ዛሬ የተገኘንበት በተለምዶ ‹‹ሀዲድ›› ገበያ አልያም ‹‹መሿለኪያ›› ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ ነው። ይህ መገኛው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሆነ ቦታ ምናልባትም የአካባቢው ልዩ ገጽታ ማሳያ ነው ቢባል መዳፈር አይሆንም፡፡
ቦታው እግረኛ እንጂ መኪና የያዘ ዝር አይልበትም። መኖሪያው ለአንቡላንስ ጭምር የተፈቀደ አይመስልም። ኮሮኮንች የበዛበት ጥርጊያ ቢሆንም ቤቶቹ እርስ በእርሳቸው የተጠጋጉና የተደጋገፉ ናቸው። በዋዛ መውጣት መግባት አይቻልም። በዚህ ስፍራ የሚኖሩ ሰዎች ቢያማቸው እንኳን የሚደርስላቸው ጎረቤት እንጂ አንቡላንስ አይሆንም። አያድርገውና እሳት ቢነሳ አብረው ከመጋየት የዘለለ ምርጫ አይኖራቸውም። የእሳት አደጋ መኪና መግቢያ ይሉት አይታሰብበትም።
ስፍራው እንዲህ ይባል እንጂ አይጠላም። እንደውም ይመረጣል፤ ይወደዳል። ምክንያቱም ድሆችን ሳይንቅ እፎይታን ይሰጣል። በጉልበት፣ በአቅም የደከመውን በዝቅተኛ ዋጋ ያሳርፋል። ከሁሉም የሚበልጠው ደግሞ የእርስ በእርስ መተጋገዝ ያለበት መሆኑ ነው፡፡
ስፍራው የጨነቀው ችግሩን የሚረሳባቸው፣ በርካታ አጋጣሚዎችም አሉት። ከነዚህ አንዱ መልካም የስራ እድል መኖሩ ነው። ብዙ ቤቶች ከሌሎች ጋር ተጋርተው የገቢ ምንጭ ያስገኛሉ። ሌሎች ደግሞ ከእነርሱ የባሱትን እያዩ እንዲጽናኑ ይሆናል። ከምንም በላይ ደግሞ መልካም ጉርብትናው ሁሉንም ችግር ገደል የሚሰድ ነው፡፡
በስፍራው የራበው አይመለስም፣ በኪሱ አቅም ይመገባል። የታረዘም ይለብሳል። የዚህ ስፍራ ድንቅ ጉዳይ በሚገኘው ጥቂት ገንዘብ ቤት ተደጉሞ፣ ችግር ተሸፍኖ ልጆች ለቁምነገር መብቃታቸው ነው። ይህንን ምስክርነት የሚያረጋግጡልን የዛሬዋ የ‹‹እንዲህም ይኖራል›› አምድ እንግዳችን ወይዘሮ ገበያነሽ መንገሻ ናቸው። ገበያነሽ በአካባቢው በዝቅተኛ ዋጋ ቤት በማከራየት ኑሯቸውን የሚገፉ ወይዘሮ ናቸው።
ወይዘሮ ገበያነሽ ሥራቸውን ‹‹አሀዱ›› ያሉት ጫማ ፋብሪካዎች ውስጥ ነበር። በጫማ ስፌት ሙያ 32 ዓመታትን አሳልፈዋል። 1983 ዓ.ም ግን ለእርሳቸው መልካም ሆኖ አልመጣም። ዓመታትን በሥራ ከዘለቁበት፣ ድርጅት በሰራተኛ ቅነሳ ሰበብ ተሰናበቱ። ብዙ ከለፉበት፣ ሙያን ካካበቱበት ሥራ ድንገት ለቀው የት እንደሚደርሱ ግራ ገባቸው፡፡
ወይዘሮዋ እንጀራን ፍለጋ ባዘኑ፣ ተንከራተቱ። በሙያቸው ሊቀጥሯቸው የሚችሉ ተቋማትን ያለ እረፍት ማፈላለግ ያዙ። አንድ ቀን ‹‹ኢትዮ ጣሊያን›› ጫማ ፋብሪካ የካበተ ልምዳቸውን መዝኖ በሙያቸው ቀጠራቸው። እጆቻቸው ዳግም በጫማ ስፌት ላይ ዋሉ። ‹‹እፎይ›› ማለት ሲጀምሩ ፋብሪካው ዓመታትን ያሻገራቸው አልሆነም።
በወቅቱ ጣሊያኖቹ በመክሰራቸው ፋብሪካውን ሊዘጉት ተገደዱ። የነበሩት ሰራተኞችም ሊበተኑ ግድ ሆነ። እናት ገበያ ድንገቴው አጋጣሚ ፈተናቸው። ሦስት ልጆቻቸውን በወጉ ለማስተዳደር ኑሮ ያንገዳግዳቸው ያዘ።
ባለቤታቸው ወታደር ነበሩ። ግዳጅ ሳሉ ተሰውተዋል። ሁሉም ልጆች የእርሳቸውን እጅ ናፋቂ ናቸው። ወይዘሮዋ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ተጋቡ። ሰማዩ የተደፋባቸው ያህል ጨነቃቸው። ከስራ ሲሰናበቱ ቀናትን የሚያሻግር እንኳን ገንዘብ አልያዙም። ያላቸውን ሸጠው ልጆቻቸውን የሚመግቡበት ጥሪት አላቆዩም፡፡
ዘወትር ስራ ፍለጋ ማልደው ይወጣሉ። ያለአንዳች ውጤት ይመለሳሉ። በአንድ አጋጣሚ ግን በሙያቸው ብቻ ስራ ፈልገው እንደማይዘልቁ ገባቸው። በደሞዝም ሆነ በሙያ የማይመጥናቸውን ስራ ለመስራት ወሰኑ። በላይአብ ሞተርስ ስፔርፓርትና መገጣጠሚያ ድርጅት ተቀጥረው በጥበቃ ስራ ዘብ ቆሙ፡፡
ምን የከፋ ችግር ቢገጥማቸው እጅ የማይሰጡት ወይዘሮ ገበያነሽ፤ ዝቅ ብሎ መስራት አንድ ቀን ከፍ እንደሚያደርጋቸው ያውቃሉ። ለልጆቻቸው የተሻለውን ለመስጠት የሙያውን ታላቅነት ተቀብለው በብርታት ስምንት ዓመታትን አሳለፉ።
‹‹እግዚአብሔር የሚወደውን ይፈትናል። እኔም በብዙ ተፈትኜ ተስፋ የቆረጥኩበት ጊዜ ነበር›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ በዚህ ድርጅት ሳሉ የሚወዷት ልጃቸው በኩላሊት ህመም በጠና ስለመታመሟ ያስታውሳሉ፡፡በወቅቱ በቀላሉ የሚያሳክሟት አልሆኑም። ህክምናው አቅምን ይፈትናል፡፡
ክፍያው እንደሳቸው ጥበቃ ለሚሰራ ቀርቶ በቂ ገቢ ላለው ሀብታም እንኳን አይደፈርም። ለአንድ ጊዜ ዲያሌሲስ ብቻ ከ1800 ብር በላይ ያስፈልጋል። በመንግስት ሆስፒታል በቀላል ወረፋ ስለማይገኝ የግል መታከም ግድ ሆኗል። በጊዜው ከዲያሌሲሱ ክፍያ ባሻገር ለሌሎች ወጪዎች የሚከፍሉት ክፍያ ከአቅማቸው በላይ ነበር።
የወይዘሮ ገበያነሽ ስቃይ በአንዱ ብቻ አልበቃም። የታማሚ ልጃቸውን ወጪ ለመሸፈን እየተንገዳገዱ ሳለ ሌላ ክፉ ገጠመኝ አገኛቸው። በድንገት ሁለተኛው ልጃቸው በስኳር በሽታ ታመመ። አንዱን ተወጣሁ ማለት የጀመሩት እናት በሁለተኛው ችግር ተስፋቸውን አሟጠጠው።
የመጀመሪያዋን ልጃቸውን ሲያስታምሙ የሥራ ባልደረቦቻቸው የአቅማቸውን ያግዟቸው ነበር። ገንዘብ የሌላቸውም ተራቸውን እየሸፈነላቸው ቆይተዋል። ሁለተኛው ችግር ሲመጣ ግን ሁሉ ነገር ከበዳቸው። ለየትኛው ልጃቸው እንደሚሆኑ ግራ ተጋቡ።
አንደኛው ምግብ፣ ሌላኛዋ ደግሞ የዲያሊስስ ህክምና ወጪ ያስፈልጋታል። እሳቸው የትኛውንም ማሟላት አይችሉም። ዘወትር እንዳለቀሱ፣ እንዳዘኑ ዘልቀዋል። እናት ናቸውና ልጆቻቸውን ‹‹ይሙቱ›› ብለው አልተዋቸውም። ቀን እየሰሩ፣ ሌሊቱን በማስታመም ደክመዋል። እርሳቸው ሳይበሉና ሳይለብሱ ለእነሱ ህክምና እየደጎሙ ከአቅማቸው በላይ ለፍተዋል።
በሁለት ልጆቻቸው ህመም እየተሰቃዩ የቆዩት ወይዘሮ፤ ይባስ ብሎ ድንገቴ ችግር ገጠማቸው። ልጆቻቸውን እየደጎመላቸው የቆየው ሥራ በአንድ አጋጣሚ ቆመ። ለእሳቸው እንዲህ መሆኑ ሌላ ህመም ነበር። በወቅቱ የድርጅቱ ቦታ መቀየር ከሌሎች ቅርንጫፎች ጋር ሰራተኛው እንዲቀላቀል ተገደደ፡፡
ይህ እውነታ ሁለት የሴት የጥበቃ ሰራተኞችን ቀንሶ ከስራ አስወገደ። አንደኛዋ እሳቸው ነበሩ። አሁን ነገሮች የባሱ፣ ሆኑ። የበዛ ጭንቀታቸው ‹‹ከልጆቼ ቀድሜ እኔ መሞት አለብኝ›› እስከማለት አደረሳቸው።
ራሳቸውን ማረጋጋት ያልቻሉት ባለታሪካችን፤ ችግሩ ባሰባቸው። ይህ ክፉ አጋጣሚ ደግሞ ብቻውን አልመጣም። መጀመሪያ የታመመችውንና ጧሪ፣ መከታዩ ያሏትን ትልቋን ልጃቸውን በሞት ተነጠቁ። ሀዘናቸው ከፋ፣ ውስጣቸው ደም አነባ። እናት ገበያ ጠዋት ማታ ‹‹እዬዬ›› ማለት ልምዳቸው ሆነ።
ጥቁር ልብሳቸውን ሳይለውጡ፣ ሀዘናቸውን ሳይረሱ፣ ሌላ ሀዘን ሆነ። በዓመቱ ወንዱ ልጃቸው ተደገመ። የ21 ዓመት ወጣትና የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነበር። ገበያነሽ ሕይወት ከበዳቸው። መኖር አስጠላቸው። አሁን አንድ ልጅ ቀርቷቸዋል። የልጃቸው ልጅ ጭምር ተስፋቸው ነው፡፡
የእነሱ መኖር ራሳቸውን እንዳያጠፉ፣ ነገን በጭላንጭል እንዲያዩ ምክንያት ሆኗል። ይህ እውነት ለእነዚህ ልጆችስ ማን አላቸው እንዲሉ አስችሏቸዋል። ሀዘናቸውን ለመርሳት እንዲታገሉ ሰበብ ሆኗል።
ወይዘሮ ገበያነሽ በትዳር ሕይወታቸው ይኖሩ የነበሩት አራተኛ ክፍለ ጦር አካባቢ ነበር። አካባቢው ለልማት በመፈለጉ ግን ከቦታው እንዲነሱ ተደረጉ። ይህ የሆነውም በደርግ ጊዜ ነው፡፡፡ከጊዚያት በኋላ ወደዚህ ቦታ መጥተው እንዲሰፍሩ ሆኑ፡፡
በወቅቱ ቆርቆሮ በቆርቆሮ ተሰርቶ መደዳውን ነበር የተሰጣቸው። እናም ያለአባት የሚያሳድጓቸውን ልጆች በብርድና በሀሩር አላሰቃይም ብለው ቤቱን ከቆርቆሮ ወደ ጭቃ ቤት ቀየሩት። በእርግጥ ይህንን ያደረጉት ለልጆቻቸው በሚል ብቻ አልነበረም። የባለቤታቸውንም ስም በመልካም ለማስጠራት እንጂ። እርሱ ቢኖር ኖሮ ይህንን ያደርግ ነበር እንዲባል አይፈልጉምና ምንም እንዳልጎደለባቸው ለማሳየት የአቅማቸውን አድርገዋል። በዚህም ብዙዎች ይኮሩባቸዋል፤ ከአካባቢው ብዙ ሰዎች ‹‹ጠንካራ ነች›› ይሏቸዋል።
ወይዘሮ ገበያነሽ ልጆቻቸውን ማስረሻ ይሆነኛል ያሉት የልጅ ልጃቸው ምን እንኳን እርሳቸው ጋር ባይኖር በየጊዜው ይጠይቁት። ይንከባከቡት ነበር። ልፋታቸው አልተቆጠረም። ሀሳባቸው አልሰመረም። እርሱንም እንደእናቱ በከባድ ህመም በሞት ተነጠቁ። ልጁ በጉበት በሽታ ሲሞትባቸው ሀዘናቸው እጅግ ከባድ ነበር። ለረጅም ጊዜም በሀዘን ስቃይ ቆይተዋል።
ገበያነሽ ጉልበታቸው በደከመ፣ ደጋፊ፣ ጧሪና ቀባሪ በሚሹ ጊዜ ጎዶሏቸውን ያስባሉ። እኩያ የሚባሉ ልጆቻቸውን ማጣታቸው ልባቸውን ሰብሯል። አሁን ልጆቻቸውን መርሳት ባይችሉም የደከመ ጉልበታቸውን ለበለጠ ድካም ሳያጋልጡ መሥራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ናቸው ፡፡
ዛሬ ላይ በዝቅተኛ ዋጋ ልጃቸው ማከራየት የጀመረችው የአልጋ ኪራይ ቀጥለዋል። ከሞት የተረፈ አንድዬ ልጃቸውንና ሊያሳድጓት ያመጧትን ልጅ በሚያገኙት ገቢ ያስተዳድራሉ። የመኖሪያ ቤት ችግር ለብዙዎች ፈተና ነው። የመሰሎቻቸው ሕይወት ከዚህ የተለየ አይደለም። በተለይ የነ ገበያነሽን መንደር የመሰሉ ለዘመናት ኋላቀር የሆኑና ያለ ፕላን የተለጠጡ ነበር አካባቢዎች የፈተናው ገፈት ቀማሾች ናቸው።
እርሳቸው ግን በሌሎች ፈተናዎች የቤቱን ጉዳይ ተወጥተውታልና የከፋ ችግር አልገጠማቸውም። ይልቁንም አልጋ አከራይ ሆነው ተጠቃሚ ሆነዋል። አሁን ላይ በላይ ክፍል ሰርተው የሚያከራዩት ቤት በለስ ቀንቷቸው በደርግ ጊዜ ቀበሌ የሰጣቸው ነው። አነስተኛ ክፍያ ለመንግስት እየከፈሉ መኝታ ክፍል ሳያምራቸው ሳሎናቸውን መኝታ አድርገው የገቢ ምንጫቸው አድርገውታል።
ቤቱ ለደህንነታቸው ሲባል በግርግዳ የተለየ ሲሆን፤ የራሱ የሆነ በር አለው። ክፍሉ ግን እጅግ ጠባብ የሚባል ነው። በአንዱ ክፍል የሚሆነው በሌላው ክፍል በቀላሉ ይሰማልና እንቅልፍ ይናፍቃል። ምንም ምርጫ የላቸውምና ገቢው የቤተሰቡን ጉሮሮ የሚሞሉበት እንጀራቸው ሆኗል። አሁን ወይዘሮዋ ምንም ሥራ የላቸውም፤ ጉልበታቸውም ቢሆን ደክሟል። ምርጫ ባይኖራቸውም መፍትሄ ይሆነኛል ያሉትን ተግባር እየከወኑ ነው።
አልጋ ኪራዩ ልክ እንደ አውቶቡስ ተራው ‹‹ኬሻ በጠረባ›› ይሉት አይደለም። ከወለል ያለፈ አልጋን ብቻ የያዘ ኪራይ ነው። ስለዚህም በዝቅተኛ ዋጋ ማለትም በ30 ብር አንድ ሰው አንድ አልጋ ይዞ ማደር እንዲችል አድርገው ገቢ እያገኙ የሁለቱን ልጆች ወጪና የዕለት ምግባቸውን ይሸፍናሉ። ተደራራቢ ቆጡ በG+8 ድረስ ያለ ሲሆን፤ ክፍያው እንደ ከፍታው ይለያያል። ከፍ ካለው ቆጥ ላይ የሚተኛ ሰው ከፍ ያለ ዋጋ መክፈል ይጠበቅበታል። ምክንያቱም ለመሰረቅና በቀላሉ ፣ ለአደጋ ለመጋለጥ አይመቻችም።
ወይዘሮ ገበያነሽ አልጋ ሲያከራዩ ተመራጭ ናቸው። ልክ በትላልቅ ሆቴሎች እንደሚደረገው ‹‹ዕቃዬ ይሰረቃል›› የሚል ስጋት ያለው ሰው ንብረቱን ለሪስፕሽን እንደሚያስረክበው በሃዲድ መንደርም ስጋት የገባው ሰው ንብረቱን ለወይዘሮ ገበያነሽ አስረክቦ ያለስጋት እንቅልፉን ይለጥጣል።
ወይዘሮ ገበያነሽ በብዙ ነገር ተፈትነዋል፤ የሰዎችን የችግር ጥግ አይተዋል። በዚህም አልጋ ሲያከራዩ የልጆቻቸው ስቃይና የቤተሰባቸው የኑሮ ሁኔታ ፊታቸው ድቅን ይላል። ስለዚህም ተከራዮቻቸውን ምንም እንኳን ዘመኑ ሰው ለሰው የሚተማመንበት ባይሆንም እርሳቸው ግን በጎነት ይከፍላል ብለው ስለሚያምኑ ልክ እንደቤተሰባቸው አድርገው ነው የሚቀበሉት። በዓል ሳይቀር ያላቸውን አብሮ በመቋደስም ነው የሚያሳልፉት።
ከዚያም ከፍ ሲልም በቤት አዳሪዎቹ የተለያዩ ሰዎች በመሆናቸው መጥፎ ጠረኖች እንዳያስቸግራቸው በቂ ውሃ ያቀርባሉ፤ ካልሲያቸውን የሚያጥቡበት፤ እግራቸውን የሚታጠቡበት ሳሙና ጭምር ይሰጧቸዋል። አልጋ ተከራዮቹ የሚመጡበት ሰዓት የተወሰነ ሲሆን፤ ወደ አልጋ የመግቢያ ሰዓት እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ብቻ ነው። ሆኖም የተቸገረና የሚያውቁት ሰው ከመጣ ቦታ ካላቸው ይከፍቱለትና ከመንገድ ላይ አዳር ይገላግሉታል።
የወይዘሮ ገበያነሽ ደግነት በዚህ ብቻ አያበቃም። ላርፍድ ያለ ሰው እስከ ሁለት ሰዓት እንዲተኛ ይፈቀድለታል። ኑሯቸውንና ጎዶሏቸውን ለመሙላት ሲሉ መክፈል ላልቻለ ሰው ከልጆቻቸው ጉሮሮ ቀንሰው የሚያድርበትን እድል ይሰጣሉ። ምክንያቱም በእርሳቸው ልምድና እምነት ‹‹ቤት የእግዚአብሔር ነው›› እኛም የብርቱዋ እናት ደግነት ለሁሉም፤ ብርታት ጽናታቸውም ለሴቶች ተምሳሌት ይሁን ! እንላለን። አበቃን።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም