የመጽሐፉ ፀሐፊ አቶ ብሩህ ዓለምነህ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ፍልስፍና ፩ እና ፪፤ እንዲሁም ባለፈው ዓመት መስከረም 2010 ዓ.ም ፡፡ ያሳተሙትን ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና››ን መጽሐፍ እንካችሁ ብለውናል፡፡
እንደ ማሳሰቢያ ይቆጠር! ይህ ሙያዊ አስተያየት ሳይሆን አስተውሎት ነው፡፡‹‹ፍልስፍና ፫›› ከቀደምቶቹ ‹‹ፍልስፍና ፩››እና ‹‹ፍልስፍና ፪›› ለየት የሚያደርገው ኢትዮጵያዊ ይዘት ባላቸው ሐሳቦች መሞላቱ ነው፡፡ይሄ የሆነበት ምክንያት ደግሞ መጽሐፉ የተዘጋጀው ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› መጽሐፍ ውስጥ ገዥ ከሆኑ ጽንሰ ሐሳቦች ውስጥ ሃይማኖት፣ታሪክና ዘመናዊነት ይገኙበታል፡፡
‹‹ፍልስፍና ፫›› መጽሐፍ በ148 ገፆች እና በስድስት ዋና ዋና ክፍሎች የቀረበ ሲሆን በይዘቶቹም በመጀመሪያው ክፍል ቅኔና ፍልስፍና መስተጋብር ነው፡፡በጣም ብዙ ሰዎች «የኢትዮጵያ ፍልስፍናና ፈላስፎች በዋነኛነት ቅኔ እና ባለቅኔዎች ናቸው» ብለው ይከራከራሉ፡፡የመጀመሪያው ክፍልም ይህንን የሚሞግት ነው። በሁለተኛው ክፍል ሃይማኖትና ዘመናዊነት፣ በሦስተኛውም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ፍልስፍና፣ በአራተኛው ክፍልም የተፈጥሮ ፍልስፍና፣ በአምስተኛውም ክፍል የሃይማኖት ፍልስፍና እና በመጨረሻውም በስድስተኛው ክፍል በሥነ ውበት ላይ ያጠነጠኑ ጉዳዮችን ያነሣል፡፡
ፀሐፊው በአንደኛው ክፍል መጀመሪያ ገፅ ላይ ‹‹ለመሆኑ ቅኔ ፍልስፍና መሆን ይችላል?›› በሚል ጥያቄ ይጀምራሉ፡፡ ይሄን ጥያቄ ለማንሳት መነሻ የሆናቸው በኢትዮጵያ ፍልስፍና መጽሐፋቸው ውስጥ እንደ ኢትዮጵያ ፍልስፍና የተተነተኑት የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት ፍልስፍናዎች ብቻ በመሆኑና የቅኔን ፍልስፍናነት እንደ ኢትዮጵያ ፍልስፍና ባለመዳሰሱ ምክንያት የቤተክርስቲያን ምሁራን ባነሱባቸው ቅሬታ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
መጽሐፉ በገፅ 10 ላይ ስለቅኔ ምንነትና ትርጉም ከመልዓከ አድማሱ ጀንበሬ መጽሐፍ በመዋስ እንዲህ ሲል ያስቀምጣል ‹‹ቅኔ አንድ ሰው ስለአንድ ነገር ወይም ድርጊት ያገኘውን ዕውቀት ወይም ምስጢር ምሣሌ መስሎ፣ ምስጢር ወስኖ፣ ቃላት መጥኖ፣ በአዲስ ግጥም የሚቀርብበት ድንገተኛ ድርሰት ነው፡፡›› ይለናል፡፡
ፀሐፊው ከላይ የተቀመጠውን የቅኔ ትርጉም
ከንባብ የተወለዱ ልሂቃን
በመንተራስ ስለቅኔ ፍልስፍና አለመሆን ያላቸውን አቋም በገፅ 11 ላይ እንዲህ ይሉናል ‹‹እኔ «ቅኔ ፍልስፍና መሆን አይችልም፤ የኢትዮጵያን ፍልስፍናም ከቅኔ ውስጥ ማግኘት አይቻልም፤ ቅኔን ወደ ፍልስፍና ማጠጋጋት ሳያስፈልግ በራሱ ውበት እንደ አንድ የሥነ ጽሑፍ ዘውግነት መታየት አለበት» ብለው ከሚከራከሩ ሰዎች ውስጥ ነኝ፡፡ ይሄ ማለት ግን በግጥም ውስጥ ምንም ዓይነት ፍልስፍናዊ ሐሳቦችን ማንሳት አይቻልም ማለት አይደለም፡፡ ፍልስፍናዊ ሐሳቦች በግጥምም፣ በልብ ወለድም፣ በስዕልም… ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ዋናው ነገር ፍልስፍናዊው ሐሳብ የሚቀርብበት መንገድና ቅርፅ ሳይሆን የሐሳቡ አመክኖያዊ ትስስርና ፅናት ነው፡፡›› …. ይሉንና ቅኔ ፍልስፍናን ሊያዋልድ የማይችልበትን ሁኔታ በመቀጠል ይናገራሉ ‹‹እንደ እውነቱ ከሆነ ቅኔያችን ፍልስፍናን ሊያዋልድ ያልቻለበት አንድ መሠረታዊ ምክንያት አለ ይኸውም ቅኔያችን የተለያዩና የተበታተኑ (ብዙ ጊዜም እርስ በርስ የሚጣረሱ) ሐሳቦችን መያዙ ነው፡፡›› ይሉናል፡፡
ፀሐፊውን የምላቸው ነገር ቢኖር ‹‹እውን ቅኔን በደንብ አጥንተውታልን??›› ብዬ እጠይቃቸዋለሁ››፡፡
ከላይ በገጽ 10 የቅኔን ትርጉምና ምንነት ከመልዓከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ተውሰው ሲያስቀምጡ ‹‹ቅኔ ስለአንድ ነገር ወይም ድርጊት ያገኘውን ዕውቀት ወይም ምሥጢር ምሳሌ መስሎ፣ ቃላት መጥኖ፣ በግጥም መልክ የሚያቀርብ ድንገተኛ ድርሠት መሆኑን›› ቢገልፁም ከታች ደግሞ ቅኔ ፍልስፍናዊ ሐሳብ የሚቀርብበት መንገድና ቅርፅ እንዳልሆነ በገፅ 12 ላይ ይገልፃሉ፡፡ግን ደግሞ ቅኔ እንዲህ መሆኑ ከፍልስፍና ያጠጋጋዋል እንጂ አያርቀውም ብዬ አስባለሁ፡፡
አንደኛ ነገር ቅኔ በግጥም ብቻ ሳይሆን በዝርውም ይገለፃል፡፡ ፀሐፊው ቅኔን በግጥም ብቻ ነው የሚያውቁት ብዬ እንድደመድም አድርጎኛል፡፡ ቅኔ በግጥም መልክ በድንገተኛነት ቢቀርብም ከጀርባው ግን ዕውቀትን ያዘለ ነው። ዕውቀት ደግሞ በምክንያትና በአስረጂዎች ትስስር የሚገኝ የመጨረሻ ግኝት ነው፡፡ ስለዚህ ቅኔ ፍልስፍናን ማዋለድ የማይችለው በቂ የሆነ አመክኖያዊ ትስስር የለውም የሚለው ድምዳሜ አሳማኝና አመክኖያዊ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ቅኔ ዕውቀት አለው ካልን፤ ዕውቀት ብለን ስንበይን ደግሞ በውስጡ አመክኖያዊ ትስስር ያለው በመሆኑ ነውና፡፡
ሌላው ፀሐፊው ‹‹ቅኔ የተለያዩና የተበታተኑ ሐሳቦችን (ብዙ ጊዜም እርስ በርስ የሚጣረሱ) በመያዙ›› ምክንያት ፍልስፍናን አያዋልድም ብለዋል፡፡ የተበታተኑ ሃሳቦች ፍልስፍና መሆን አይችሉም ያለው ማነው? ማነው ፍልስፍናን ገድቦ ያስቀመጠው? ሌላው ደግሞ ሁሉንም ቅኔ በአንድ ሙቀጫ መውቀጣቸው ሳያንሳቸው እዚህ ድምዳሜ ላይ ያደረሳቸውን አስረጂዎቻቸውን እንኳን አልዘረዘሩም፡፡ በዚህ ላይ ማስረጃዎችንና ምሣሌዎችን ቢያስቀምጡ ኖሮ ለድምዳሜአቸው ጥሩ ማስረጃ ይሆን ነበር፡፡
ከዚሁ ሃሳብ ሳንወጣ ፍልስፍና በጥበብ ሊገለፅ የማይችልበትን ምክንያት ሳያስቀምጡ ቅኔ በግጥም መልክ መቅረቡ ፍልስፍና አያስብለውም በሚል አጠቃለው አስቀምጠዋል፡፡ አደናጋሪው ነገር ፀሐፊው በገጽ 12 ላይ ይህንን ጉዳይ ሲያብራሩ ‹‹ቅኔ ከፍ ያሉ ፍልስፍናዊ ሐሳቦች ጭምር የሚንፀባረቅበት ቢሆንም ግጥም መሆኑ ግን ይጎትተዋል›› ይሉናል፡፡
ፀሐፊው ከዚህ አባባላቸው እንኳን የአመክኖያዊ መፋለስን እናገኝባቸዋለን። አንደኛ ነገር ቅኔ ከፍ ያሉ ፍልስፍናዎች የሚንፀባረቁበት ከሆነ ለምን ፍልስፍና አይሆንም?? ሁለተኛ ነገር ቅኔ በግጥም ብቻ አይገለጽምና የአባባሉን ተፋልሶ ማየት ይቻላል፡፡ ሶስተኛ ቅኔ በግጥም መገለፁ ፍልስፍናዊ ሃሳቦቹ ይጎትተዋል ብለን አምነን ብንቀበል እንኳን ፍልስፍናነቱን አይፍቀውም፡፡ መጎተቱ የፍልስፍናነቱን መንቀርፈፍ የሚገልጽበትን መንገድ እንጂ ፍልስፍና አለመሆኑን የሚያመለክት አይደለም።
በተጨማሪም ግጥም በባህሪው የተበታተነ ሃሳብ ሳይሆን አንድን ሃሳብ በአጭር ስንኞች የሚገለጽበት ጥበብ ነው፡፡ ፍልስፍናዊ ሃሳቦች በግጥም መልክ መቅረባቸው ምንድን ነው እንዲጎተት የሚያደርገው? ቅኔ በግጥም መቅረቡ ፍልስፍናነቱን አይደመስሰውም። ዋናው ጉዳይ በቅኔ ውስጥ የተነሣው ከፍ ያለው የፍልስፍና ሃሳብ መሆኑ ነው። ፍልስፍና ወደእውነት ምርምር መሄጃ መንገድ እንደመሆኑ በቅኔ ውስጥም ለምርምር የሚሆኑ ጥያቄዎችን መጫርና መልሶቹን መፈለግ የሚሻ ነው። ብዙ ፈላስፋዎችም ላነሱት ጥያቄዎች ሁሉ መልስ አላገኙም፡፡ እስካሁንም ጥያቄ ሆነው መልስ ያልተገኘላቸው ብዙ ፍልስፍናዊ ሃሳቦች ሆነው እስከዛሬ የተሻገሩ አሉና፡፡ ፀሐፊው ለድምዳሜአቸው ያቀረቡት ሃሳብ የግላቸውን እንጂ ሳይንሳዊ ማስረጃን ወይም ወጥ የሆነ ጥናትን አቅርበውና አስደግፈው አይደለም። ለዚህ ነው ከላይ ‹‹እውን ፀሐፊው ቅኔን በወጉ አጥንተውታል??›› ብዬ እንድጠይቅ ያደረገኝ፡፡
በመጨረሻም አንድ ያስገረመኝ ድምዳሜን ልጥቀስና የዛሬውን ዳሠሣ በዚሁ ላጠቃልል። ፀሐፊው በዚሁ በገጽ 12 ላይ የቅኔን በአንድ ሃሳብ ላይ ያለመፅናትን ጉዳይ ሲያነሱ፡-
‹‹ግጥም አንድ ሐሳብ ላይ ብቻ የሙጥኝ ማለት አይችልም፤ ስለማይፀና አይጠልቅም። እንደገጣሚው ተለዋዋጭ ስሜት በተለያየ ጊዜ የሚያነሳቸውም ሐሳቦች የተለያዩ ናቸው። ገጣሚ አንድን ሐሳብ ብቻ በጥልቀት እየፈተሸ መሄድ አይችልም፡፡ ይሄን ካደረገ ፈላስፋ ይሆናል፡፡ ገጣሚ ነጋ ጠባ አንድ ሐሳብ ላይ ብቻ የሚብሠለሠል ከሆነ ወደፈላስፋነት ይቀየራል፡፡›› ይሉናል፡፡
ነገር ግን የግጥምን አብይ ባህሪያት ስናጠና ግጥም ቁጥብነት እና እምቅነት፣ ምናባዊነት፣ ተጨባጭነት፣ እና ሙዚቃዊነት ባህሪዎች አሉት፡፡ ግጥም አንድ ሃሳብ ላይ ብቻ የሙጥኝ አይልም፣ አይጸናም አይጠልቅም ብለው መደምደማቸው ስህተት ይመስለኛል፡፡ በዚሁ ሃሳባቸው ‹‹ገጣሚ አንድን ሃሳብ በጥልቀት እየፈተሸ ከሄደ ፈላስፋ ይሆናል›› ይሉናል፡፡
ነገር ግን ግጥም በገጣሚው እንደሚወሰን ሁሉ ገጣሚ ከገጣሚ ደግሞ ይለያያል፡፡ ሁሉም ገጣሚ አንድ ነገር ላይ አይፀናም ብሎ ማጠቃለል ሁሉንም ገጣሚ አውቆ መጨረስ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ አንድ ገጣሚ በተለያዩና ተከታታይነት ባላቸው ግጥሞች አንድን ሃሳብ በፅናት የሙጥኝ ብሎ ሊያነሳ፣ ሊያጠይቅ፣ ሊሞግት ይችላል፡፡ በመሆኑም በዚህ አባባላቸው ምክንያታዊነታቸውን ጎዶሎ ያደርገዋል፡፡ለዚህ ሳምንት ይህንኑ ‹‹ፍልስፍና ፫›› መጽሐፍን ታነቡት ዘንድ እጋብዛለን፡፡ ሰላም !
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2011
አብርሃም ተወልደ