ዶክተር አዲስዓለም አባትሁን ትባላለች። እንደ ሀገር የሚቆጠርና የሚታይ ሥራን ከአበረከቱ ሴቶች መካከል አንዷ ነች። በተለይም በየዩኒቨርሲቲው ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ ብቸኛ ሴት ያውም አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች የቀጠለች በመሆኗ በአብነት የሚያስጠቅሳት ነው። በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከሚገኙ ኮሌጆች ትልቁ ለሆነው የተፈጥሮና ኮምፒውቲሽናል ሳይንስ ኮሌጅ በ70 ዓመት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት ዲን በመሆንም ከሶስት ዓመታት በላይ መርታለች። ከዚያ ባሻገር የአዲስ አበባ ምክር ቤት የመንግስት በጀትና ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ በጸሐፊነት በማገልገል ላይ ትገኛለች። እናም ይህን መሰል ተሞክሮዋ ብዙዎችን የሚያስተምር በመሆኑ ለዛሬ የሴቶች ቀን እንግዳችን በማድረግ ከብዙ አስተማሪ ሕይወቷ በጥቂቱ ጨለፍ አድርገን ለአንባቢያን እነሆ ብለናል።
ትንንሾቹ እጆች ለአረቄ ማውጣት
ተወልዳ ያደገችው በአማራ ክልል ደብረማርቆስ ከተማ ነው። በኑሯቸው በጣም ዝቅተኛ ከሚባሉ ቤተሰቦች የተገኘች ናት። በመሆኑም በልጅነቷ ወቅት ችግሮችን እንዴት መጋፈጥና ማሸነፍ እንደሚቻል ሕይወት ራሷ ስላስተማረቻት ጠንቅቃ አውቃዋለች። በማገልገል ውስጥ ያለውን መለወጥም አሳምራ ተረድታዋለች። በተለይም ለቤተሰብና ለጎረቤት መታዘዝን ያለውን ጠቀሜታና በረከት በደንብ የተገነዘበችበት ጊዜ ነው።
ሴት ከወንድ ታንሳለች የሚለውን ሳታውቅ የማደጓ ምክንያትም ይህ በድህነት ውስጥ ያለው ጥረቷ ነበር። ሁሉም ላይ አሸናፊ እንደምትሆን አሳይቷታል። በጣም ጎበዝ መሪ እንደሆነችም አረጋግጦላታል። ምክንያቱም እናቷ የእርሷ አርአያ ናቸው። አባቷ የጥበቃ ሰራተኛ በኋላም ተላላኪ እና መዝገብ ቤት ሰራተኛ በመሆናቸው በቂ ገንዘብ አያገኙም ነበር። ስለዚህም አጋዥና ቤቱን የሚደጉም ሌላ ሰው ግድ ያስፈልጋል። እኚህ ሰው ደግሞ እናቷ ሲሆኑ፣ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ደግሞ በሚገባ ተወጥተዋል። አረቄ ሳይቀር አውጥተው እየሸጡ ቤቱ እንዳይጎል ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ ለትንሿ አዲስዓለም መሰረትም መወጣጫ መሰላል ነበር። በምን መልኩ ቤተሰቡን ማገዝ እንደምትችልም አሳይቷታል።
ከሦስት ኪሎ ሜትር በላይ በባዶ እግሯ እየተጓዘች እንጨት ለቅማ በማምጣት ለእናቷ የተረፈችውም በዚህ ምክንያት ነው። አደግ ስትል ደግሞ ከዚህ በበለጠ ሥራ እንድትሰማራ ሆናለች። ራሷን በመቻል ከቤተሰቡ ጫንቃ ላይ መውረድም ችላለች። ይህም ልክ እንደእናቷ አረቄውን በማውጣት ለደብተርና ለእስኪርብቶ እንዲሁም ለልብሷ ወጪ እንዳያስቡ አድርጋለች።
አዲስዓለም፣ ስራ የማይደክማት ልጅም ነች። የትምህርት ፈረቃዋን ጠብቃ ከትምህርት በኋላ እንጨት ለመልቀም ዘወትር ከሦስት ኪሎ ሜትር ያላነሰ መንገድን በባዶ እግሯ ትጓዛለች። ከዚያ ስትመለስም አረቄ ማውጣቱ ላይ ትጠመዳለች። እናቷም ሥራ ስለሚበዛባቸው እርሳቸውን ታግዛለች። ከምትሰራቸው ስራዎች መካከል እንጀራ መጋገርና ወጥ መስራት ዋንኛው ተግባሯ ነው። ይህ የጀመረው ገና በስምንት ዓመቷ እንደነበርም አትረሳውም።
አዲስዓለም፣ ቤተሰብን የምታስደስተው በሥራ ብቻ አይደለም። በሌሎችም ተግባሮቿም ጭምር እንጂ። ለታናናሾቿ አርአያ በመሆንና ቤተሰቦቿን ደግሞ በማዝናናት ትታወቃለች። በማዝናናቱ የአባቷን ህመም ታስረሳለች። እንዴት ከተባለ ወንድሟ በክራር እርሷ ደግሞ በእስክስታ ነው። በእድሜ እኩዮቿ ለሆኑ ትልቅ ምሳሌም የምትሆን ናት። ለአብነት በሽልማቷ ወቅት በምታደርገው ንግግር ሁሉንም የአካባቢዋን ልጆች ታበረታቸዋለች። ወላጆችም በተለይም ሴት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኳቸው በዓይናቸው እያዩ እንዲያረጋግጡ አድርጋቸዋለች።
አዲስዓለም፣ በብዙ ሥራ ብትጠመድም ወላጆቿ የመጫወቻ ጊዜ ስለሚሰጧት ታከብራቸዋለች። ሥራዋን ከጨረሰች በኋላ ከወንዶች ጋር ሳይቀር እግር ኳስ ትጫወታለች። በዚህ እንኳን ማንም ምንም አይላትም። ምክንያቱም በትምህርቷም ሆነ ቤተሰቧን እንዲሁም ጎረቤቱን በማገልገል ማንም አያክላትም።
የ50 ሳንቲም ከረሜላና ሒሳብ
ዶክተር አዲስዓለም፣ የትምህርት አይነቶች ላይ ብዙ ምርጫ አልነበራትም፤ ሁሉንም በተለየ ትኩረት ትወዳለች። በተለይ የሳይንስ ትምህርቶችን ማበላለጥ አትፈልግም። አንድ አጋጣሚ ግን ነገሮችን እንዲቀየሩ አደረጋቸው። ይህ አጋጣሚም የ5ኛ ክፍል ተማሪ እያለች የተፈጠረ ነው። ጋሽ እምሩ የሚባለው የ5ኛ ክፍል የሂሳብ መምህሯ በክፍል ውስጥ ጥያቄ ይጠይቃል። ማንም የሚመልስ አልነበረም። ከእነርሱ ክፍል በፊት ጥያቄውን ሁሉም ክፍል ላይ ጠይቆታል። ነገር ግን ሊመልስለት የሚችል ተማሪ አላገኘም። እነዶክተር ክፍል ግን እርሷ ተገኘች። በዚህም መልሷ መምህሩ የሚይዘውን የሚጨብጠውን ነበር ያጣው። ትንሿን አዲስዓለምን ታቅፎ በሁሉም ክፍል ይዟት እየዞረ ‹‹የሒሳቧን ንግስት ተመልከቷት›› ማለትን ብቻ ነው የመረጠውም። ግን ይህም አልበቃውም። ከኪሱ 50 ሳንቲም አውጥቶ ከረሜላ እንድትገዛ ሰጣት።
ከሁሉም ከአዕምሮዋ የማይጠፋውም ይህ ተግባሩ ነበር። ምክንያቱም ማስጨብጨቡን ለምደዋለች። መምህር ግን በዚህ ደረጃ ተደስቶባት ሳንቲም ሰጥቶ ከረሜላ እንዲገዛ መደረጉ ጭራሽ የማይገመት ነው። ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰቦቿ ጭምር በእርሷ ተስፋ የነበራቸው የዚያን ጊዜ ጀምሮም ነው። ስለዚህም ይህንን አጋጣሚ የማትረሳው አድርጋ ለዘላለም አስቀጥለዋለች። የሂሳብ ትምህርቱን ቋሚ ምርጫዋ አድርጋም ዛሬ ድረስ ይዛው የዘለቀችውም ያለምክንያት አይደለም።
ዶክተር አዲስዓለም፣ መሆን የምትፈልገው ፋርማሲስት ነበር። ምክንያቷም በጣም የምትወዳቸው እና የምትሳሳላቸው የአባቷ ዘወትር መታመም እና በሽታቸው በሚሄዱበት ሃኪም ቤት በውሉ ባለመታወቁ እርሳቸውን መፈወስ የሚችል መድኃኒት ተመራምራና አጥንታ በማግኘት አባቷን በማከም ከጭንቀታቸው ማሳረፍ የሁልጊዜ ህልሟ ነበር። ነገር ግን ከፍተኛ ውጤት አግኝታ የተመደበችው በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ስለነበረ የምትወደውን የሂሳብ ትምህርት ለመማር ወሰነች። ሦስተኛ ዲግሪዋ ድረስ በሒሳብ ትምህርት የተጓዘችውም በዚህ የተነሳ ነው።
አዲስዓለም፣ በሁሉም ክፍል ላይ ትምህርቷን ስትከታተል የማንበቢያ ጊዜዋ ከአንዷ ቀን በስተቀር ውስን ነው። ምክንያቱም በሥራ ስትደክም ትውላለች። ትንሽ እንኳን እፎይ ብላ የምታጠናው የጥበቃ ሰራተኛ የሆኑት አባቷ ዘንድ ለአዳር ስትሄድ ነው። አስጠኚ ጭምር ታገኝበታለች። ምክንያቱም እርሳቸው እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋልና ያስጠኗታል። ሌላ የማጥኛ ጊዜዋ ሙሉ ቀኗን የምታሳልፍበት የተለየችዋ ቅዳሜ ናት። በቤት ውስጥ ምንም ሥራ አትታዘዝበትም፤ ማንም አይረብሻትም። የማጥኛዋና የቤት ሥራዋን መስሪያ ቀን ተደርጋ ተወስናላታለች።
የቁጥር ሥራ አብዝታ ስለምትሰራም ሙዚቃ ቢከፈትም ጭምር ለእርሷ ቦታ የለውም። ጆሮ ሳትሰጥ ልዩ ትኩረቷን ጥናቷ ላይ ብቻ ነው የምታደርገው። ምክንያቱም በርትታ መማሯና ውጤታማ መሆኗ ለእርሷ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቡ ጭምር እንደሚጠቅም ታውቃለች። በዚህም ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የደረጃ ተማሪ ነበረች። በየጊዜው ትሸለማለችም። በዚህም የአካባቢው ሰው ሳይቀር አርአያ የሚያደርጋት ልጅ ሆናለች። በእርግጥ ለዚህ ያበቃት የቤተሰቦቿ ሁኔታ ነው፤ እነርሱን ከዚህ ችግራቸው ማላቀቅ የምትችለው ጠንክራ ስትማር ነው። ስለዚህም የቤተሰቦቿ ውርስ ትምህርቷ ብቻ መሆኑን አውቃ ታጠናለች፤ ጠንክራ ትማራለችም።
እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በነበራት የትምህርት ጉዞ አንድም ቀን ጫማ አድርጋ የማታውቀው አዲስዓለም፤ ትምህርቷን አሀዱ ያለችው በአብማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተከታትላበታለች። ከዚያ ወደ ደብረማርቆስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛወረች። እስከ 12ኛ ክፍል ተምራም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የትናንቱን ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ የዛሬው ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲን መቀላቀል ችላለች።
በኮሌጁ የሒሳብ ትምህርት ክፍል ውስጥ ከተመዘገቡ 60 ተማሪዎች መካከል ብቸኛ ሴት ነበረች። ይህንን ያዩ ጓደኞቿ እና የቤተክርስቲያን ልጆች ሂሳብ መማር ከባድ ነው እያሉ የትምህርት ክፍሉን እንድትቀይር ጎተጎቷት። እርሷ ግን ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ አለች። ምክንያቱም አቅሟን በሚገባ ታውቀዋለች። ይህንን ልበ ሙሉነቷን ደግሞ ብዙዎች ውጤታቸው ሲበላሽ እርሷ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ አስደንቃቸዋለች። እንዲህ እንዲህ እያለችም ከኮሌጁ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የመጀመሪያ ዲግሪዋን በሒሳብ ትምህርትም አጠናቀቀች።
ከተወሰኑ ዓመታት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ የመጀመሪያ ልጇን ወልዳ ሁለት ዓመት ያልሞላውን ልጅ ለእናቷ ሰጥታ ሥራ ለቃ ነበር እየሰራች ለመማር ወደ አዲስ አበባ የመጣችው። ሁለተኛ ዲግሪ የሚያስተምረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ስለነበርም በርካታ ተማሪ የመግቢያ ፈተና ይወስዳል። እናም ከተመረጡና ፈተናውን ከአለፉት ውስጥ አንዷ ሆና ትምህርቱን እንድትጀምር ተደረገች። ይህ ሲሆን ግን ቤት ለቤት እያስጠናች የራሷን ገቢ እያመነጨች ነው።
ቆርጠው ከተነሱ የማይታለፍ ነገር የለም የምትለው ዶክተር አዲስዓለም፣ ብዙም ሳትቆይ የበለጠ የምትሰራበትን አጋጣሚ አግኝታለች። አዲስ አበባ በመጣች በሁለት ወር ውስጥ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ የቅጥር ማስታወቂያ በማውጣቱ እዚያ እየሰራች እንድትማር እድል አግኝታለች።
ኮተቤ 15 ሰዓት እያስተማረች ተጨማሪ የተለያዩ ቦታዎች ላይ እየሰራች፤ የዘጠኝ ክሬዲት ኮርሶችን እየወሰደች የቀደመውን ውጤታማነቷን አላስተጓጎለችም። በተጨማሪም የሁለት ዓመት ልጇን ከእናቷ በማምጣት የእናትነት እና የሚስትነትን ኃላፊነት ደርባ በአግባቡ ትወጣ ነበር። በዚህ ሁሉ ውስጥም በትምህርቷ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የማዕረግ ተሸላሚ በመሆን የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን እንደወትሮው ሁሉ በአመርቂ ውጤት አጠናቀቀች።
ዶክተር አዲስዓለም፣ የትምህርት ጉጉቷ በዚህ አላበቃም፤ ሁለተኛ ልጇን ከወለደች ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በኋላም የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት እድል በሳንዱች ፕሮግራም በስዊድን ሀገር በማግኘቷ ልታልፈው አልፈለገችም። ስለዚህም የመጀመሪያ ስድስት ወሩን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ስትከታተል ቆይታ በቀጣይ ስድስት ወሩን ትምህርት ደግሞ በስዊድን ስቶክሆልም ዩኒቨርሲቲ ለመከታተል ወደስፍራው አቀናች።
ይህንን ስታደርግ ደግሞ ልጆቿን ለባለቤቷ ሃላፊነት በመስጠት ነው። በዚህ ሁኔታ ስድስት ወር አዲስ አበባ ስድስት ወር ስዊድን በመመላለስ ከአምስት ዓመት የትምህርት ጉዞ በኋላ የሦስተኛ ዲግሪዋን አጠናቅቃለች። ጥረቷም የመጀመሪያዋ ሴት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሒሳብ ትምህርት ክፍል ሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂ አድርጓታል። በእርግጥ ሁለተኛ ዲግሪዋን ስትማርም ከ70 ተማሪዎች እርሷ ብቻ ሴት ነበረች።
በ70 ዓመት ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ዲን
የአዲስዓለም የሥራ ሀሁ የጀመረው በአማራ ክልል በከሚሴ ከተማ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሒሳብ መምህር በመሆን ነበር። በወቅቱ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላት ሌላ ሴት አስተማሪ አልነበረችምና ብዙዎች ይገረሙባት ነበር። በዚህም የዞኑ የመምህራን ማህበር የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ሆና አገልግላለች። ከዚያም በጋብቻ ምክንያት የሥራ ቦታዋን ወደ ደቡብ ጎንደር ጋይንት ንፋስ መውጫ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አድርጋ ለሦስት ዓመታትም ቆይታበታለች።
ቀጣዩ ሥራዋ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪዋን እስክትጨርስ ድረስ ያገለገለችበት ስፍራ ነው። ጎን ለጎን ምኒልክ ነርሲንግ እስኩል በትርፍ ሰዓት ታስተምርም ነበር። ሁለተኛ ዲግሪዋን ስትማር የነበራትን ትጋት፣ ታታሪነትና ከፍተኛ ውጤት ያዩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙት አማካሪዋን ቀስቅሶ በሌላ ቦታ የምትሰራበትን አጋጣሚ ፈጠረላት። እኔን የምትተካው እርሷ ነች በማለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንድትቀጠር አደረጓት።
መጀመሪያ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀለችው በመምህርነት ነበር። ከአምስት ወራት በኋላ ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ፕሮግራም ዩኒት ኃላፊነት ተሰጣት። አዲስዓለም ከሁሉም ሥራ በላይ ማስተማርን አጥብቃ ትወዳለች። ምክንያቱም በእርሷ እምነት ማስተማር መምራት ነው። ሥራ ተኮር ተግባር መከወን ነው። ከሰው ጋር የሚያጋጭ ሳይሆን የሚያስተሳስር እንደሆነም ከ16 ዓመት በላይ በማስተማር ያገለገለችበት የማስተማር ስራዋ አሳውቋታል። በነዚህ የስራ ዓመታትም በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይም አገልግላለች። ከዚህም ውስጥ አንዱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካሉት ትላልቅ ኮሌጆች አንዱ የሆነውን የተፈጥሮና ኮንፒውቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ በተለምዶ አራት ኪሎ ካምፓስን በዲንነት መምራት ነው።
በዲንነት በርካታ ስራዎችን የሰራች ሲሆን፤ በተለይም እርዳታ ለሚሹ ተማሪዎች ከተለያየ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ማመቻችት፥ ሴት ተማሪዎችን የማበረታቻ የልምድ ልውውጦችን ማዘጋጀቷ ከአብራኳ ክፋዮች ባሻገር ሌሎች ልጆችን የፈጠረችበት ነው። ለአብነት በሴቶች ክበብ ውስጥ ሴቶች በማደሪያቸው (ዶርማቸው) ውስጥ የራሳቸው የውይይት ጊዜ እንዲፈጥሩ እድሎችን ማመቻቸቷ አንዱ ነበር። ውይይቱ ቀን በቀን የሚደረግ ሲሆን፤ ችግሮቻቸውን ተወያይተው ለመፍትሄ የሚሰሩበት እንዲሆን በብዙ መልኩ ደግፋቸዋለች። እነርሱም ስኬታማም ሆነውበታል። በእያንዳንዱ ውይይት ላይ በቻለችው ሁሉ ትገኝና የራሷንና የገጠማትን ነገር እያጋራች ታወያያቸዋለችና ብዙ ልምድም የቀሰሙበት ነው። በዚህም በተማሪዎቹ ዘንድ እንደ ሁለተኛ እናት ሆና ትቆጠራለች።
ሌላው የሰራችው ተግባር ተፈጥሮ ሳይንስ የሴቶች የምርምር ግሩፕ መስርታ እርስ በእርስ የመረዳዳት ባህላቸውን እንዲያዳበሩ ማድረግ ነው። ትልልቅ የሚባሉ ውድድሮችን በምርምሩ ዘርፍ እንዲያደርጉ አስችላለች። ለአብነት ስምንት የሚሆኑ ሥራዎችን ሰርተው በውድድር ውስጥ በመሳተፋቸው አምስቱን የማሸነፋቸው ምስጢር እርሷ ናት። ለሴቶች ብቻ የሚሉትን በብቸኝነት መሳተፍም እንዲችሉም እድል ሰጥታቸዋለች። በተመሳሳይ ሴቶች በምርምር አይሳተፉም የሚባለውን አባባል በመጠኑም ቢሆን አስቀርታለች።
ዶክተር አዲስዓለም፣ ለግቢው የአስተዳደር ሰራተኞችም የምትተኛ አይደለችም። በርካታ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በማሰጠት የተሻለውን ነገር እንዲያገኙ አድርጋለች። በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲው የሚጠቀምበትን ሁኔታም አመቻችታለች። ለምሳሌ፡- በግቢው ውስጥ የከርሰ ምድር ውሃ በማስወጣት የውሃ ወጪዎችን ማስቀረት ችላለች።
ዶክተር አዲስዓለም በተጨማሪም የፕሮግራም ኮርድኔተርነት፤ በበርካታ ተቋሞች የቦርድ አባል በመሆን አገልግላለች። አዲስዓለም የኢትዮጵያ የሒሳብ ባለሙያዎች ማህበር መስራችና ገንዘብ ያዥ በመሆን ለሦስት ዓመታት አገልግላለች። አምስት የሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራትን ያካተተው የምርምር ግሩፕም አባል ናት። በዚህም የምርምር ስራዋን እንድታሰፋ አድርጓታል። ምርምሯ በአብዛኛው ልዩ ትኩረቱ መሰረታዊ የሂሳብ እውቀቶች ላይ መተንተን ሲሆን፤ ይህንን ደግሞ በተለያዩ ሀገራት በመዘዋወር ታቀርባለች። በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሒሳብ ወርክሾፖችን ሲዘጋጁ በአዘጋጅ ኮሚቴ አባልነት ታገለግላለች።
የዩኒቨርሲቲው አንዱ ተልዕኮ በሆነው የማህበረሰብ አገልግሎት ላይ በስፋት ትሰራለችም። ለዚህም ማሳያው በተለይም አራዳ ክፍለ ከተማ ላይ ያከናወነቻቸው ተግባራት ናቸው። ለምሳሌ በዚሁ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ላይ ማህበረሰቡ በርካታ ዓመታትን በውሃ ችግር አሳልፏል። እርሷም ይህንን ችግር በቅርብ ትከታተለው ነበርና ተዳፍኖ የቆየውን የከርሰ ምድር ውሃ በፕሮጀክት አስቆፍራ ማህበረሰቡም ሆነ የዩኒቨርሲቲውን ተጠቃሚ እንዲሆን አስችላለች። አሁን ውሃው በአራት ቦኖ በፓይፕ ተደርጎ እንዲሰራጭ ሆኗል።
ዶክተር አዲስዓለም፣ ሌላም በማህበረሰብ አገልግሎት የሰራችው ሥራ አለ። ይህም የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት የሚያገኙበትን አጋጣሚ የፈጠረው ነው። የጋራ መጸዳጃቸው ወደ ውስጥ ሰመጠባቸው። በዚህም ማህበረሰቡ ችግር ውስጥ ወደቀ። በቀላሉ ለመስራትም የሚቻልበት ሁኔታ ላይ አልነበረም። እርሷ ግን አይቻልምን አታውቅምና በፕሮጀክት አስተባብራ ወደ 400 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ በአዲስ መልኩ እንዲሰራ አደረገችው። በሦስተኛ ደረጃ አዲስዓለምን ከማህበራዊ አገልግሎት ጋር ያገናኛት ነገር የአካባቢው ሰው የመንገድ መብራት ነበር። መብራቱ ባለመኖሩ የተነሳ ማህበረሰቡ ለተለያዩ ችግሮች እንዲጋለጥ ሆኗል። ይህንን የተመለከተችው አዲስዓለምም መፍትሄ ለመስጠት እጆቿን ወደ አጋሮቿ ዘረጋች፤ ተሳካላትም። የመብራት ግብአቱን ከማህበረሰቡ በተሰበሰበ ገንዘብ የተገዛ ሲሆን፤ ቋሚ የመብራት ስርጭቱን ደግሞ ከዩኒቨርሲቲው እንዲጠቀሙ አድርጋለች። በዚህም ዩኒቨርሲቲውን እንደቤተሰቡ የሚያየው ማህበረሰብን ፈጥራለች።
ይህና መሰል ሥራዋ ማህበረሰቡ ልብ ውስጥ የገባላት ዶክተር አዲስዓለም፤ በዘንድሮው ምርጫ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባልና የመንግስት በጀትና ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ በጸሐፊነት እንድታገለግል አስችሏታል። ድምጽዋን ተጠቅማም አሁን ላይ ሀገሯን እያገለገለች ትገኛለች። በዚህም በርካታ ተግባራትን በቻለችው ልክ እየከወነች ትገኛለች።
‹‹ሴትነት ከማህበረሰቡ የተበረከተልኝ ስጦታ ነው›› የምትለው ዶክተር አዲስዓለም፣ ከልጅነቷ ጀምሮ አብዛኛውን ወጪ የምትሸፍን፣ የቤቱን ሸክም የምትሸከምና በኃላፊነት ሰርታ ቤቱን ቀጥ አድርጋ የምትኖረው ሴት ልጅ እንደሆነች አይታ ያደገች ነች። በዚህም ዛሬን አስባ ስትሰራ ትናንትን እያስታወሰች ለነገ የሚሆነውን እያለመች ነው። ይህ ደግሞ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ተመራጭ ካደረጋት ባህሪ መካከል አንዱ ነው።
መሪነት ለሴት ልጅ ችሮታ አይደለም
‹‹እንደሴት አይደለም፤ ታችኛው ክፍል ላይ መሪ ሆነሽ ላይኛውም ላይ ብትሆኚ ወደታች የሚስቡሽ ሰዎች አይጠፉም። ወድቀሽ እንድትታይ ብዙ የሚቆፍሩ አሉ። በተደጋጋሚ ገጥመውኛልም። ነገር ግን መሪ ስትሆኚ ለእነዚህ ነገሮች እጅ መስጠት የለብሽም። ኃላፊነት እስከተሸከምሽ ተረድተሸ ክፍ ብለሽ መታየት አለብሽ። ይህ የሚመጣው ደግሞ ከወንዶች ሦስት እጥፍ ስትሰሪ ነው። መሪነት ለሴት መቼም ቢሆን ሥራ እንጂ ችሮታ አይደለም። ከሰራሽ ሊጥልሽ የሚፈልገው ጭምር ያከብርሻል፤ እናም ሴት ልጅ ውድቀቷን የምትቀንሰው ሰርታ በማሳየት ብቻ እንደሆነ ማመን ያስፈልጋል›› የምትለው ዶክተር አዲስዓለም፣ ‹‹ለሴቶች ጥንካሬ ምንጩ ተፈጥሯቸው ነው። ባህል ሲጎትታቸው በተፈጥሮ ሰርተው ያሸንፋሉ የሚል አቋም አለኝ›› ትላለች።
‹‹የሴቶች ፈተና የሚመጣው ከቤተሰብ ጭምር ነው። ለምሳሌ ልጆች ይበልጥ እናታቸውን ይፈልጋሉ፤ ቤቱ በራሱ ያለእናት ሙሉ አይሆንም፤ ትዳርም እንዲሁ። ከዚያም ባሻገር ማህበራዊ ሕይወት ጭምር የሚሞላው በሴት ነው። ስለዚህም ሸክምሽ የሚሆነው ሦስት እጥፍ ነው። እናም የምንተኛበትን ሰዓት ፣ ከማህበራዊ ተሳትፎ በመጠኑና ከቤተሰብ ጭምር በትንሹ ጊዜን ማዋጣት ግድ ይላል።›› የምትለው ዶክተር አዲስዓለም፣ ማህበረሰቡ ውስጥ ያለውንም ምልከታ መቀነስ ያስፈልጋል ስትልም ትገልጻለች። በተለይም በሴት መመራት የሚያመውን ሰው እንኳን መሪ ሆነች ማሰኘትን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ምርጫው መስራትና መስራት ብቻ ነውም ስትል ትመክራለች።
የሕይወት ፍልስፍና
‹‹እኛ ሳንሆን ፈጣሪ የእኛን መንገድ ይመርጣል›› የአባቷ የዘወትር ንግግር ነው። የእርሷም መርህ ነው። ማንም ሰው የሚያስጨንቀውን ነገር ተሸክሞ መዞር የለበትም። ምክንያቱም ጭንቀት አሲድ ነው። አሲድ ደግሞ ያጠፋል። ስለሆነም በዚያ እየተቃጠሉ ከመጥፋት ለችግሩ መፍትሄ መሆን ይገባል የሚል አቋምም አላት። ቅንነትን አስቀድመንና በመልካም ነገሮችን ተርጉመን አሲዱን ማምከን ከሁላችንም ይጠበቃል -ሌላኛው መርህዋ ነው።
ሽልማት
ተማሪዎቿ ምርጥ የሒሳብ መምህርት በሚል የሸለሟት አንደኛው ነው። በአመራር ብቃቷ አንቱታን ያተረፈች ነች። ተምሳሌት ነች በሚልም በርካታ ሽልማቶችን ከተለያዩ አካላትና ተቋማት አግኝታለች። ለአብነት ኢንተርናሽናል ሳይንስ ፕሮግራም ( ISP) በኢትዮጵያ በሒሳብ የሴቶች አመራርን ለማጠናከር ላበረከተችው አስተዋፅዖ እኤአ የ2022 ምርጥ አርአያ ሴት መሪ በማለት እውቅና ሰጥቷታል። በቅርብ በጀርመን ሀገር ለአፍሪካ ጀማሪ መሪዎች የሚሰጠውን ስልጠና ለመከታተል ከ30 የአፍሪካ ሀገራት ከተውጣጡ መሪዎች መካከል የስልጠና እድል አግኝታለች።፡
መልዕክት
እኛ ሴቶች ‹‹እባክሽን እዚህ ላይ ተቀመጭ›› እስክንባል መጠበቅ የለብንም። ልክ እንደወንዶች ሁሉ ተሻምተን የሚገባንን ቦታ ማግኘት አለብን። ከዚያ ባሻገር ሴቶቹ ለሴቶቹ ያለንን ክብር መጨመር ይገባናል። አንዳንችን ከአንዳችን የተሻልን ከሆንን ተደጋግፎ መውጣትን ማጎልበት ይጠበቅብናል።
ሴቶችን በአቅም ማሳደግ ላይ ከመንግስት አካል አለያም ከሌሎች ድርጅቶች እድል እስኪሰጥ መጠበቅ አይገባንም። የየራሳችንን ድርሻ መወጣት ላይ ማተኮር ይገባል። አንሺውም አድራጊውም እኛ መሆን ይጠበቅብናል። በሴቶች ላይ የሚመጡ ፈተናዎች መቼም አይቆሙም። መግታት ግን ይቻላል። ለዚህ ደግሞ በአንድነት መቆም ያስፈልጋል። ሴቶችን ማበርታትና ወደ መሪነት ማምጣት ይገባል። ይህ ሲባል ግን ለግብዓት ፍጆታ፣ አበቃን ለማለት፣ ኮታ ለመሙላት መሆን የለበትም። እንደሚችሉ አምነን ወንበሩን በማቆናጠጥ ነው። ምክንያቱም ይችላሉ። የተሻሉ ሆነውም በብዙ ቦታዎች እየታዩ ናቸው። ስለዚህም ጠንካሮችን ፈልጎ ቦታውን መስጠት ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው።
ለሴቶች ብዙ እድሎች አሉ። ነገር ግን መሞከር ላይ በጣም ችግር አለብን። በዚህም መልካም እድሎችን እንዳንጠቀምባቸው ሆነናል። እኔ በቤት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአካባቢዬ ላይ ሳይቀር ለሴቶች አርአያ መሆን የቻልኩት ውጤታማነቴን አስጠብቄ በመሄዴ ነው። በተለይም 12ኛ ክፍል ላይ ከፍተኛ ውጤት አምጥቼ ማለፌና ዩኒቨርሲቲ መግባቴ የብዙዎችን ቤተሰቦች በትምህርት ላይ ያላቸውን አስተሳሰብ እንድቀይር አድርጎኛል። አሁንም ለሴቶች እድል እየሆንኩ ነው። እናም ለሌሎች እህቶቼ የማስተላልፈው መልዕክት እነርሱም ለሌሎች እድል ሰጪ ይሁኑ የሚል ነው። ምክሯ ገንዘባችሁ ይሁን በማለት ለዛሬ የያዝነውን አበቃን። ሰላም!!
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን
“እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ!”
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም