አዲስ አበባ፦ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ የግል አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ሚናቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በተለያዩ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙ የግል አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ ምክክር አካሂዷል።
በመድረኩ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ የግል አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ሚና የጎላ መሆን አለበት።
ኤጀንሲዎቹ ወጣቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያለውን ክህሎት እንዲያሳድግ በተሻለ መንገድ ከተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር መስራትና በርካቶች የስራ ዕድል እንዲያገኙ ማገዝ አለባቸው ብለዋል።
በተጨማሪም ኤጀንሲዎች ከሚገባቸው በላይ ክፍያ ባለመጠየቅ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ሰላማዊ እንዲሆን እንዲሁም ሰራተኞች መብታቸውንና ግዴታቸውን አውቀው በሰሩት ልክ ገቢ እንዲያገኙ ማድረግ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉ የገለጹት አቶ ንጉሱ፤ መንግሥትም ችግሮቹን ለመፍታት ከኤጀንሲዎች ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ምቹ የሥራ አካባቢዎችን መፍጠር እንዲቻል መንግስት አዳዲስ ደንቦችንና መመሪያዎችን በስራ ላይ እንደሚያውልም ተናግረዋል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍም ተመሳሳይ የውይይት መድረኮች ቀጣይነት ባለው መልኩ ማካሔድ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
በመድረኩ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ስራ ስምሪትና ማስፋፊያ ኃላፊ አቶ ደጀኔ በቀለ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የስራአጥ ምጣኔው ስምንት በመቶ እንደሆነ ገልፀው፤ በከተማዎች የሚታየው የስራ አጥ ቁጥር ከገጠር ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር የሥራ አጥ ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተናግረው፤ የግል አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሴቶችን ስራ አጥነት በመቀነስ ረገድ ተጨማሪ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
በየጊዜው ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ወጣቶች በሥራ አጥነት ችግር ላይ ሲወድቁ እንደሚስተዋል አንስተው፤ ኤጀንሲዎች ከተቋማት ጋር በትብብር በመስራት የችግሩን ግዝፈት የሚመጥን ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ከተማና አማራ ክልል ከፍተኛውን የኤጀንሲዎች ቁጥር እንደሚይዙ የተገለፀ ሲሆን፤ በዝቅተኛ ደረጃ ሀረር እና ሶማሌ ክልሎች ላይ በንጽጽር በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ኤጀንሲዎች እንደሚንቀሳቀሱ አስታውቀዋል።
በቀጣይም ኤጀንሲዎች የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት ከሰራተኞችና ከሌሎች አካላት ጋር በጋራ ለመስራት የሚረዳ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባቸው ተጠቁሟል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ መሻሻል የሚገባቸው የሕግ ማዕቀፎችን በአጠቃላይ ፈትሾ ማሻሻል፣ ከኤጀንሲ አደረጃጀቶች ጋር በጋራ የሚሰራበትና ቋሚ ግንኙነት እየተደረገ ስራዎች የሚገመገሙበትን ሥርዓቶች መዘርጋት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸው ተገልጿል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የስራ አጥ ቁጥር ችግሩን ለመቀነስ እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ኤጀንሲዎችን ጭምር በማስተባበር ለ14 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር አቅዷል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ10 አመት ዕቅዱን ተግባራዊ እያደረገ ሲሆን፤ እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ ለ20 ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየሰራ እንደሆነ አስታውቋል።
በምክክር መድረኩም የክልል የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ከተለያዩ የግል አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የተወጣጡ ተወካዮች ተገኝተዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም