ከዓለማችን ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች አንዱ በሆነው የቶኪዮ 2023 ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል። በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ የተሰጠው የቶኪዮ ማራቶን ከትናንት በስቲያ ሲካሄድ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶች ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘው በማጠናቀቅ በፍፁም የበላይነት በድል አንፀባርቀዋል። በሴቶች መካከል በተካሄደው ውድድርም ቀዳሚውን ደረጃ ቢነጠቁም ከሁለት እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል።
የአንድ አገር አትሌቶች ለአሸናፊነት ድንቅ ፉክክር ባደረጉበት ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በቶኪዮ ማራቶን የተወዳደረው ኢትዮጵያዊው አትሌት ጫሉ ዲሶ ከአገሩ ልጆች የገጠመውን እልህ አስጨራሽ ፉክክር በድንቅ አጨራረስ ብቃት በድል መወጣት ችሏል። በዚህም 2:05:22 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ሆኖ በማጠናቀቅ የድሉ ባለቤት ሆኗል። ይህ አትሌት ባለፈው ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ ለመወዳደር በተጠባባቂነት ተመርጦ ወደ ሩቅ ምስራቋ አገር ቢያቀናም መወዳደር አልቻለም። አሁን ግን በግሉ ቶኪዮ ላይ የቻምፒዮኖቹን ዓለም የተቀላቀለበትን ውጤት ከማስመዝገቡ ባሻገር በቀጣይ ሃንጋሪ ቡዳፔስት በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አገሩን ወክሎ በቋሚነት የሚወዳደርበትን እድል ማስፋት ችሏል።
እስከ ውድድሩ የመጨረሻ ጥቂት ሜትሮች አስደናቂ የአልሸነፍ ባይነት ትግል ያደረገው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ኢሳ መሐመድ በአገሩ ልጅ ድንቅ አጨራረስ ተበልጦ በተመሳሳይ 2:05:22 ሰዓት በሽርፍራፊ ማይክሮ ሰከንዶች ልዩነት ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል።
በዚህ ውድድር አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ካጠናቀቁት አትሌቶች በተጨማሪ ሶስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ፀጋዬ ከበደም ለአሸናፊነት የተደረገው ድንቅ ፉክክር አካል ሆኖ እስከመጨረሻ ዘልቋል። ይሁን እንጂ በሁለቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሶስት ማይክሮ ሰከንዶች ተቀድሞ 2:05:25 በሆነ ሰዓት የነሐስ ሜዳሊያውን ደረጃ በመያዝ የዘንድሮውን የቶኪዮ ማራቶን በማይረሳ አስደናቂ ፉክክር እንዲታጀብ አድርጓል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የቀዳሚነቱን ደረጃ ለኬንያዊቷ አትሌት ሮዝመሪ ዋንጂሩ አሳልፈው በሰጡበት ውድድር አንዲት አትሌት የተለየ ትኩረት ተሰጥቷት ነበር። ይህች አትሌት አርባ ሁለት ኪሎ ሜትርን ለሃያ አምስተኛ ጊዜ በዘንድሮው ቶኪዮ ማራቶን የተወዳደረችው ኢትዮጵያዊቷ አሸቴ በከሪ ናት።
ላለፉት 12 ዓመታት በመላው ዓለም በተካሄዱ ዕውቅ የማራቶን ውድድሮች ላይ በመሳተፍ እጅግ ከፍተኛ ልምድ ያካበተችው
ይህች ድንቅ አትሌት ቫሌንሺያ፣ ሮተርዳም፣ በርሊን፣ ለንደንና ሌሎች ታላላቅ ማራቶኖች ላይ በመሮጥ ስኬታማ ነች። እአአ 2021 ላይ በለንደን ማራቶን ሶስተኛ ሆና ስታጠናቅቅ የገባችበት 2:18:18 ሰዓት ዘንድሮ ቶኪዮ ላይ ሃያ አምስተኛ ውድድሯን ለማሸነፍ ያበቃታል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ይሁን እንጂ ባለፈው ዓመት በዚሁ ቶኪዮ ማራቶን ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው የሰላሳ አራት አመቷ አትሌት ዘንድሮ ቀዳሚ ሆና ሳታጠናቅቅ ቀርታለች። የ2019 የበርሊን ማራቶን አሸናፊዋ አትሌት አሸቴ ቀዳሚ ሆና ባታጠናቅቅም 2:19:11 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ሆና በመፈፀም ከስኬታማነት አልራቀችም።
ውድድሩን በድንቅ ብቃት ማሸነፍ የቻለችው ባለፈው ዓመት በበርሊን ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ኬንያዊቷ አትሌት ሮዝሜሪ ዋንጂሩ 2:16:28 ሰዓት በማስመዝገብ ነው ባለ ድል የሆነችው። ኬንያዊቷን አትሌት ተከትላ በጥቂት ሰከንዶች ልዩነት ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፀሐይ ገመቹ 2:16:56 ሰዓት አስመዝግባለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማራቶን ተፎካካሪ መሆን የቻለችው ይህች አትሌት በአምስተርዳም ማራቶን 2:18:59 ሰዓት ማስመዝገቧ ይታወሳል። ዘንድሮ ቶኪዮ ላይ ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ይህን ሰዓቷን ከሁለት ደቂቃ ባላነሰ ሰዓት ማሻሻሏም ወደ ፊት በርቀቱ ትልቅ ተስፋ እንዲጣልባት አድርጓል።
ባለፈው ዓመት በርሊን ማራቶን ላይ ተሳትፋ አራተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ወርቅነሽ ኢዴሳ 2:20:1 በሆነ ሰዓት በዘንድሮው ቶኪዮ ማራቶንም አራተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም