ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና የልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ቢሮዎች ያሉባት ነች። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ለማይስ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። የማይስ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፉ በዋናነት የጉባኤ፣ የአውደ ርእይና ባዛር፣ የንግድ ውይይትና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ዋና ማጠንጠኛው በመሆኑ አገሪቱ ምጣኔ ሃብቷን እንድታሳድግ፣ ተመራጭ የስብሰባ ቱሪዝም ከተማ እንድትሆንና ያንን ተከትሎ ዜጎች በሚፈጠረው የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልዩ እድል ይሰጣል።
መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት ተከትሎም የማይስ ኢትዮጵያ የኮንቬንሽን ቢሮ ከሁለት አመት በፊት በይፋ ተመስርቷል:: ይህ ቢሮም ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፍ ጉባኤዎች እና ሁነቶች የቱሪዝም ተጠቃሚ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበታል።
የዝግጅት ክፍላችን ባሳለፍነው ሳምንት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎችና የሥራ አስፈፃሚ ጉባኤ በመዲናዋ አዲስ አበባ መካሄዱን ተከትሎ “የስብሰባ ቱሪዝምና የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታን” የሚያሳይ ዳሰሳ ማድረጉ ይታወሳል። በዛሬው አትማችን ደግሞ “የማይስ ቱሪዝምን የሚመራው የኮንቬንሽን ቢሮ ከተቋቋመ ወዲህ የተሰሩ ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶች ምን ምን ናቸው?” በሚል በቱሪዝም ሚኒስቴር የማይስ ቱሪዝም የኮንቬንሽን ቢሮ የሽያጭ ዴስክ ማኔጀር ከሆኑት ከአቶ ብዙዓለም ጌቱ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ!!
አዲስ ዘመን፦ በቱሪዝም ሚኒስቴር ስር የኮንቬንሽን ቢሮ ከሁለት ዓመት በፊት ተቋቁሟል። ይህንን ቢሮ ለማዋቀር ያስፈለገበት ዓላማና ግብ ምን ነው?
አቶ ብዙዓለም፦ የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮን ማቋቋም ያስፈለገበት ዋንኛ ምክንያት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ስብሰባ፣ ኮንፍረንስ፣ ማበረታቻ ሁነቶች ተጠቃሚ እንድትሆን ታሳቢ በማድረግ ነው። አገሪቱ በዘርፉ ያላትን አቅም እንድትጠቀም እና የማይስ ቱሪዝም ፅንሰ ሃሳብን ለማስረፅ ቢሮው አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ካስተናገደችበት ጊዜ አንስቶ ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ መድረኮችን ስታዘጋጅ ቆይታለች። ሆኖም የስብሰባ ቱሪዝምን በተደራጀ መልኩ ማዋቀርና በትኩረት መስራት ስላልተቻለ ቀደም ሲል የተዘጋጁትም ሆኑ አዳዲስ ሁነቶች ወደ ሌሎች አገራት እንዲሄዱ ምክንያት ነበር። አሁን ይህንን ክፍተት ለመቅረፍ በማሰብ በተደራጀ መልኩ እየተሰራ ነው።
ቢሮው ኢትዮጵያ የንግድ ሁነቶች መዳረሻ እንድትሆን የልማት ስራዎችን በቀዳሚነት ሲሰራ ሌላው የኮንቬንሽን ማእከላትን በተመሳሳይ በማልማትና የገበያ ስራ በመስራት አገሪቱ በገቢ ተጠቃሚ እንድትሆን ይሰራል።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ በማይስ ቱሪዝም አቅም እንዳላት ለማሳየት በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ብዙዓለም፦ ኢትዮጵያ የንግድ ሁነቶች ወይንም የኮንፍረንስ መዳረሻ መሆኗን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁነቶችን የሚገበዩ “International event buyers” የሚገኙባቸው ታላላቅ ኤግዚቢሽኖች፣ የንግድ ትርኢቶች (በስፔን ባርሴሎና የሚካሄደው አይ ቢቲ ኤም፤ በጀርመን ፈራንክፈርት አይ ኤም ኤክስ፤ በላስ ቬጋስ “ቬጋስ” የተሰኘ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የሚደረጉ) የንግድ ሁነቶች አሉ። በእነዚህ መሰል ሁነቶች ላይ በመገኘት ኢትዮጵያ ያላትን የማይስ ቱሪዝም አቅምና ሁነት የማሰናዳት ብቃት ካስተዋወቅን በኋላ በተለያዩ የጨረታ ዘዴዎች በመግባት አሸንፈን ጥቅሙን ወደ አገራችን ለማምጣት አቅደን እየሰራን ነው። የኮንቬንሽን ቢሮው እየሰራ ያለውና ለመስራት ያሰበውም በዚህ መንገድ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ቢሮው ከተቋቋመ ጀምሮ እስካሁን የሰራችሁት ስራና ያስመዘገባችሁት ውጤት ምንድን ነው?
አቶ ብዙዓለም፦ የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ በይፋ የተመሰረተበት ጊዜ የኮቪድ ወረርሽኝ የተከሰተበት ወቅት ነበር። በዚህ ምክንያት ዓለም አቀፍ ሁነቶች በአዲስ እይታ እና አቅጣጫ እየተካሄዱ ነበር። በተለይ በዲጂታል ሚዲያ “virtual meeting” የሚካሄድበት ነበር። በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ሊካሄዱ የነበሩ ብዙ ሁነቶችና ስብሰባዎች ተሰርዘዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ቢሮውን ማደራጀት፣ ብቁ ባለሙያ ማፍራትና በአፍሪካ ውስጥ ጥቂት የኮንቬንሽን ቢሮ ያላቸው አገራት ጋር ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችል አቅም መገንባት ላይ ትኩረታችንን አድርገን ስንሰራ ቆይተናል። በተለይ ባለሙያዎችን ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የማሰልጠን ስራዎችን ሰርተናል። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥም ለመስራት የቻልነው ሰራተኞችን ማብቃት ነው።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ትልቅ አቅም እንዳላት ቢታወቅም በአዲስ አበባ ምን ያህል ብቁ ሆቴሎች እንዳሉና ሁነት ስብሰባዎችን ከማዘጋጀት አንፃር ያላቸውን አቅም የመለየት ስራን እያከናወንን ነው። ሌላው በክልል ከተሞች (በሁለተኛ ከተማነት) ብቁ የሆኑትን በተመሳሳይ እየለየን ነው። እስካሁን ድረስ “ለማይስ ቱሪዝም” ብቁ ናቸው ብለን ከለየናቸው ውስጥ ሀዋሳ፣ ቢሾፍቱ እንዲሁም ባህርዳር ይገኙበታል።
በተጨማሪ የኮቪድ ወረርሽኝ ስጋት መሆኑ ሲያበቃ በኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄዱ ለነበሩ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ድጋፍ አድርገናል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ድጋፍ ካደረግንላቸው ጉባኤዎች መካከል 17ተኛው የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ፣ ከሰሞኑ የተካሄደው የአፍሪካ ህብረትና የዓለም ሜትሮሎጂ ኮንፍረንስ ይገኙበታል። በአገር ውስጥም በተመሳሳይ የተካሄዱ ስብሰባዎችን እና መሰል የማይስ ዘርፎችን ደገፈናል።
አዲስ ዘመን፦ ተግባራችሁን በምታከናውኑበት ወቅት ያጋጠማችሁ እክል አሊያም ፈተናዎች ምንድን ናቸው?
አቶ ብዙዓለም፦ ቀደም ሲል ካነሳሁት የኮቪድ ወረርሽኝ ባሻገር በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶች አዳዲስ ሁነቶችን በአገሪቱ ለማቀድና ለማምጣት ሁኔታዎችን ከባድ አድርገውት ነበር። በአንድ አገር ውስጥ ሰላማዊ ሁኔታ ከሌለ ይህን ማድረግ አስቸጋሪ ነው። በዚህ ምክንያት የተቀዛቀዘ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ይሁን እንጂ ቀደም ብለው ማገገም የጀመሩት የቱሪዝም ዘርፉና የማይስ ንኡስ ዘርፍ ስለሆኑ ወደፊት ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች መኖራቸውን የሚያመላክት ነው።
አዲስ ዘመን፦ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ወደ አገር ውስጥ ለማምጣት ከተቋሙ ጥረት ባሻገር እውቀቱና ልምዱ ካላቸው ግለሰብ ጎትጓቾች ጋር መስራትን ይጠይቃል። በዚህ ዙሪያ የእናንተ ልምድ ምን ይመስላል?
አቶ ብዙዓለም፦ የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ እንደ ጎትጓች (lobbyist) ሆኖ ነው እየሰራ ያለው። የቱሪዝም ሚኒስትር ኮንቬንሽን ቢሮውን ቢያቋቁመም ሁነት አይደግስም። ነገር ግን ሁነቶችን ተጫርቶ ያመጣል። ከዚህ በተጨማሪ የዓለም አቀፍ ሙያ ማህበራት አባል የሆኑ ኢትዮጵያዊ ምሁራን እንዲሁም ኤክስፐርቶችን አምባሳደር በማድረግ ስብሰባዎች ሲኖሩ ወደ ኢትዮጵያ እንዲያመጡና ጨረታውን እንዲያግዙ ስትራቴጂ ቀርጸን፣ ሰነድ አዘጋጅተን ዝግጅታችንን ጨርሰናል።
አዲስ ዘመን፦ ቀደም ሲል የማይስ ቱሪዝምን ለማዘጋጀት ብቁ ናቸው ያላችኋቸውን ሁለተኛ ከተሞች የመለየት ስራ እንደሰራችሁ አንስተህ ነበር። እነዚህ ከተሞች ተመራጭ ለመሆን ምን አይነት መስፈርት ማሟላት አለባቸው?
አቶ ብዙዓለም፦ ሁለተኛ ከተማ ብለን የምንጠራቸው የማይስ መዳረሻዎች የተመረጡበት ምክንያት እና ከግምት ውስጥ የገባው መስፈርት በሆስፒታሊቲ ዘርፍ የሚያገለግሉ ሆቴሎች ያላቸው ጥራት፣ የአልጋ ብዛት፣ የጉባኤ ማከናወኛ አዳራሽና ማዕከላት ጥራትና ብዛት እንዲሁም ከቅድመ ሁነትና ድህረ ሁነት ዓለም አቀፍ ተሰብሳቢዎች ሊጎበኙዋቸው የሚችሏቸው የመስህብ ስፍራዎችና መዳረሻዎች መኖር አለመኖራቸው እንደ መስፈርት ተወስደዋል።
አዲስ ዘመን፦ በቅርቡ 36ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በዚህ ጉባኤ ላይ የኮንቬንሽን ቢሮው አገሪቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ምን ተግባራትን አከናወኗል? ምን ውጤትስ ተመዝግቧል?
አቶ ብዙዓለም፦ እንደ ኮንቬንሽን ቢሮ ሳይሆን እንደ ቱሪዝም ሚኒስቴር ከህብረቱ ጉባኤ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ያደርጋሉ የተባሉ ሥራዎች ተከናውነዋል። ከዚህ ውስጥ ለተሰብሳቢዎቹ የኢትዮጵያን ቡና የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል። በአዲስ አበባ የሚገኙ አዳዲስ የመዳረሻ ስፍራዎችን ከማስተዋወቅ ባሻገር በጉባኤው ላይ የሚሳተፉ አንዳንድ አካላት ቆይታቸውን አራዝመው የመስህብ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ለማስቻል መስሪያ ቤታችን በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል። ይህ ጉባኤ በመሪዎች ደረጃ የሚካሄድ እንደመሆኑ በፈለግነው መንገድ ገብተን ያቀድናቸውን ሃሳቦች ማከናወን አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ በቀጣይ በሚካሄዱ መሰል ሁነቶች ላይ አዳዲስ ሃሳቦችን በማምጣት ለመስራት እናስባለን።
አዲስ ዘመን፦ የአፍሪካ ህብረትን ጭምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ሲኖሩ የጎንዮሽ ሁነት ማዘጋጀትና ከዚያም ተጨማሪ ጥቅም ማግኘትን በተመለከተስ?
አቶ ብዙዓለም፦ ለዓለም አቀፍ ስብሰባ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡትን እንግዶች በአግባቡ ማስተናገድ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ትልቁ ነገር እንግዳ አቀባበልና መስተንግዶ ነው። ነገር ግን የጎንዮሽ ሁነቶችን ማዘጋጀት ላይ መሰራት እንዳለበትና ለዚያም መዘጋጀት እንደሚኖርብን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፦ በአጭርና በረጅም ጊዜ እቅድ ቢሮው ምን ለማሳካት አቅዶ እየሰራ እንደሆነ ቢነግሩን?
አቶ ብዙዓለም፦ በአጭር ጊዜ መሰራት አለበት ብዬ የማምነው ዘርፉን ማጠናከር ላይ ነው። በአሁኑ ሰዓት እያከናወንናቸው ያሉ ዓለም አቀፍ ተሳትፎዎች አሉ። በእነዚህ ሁነቶች ላይ ቢሮው ብቻ ሳይሆን ሌሎች የግል አዘጋጆችንም አሳትፈን ይዘን እንሄዳለን። በልማት ሥራው ላይ ደግሞ አገር ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላትን ማስተሳሰር ላይ ለመስራት አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው። በተጨማሪ በግል ሁነት የሚያዘጋጁ አካላትን አቅም የመገንባት፣ አቅም ያላቸውን እውቅና ሰጥቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማስቻል፣ ሆቴሎችን፣ የምግብና መጠጥ አገልግሎት የሚሰጡ የባህል አዳራሾች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የመደገፍ ስራዎችን እናከናውናለን።
በረጅም ጊዜ እቅድ ደግሞ አዲስ አበባን ተመራጭ “የማይስ” ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እንሰራለን። በአዲስ አበባ ትልልቅ የኮንፍረንስ ማእከላት አሉ። እነዚህን ማእከላት ለስብሰባ የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችን ከመያዝ አንፃር አብዛኞቹ ክፍተት የሚታይባቸው ናቸው። ይህንን ክፍተት በመሙላት የተሻለ ስራ ለመስራት በቅንጅት ለመንቀሳቀስ እናስባለን። በተጨማሪ ትልልቅ የኮንቬንሽን፣ የስብሰባና የአውደ ርእይ ማእከላት ስለሚያስፈልጉ እነዚህ እንዲገነቡ የበኩላችንን እንሰራለን። የተጀመሩትም በቶሎ እንዲጠናቀቁ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንሰራለን።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን የካቲት 19 ቀን 2015 ዓ.ም