረጊያ መልዕክቷ ነው። አዎ ወላጆች የልጆች መሪ ናቸውና እንዲሆኑላቸው የሚፈልጉትን ሆነው በማሳየት ሊመሯቸው ይገባል በማለት ሀሳባችንን ቋጨን፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም