በእድሜ ገደብ በሚካሄዱ የታዳጊና ወጣቶች ስፖርታዊ ውድድሮች ሁሌም ከዕድሜ ጋር በተያያዘ ችግሮች ይገጥማቸዋል።ዕድሜን ማጭበርበር በነዚህ ውድድሮች የተለመደና ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገትም እንቅፋት ሆኖ ዓመታትን ተሻግሯል።ይህም ለአወዳዳሪው አካልና ለሌሎች በትክክለኛ ዕድሜ ለሚወዳደሩ ታዳጊዎች ፈተና ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል።በቅርቡ በአሰላ ከተማ በተካሄደው 11ኛው የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይም ይህ ዕድሜን የማጭበርበር ችግር ጎልቶ በመታየቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ አትሌቶች ከውድድር መታገዳቸው ይታወሳል።
ፌዴሬሽኑ በወቅቱ የተወሰደውን እርምጃ በርካቶች አድንቀዋል።ፌዴሬሽኑም ይሄን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደማይታገስና እርምጃዎችን በመውሰድ እንደሚቀጥል አሳውቆ ነበር።
በዚህ ችግር የተነሳ ስጋት ተደቅኖበት የነበረውና ለመጀመሪያ ጊዜ በድሬዳዋ አስተናጋጅነት የተካሄደው 1ኛው የኢትዮጵያ ታዳጊዎች ፕሮጀክቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የነበረ ቢሆንም ውድድሩ በተፈራው ልክ የዕድሜ ማጭበርበር ችግር ጎልቶ እንዳልታየበት ተጠቁሟል።
ውድድሩ በድሬዳዋ ስቴድየም ከየካቲት 15-19/2015 የተካሄደ ሲሆን ባለፈው እሁድ በደማቅ ሁኔታ ተፈጽሟል።ውድድሩ በዋናነት ዓላማ አድርጎ የተካሄደው እ.አ.አ ከሚያዝያ 19-23/2023 በዛምቢያ ሉሳካ ለሚደረገው ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ ነው።
ውድድሩ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች በታዩ ፉክክሮች የጎላ የዕድሜ ማጭበርበር ችግሮች አልገጠመውም።
ሻምፒዮናው ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ እንደመሆኑ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ተሳትፈውበታል።ሁለት የከተማ አስተዳደሮችና ዘጠኝ ክልሎችም ተሳትፈዋል።በውድድሩ ዕድሜያቸው ከ18 በታች ወንድ 141፣ ሴት 111 በድምሩ 251 ተሳትፈዋል።ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑት ደግሞ ወንድ 132፣ ሴት 137 በድምሩ 269 ወጣቶች ተሳትፈዋል።በአጠቃላይ ከ18 ዓመት በታች፣ ከ16ዓመት፣ ከ15 ዓመት በታች በሉት የዕድሜ እርከኖች በድምሩ 641 አትሌቶች መሳተፋቸውን ተገልጿል።
ውድድሩ የአጭር መካከለኛ ፣ረጅም ርቀትና የሜዳ ተግባራትን፣ ድብልቅ ሪሌ ጨምሮ በ17 የውድድር ተግባራት በተለያየ የዕድሜ እርከኖች ፉክክሮችን በማስተናገድ እንደተጠናቀቀም ታውቋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ሥነሥርዓት ዳይሬክቶሬት አቶ አስፋው ዳኜ ውድድሩን አስመልክቶ ለአዲስ ዘመን በሰጡት አስተያየት፤ ውድድሩ የተካሄደው ከ18 ዓመት በታች ባሉ የዕድሜ እርከኖች መሆኑን ጠቁመው፣ ውድድሩ ሲካሄድ የ15 ዓመት አትሌትና የ17 ዓመት አትሌት አንድ ላይ መወዳደር ስለሌለበት ገና አቅማቸውና አካላቸው በመዳበር ላይ ያሉ የ15 ዓመት አትሌቶች የራሳቸው ውድድር እንዳደረጉ ገልጸዋል።
እንደ አቶ አስፋው ገለፃ፣ የታዳጊ ፕሮጀክቶች ሻምፒዮና መጀመሩ መልካምና ይበል የሚያሰኝ ነው።ሁሉም መነሻው ፕሮጀክት እንደሆኑና ብዙ እምቅ እውቀትና ችሎታ ያላቸው አትሌቶች እራሳቸውን የሚያገኙበት ቦታ እንደሆነም ጠቁመዋል።የፕሮጀክቶች ስልጠና እንደየውድድር ተግባሩ ሯጭ የሚሆነው ሯጭ፣ ዘላይ የሚሆነው ዘላይ እና ወርዋሪ የሚሆነው ወርዋሪ ሆኖ ብቃቱ የሚለይበት እንደሆነም አስረድተዋል።በመሆኑም በፕሮጀክቶች ታቅፈው የሚገኙ አትሌቶች ውድድር ተዘጋጅቶላቸው እራሳቸውን ችለው መወዳደራቸው ትልቅና ለወደፊቱም መቀጠል የሚኖርበት መሆኑን ተናግረዋል።
ዕድሜን በተመለከተ በየክልሎቹ የሕክምና ኮሚቴ ተዋቅሮ ማጣሪያ መደረጉን የገለጹት አቶ አስፋው፣ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ ሕክምና ባለሙያ በመታገዝ ድሬዳዋ ላይም ድጋሚ የማጣራት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።በዚህም በሻምፒዮናው ምናልባት ጥቂት ያልጠሩ የዕድሜ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ እንጂ 90% የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች በተገቢው ዕድሜያቸው ተፎካክረዋል ማለት እንደሚቻል አቶ አስፋው አብራርተዋል።
በቀጣይም ለዕድሜ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራና እንደ ሀገር ምልከታና ማጣራት (ሱፐርቪዥን) እንደሚኖር ተጠቁሟል።በማጣራቱ ሂደት ላይም የዳታ ቤዝ ተዘጋጅቶ የእያንዳንዱ ፕሮጀክት መረጃ ተመዝግቦ እንደሚቀመጥም ገልጸዋል።በዚህም አንድ በዳታ ቤዝ ውስጥ የፕሮጀክቶች መረጃ ከገባ ማንም በዕድሜ ጉዳይ ማጭበርበር እንደማይችልም አስረድተዋል።በዕድሜ ጉዳይ አጭበርብረው ወደ ውድድር የሚመጡ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ አሰልጣኞች፣ አትሌቶች በየደረጃው የማስጠንቀቂያ እንዲሁም የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከማድረግ ባሻገር እስከመታገድ የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል ፌዴሬሽኑ ግልጽ ማድረጉን ጠቁመዋል።
ከድሬዳዋው ውድድር እንደ ግባት የተወሰደውና ሊሻሻል ይገባል ተብሎ የታመነበት ጉዳይም ከዕድሜ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመው፣ ፍጹም ባይባልም እጅግ አበረታች ተስፋ መታየቱን አክለዋል።በቀጣይም ይህን ችግር ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ ጥረቱ ይቀጥላል ሲሉ አስረድተዋል።በዚህም በተገቢው ዕድሜ የሚወዳደር አትሌት ውጤታማና ለረጅም ጊዜ በስፖርቱ ውስጥ የመቆየት እድሉ ሰፊ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሠራበት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም