ዓድዋ ዛሬ ነው ! ዓድዋን በድምቀት፣ በተለየ ወኔና ስሜት የሚያከብር ትውልድ አለ።ይህ መሆኑ ድርብ ደስታን የሚፈጥር ነው። ዓድዋ የአንድነታችን ዋልታና ማገር፣ የሰውነታችን ውሀ ልክ ነው። የነጻነትና የአንድነት ዋጋ ለሚገባው ይህ እውነታ ትርጉሙ ሰፊና ጥልቅ ነው።
የአንድነት መገለጫ የሆነውን ዓድዋን በአንድነት መንፈስ በመሆን ከማክበር ባለፈ ልንኖረው ይገባል። ሰፊ በሆነች ሀገር ሳንገፋፋ ተከባብረንና ተባብረን ብናከብረው ብዙ እናተርፋለን። አባቶቻችን ሆነ እኛ ተፈጥራ ልናያት የምንሻትን ሀገር ለመፍጠር ጥልቅ አቅምም ይሆነናል ።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆነው ለአንድ ዓላማ በአንድ የተሰባሰቡበት፤ ሰው ለሚለው ትርጉም ዋጋ የከፈሉበት፤ ከኢትዮጵያ አልፈው ለአፍሪካ ብርሃን መሆን የቻሉበትና ትልቅ ዋጋ ያለው የመስዋዕትነት ውጤት ነው።
ኢትዮጵያውያን ቁርሾን ጥለው፤ ልዩነትን አስወግደው፤ እርቅን እና ይቅር ባይነትን ከሁሉ አስቀድመው፤ ከጠላት ጋር ለመፋለም በአንድነት የተመሙበት ሰውነትን አስበልጠው ነው።አጥንታቸውን የከሰከሱት፣ ደማቸውን ያፈሰሱት ሰውነትን ባከበረ ማንነት መሠረት ላይ ሆነው ነው።
በዘርና በመንደርተኝነት አስተሳሰብ/ መንፈስ ታጥረን ለአንድነትና ለሰላም ጀርባ ከሰጠን ዓድዋን ልንኖረው አይደለም ልናከብረው አይቻለንም።ዓድዋ የአንድነት ተምሳሌትና ለሰውነት የተከፈለልን ዋጋ ነውና።
በሰፊ ሀገር ላይ መገፋፋታችን ኢትዮጵያውያን አብሮ መዋጋት እንጂ አብሮ መኖር፣ መሥራት፣ ማደግና መበልጸግ አይችሉም ይሆን ?! የሚል ጥያቄ ያስነሳል።ለዚህ አልረፈደምና የአያት እና የቅድመ አያቶቻችን ዓድዋን እንደገና ለመሥራት መንቃት ይገባናል።
ዓድዋን ከመዘከር ባሻገር በተግባር መኖር ይጠበቅብናል። ድልን በመዘከር ብቻ ባለ ድል አያደርግም። አያቶቻችን በይቅር ባይነት፣ በአንድነት ተሰባስበው በጦር ግንባር የዘረኝነትን መንፈስ አሸንፈው፤ በአብሮነት አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው አንድ አገር አስረክበውናል። አያቶቻችን ያወረሱንን የድል ታሪክ መዘከር ብቻ ሳይሆን ኖረን ሕይወት ልንዘራበት ይገባል።
የዓድዋን ድል በመኖር በሌላ የታሪክ ምዕራፍ መድገም ይጠበቅብናል። በእነሱ ጀግንነት በኩራት መኮፈስ ሳይሆን፤ የድሉን መንፈስ ተውሶ በአንድነት ኖሮ፣ በሰውነት ተከባብሮ፣ ከልብ የመነጨ ይቅር ባይነት አንግሶ ሀገርን ከከፍታ ማማ ማድረስ ከዛሬው ትውልድ ይጠበቃል።
ሀገራችን የትናንቱን ዓድዋ ድል የሚመጥን ቁመና እንዲኖራት በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያው ቁመናዋም ትልቁን ድል መላበስ እንድትችል ሌት ተቀን መሥራት ፤ለዚህ የሚሆን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መፍጠር ያስፈልጋል።
እርግጥ ነው በዚህ ዘመን የሚያስወቅሱን በርካታ ችግሮች ቢኖሩንም፤ ትውልዱን ታሪክ ሠሪ የሚያደርጉት በርካታ የልማት ስኬቶች ስለመኖራቸው የሚታይ ሐቅ ነው። ለአብነት የአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ የሆነው የህዳሴ ግድብን መጥቀስ ይቻላል።
የዓባይ ጉዳይ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ሕልምና ቁጭት፤ የመሪዎች መሻት ነበር።በእኛ ትውልድ ግን ቁጭቱ ተሽሯል። በዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የህዳሴ ግድብን በራስ አቅም በመገንባት የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የመጀመሩ ብስራት ተደምጧል።በዚህ ትውልድ የተሠራው ይህ የልማት ውጤት ዓድዋን በልማት የደገመ ግዙፍ ታሪክ ነው።
ኢትዮጵያ የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ኢትዮጵያ ስንዴ ወደ ውጭ መላክ የመጀመሯ ብስራት መሰማቱ ሌላው ግዙፍ ታሪክ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‹‹በ2015 ዓ.ም ኢትዮጵያ በሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ወደ ውጭ ገበያ መላክ ትጀምራለች›› ሲሉ በብዙዎች ዘንድ እውን ስለመሆኑ ጥርጣሬን ያሳደረ ነበር።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ያሳካችው የስንዴ ኤክስፖርትን እዚህ ጋር ብናነሳ ፤በቀጣይ ሊያጎናጽፈን ከሚችለው ኢኮኖሚያዊ ነጻነት አንጻር ብዙ ሊያስብል የሚችል ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ስም በበጎ የሚቀይር ከመሆኑ ባሻገር፤ አፍሪካውያን በራሳቸው አቅም በምግብ ራስን የመቻል እምቅ አቅም እንዳላቸው ያስመሰከረ በጎ ጅምር ነው።
በሀገራችን ተስፋ ሰጪ የሆኑ የልማት ውጤቶች እየተመዘገቡ ስለመሆኑ ከላይ የጠቀስናቸው ማሳያዎች አፍ አውጥተው ይመሰክራሉ።እነዚህ ስኬቶች የአንድነት ውጤቶች፣ የትብብር መንፈስ ውላጆች የኛ ዘመን ዓድዋዎች ናቸው።
በአጠቃላይ የአያቶቻችንን ዓድዋ ስናከብር፤ የእኛን ዓድዋ ተሸንፈን መሆን የለበትም።በዚህ ዘመን በድህነት መረታታችን፣ በሰላም ማጣት መከበባችን፣ በኢኮኖሚ ተግዳሮት ውስጥ መሆናችን እና የሰውን ልጅ ሕይወት በምን ቸገረኝነት አደጋ ውስጥ መክተታችን ለዓድዋ የማንመጥን ያደርገናል።
የአያት፣ ቅድመ አያቶቻችን የታሪክ ጥላ መከተል ትልቅ አያደርግም።ስለዚህ ከዓድዋ የድል መንፈስን ብቻ ሳይሆን፤ የአንድነት ውል ማሰሪያ፤ የሰውነት ጥልቅ ምስጢርነትን በመዋስ በልማቱ አዲስ ታሪክ በመሥራት የኛን ዓድዋ እናዋልድ ።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም