(የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዓድዋ በዓል አስመልክተው ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል)
እንኳን ለ127ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
የዓድዋን ድል ከፍ አድርገን እንድናከብረው የሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋነኛው ምክንያት ድሉ የሁላችንም በመሆኑ ነው። በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ላይ ብንዘዋወር በዓድዋ ጦርነት ያልተሳተፉ ቀደምቶች የበቀሉበት ምድር አይገኝም። ሁሉም እንደ አቅምና ችሎታው ደምና ላቡን አፍስሷል፤ አጥንት-ሥጋውን ገብሯል፤ እውቀት ችሎታውን አዋጥቷል። አያት ቅድመ አያቶቻችን ያንን ሁሉ ዋጋ የከፈሉት ለግዛት አንድነት፤ ለኢትዮጵያዊነት ክብር እና ለአገር ሉአላዊነት ነው። ዛሬ የምንኮራበት ማንነት፣ እንዳሻን የምንቦርቅበት ነፃነት፣ ውለን የምናድርባት አገር ያገኘነው በእነሱ መስዕዋትነት ነው። ዓድዋ የሁላችን አርማ ነው የምንለውም በዚህ ምክንያት ነው።
በሁላችን እውን የሆነ፣ ለሁላችን የተበረከተ ውድ ስጦታችን በመሆኑ ዓድዋን እንደከበረ እንቁ በስስት እናየዋለን። በብዙ ነገሮች ላንተሳሰር እንችላለን፤ ዓድዋ ገመድ ሆኖ ያስተሳስረናል። በብዙ ጉዳዮች ላንመሳሰል እንችላለን፤ ዓድዋ ቀለምና ቅርጽ ሰጥቶ ያመሳስለናል። በብዙ ነገሮች ላንግባባ እንችላለን፤ ቅድመ አያቶቻችንን አግባብቶ በአንድ አውድማ ያጋደለ «የዓድዋ ድል» ያግባባናል።
ዛሬ የግዛት አንድነታችንን የሚፈታተኑ ኃይሎች ከጉያችንም ይብቀሉ ከውጭ፣ የቅድመ አያቶቻችንን አደራ ትቢያ ላይ ሊጥሉ የተነሱ ናቸውና የሁላችንም ጠላቶች ናቸው። በነፃነትና ሉአላዊነታችን ላይ የሚሰነዘሩ እኩይ እርምጃዎች በመከራ የወረስናት ኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ እንደበቀሉ እባጮች ቆጥረን እንፋለማቸዋለን። ኢትዮጵያን ለማሳነስና ኢትዮጵያዊነትን ለማኮሰስ ሌት ተቀን ሴራ የሚጎነጉኑ አካላት፤ ዓድዋ ያጋመደንን ማንነት ሊበጥሱ እንደተሳሉ ምላጮች አስበን በጋራ እንታገላቸዋለን።
ዓድዋ የጎራዴና የመድፍ፣ የጦርና የጠብመንጃ፣ የጋሻና የባሩድ ፍልሚያ የፈጠረው ድል ብቻ አይደለም። ወኔና ጀግንነት፣ ጥበብና መደመር የተባሉ እሴቶች ውጤት ጭምር እንጂ። በመሣሪያ ብዛትና ጥራት የሚበልጠንን ጠላት ያሸነፍነው በእነዚያ እሴቶች የበላይነት ስለነበረን ነው። ጣልያን የቱንም ያህል ዘመናዊ ጦር መሳሪያ ቢታጠቅ የኢትዮጵያውያንን ወኔና ጀግንነት መርታት አልቻለም፤ የቱንም ያህል ጠንካራ ምሽግ ቢገነባ የቀደምቶቻችን ድምር ጉልበት አልመከተም፤ የቱንም ያህል ባንዳዎችን በጥቅምና በድርጎ ቢያባብል ከጦር መኮንኖቻችን ዘዴና ብልሃት አላመለጠም።
በብዙ ምክንያቶች የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ያለው ትርጉም ከጊዜ ጋር ዋጋው እየጨመረ እንደሚሄድ ተቀማጭ ገንዘብ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። ትውልድ ሁሉ እየመነዘረ ሰላም፣ ልማት፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ጽናት፣ ጀግንነት፣ ክብርና ልዕልና ሊገዛበት የሚችል፤ ኩራትም እራትም የሚሆን፤ ቀደምቶቻችን ያስቀመጡልን አንጡራ ሀብት ነው። ይህ አንጡራ ሀብት ባለፉት መቶ ዓመታት በተደጋጋሚ የተቃጣብንን ወረራ እንድንመክት አድርጎናል። ይህ አንጡራ ሀብት ቅኝ ግዛትንና ቅኝ ገዥዎችን እንድንመክት አድርጎናል። ይህ አንጡራ ሀብት ሊፈርሱ ነው ከተባልን በኋላም እንደ ንሥር ታድሰን እንድንበረታ አስችሎናል። ይህ አንጡራ ሀብት በማይከፋፈል ኅብረ ብሔራዊነት፣ በማይጠቀለል አንድነት ጸንተን እንድንኖር አብቅቶናል።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣
የዓድዋን ድል ስንዘክር አራት አካላትን ልናስታውስ ይገባል። የዘመቻው መሪዎችን፣ የጦር ዘማቾችን፣ የጦሩ ደጀኖችን እና የዘማቾቹ መሠረት የሆነውን ሕዝብ። የዓድዋን ዓይነት ድል ለማምጣትም እነዚህ ኃይሎች ተስማምተው፣ ተቀናጅተውና ተናብበው ለአንድ አገራዊ ዓላማ መሥራት ነበረባቸው።
ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ መላውን የኢትዮጵያን ጦር አስተባብረው መርተዋል። ተገቢውን ጊዜና ሁኔታ መርጠው፣ የውስጥ ዐቅምና የውጭ ድጋፍን አስተባብረው፣ በአመራር ጥበብና በዲፕሎማሲ ብልሃት ችግሮችን እያለፉ፤ መቶ ሺዎችን ያስተባበረና ያስተሣሠረ፣ በዓለም በንቅናቄው እጅግ አስደማሚ የሆነ ዘመቻና ድል መርተዋል። የመሪ ብልህነት ቸኩሎ በመወሰን አይታወቅም። ተገቢውን ውሳኔ በተገቢው ጊዜና ሁኔታ በመወሰን እንጂ። ከ1881 ዓ.ም ጀምሮ በጣልያኖች ምክንያት የገባው የከብት በሽታ ለአራት ዓመታት ሕዝቡንም ከብቱንም ጎድቶት ነበር።
ከፍተኛ ረሃብም ተከሥቶ ነበር። ምንም እንኳን ጣልያን ወሰን እየገፋ መምጣቱ ቢታወቅም ክፉው ቀን እስኪያልፍ፣ መሣሪያውም ከውጭ እስኪገባ መታገስ ይፈልግ ነበር።
ባለ ሦስት እርከን ከነበረው አመራር የምንወስደው ትምህርት አለ። ከላይ ንጉሠ ነገሥቱ፤ ቀጥሎ የየአካባቢው መሪዎች፣ ከዚያም የጦር አበጋዞቹ። የየአካባቢው መሪዎች አንዳንዶቹ ከንጉሡ ጋር የማይስማሙ ናቸው። ብሔራዊ ጥቅም ግን አንድ አደረጋቸው። አንዳንዶቹ ሸፍተው ነበር። አገር ተወረረ፣ ድንበር ተደፈረ ሲባሉ ግን የግል ጠባቸውን ርግፍ አድርገው ለኢትዮጵያ ዘመቱ።
አንዳንዶቹ በነበረው የአስተዳደር ሥርዓት የማይስማሙ ነበሩ። አገር የሚያጠፋ ጠላት ሲመጣ ግን ልዩነታቸውን ችለው፣ አለመስማማታቸውን ከኢትዮጵያ በታች አድርገው ዘመቱ። ያንን ሁሉ መኳንንትና መሳፍንት፣ ያንን ሁሉ የየአካባቢ ገዥ፣ ያንን ሁሉ የየማኅበረሰቡ መሪ ለአንድ ዘመቻ ያስተባበረው ምንድን ነው?
ሥርዓቱ፣ አስተዳደሩ ወይም ርእዮተ ዓለሙ አይደለም። ከሁላችንም ኢትዮጵያ ትበልጣለች የሚለው እምነት እንጂ። ከክብራችንም፣ ከልዩነታችንም፣ ከቅሬታችንም፣ ከጠባችንም፣ ኢትዮጵያ ትበልጥብናለች ብሎ ማሰብ እንጂ። ከዚህ የምንወስደው ትምህርት አለ።
በዚህ ኅብረ ብሔራዊነትና አገራዊ አንድነት ጎልቶ በታየበት ታላቅ ዘመቻ ያልተሳተፈ ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ አልነበረም። ከየአቅጣጫው የመጡትን ብሔር ብሔረሰቦች ያግባባቸው ቋንቋ «ነፃነት» ሲሆን፤ ያንን ሁሉ ጦር ወደ አንድ ዕዝ ያመጣው ሥርዓት «ኢትዮጵያዊነት» ይባላል። ከዚያ በፊት በዚያ መጠን፣ ከአራቱ ማዕዘን የመጡ ኢትዮጵያውያን በአንድ ቦታ ተገናኝተው አያውቁም። እንደ ዛሬው ብዙሃን-መገናኛ ባልነበረበት ዘመን የአዋጁ ዜና በፍጥነት እንዲዳረስ ያደረገው በሁሉም ዘንድ የነበረው የአገር ፍቅር ስሜት ነው።
የዓድዋ ድል የፊት አውራሪዎች ድል ብቻ አልነበረም፤ የደጀኖች ድል ጭምር እንጂ። የጠላትን መረጃ ያመጡ የደኅነት ጀግኖች፤ ከተለያዩ አገራት የመሣሪያ ድጋፍ ያስገኙ የዲፕሎማሲ ጀግኖች፣ ጦሩን ሲያበረታቱ የነበሩ የኪነ ጥበብ ጀግኖች፤ ጦሩን ለዓላማ ሲያጸኑ የነበሩ የሃይማኖት አባቶች፣ ስንቅ ሲያዘጋጁና ሲያቀብሉ የነበሩ ሥራ ቤቶች፣ ቁስለኛ ሲያክሙ የነበሩ የሕክምና ጀግኖች፣ መንገድ ሲቀይሱና ሲያስተካክሉ የነበሩ የምሕንድስና ጀግኖች፣ ታሪክ ሲመዘግቡ የነበሩ ጀግኖች ነበሩ። ያልዘመተ ባለሞያ፣ ያልተሳተፈ ጥበብ አልነበረም። ልጆችና አዛውንቶች፣ ሴቶችና ወንዶች፣ ሁሉም እንደሙያና ችሎታው በተለያዩ ግዳጆች ዘምቷል። ኢትዮጵያ እዚህ የደረሰችው፤ ወደፊት የምትጸናውና የምትለማውም በዚህ መልኩ እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል።
የዚህ ሁሉ ገድልና ድል መሠረቱ ግን ሕዝቡ ነው። ጀግኖቹን ያፈራው ሕዝቡ ነው። ጀግንነት ባህላችን እንዲሆን ያደረገው ሕዝቡ ነው። ልዩነት በኅብረ ብሔራዊ አንድነት፤ ግጭት በዕርቅ፣ ጠብ በፍቅር፣ የግል ጥቅም በአገር ጥቅም እንዲሸነፍ ያደረገው ሕዝቡ ነው። ስንቁን ያዘጋጀው፣ እየሸለለና እየፎከረ ጀግኖቹን የሸኘው ሕዝቡ ነው። ከየቦታው መሣሪያ አፈላልጎ ጀግና ያስታጠቀው ሕዝቡ ነው። ጦሩ ግንባር ሲዘምት አካባቢውን የጠበቀው ሕዝቡ ነው። ከድል በኋላ አገር እንዳትራብ እህል ያመረተው፣ ከብቱን የጠበቀው ሕዝቡ ነው። የተሠዉትን ልጆች ያሳደገው፣ የቆሰሉትን ጀግኖች የተንከባከበው ሕዝቡ ነው። ድል አድራጊ ሕዝብ በሌለበት ድል አድራጊ ሠራዊት እንደማይፈጠር መዘንጋት የለበትም።
ውድ የአገሬ ልጆች፣
የዛሬዋም ኢትዮጵያ አራቱ ኃይሎች ለአንድ ዓላማ እንዲቆሙላት ትፈልጋለች። መሪዎች፣ ዘማቾች፣ ደጀኖች እና መሠረቶች። ዓላማችን አንድ ነው፤ ኢትዮጵያን በሁለመናዋ የበለጸገች አፍሪካዊት አገር ማድረግ። በየደረጃው ያሉ መሪዎች፣ በየተቋማቱ ያሉ ዘማቾች፣ ዘማቾቹን በዕውቀት፣ በገንዘብ፣ በምክር፣ በተግሣጽ፣ በሐሳብ፣ በጥበብ የሚደገፉ ደጀኖች፣ የዚህ ሁሉ ባለቤትና ተጠቃሚ የሚሆነው ሕዝብ አንድ ሆነን ካልሠራን ግን ብልጽግና ምኞት እንጂ ሕይወት አይሆንም። እንኳን ታሪክ ሠሪ ታሪክ ዘካሪም አንሆንም።
የዓድዋ ዘማቾች ከወረርሽኝና ከተፈጥሮ ፈተና ጋር ታግለዋል፤ በአስተዳደርና በአገዛዝ መንገድ ልዩነት ነበራቸው። የውጭ ጫና ገጥሟቸዋል። የውስጥ ባንዳ ፈትኗቸዋል። ይህ ሁሉ ግን ከኢትዮጵያ በታች ነው ብለው ለአንድ ዓላማ ታግለዋል። ለአንድ ዓላማ ተሠዉተዋል። ካገኙት ይልቅ የሰጡን ይበልጣል። ከተጠቀሙት ይልቅ የጠቀሙን ይበልጣል። ለአገሩ የሚሠራ ሰው መንገዱ ይሄው ነው።
ዛሬም ፈታኞችና ፈተናዎች ከፊታችን አሉ። የጀግኖች መለኪያ ግን እነዚህን ፈተናዎች ለነገው ተስፋ ብሎ ማለፍ ነው። በተከፈለልን ዋጋ እየኖርን ነውና እኛም ለሚመጣው ትውልድ ዋጋ መክፈል አለብን። በወቅቱ ኢትዮጵያ በአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች መከበቧን፣ በውስጥ በከብት እልቂትና በረሃብ መፈተኗን ብቻ ብትመለከት ኖሮ ብርታትና ወኔ አይኖራትም ነበር። ችግሮቹን ብቻ የሚቆጥር ሕዝብ ዕድሎቹ ያመልጡታል። ዕድሎቹን ቆጥሮ የሚጸና ግን ችግሮቹን ያሸንፋል። ዓድዋ በችግር ተተብትቦ መቅረትን አላስተማረንም፤ ዕድልን ቆጥሮ ችግርን መሻገር እንጂ። ከትናንት ይልቅ በነገ ላይ ካተኮርን፣ ሁሉን ነገር ከኢትዮጵያ በታች ካደረግን፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ካጸናን፣ እንደ ጉም የከበበን ፈተና ሁሉ እንደ ጢስ በንኖ ይጠፋል። ያኔ በድህነትና በኋላ ቀርነት ላይ፣ በመለያየትና በመከፋፈል ላይ የዓድዋ ድል ይደገማል።
መልካም የድል በዓል ለሁላችንም ይሁን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ
ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
የካቲት 22፤ 2015 ዓ.ም
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2015