ኢንዱስትሪዎች በተለይ ትላልቆቹ ከሚያስፈልጋቸው የሀይል አቅርቦት የተወሰነውን ከድንጋይ ከሰል ነው የሚያገኙት። ሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ በዋነኝነት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ዋና የግብአቱ ተጠቃሚዎች ናቸው። የኤሌክትሪክ ሀይል እጥረትና በርካታ ኢንዱስትሪዎች ባሉበት ሀገር ይህ የሀይል አማራጭ በከፍተኛ ሁኔታ ይፈለጋል።
የድንጋይ ከሰል በኢትዮጵያ በተለይ በሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች በስፋት አገልግሎት ላይ ይውላል። ለነዚህ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለኃይል ግብአት የሚውለው ምርት ከደቡብ አፍሪካና ከተለያዩ ሀገራት በግዥ ይቀርባል። ለግዢም በዓመት ከ300 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ እንደሚወጣ በተለያየ ጊዜ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ኢትዮጵያ በምድር ውስጥ ካሏት የወርቅና የጌጣጌጥ ማዕድናት፣ የተፈጥሮ ጋዝና ሌሎች የማዕድን በረከቶቿ መካከል አንዱ የድንጋይ ከሰል ነው። መጠኑ ይለያይ እንጂ የድንጋይ ከሰል ሀብቷ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደሚገኝና በተለይም ደግሞ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከፍተኛ ክምችት መኖሩን፣ በጥቅሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን ቶን በላይ የሚገመት የድንጋይ ከሰል ክምችት ስለመኖሩም መረጃዎች ያመለክታሉ።
“ይሁን እንጂ የሀገር ውስጥ ሀብት የሆነው ድንጋይ ከሰል የአመድ ይዘቱና የእርጥበት መጠኑ፣ ኃይል የማመንጨት አቅሙን አነስተኛ ያደርገዋል” የሚሉ ምክንያቶች በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘንድ ይነሳል፤ በዚህ የተነሳም የማእድኑ ተፈላጊነት ዝቅተኛ ነው ይባላል። ማእድኑ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚደረገው ከውጭ ከሚገባ የድንጋይ ከሰል ጋር በመቀላቀል መሆኑም ይገለጻል።
በዚህ ወቅት እያጋጠመ ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ግብአቱን በግዥ ከውጭ ማስገባት ከፍተኛ ፈተና እየሆነ በመምጣቱ ምክንያትና የሀገር ሀብትንም ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል በሚል እሳቤ ከውጭ በግዥ የሚገባውን በሀገር ውስጥ በማምረት ለመተካት መንግሥት ባለፉት ጊዜያቶች የተለያዩ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል። ዘርፉን የሚመራው የማዕድን ሚኒስቴር በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የድንጋይ ከሰል ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የሚል እቅድ ይዞ ሲንቀሳቀስ መቆየቱም ይታወቃል።
ምርቱን በሀገር ውስጥ ለመተካት ከሚያስፈልጉ ሥራዎች አንዱ ጥራቱን አሳድጎ ወይንም ሊኖረው የሚችለው የኃይል መጠን እንዲኖረው በማድረግ የታጠበ ድንጋይ ከሰል አምርቶ ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ማሽን ፋብሪካ መትከል ወይንም ማቋቋም ነው።
በዚህ ረገድም የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በዘርፉ እንዲሰማሩ በመንግሥት በኩል በተደረገው እንቅስቃሴ የታጠበ የድንጋይ ከሰል አምርተው ለሚያቀርቡ 8 አምራች ኢንዱስትሪዎች ፍቃድ በመስጠት የሀብት ክምችቱ በሚገኝባቸው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ከኩባንያዎቹ የሚጠበቀው የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ማሽን በመትከል ወደ ሥራ መግባት ነው። የፋበሪካዎቹ መከፈት ደግሞ ለአካባቢው ማህበረሰብ በተለይም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ይጠቅማል። ጎን ለጎንም ኩባንያዎቹ በሚሰጡት ማህበራዊ አገልግሎቶች የህብረተሰቡን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ይፈታል ተብሎ ይታሰባል። የመንግስት ውሳኔም ይህንን ፋይዳ ግምት ውስጥ ያስገባ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ለመሆኑ መንግሥት ከያዘው እቅድ አንጻር ጥረቶቹ ምን ውጤት አስገኙ? እንደተባለው በተያዘው በጀት ዓመት የድንጋይ ከሰልን በሀገር ውስጥ ለመተካት የተያዘው እቅድ ተሳክቷል? የበጀት ዓመቱ ወደ ሰባተኛ ወር እየተሸጋገረ ይገኛል። በዚህ ዙሪያ ሲሚንቶ አምራች አንዱስትሪዎች፣ ግብአቱን ከውጭ በግዥ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባው የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እና የማዕድን ሚኒስቴርን አነጋግረን ያጠናከርነው የሚከተለውን ዳሰሳ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ገዛኸኝ ደቻሣ በድንጋይ ከሰል ላይ አዲስ ነገር እንደሌለ ይገልጻሉ፤ ፋብሪካው እንደቀደመው የድንጋይ ከሰል ከውጭ እያስገባ ይጠቀማል። የሀገር ውስጡ ምርት ከውጭው ጋር እየተደባለቀ ካልሆነ በስተቀር ለብቻው ጥቅም ላይ እንደማይውልም ይናገራሉ። መንግሥት የያዘው ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት እቅድ በአጭር ጊዜ ይሳካል የሚል እምነት እንደሌላቸውም አስታውቀዋል።
ስራ አስኪያጁ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ፣ በአሮሚያ ክልል ወለጋ እና አርጆ አካባቢዎች የድንጋይ ከሰል ክምችት መኖሩን ጠቅሰው፣ እነዚህ አካባቢዎች ደግሞ የፀጥታ ስጋት ያለባቸው ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ልማት ይካሄድባቸዋል ብሎ ለመገመት ያዳግታል ሲሉ ገልፀዋል። አቅርቦቱን በተመለከተም ችግር እንዳልገጠማቸውና ግዥውንም የሚፈጽሙት በብር እንደሆነ አመልክተዋል።
እንደ ኢንጂነር ገዛኸኝ ገለፃ፤ የድንጋይ ከሰሉ የሚገዛበት ዋጋ ተለዋዋጭ በመሆኑ ስለዋጋው እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። ባለፈው ወር አንዱ ቶን የድንጋይ ከሰል በ23ሺ ብር ሂሳብ ነው የተገዛው። ግዥው የሚካሄደውም የድንጋይ ከሰሉ የኃይል መጠን የሚፈለገውን መስፈርት ያሟላ መሆኑን እየተረጋገጠ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ፋብሪካዎች ሥራ እንዳያቆሙ፣ የግንባታው ዘርፍም እንዳይስተጓጎል ማድረግ እንጂ የዋጋ ሁኔታ ጥያቄ እንዳልሆነ ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለማርያም ጥራቱን ጠብቆ የተመረተ የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ በግዥ የሚገባውን ለመተካት በመንግሥት በኩል ተይዞ የነበረው እቅድ የሚፈለገውን ውጤት አለማስገኘቱን ይናገራሉ። በዚህ ምክንያትም ከውጭ በግዥ የማስገባቱ ሂደት ቀጥሏል ነው ያሉት።
‹‹አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ግብአቱን በሀገር ውስጥ ማግኘት ቢችሉ በዋጋም ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር፤ መንግሥትም የግዥ ወጭን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ድርጅታችንም እዚህ ሥራ ውስጥ አይገባም ነበር›› ያሉት አቶ ታደሰ፤ በሀገር ውስጥ አቅም እስኪፈጠር አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ሥራ ማቆም ስለሌለባቸው፣ የግንባታ ዘርፉንም ለመደገፍ እንዲሁም በዘርፉ ውስጥ በተለያየ ሥራ በስፋት የተሰማራው ኃይል እንዳይጎዳ፣ ድርጅቱ ከውጭ በማስገባት ግብአቱን እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
እንደ አቶ ታደሰ ማብራሪያ፤ የግብአት ጥያቄው ሰፊ ነው። በሚቀርበው ጥያቄ ልክ ማቅረብ ባይቻልም በተቻለ መጠን ጥረት ይደረጋል። ቀደም ሲል አንዳንድ ወር በማለፍ ነበር ግዥው ተፈጽሞ የሚቀርበው። ፍላጎቱ ከፍተኛ በመሆኑ ይህን ለማስተካከል ጥረት ተደርጓል። በዚህ የካቲት ወር 2015ዓ.ም ሁለት መርክብ ለማምጣት ግዴታ ውስጥ ተገብቷል። ሁለት መርከብ አንድ መቶሺ ሜትሪክ ቶን ነው። የድንጋይ ከሰል ከውጭ የሚገዛበት ዋጋ ልክ እንደ ነዳጅ ዋጋ አንዴ ከፍ፤ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ የሚል በመሆኑ ትክክለኛውን ዋጋ ለማስቀመጥ ያስቸግራል። አንድ መርከብ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ይገመታል።
ድርጅቱ ፍላጎትን፣ አቅርቦትናን ወጭን በተመለከተ አቶ ታደሰ ሲያብራሩ፣ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመሥጠቱ ነው ግዥው እንደቀጠለ የሚናገሩት። ከአንድ መርከብ ወደ ሁለት በማሳደግ አንድ ወር በመዝለል ይከናወን የነበረንም ግዥ ማሻሻል የተቻለውም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ይገልፃሉ። ግዥው የሚፈፀመውም በአምራች ኢንዱስትሪዎች ጥያቄ መሰረት መሆኑን ያስረዳሉ። ከፍተኛው የግብአት ተጠቃሚም ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ መሆኑን ገልፀዋል። ሙገር፣ ናሽናል ሲሚንቶ፣ደርባና በቅርቡ ወደ ሥራ የተመለሰው መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካና ሌሎችም ደንበኞች መሆናቸውን አመልክተዋል።
የዝግጅት ክፍላችንም የድንጋይ ከሰል ምርትን በአገር ውስጥ ለመተካት የተጀመረው እቅድ ለምን እንዳልተሳካ ለማእድን ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቦ ነበር። በምላሹም በመንግስት በኩል ድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለማምረት ታቅዶ በነበረው መሰረት ብዙ ርቀት ቢጓዝም ስኬት ላይ እንዳልደረሰ የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስን ይገልጻሉ። ልማቱ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር፣ የአምራች ኩባንያዎች የብድር ጥያቄ ምላሽ አለማግኘት፣ አንዳንድ ኩባንያዎች ወደ ሥራ አለመግባታቸው፣ኩባንያዎች ለድንጋይ ከሰል ማጠቢያ የሚውለውን ማሽን ለመትከል የሚወስድባቸው ጊዜ ለእቅዱ አለመተግበር ከሚጠቀሱ ምክንያች መካከል መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል። በነዚህ ምክንያቶች የተነሳ የታጠበ የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለማምረት የተደረገው ጥረት የተፈለገውን ያህል እንዳልተሳካ ነው የገለጹት። እነዚህ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙም የድንጋይ ከሰል ልማት ተስፋ የተሟጠጠ እንዳልሆን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ ዝቅተኛ የሆነውን የሀገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል የማቃጠል አቅም በመጨመር አልምተው ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ ከመንግሥት ጋር ውል ገብተው የሥራ ፈቃድ ወስደው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የልማት ቦታ ከወሰዱት 8 ኩባንያዎች መካከል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተሰማራው “ዮ ሆልዲንግ” የተባለ ኩባንያ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ማሽን ተከላውን አጠናቅቆ በተያዘው በጀት ግማሽ አመት ወደ 36ሺቶን የድንጋይ ከሰል ማልማት ችሏል።
ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዳውሮ አካባቢ የተሰማራው ኩባንያም የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ማሽን በማጓጓዝ ሂደት ላይ እንደሆነ ጠቅሰው፣ እስከ ሰኔ ወር2015 ዓ.ም ተከላውን አጠናቅቆ የሙከራ ምርት እንደሚያመርት ይጠበቃል ብለዋል።
በአጠቃላይ ጥሬ ድንጋይ ከሰል ለማምረት /ዜሮ ነጥብ አራት ሁለት ሚሊየን (0.42ሚሊዮን) ቶን/ ከተያዘው እቅድ ወደ አምስት በመቶው ተመርቶ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ማቅረብ መቻሉን አስረድተዋል። በፀጥታ ስጋትና በተለያየ ምክንያት ወደ ልማት ያልገቡትንም በመለየት የሚስተካከለውን በማስተካከል፣በተለይም ከክልሎች ጋር በቅርበት በመሥራት ልማቱን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ቀድሞ ሥራ ውስጥ በመግባት በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኘውን “ዮ ሆልዲንግ” ኩባንያን በማጠናከርና ለሌሎችም አርአያ እንዲሆን በማድረግ በመንግሥት በኩል ያላሰለሰ ጥረት ይደረጋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ እንዲህ በጥሩ ሁኔታ ላይ ለሚገኙት ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሪ ጥያቄያቸውን መመለስ ከተቻለ ውጤታማ መሆን ይቻላል ብለዋል።
አንዳንዶቹ ከመንግሥት አቅም በላይ የሆኑ ምክንያቶች ቢሆኑም ፣ ከፀጥታ ስጋት ውጭ በሆኑ አካባቢዎች የተሰማሩ ኩባንያዎች ለአብነትም በጉራጌ አካባቢ ቦታ ወስደው ወደ ልማት ያልገቡትን ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፤ የሥራ ፈቃድ ከወሰዱ 8 ኩባንያዎች መካከል ጉራጌ ዞን ላይ የተሰማራው ኩባንያ ምክንያታዊ ባለመሆኑ መንግሥት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶታል። በቀጣይም ለውጥ ከሌለ ፈቃድ እስከመሰረዝ እርምጃ ይወሰዳል።
በማዕድን ልማት በግልጽ በህግ ላይ ከተቀመጠ ተጠቃሚነት ውጭ በአንዳንድ አካባቢዎች ስለሚነሱ የጥቅም ጉዳዮችም ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስረዱት፤ ህግ ማውጣት የሚገባው አካል ካወጣው ህግ ውጭ በአካባቢ ላይ የሚወጣ ህግ የለም። አልሚዎች በአካባቢ ልማት ላይ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ በህግ ላይ የተቀመጠ በመሆኑ ያንን ተፈፃሚ ያደርጋሉ።
ለልማቱ እንቅፋት የሆኑ ከህግ ውጭ የሆኑ ጥያቄዎችም ከክልል አስተዳደሮች ጋር በጋራ ውይይትና ግንዛቤ በመፍጠር የሚፈታ እንደሆነም ነው የተናገሩት። መነሻው ወጣቱ ከሀብቱ ይጠቀም የሚል ቢሆንም፣ ይህም በህግ የሚመለስ መሆኑንና አካባቢው ሲለማ ተጠቃሚነትም አብሮ እንደሚመጣ መገንዘብ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እንደሚኖሩ በቅድመ እቅድ ላይ አመላካች ነገር እንደሚኖር ይገመታል ሲሉም ይገልጻሉ። ይሄ ግምት ውስጥ አልገባም ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ሚኒስትር ዴኤታው ‹‹መነሻው ሀገር ውስጥ ሀብት እስካለ ድረስ ፈጥነን በማልማት ተኪ ምርትን እናምርት የሚል ነበር። ይሄ ሀሳብ አሁንም ይቀጥላል። ተኪ ምርት እናምርት ሲባል አንዱ በጥሬው ማቅረብ ነው። ሌላው ደግሞ እሴት የተጨመረበት ምርት ማቅረብ ነው። ይሄ በተባለው ጊዜ ባይሳካም በቀጣይ የሚፈጸም እንደሚሆን ግን ተስፋ ሰጪ ነገሮች አሉ›› በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2015