ኢትዮጵያ የበርካታ ሃገር በቀል እውቀቶች ባለቤት መሆንዋ ህዝቦቿ በአንድነትና በመከባበር ለዘመናት እንዲኖሩ ምክንያት መሆናቸው ይታመናል ። በተለይ ዘመናዊ የመንግስት መዋቅር ባለተዘረጋባቸው ዘመናት እነዚህ ሃገር በቀል እውቀቶች የማህበረሰቡ ህግና ደንብ ሆነው በስርዓትና በመግባባት እንዲኖሩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው። አሁንም ድረስ ቢሆን በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች በሚባል ደረጃ እነዚህን እውቀቶች መሰረት ያደረጉ የሽምግልና እና የዳኝነት ስርዓቶች ከዘመናዊ የፍትህ አገልግሎት ጎን ለጎን ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ ።
ከእነዚህ ጥንታዊና ባህላዊ ስርዓቶች መካከል በጋሞ ብሔረሰብ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለውና አሁንም ድረስ ማህበረሰቡ በእጅጉ አክብሮ የሚጠቀምበት፤ የሚዳኝበት፤ እርቅ የሚፈፅምበት ‹‹የጎሜ›› ስርዓት ዋነኛው ነው ። ጎሜ የሚለው ይህ ቃል በመሰረታዊነት እርም ወይም ሃጥያት የሚል ትርጓሜ ያለው መሆኑን የጋሞ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የስነምግባር ባለሙያ አቶ ዘነበ በየነ ይናገራሉ ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በህብረተሰቡም ሆነ በፈጣሪ እጅግ የተወገዘ በደል የፈፀመ ሰው ደግሞ ጎሜ ሆነበት ወይም ጎሜ ፈፀመ ይባላል ። በጋሞ ብሔረሰብ ጎሜ ራሱ እንደ ህገ-ደንብም፤ እንደ ፍትሐብሔርም እንደወንጀለኛ መቅጫም እንደመፅሐፍ ቅዱስም ሆኖ የሚያገለግል ባህላዊ ስርዓት ነው ።
አቶ ዘነበ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በጋሞ ባህላዊ ግጭት አፈታት ዙሪያ ጥናት አጥንተዋል፤ ይህንንም የጥናት ስራቸውን ወደ መፅሐፍነት አሳድገው ለንባብ አብቅተዋል፤ በተጨማሪም የጋሞኛ ምሳሌያዊ አነጋገር መፅሐፍም አሳትመው ለህብረተሰቡ አድርሰዋል ። እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በጋሞ ብሔረሰብ የጎሜ ስርዓት አይነቶቹ በርካታ ናቸው ። ለምሳሌ በሃሰት መመስከር በጎሜ ስር ከሚካተቱ ሃጥያቶች ዋነኛው ሲሆን በአጋጣሚ እንኳን አንድ ሰው የሃሰት ምስክርነት ቢሰጥ የጎሜ ቅጣት ያገኘዋል ተብሎ ስለሚታመን ህብረሰተቡ በየትኛውም ቦታ ላይ እውነቱን ብቻ ለመናገርና ለመመስከር ይጠነቀቃል፡፡
‹‹የሰው ድንበር ወይም ወሰን የገፋ አልያም ዝሙት የፈፀመ ፤ ሰው የገደለ፤ የሰው ንብረት ያቃጠለ ፤ የካደ ሁሉ ተግባራት ጎሜ የሚያስከትሉ ናቸው›› ያሉት አቶ ዘነበ፤ በደሉን ተላልፎ የተገኘ ሰው ይደኸያል፤ ንብረቱን ያጣል፤ ሊሞትም ይችላል ። በተመሳሳይ ማህበረሰቡ በአንድ ላይ ሆኖ የሰሩት በደል መተላለፍ ወይም ሃጥያት ከሆነ ማህበረሰቡ ዝናብ እጥረት ወይም ረጅም ጊዜ ዝናብ አልያም ፀሃይ መሆን ጎሜ ከሚያስከትላቸው እርግማኖች መካከል የሚጠቀስ እንደሆነም ያስረዳሉ ።
እንዲሁም የከብቶች ሞትና የአንበጣ መንጋ መከሰት የጎሜ ምልክቶች እንደሆነ አቶ ዘነበ ይጠቅሳሉ። ‹‹እነዚህን ምልክቶችን አባቶች ካዩ አባቶች ይህንን ችግር የሚፈቱበት ስርዓት አስቀምጠዋል ። በዚያ ስርዓት መሰረት ከጎሜው ነፃ ለመውጣት ጥረት ያደርጋሉ›› ሲሉ ያብራራሉ ።
ከቤተሰብ አባወራ ጀምሮ እስከ ጎሳ መሪና የሃገር ሽማግሌዎች ድረስ የጎሜው የማንፃት ስራ የመፈፀም ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያው፤ የግለሰብ ጎሜ ከሆነ የግለሰቡ አባት አልያም አያት ጎሜውን የሚጨርስበት ስርዓት መቀመጡን ያስረዳሉ ። ጎሜው ማህበረሰባዊ ከሆነ ደግሞ በአካባቢው አጠራር ካኦ (ንጉስ)፤ ኡዱጋ፤ ማጋ ፤ግራሻ የተባሉ አለቆችና ባህላዊ መሪዎች መኖራቸውን ያመለክታሉ ።
እንደአቶ ዘነበ ማብራሪያ፤ የጋሞ ህዝብ በአብዛኛው የዳኝነት ወይም የእርቅ ስርዓቱን የሚፈፅመው ዱቡሻ በተባለው የፍርድ አደባባይ ላይ ነው ። ዱቡሻ በጋሞ ብሔረሰብ ለስብሰባ የሚቀመጡበት ቦታ ሲሆን ለብሔረሰቡ ሽማግሌዎች እንደ እንደባህላዊ ስብሰባ አዳራሽ ወይም የፍርድ አደባባይነት ያገለግላል ። በዚህ ሥፍራ ማንኛውም አለመግባባትና ግጭት በብሔረሰቡ ሽማግሌዎች በባህላዊ ግጭት አፈታት ስርዓት መሰረት ይፈታል ። በብሔረሰቡ ባህል መሰረት በዱቡሻ የማይፈታ አለመግባባት አይኖርም ። ምክንያቱም ደግሞ ዱቡሻ የመከባበርና የመደማመጥ እንዲሁም ይቅር የመባባያ መድረክ ነው ። ዱቡሻ የበደለ ተገቢውን እርምት የሚወስደበትና ተበዳይ የሚካስበት በአጠቃላይ እርቅ የሚወርድበት ስርዓት ነው ።
‹‹ዱቡሻ የራሱ ስነስርዓት አለው›› የሚሉት ባለሙያው፤ በዚህ መሰረት ዱቡሻ ላይ የሚካሄድ ማንኛውም ስብሰባ (ዱላታ) ወደ ዱቡሻ አለመግባባትን ለመፍታት በሽምግልና የሚመጣ ሽማግሌ የመልካም ስብዕና እና የንፁህ ህሊና ምልክት የሆነው የጋሞ አባቶችን አለባበስ ሊያሟላ እንደሚገባ ያስረዳሉ ። ይህም ማለት ባለደማቅ ቀለሙን ዱንጉዛ ጋቢ ወይም ኩታ መደረብና የብሔረሰቡ ሽማሌዎች የክብር በትር የሆነውን ጻንባሮ (ሆሮሶ) መያዝ ይጠበቅበታል ።
በዚህ የፍርድ አደባባይ በዳይና ተበዳይ እውነት እውነቷን ብቻ በግልፅ የሚናዘዙበት፤ ሽማግሌዎችም ፈጣያቸውን መካከል አድርገው የግራ ቀኙን ሰምተሰው በቅንነት በሃቅ ይፈርዱበታል ። ለዚህ ባህላዊ ስርዓት ታዲያ ማንኛው የጋሞ ማህበረሰብ ከሊቅ እስከ ደቂቁ ይገዛል፤ ይታዛዛል ። ይህንን ያልፈፀመ ሰው ጎሜ (እርም ወይም ሃጢያት) ይሆንበታል ተብሎ ስለሚታመን የሽማግሌዎቹ ውሳኔ ከማክበርና ከመቀበል ውጪ አማራጭ አይኖረውም ። ጎሜ በጋሞ ማህበረሰብ በሁለት ወይም በብዙ ሰዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ዳግም እንዳይነሳና በዘላቂነት በመፍታት የነገ መጻይ ዕድል ተስፋቸውን በጋራ የሚያልሙበት ሥርዓት ነው ።
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ እንደማህበረሰብም ሆነ እንደግለሰብም ከአቅም በላይ የሆኑ ነገሮችን የሚፈታው ማካ የተባለው ባህላዊ ቄስ አማካኝነት ሲሆን፤ ውሃና ቅጠል በመያዝና ባህላዊውን አልባሳት ለብሶ የማንፃት ስርዓት ያካሂዳል ። ጎሜው ከወሰን ጋር ተያይዞ የመጣ የነፍስ ግድያ ወይም ግጭት ከሆነ ኡጋዴና አርዴና የሚባሉ አገናኛ አካላት አሉ ። እነኚህ አገናኞች ማካ ከሚባለው ባህላዊ ቄስ ጋር ሆነው የነፍስ ግድያውን የፈፀመ ግለሰብ በግ ወይም ከብት አርዶ አንጀቱን በማውጣትና በፈርሱ ላይ ሁለቱም ወገኖች (ገዳይና የሟች ቤተሰብ) እንዲረግጡት ያደርጋሉ ። እርስበርሳቸው ስጋ እንዲጎራረሱ በማድረግ እርቅ ይወርዳል ።
‹‹በአንድ በደል መተላለፍ ምክንያት በአባት፤ እናት፣ አያት እና የጎሳ መሪ የተረገመ ግለሰብ ካለም እርግማኑን በይቅርታ ካስረሱ በኋላ ካሳ በማስከፈል ጉሜውን ለዘለቄታው እንዲቋጭ ያደርጋሉ›› ሲሉ አቶ ዘነበ ያብራራሉ ። በሌላ በኩል ደግሞ ከክህደት ጋር የሚያያዝ ጎሜ ከሆነ በዳዩ ግለሰብ የካደውን ገንዘብ በመመለስ ለግለሰቡ ይቅርታ ጠይቆ ንስሃ ከገባና ተበዳዮች ይቅርታ ካደረጉ ከጎሜው የሚነፃበት አግባብ መኖሩም ያመለክታሉ ። በጋሞ ማህበረሰብ በተመሳሳይ መልኩ የሚፈፀሙ ከ100 በላይ የሚሆኑ የጎሜ አይነቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ አፈፃፀማቸውና ስርዓታቸው ግን እንደየበደሉ አይነት ልዩነት ያለው መሆኑን ነው ያስገነዘቡት ።
የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሞናዬ ሞሶሌ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ዱቡሻ በጋሞ ብሔረሰብ እርም የሆነውን ነገር የሚረግምበትና እርግማኑን የሚያፀናበት መድረክ ነው ። በዚህ መድረክ ላይ ውሸት ፈፅሞ መናገር አይቻልም ። ይህንን ከተላለፈ ደግሞ እርግማኑ ሁሉ ይደርስበታል ተብሎ ስለሚታመን በዚህ አደባባይ ላይ እውነት ብቻ ነው የሚነገረው ። ይህ ባህላዊ ስርዓት ደግሞ ስርዓት ህዝቡ ከመጥፎ ስራዎች ራሱን እንዲቆጥብ ከማድረግ አንፃር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ።
‹‹ጎሜ ከእምነት ጋር የተያያዘ ነው፤ በተለይ የጋሞ ህዝብ እውነት መናገር ስለሚወድ የፈጠሪን ትዕዛዝና እውነት ማስቀደም ይመርጣል›› የሚሉት ኃላፊው፤ ይህ ስርዓት ፈጣሪን ከመፍራት ጋር የሚያያዝ ስለሆነ ከጥንት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በጋሞ ማህበረሰብ ሲወርድ ሲዋረድ ተጠብቆ መቆየቱን ያመለክታሉ ። ስርዓቱ በከተማም ሆነ በገጠር አሁንም ድረስ በማህበረሰቡ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ስርዓት አስታውሰው፤ በተለይ በገጠር ያለው ማህበረሰብ የሚከብረውና አሁንም ከምንም በላይ የሚገለገልበት ስርዓት መሆኑን ነው የጠቆሙት ።
አቶ ዘነበም በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ የጎሜ ስርዓት እስካሁን ተጠብቆ መቆየቱን ይስማማሉ፤ ይሁንና ‹‹እርግጥ፤ ከተሞች አካባቢ ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች መስፋፋት ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ የሃሰት ክሶች፤ የሃሰት ምስክሮች ይበዛሉ ። ያም ሆኖ በገጠሩ አካባቢ ማለትም በ14ቱም የጋሞ ወረዳዎች ላይ በስፋት በእምነትም ሆነ በባህል አባቶችም ይህንን የጎሜ ስርዓት ይተገብራሉ›› በማለት ነባራዊ ሁኔታ ይናገራሉ ።
ያም ቢሆን አብዛኛው ማህበረሰብ ወደ ዱቡሻ (የፍርድ አደባባዩ) የሚወርድ ማንኛውንም ጎሜ የሆነ ድርጊት ላለመፈፀም ይታገላሉ፤ ፈፅመው ከተገኙ ደግሞ ይቅርታ ጠይቀው ከጎሜው ለመንፃት የሚያስችሉ ስርዓቶችን መከተል የሚጠበቅባቸው መሆኑን ያስረዳሉ። በጋሞ ማህበረሰብ ዘንድ በዚያ መልኩ አለመግባባቶችና ቅራኔዎች የሚፈቱት መሆሩን ጠቅሰው፤ ‹‹በመደበኛ ፍርድ ቤት ከሚመጣው መዝገብ ይልቅ ጎሜ ላይ የሚያልቀው ብዙ ክስ የሚበልጥ ነው›› ይላሉ፡፡
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ በከተሞች አካባቢ 16 መወቅሮች ላይ ፍርድ ቤቶች አሉ፤ እዚያ አካባቢ የሚመጡ ምስክሮች በሃሰት መመስከር አዝማሚያዎች አሉ ። ይህም እየሆነ ያለው ከተሞች ላይ በአብዛኛው የሚኖረው ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡና የጋሞን ባህልና ወግ የማያውቁ በመኖራቸው እና ከተሜው የአካባቢውን ህብረተሰብ ጠብቆ እንዲቆይ በማድረግ ረገድም ተከታታይነት ያለው ስራ ባለመሰራቱ ነው ። በገጠር ግን የትኛውም ግለሰብ በሃሰት ለመመስከር አይደፍርም ። ቤተዘመዶቹም ቢሆኑ ጥፋቱን እያወቁ በሃሰት መስክሮ እርግማን እና የፈጣሪ ቁጣ እንዲመጣበት ስለማይፈልጉ አስቀድመው ይከላከላሉ ።
አሁንም ቢሆን ግን የማህበረሰቡን ባህልና ወግ ጠብቆ የቆየው የህብረተሰብ ክፍል በርካታ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዘነበ፤ ለዚህም አብነት አድርገው የሚጠቅሱት ከሁለት ዓመት በፊት በአርባ ምንጭና በሌሎችም የጋሞ ተወላጆች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት የጋሞ አባቶች በባህላቸው መሰረት ሳር ይዘው በመውጣት የፈፀሙትን የማረጋጋት ስራ ነው ።
‹‹ባህሉ አሁንም ተጠብቆ ስለቆየ ነው ወጣቶቹም የአባቶችን ተግሳፅ ሰምተው መመለስ እና መረጋጋት ማምጣት የተቻለው›› ሲሉ ይናገራሉ ። ከዘመናዊ የፍትህ ስርዓቱ ጋር ግጭት ሳይፈጥር እርስ በርስ ተመጋግቦ የሚሄድበት ሁኔታ መኖሩ በአካባቢው የተረጋጋና ሰላማዊ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ ። አብነት አድርገውም ‹‹አባቶች አንድ ነፍስ ገዳይ ተይዞ ቢታሰር እስራቱን አይከለክሉም ። ሆኖም ሀገር ቤት ሌላው ወገን እርስ በርስ ቂም በቀል ቁርሾ እንዳይቀጥል ባህላዊ ስርዓት አማካኝ ጎሜ እንዳይፈጠር ሽምግልና ስርዓት ይፈፅማሉ›› ሲሉ ይጠቅሳሉ ። የታሰረው ሰው የእስር ጊዜውን ጨርሶ ሲወጣም ዳግመኛ ባህላዊ ስርዓቱ ተፈፅሞ ከህብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀል የሚደረግ መሆኑን ያብራራሉ ።
ይህንን የጋሞ ሀገር በቀል እውቀትና ተሞክሮ በሌሎች አካባቢዎችም ማስፋት ጠቃሚ እንደሆነ ያነሳሉ። በተለይ ደግሞ ልዩነቶች እየሰፉና የግጭት ሁሉ ምንጭ እየሆኑበት ባሉበት በዚህ ጊዜ ማህበረሰቡ የሚቀበለውን እንደ ጎሜ ሥርዓት የመሰሉ ባህላዊ ክንውኖችን ስራ ላይ ማዋሉም ሆነ ተጠብቀው እንዲቆዩ ማድረጉ ሃገራዊ ፋይዳው የጎላ ነው ። በተለይም ኢትዮጵያ ሃገር በቀል እውቀትን ተጠቅማ እፈታዋለው ብላ ለያዘችው ችግሮች እየተደረገ ያለው የምክክር ሂደት እንደአንድ መልካም ተሞክሮ ሊወሰድ ይገባል ።
አቶ አቶ ሞናዬ ጎሜ ለማህበረሰባዊ መረጋጋት ፤ ለልማት፤ ለአብሮነት ፤ ለመከባበር ፤ ለፍትህና ለርዕት መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ያነሳሉ። ‹‹ይህ የጋሞ ህዝብ እሴት አስጠብቆ ማቆየቱ ለሃገር ሰላም፤ ለፍትህ መስፋፋት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል። በህዝቦች መካከል ልዩነቶችና ግጭቶች እንዲጠፉ በምትኩ ፍቅርና መተሳሰብ እንዲሰፋፋ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው›› ይላሉ ። ከሁሉ በላይ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለው ትውልድ እንዲኖር በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ እንደሆነ ያመለክታሉ ።
በተጨማሪም በባህላዊ እርቅ የተፈታ ቁርሾ አንዱ ሌላውን ቆይቶ እንዳያጠቃ ከፍተኛ መተማመን ይፈጥራል፡፡ ባይ ናቸው ። ‹‹ሌላው ይቅርና መንግስት በሰላምና በልማት ረገድ ለሚሰራቸው ስራዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው›› ሲሉ የተናገሩት ኃላፊው፤ ይህ እሴት እንዳይሸረሸር ሲባልም ዞኑ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ያስረዳሉ። ‹‹ ከእነዚህም መካከል በጋሞ ህብረተሰብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የዱቡሻ ስርዓት ዩኒስኮ ላይ ለማስመዝገብ እየሰራን ነው›› ብለዋል ። በተጨማሪም የዚሀን እሴት አስፈላጊነት እና ቀጣይነት ለማረጋገጥ ያስችል ዘንዳም ወደ ህዝቡ በማውረድ በህብረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2015