ወርሃ የካቲት በአትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ሥፍራ አለው፡፡ የአትዮጵያውን የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ በደም እና በአጥንት አሻራ የተፃፈበት ነው፤ ከእነዚህ አበይት የታሪክ ክስተቶች አንዱ የዓድዋ ድል ነው፡፡ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡ የመላው ዓለም ተፈጥሯዊ ግብር እና ሰብአዊ ክብር የታደሰው፤ በእውነት በፍትህ እና በህልውና ላይ የተቃጣው ጥቃት ድባቅ የተመታው በዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ታላቅ ድል ነው፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በግሩም ስነስርዓት የተደራጀ ግዙፍ የኢትዮጵያ ሠራዊት የማይታሰበውን ፈጽሟል። ወራሪው የጣሊያን ኃይል ላይ ድባቅ በመምታት ድልን ተቀዳጅቷል። ስግብግብነት በተጠናወተው የአውሮፓውያን መስፋፋት፤ ኢትዮጵያ ነጻነቷን በተሳካ መልኩ አስጠብቃለች ሲሉ ያነሳሉ፤ ዝነኛው የታሪክ ፕሮፌሰር ራይሞንድ ዮናስ፦ «የዓድዋ ጦርነት፤ በዘመነ ቅርምት የአፍሪቃ ድል» በተሰኘው መጽሐፋቸው።
ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት፤ በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮፓ ወራሪ ጦር የካቲት 23 ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት ግድም ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ማሸነፉን አረጋግጧል ይለናል የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ በርክሌይ፡፡ የዓድዋ ጦርነትና ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ በተሰኘና ዳኘው ኃይለሥላሴ ወደ አማርኛ በተረጐሙት መጽሐፍ ላይ፤ የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ፈረሱ ላይ ሆኖ የጋሻውን እምብርት መሬት ላይ እያጠቀሰ ጐራዴውን አየር ውስጥ እየቀዘፈ በተቆጣና በቆረጠ መንፈሥ በጀግንነት ተዋግቷል፡፡
ጦርነቱ በተጀመረ ከአምስት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሃምሣ ስድስቱም የኢጣሊያ መድፎች ሙሉ ለሙሉ ተማርከዋል፡፡ የቅኝ ገዢውን ወራሪ ሠራዊት ከመሩት ጀኔራሎች ጄኔራል አልቤርቶኒ ሲማረክ የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ከጥቂት አጃቢዎቹና በሽንፈት ከተበታተኑ የጣሊያን ወታደሮች ጋር ሸሽቷል፡፡
በዚህ ድብልቅልቅ ያለ ውጊያ ከሃምሣ ስድስቱ የጣሊያን መድፎች በተጨማሪ ብዙ ሺህ ቀላልና ከባድ መትረየሶች እንዲሁም የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎች በአሥር ሺዎችና በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ መሰል ጥይቶቻቸው ጋር ተማርከዋል፡፡ በአጠቃላይ ምርኮው ወደ አዲስ አበባ የተጓጓዘው በአምስት መቶ አጋስሶች ተጭኖ ነው፡፡
ታላቁ የጥቁር ህዝቦች ድል የዓድዋ ድል በመላው ዓለም ፖለቲካ ላይ ከፍተኛና ዋነኛ ለውጦች አምጥቷል፡፡ የእንግሊዝ ጋዜጦች በዓድዋ ድል ማግስት የዓለም ታሪክ ተገለበጠ ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪካ ተቀሰቀሰ … ብለው ፃፉ፡፡ ዘመናዊት ኢትዮጵያን የፈጠሩ የተባሉት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በሌሉበት እና በአካል ባልተገኙበት የነፃነት ተጋድሎ መሪዎች ጉባኤ የአፍሪካ ብሎም የመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መሪ ተደርገው ተመረጡ፡፡
ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ወቅት በዋናው የጦር ግንባር ገጥማ በፍልሚያ ድል ማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ በአጠቃላይ በአራት መስክ ሠለጠነች በምትባለው አውሮፓዊት ሀገር ጣሊያን ላይ ድል ተቀዳጅታለች፡፡ ይኸውም፡- በጦርነት እና በወታደራዊ መረጃ (Military Security intellegence) ፤ በዲፕሎማሲና በፖለቲካ ጥበብ ነው፡፡
ለጦርነቱ መጀመር መነሻ የሆነው የውጫሌ ውል ነው፡፡ የውጫሌ ውል አንቀጽ አሥራ ሰባት የጣሊያንኛው፡- ኢትዮጵያ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን ግንኙነት በጣሊያን መንግስት በኩል ማድረግ አለባት ሲል፤ አማርኛው ደግሞ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን ግንኙነት በጣሊያን መንግሥት በኩል ማድረግ ትችላለች ይላል፡፡
የአማርኛው የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና ልዕልና ያከብራል፤ የጣሊያንኛው የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና ልዕልና መድፈር ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ክብሯንና ጥቅሟን ይነካል፡፡ ይሄን የተገነዘቡት የኢትዮጵያ መሪዎች የውሉ አንቀጽ አሥራ ሰባት የጣሊያንኛ ትርጓሜ የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም በማይነካና ሉአላዊነቷን በሚያከብር መልኩ እንዲስተካከል በተደጋጋሚ ወተወቱ፡፡ መወትወቱ ውጤት ሳያመጣ ሲቀር፤ ጣይቱ ለምኒልክ ‹‹መዘግየት አደገኛ ነው›› አሉ፤ ስለዚህ ጉዞ ወደ ወሳኙ ጦርነት ማድረግ የግድ ሆነ፡፡
የኢትዮጵያን ሀገራዊ ክብርና ጥቅም ህልውናና ልዕልና ቢሆን በውድ፤ ካልሆነ ደግሞ ሳይወድ በግድ ማስከበርና ማስጠበቅ የመንግሥት ዋነኛ ግዴታና ኃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውን ጦር እንግተም በወታደራዊ መረጃ (Military Security intellegence) ብልጫ፤ ሠለጠነ የተባለውን የአውሮፓ ኃይል አሸንፈው ጣሊያኖች ባልፈለጉት ቦታና ባልመረጡት ጊዜ ወደ ጦርነት እንዲገቡ አደረጉ፡፡
በወታደራዊ ሣይንስ (Military Science) አገባብ ለጦርነት የተንቀሳቀሰ አንድ ሠራዊት ወዲያውኑ ወደ ጦር ግንባር መግባት አለበት፤ ይሄ አንድ ነጥብ ነው፡፡ ሌላው ነጥብ አንድ ለግዳጅ የተንቀሳቀሰ ሠራዊት ለመሰናዶም ሆነ ለመከላከል ውጊያ በአንድ የመከላከያ ወረዳ ከሠፈረ በዚያ መከላከያ ወረዳ ከስድስት ወራት በላይ መቆየት የለበትም፡፡
በአንድ ቦታ ላይ ከስድስት ወራት በላይ ከቆየ ሊደርስ የሚችል የወታደራዊ ሥነልቦና ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ የመሸገበትን የመከላከያ ወረዳ እየተለመማመደ ሲሄድ ስለሚዘናጋና የውጊያ ስሜቱ እየቀነሰ ወይም እየቀዘቀዘ ስለሚመጣ አሸናፊ ሆኖ ጦርነትን ማጠናቀቅ ከባድ ነው። ከሎጂስቲክ አኳያ የውጊያ ዝግጁነቱም አደጋ ላይ ስለሚወድቅ በሌላ አነጋገር ስንቅ እየጨረሰ ስለሚሄድ በእነዚህ ምክንያቶች በአፋጣኝ ወደ ጦርነት መግባት ለሠራዊቱ ድል አድራጊነት ትልቅ ጥቅም ነበረው።
በዛን ጊዜ ኢትዮጵያ ሠላም ሲሆን፤ ገበሬ በጦርነት ጊዜ ጀግና ተዋጊ እንጂ ዘመናዊ ወታደራዊ መሠረት Professional Army አልነበራትም። በዚያ ዘመን ለአንድ መቶ ሃያ ሺህ ሠራዊት የሎጂስቲክ አገልግሎት እየሰጡ ለረጅም ጊዜ መቆየት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ስለዚህ የጀግንነት ግለት ሳይበርድ የሎጂስቲክ (ስንቅ ትጥቅ መድሃኒት) አቅም ሳይዳከም በፍጥነት ጦር መግጠም እጅግ አስፈላጊ ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት ጦርነቱን ፈጥኖ ለመግጠም ጣሊያኖች ወደ ዓድዋ መምጣት አለባቸው፤ ወይም ደግሞ የእኛ ሠራዊት ጣሊያኖች ወደመሸጉበት የኤርትራ ከፍተኛ ቦታዎች መሄድ አለበት፡፡ ከነዚህ ሁለት ሁኔታዎች የአንደኛው መሆን የግድ ነበር። ወደ ጣሊያኖች መሄድ ከፖለቲካ ሁኔታዎች ባሻገር ከወታደራዊ ሳይንስ አንፃር የሚመረጥ አይደለም።
በወታደራዊ ሣይንስ ደግሞ ወታደራዊ መረጃ ለወታደራዊ ግጃጅ አፈፃፀም ዋነኛና ወሣኝ ጠቀሜታ አለው፡፡ በዓለም ላይ ከተደረጉ አብዛኞቹ ጦርነቶችም ድል አድራጊዎች ድላቸውን የሚቀናጁት የወታደራዊ መረጃ ብልጫ የነበራቸውና ፍትህና እውነትን ፖለቲካዊ መሠረት ያደረጉት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ሁለቱም ነበራት፤ ኢትዮጵያዊያን ዓላማቸው የሀገራቸውን ጥቅምና ክብር እንዲሁም ህልውና እና ልዕልና ማስከበር፤ ነፃነታቻውን ማስጠበቅ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የፍትህና የእውነት ጥያቄ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ከውጪ ወራሪዎች ጋር ባደረገቻቸው ጦርነቶች ሁሉ፤ እውነትና ፍትህን መሠረት አድርጋለች። ስለዚህ ድልን ተቀናጅታለች። በዓለም አደባባይ ደምቃ ታይታለች፡፡ ይህንን ታሪክ ተክለፃዲቅ መኩሪያን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን የታሪክ ተመራማሪዎችና የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ፀሃፊያንና ተመራማሪዎች በተለያዩ መጻሕፍቶቻቸው ይሄንን እውነት ጽፈውታል፡፡
ድሉን ተከትሎ የድሉን ትርጉም ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው በሰባተኛ ዓመቱ በ1895 ዓ.ም (እ.ኤ.አ በ1903) አዲስ አበባ አሁን ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ያለበት ሥፍራ ምኒልክ አደባባይ ላይ ነው። ዲፕሎማቶችና የውጭ ሀገር መንግሥታት ተወካዮች አርበኞች የመንግስት ባለሥልጣናት በድል በዓሉ ላይ እየተገኙ ሲከበር መቆየቱን ጳውሎስ ኞኞ የኢጣሊያና የኢትዮጵያ ጦርነት በተሰኘ መጽሐፉ ላይ ጽፎአል፡፡ እንዲሁም ከዛ ጊዜ ጀምሮ የድል በዓሉ በተለያዩ ኩነቶች እየተዘከረ ዛሬ ላይ ተደርሷል፡፡ ዘንድሮም 127ኛው የድል በዓሉ በድምቀት ይዘከራል፡፡
አከባበሩም ኢትዮጵያውያን ነጻ የወጣንበት ብለው ሳይሆን በኩራት የድል ቀናችን እያሉ በልዩ ሁኔታ የሚያከብሩት ታላቅ ቀን ነው። የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ከጥግ እስከ ጥግ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ተምመው በአንድ ጥላ ስር እንዲሰባሰቡ ያደረገ ታሪካዊ ክስተት በመሆኑ የኢትዮጵያውያንን ትብብር እና አንድነት ከማሳየቱም በላይ ለመላው የጥቁር ህዝብ የነፃነት ምልክት መሆናችንን ማሳያ ነው፡፡ ታድያ ዛሬ ላይ የአሁን ትውልድ የጋራ ታሪክ ያለን ህዝቦች መሆነችንን አውቆ፤ቀደምት አባቶቻችን በጊዜው በተለያየ ምክንያት የነበሩ ልዩነቶችን እና አለመግባባቶችን ወደ ጎን በመተው ባሪያ አድርጎ በቅኝ ግዛት ለመግዛት የመጠን ወራሪ ሀይል እንዴት በአንድነት ድል ማድረግ እንደቻሉ በእውን ሊገነዘበው ይገባል፡፡
በእርግጥ ኢትዮጵያውያን የተለያየ ባህል እና ቋንቋ ያለን ህዝቦች ነን፡፡ ብዝሃነትን ውበት አድርገን በመቀበል አንድ አድርጋ በምታቅፈን ኢትዮጵያ ጥላ ስር ተሰበስበን እንደ ቀደምት አባቶች ይህ ትውልድም ዓድዋን ማክበር ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ ልትረታው የሚገባውን መጥፎ ሰንኮፍ ድህነት እና ኋላቀርነትን መንግሎ መጣል አለበት፡፡
ዛሬም ድረስ በኩራት የሚነሳው ያለፈው የአባቶች የትኛውም ታሪክ የአሁን ዘመን ትውልድ አስተዋፅኦ የለበትም፡፡ የአሁኑ ትውልድ ራሱ የሚነሳበትን የሚያኮራ ታሪክ መፃፍ አለበት፡፡ ይህ ትውልድ የእነዛን ዘመን የኢትዮጵያ አባቶችን ውለታ የሚከፍለው፤ የኢትዮጵያን አንድነት በማስጠበቅ እና ኢትዮጵያን በማበልፀግ መሆን አለበት ባይ ነኝ። ሰላም!
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም