በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለሶስት አመታት ተቋርጠው የነበሩት የሰራተኛው ስፖርት ውድድሮች ባለፈው ጥር 07/2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በተካሄደው የበጋ ወራት ውድድሮች የመክፈቻ መርሃግብር መቀጠላቸው ይታወሳል። ከስድስት ወራት ላላነሰ ጊዜ በአስር የስፖርት አይነቶች በርካታ ፉክክሮችን የሚያስተናግዱት የሰራተኛው የበጋ ወራት የስፖርት ውድድሮች ባለፉት ሳምንታትም ቀጥለው በጥሩ መነቃቃት እየተካሄዱ ይገኛሉ።
ከፍተኛ ፉክክር በሚያስተናግደው የወንዶች እግር ኳስ ውድድር ባለፈው ሳምንት ስድስት ጨዋታዎች በተለያዩ ሜዳዎች የተካሄዱ ሲሆን፤ ሁሉም ጨዋታዎች በመሸናነፍ ተጠናቀዋል። ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ንፋስ ስልክ ፔፕሲ ኮላ ፋብሪካን 4ለ0 የረታበት ጨዋታ የመጀመሪያው ነው። ኢትዮ ቴሌኮም ረጲ ሳሙና ፋብሪካን 2ለ1 በሆነ ውጤት የረታበት ጨዋታ ጥሩ ፉክክር ከታየባቸው መርሃግብሮች አንዱ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ቃሊቲ ብረታብረት ፋብሪካን በተመሳሳይ 2ለ1 ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግ ካምፓኒ ፍል ውሃ አገልግሎት ድርጅትን 5ለ2 ያሸነፈበት ጨዋታም በሳምንቱ መርሃግብር በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት ሆኗል። ኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስን 2ለ0 ሲረታ፣ ሆራይዘን አዲስ ጎማ ሞኤንኮ ኩባንያን 1ለ0 ያሸነፈበት ጨዋታ በጠባብ ውጤት የተጠናቀቀ መርሃግብር ነው።
በሰራተኛው ስፖርት ሌላው ጠንካራ ፉክክር የሚደረግበት የቮሊቦል ውድድር በወንዶች ሁለት ጨዋታዎችን ያስተናገደ ሲሆን፣ ሙገር ሲሚንቶ ኢትዮ ቴሌኮምን 3ለ0፣ መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢትዮጵያ ግብርና ስራዎችን 3ለ1 በሆነ ውጤት መርታት እንደቻሉ ከውድድሩ አዘጋጅ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን(ኢሰማኮ) ስፖርት ክፍል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በወንዶች ጠረጴዛ ቴኒስ በተካሄዱ ሶስት ጨዋታዎች ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካን 3ለ0 ሲረታ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አንበሳ የከተማ አውቶቡስን 3ለ1እንዲሁም ፋፋ የምግብ ፋብሪካ ሞኤንኮን 3ለ0 ማሸነፍ ችለዋል። በተመሳሳይ በሴቶች ጠረጴዛ ቴኒስ በተካሄደ ብቸኛ ውድድርም በወንዶች ሽንፈት የገጠመው አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት በሴቶች ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግን 3ለ0 መርታት ችሏል። በዳርትና ቼስ ውድድሮች በሳምንቱ የተካሄዱ በርካታ ፉክክሮችም በመሸናነፍ መጠናቀቃቸው ታውቋል።
የሰራተኛው የበጋ ወራት ውድድሮች ዛሬና ነገ ቀጥለው ሲውሉም በተለያዩ ሜዳዎች የሚካሄዱ ፉክክሮች ይጠበቃሉ። በተለይም በአንደኛና ሁለተኛ ዲቪዚዮን በሚካሄዱ ውድድሮች ጠንካራ ፉክክር ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በርካታ ጨዋታዎችም በተለያዩ ሜዳዎች እንደሚከናወኑ ታውቋል። ከነዚህ መካከል ነገ በጎፋ ካምፕ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ከዮሐንስ ቢፍ ኢንጂነሪንግ በአንደኛ ዲቪዚዮን የሚያደርጉት ፉክክር ተጠባቂ ነው። በተመሳሳይ ዲቪዚዮንና ሜዳ ነገ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ከ ኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ይገናኛሉ። በዚሁ ዲቪዚዮን ነገ ኢትዮ ቴሌኮም ከኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች በስብስቴ ነጋሲ ትምህርት ቤት ሜዳ የሚያደርጉት ጨዋታም ይጠበቃል። በዚሁ ሜዳ ላይ ነገ በሁለተኛ ዲቪዚዮን እግር ኳስ ውድድር መከላከያ ኮንስትራክሽን ከይርጋለም አዲስ ጨርቃጨርቅ የሚያካሂዱት ጨዋታም የዚህ ሳምንት መርሃግብር ይሆናል። በዚሁ ዲቪዚዮን በዳግማዊ ምኒልክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነገ ሁለት ጨዋታዎች ሲካሄዱ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ሆራይዘን አዲስ ጎማን፣ፍል ውሃ አገልግሎት ድርጅት ኢትዮጵያ ልማት ባንክን ይገጥማሉ።
ዛሬ በሴቶች ቮሊቦል አንደኛ ዲቪዚዮን የሚካሄደው አንድ ጨዋታ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎትን ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ያገናኛል። በተመሳሳይ ውድድር የወንዶች ሁለተኛ ዲቪዚዮን ደግሞ ሆራይዘን አዲስ ጎማ ከመከላከያ ኮንስትራክሽን፣ ቃሊቲ ብረታብረት ከአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የሚጫወቱ ይሆናል። በጠረጴዛ ቴኒስ፣ዳማ፣ዳርትና ቼስ በሁለቱም ፆታ ዛሬ የሚካሄዱ የቤት ውስጥ ውድድሮችም ተጠባቂ ናቸው።
በአገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ እንቅስቃሴ ከሚደረግባቸው የስፖርት መድረኮች አንዱ በሰራተኛው መካከል የሚካሄደው ስፖርታዊ ውድድር ነው። በኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን(ኢሰማኮ) አማካኝነት በየአመቱ በሶስት የተለያዩ መድረኮች የሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች በርካታ ቁጥር ያለው ተሳታፊ የሚያስተናግዱ ናቸው። የበጋ ወራት ውድድሮች፣አገር አቀፍ የሰራተኞች ውድድርና አለም አቀፉን የሰራተኞች ቀን ሜይዴይን አስመልክቶ የሚካሄዱት ሶስት የውድድር መድረኮች በኢትዮጵያ ረጅም አመት ያስቆጠሩ መሆናቸው ይታወቃል። እነዚህ የውድድር መድረኮች የተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞቻቸውን የሚያሳትፉባቸውም ናቸው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም