ከተወለዱባት ሀዲያ አካባቢ ከሚገኝ የገበሬዎች መንደር የተገኙት ዶክተር መለሰ ማሪዮ በልጅነታቸው የእውቀት ቀንድ የተባሉ ጎበዝ ተማሪ ነበሩ። በወቅቱ 12ኛ ክፍልን ጨርሶ ዩኒቨርሲቲ መግባት እንደ ብርቅ የሚታይበት ጊዜ ስለነበር አብረዋቸው ከተፈተኑት ሶስት መቶ ሀምሳ ተማሪዎች ሁለቱ ብቻ ሲያልፉ እርሳቸው አንዱ ነበሩ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ክፍል በባዮሎጂ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በእፅዋት ሳይንስ ጨረሱ። 3ኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግሮ ባዮ ዳይቨርሲቲ በሚባል የትምህርት ዘርፍ ጨረሱ።
ሥራ የጀመሩት በሁለተኛ ደረጃ መምህርነት በሀላባ በሚገኝ ህፃናት አምባ ትምህርት ቤት ነበር። ለስምንት ዓመታት አገልግለዋል። በመቀጠል ዲላ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመምህርነትና ተመራማሪ በመሆን፤ በተለያዩ የዩኒቨርሲቲው ኃላፊነት ቦታ ላይ ከ15 ዓመታት በላይ አገልግለዋል። ከዛም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በነበሩበት ወቅት ተቋማት በኤክስፐርቶች ይመሩ በሚል ሀሳብ የብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በመሆን ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል፤ አሁንም እያገለገሉ ይገኛሉ።
በዩኒቨርሲቲና በብዘሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ውስጥ በርካታ ከብዝሃ ህይወት ጋር የተገናኙ ምርምሮችን ከማድረጋቸው በሻገር፤ አሁንም በበጎ ፈቃደኝነት ኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተለያዩ ሙያዊ ድጋፎችን ያደርጋሉ። ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉ የ3ተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ያማክራሉ።
በተጨማሪም የዲላ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ፤ የጉለሌ ቦታኒካል ጋርደን ቦርድ፤ የግብርና ሴክሬተርያት ፅህፈት ቤት የቦርድ አባል፤ የዓለም አቀፉ የብዝሃ ህይወት ስምምነት የኢትዮጵያ ፎካል ፐርሰን ሆነው አገልግለዋል፤ ስምምነቱን ከፈረሙት 196 አገራት አፍሪካን በመወከል በዓለም ካሉ 10 የቢሮ አባላት ውስጥ አንዱ በመሆን የአፍሪካ የብዝሃ ህይወት ችግሮችን በማንሳት የሚሰሩ ሰው ሆነው ከአራት ዓመት በፊት ጀምሮ እያገለገሉ ይገኛሉ። እነኚህን ተመራማሪ በብዝሃ ህይወት ዘርፍ እና አጠቃላይ ስላላቸው ተሞክሮና የተለያዩ የህይወት ልምዳቸው በዚህ መልኩ አካፍለውናል። መልካም ቆይታ።
አዲስ ዘመን፤- በርካታ ምርምሮችን አድርገዋልና ምን ምን አይነት አካባቢዎች የነካኩ ምርምሮችን ሰርተዋል?
ዶክተር መለሰ፡- ምርመር ካደረኩባቸው ዘርፎች አንዱ መድኃኒታዊ እጽዋትን ፈዋሽነት በጥናት ማረጋገጥ አንዱ ነው። በአብዛኛው ጥብቅ ደኖች ውስጥ ያሉ መድሀኒቶችን የማጥናት ስራ ይሰራል። በጥናቱ መሠረት ከ100 ሺህ በላይ መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋት በአካባቢው እንደሚገኙም ተረጋግጧል።
እንደነ ቻይና ያሉ በኢኮኖሚ የበለጸጉ አገራትም ባሕላዊ ሕክምናን ከዘመናዊው ጋር አጣምረው በሚገባ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። የአሜሪካ ብሔራዊ የጤና ተቋምም የቻይናን ባሕላዊ መድኃኒት ውጤታማነቱን እና ሁነኛ አማራጭ መድኃኒት መሆኑን አረጋግጧል፤ ጥቅም ላይ እንዲውሉም ፈቅዷል። በዚህ ወቅትም የቻይና ባሕላዊ መድኃኒት ፈዋሽነቱ ውጤታማ በመሆኑ በርካታ ተጠቃሚዎች አሉት። ለአገሪቱ ዜጎችም እንደ አንድ ሙያ ተደርጎ ተወስዷል።
በእኛም አገር ባሕላዊ መድኃኒት የጥንት አያቶቻችን ያወረሱን የአገር በቀል ዕውቀት ነው። ይህ ውርስ በአግባቡ ተጠብቆ ባለመቆየቱ እጽዋቱ የሚሰጡትን አገልግሎት በአግባቡ መጠቀም እንዳንችል አድርጎናል። የአገር በቀል እውቀቶችን ትሩፋት ለመካፈልና ለቀጣይ ለትውልድ ለማስተላለፍ፣ በመጥፋት ላይ ያሉ መድኃኒታዊ እጽዋትን ማልማት፣ አጠቃቀማቸውንና ያላቸውን ፋይዳም ከአባቶች በመጠየቅ ወቅቱ እና የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ በሚፈቅደው መልኩ በዘመናዊ መንገድ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ሌሎች በመጥፋት ላይ ስላሉ ደኖች፤ ስለ አዝእርትና ሆርቲ ካልቸር፤ ዝርያቸው እየጠፉ ስላሉ እንስሳትና ሌሎች ጥናቶችን በየጊዜው ስናደርግ ቆይተናል።
በአገራችን አንደ ባህል ሆኖ ጓሮ አካባቢ ዳማከሴና ጤና አዳምን መትከል የተለመደ ነው። ብርድ ብርድ የሚል ስሜት ሲሰማ ዳማከሴን አሽቶ ከቡና ጋር መጠጣት ማሽተትም ለምች ፍቱን መድኃኒት ነው ይባላል። ለራስ ህመም ጠንከር አድርጎ ማሰር፣ ለጉንፋን ዝንጅብል በማር፣ ለሆድ ድርቀት ተልባን በጥብጦ መጠጣት ብዙ ኢትዮጵያውያን ለራሳቸው ሆነ ለወዳጆቻቸው ፈውስ ብለው የሚመክሯቸው መሆናቸው የባህል ህክምናን እንደፈውስ አድርጎ የመቀበል ዝንባሌያችን ከፍ ያለ መሆኑን ያመለክታል። በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በከተማም በሽታ ባስ ካላለ ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ የተለመደ አይደለም፤ ቤት ውስጥ የተገኘውን በሙሉ ተጠቅሞ ፈውስን ፍለጋ ተቀዳሚ ምርጫችን እናደርገዋለን።
ባህላዊ ህክምና በሥሩ በርካታ የባህል መድኃኒት ዘርፎችን ያቅፋል። በተለይ ከባህላዊ መድኃኒት ዘርፍ ውስጥ ባህላዊ የዕፅዋት መድኃኒት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል። ባህላዊ መድኃኒት ከጥንት ጀምሮ ዛሬ ድረስ በተለያዩ ማህበረሰቦች ዘንድ በህክምናው መስክ ከፍተኛ የሆነ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሀገረ ሰባዊ የዕውቀት ዘርፍ ነው። ይህን ሀገረሰባዊ የእውቀት ዘርፍ እንዲያድግ ደግሞ ተፈጥሮ የለገሰችውን መድኃኒታማ ቅጠላ ቅጠልና ሥራ ሥር መንከባከብ የግድ ነው።
ኢትዮጵያ ከ6500 እስከ 7500 የአበባ ዕፅዋት አላት ተብሎ ይገመታል። ከዚህ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመድኃኒትነት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ጥናቶች ያመለክታሉ። በአብዛኛው ከእነዚህ መድኃኒታማ ተክሎች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ዱር በቀል ናቸው። እኛ አገር ጥናቶች ዝም ብለው እንዲታተሙ ይደረጋል፤ ይህ ደግሞ የማህበረሰብ ሀብትን አሳልፎ እንደመስጠት ነው። ስለዚህ ያለንን የምርምር አቅም ወደ ፋብሪካ ምርትነት በመቀየር ውጤታማ መሆን አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ብዝሃ ህይወት ምንድን ነው?
ዶክተር መለሰ፡- ብዝሃ ህይወት ማለት በመሬት ላይ ያሉ ሁሉም ስነ-ህይወታዊ ሀብቶች፣ እፅዋት፣ እንስሳትና ደቂቅ አካላት እንዲሁም በውስጣቸው የያዟቸው ዘረ- መሎችና እነዚሁ የሚፈጥሯቸውን ውህዶች የሚያካትት ነው። በመሆኑም ብዝሃ ህይወት በዓለም ላይ የ ህያዋን ዝርያዎችን ያካተቱ ዛፎች፣ የሣር ዝርያዎች፣ ቁጥቋጦዎች፣ በራሪ አዕዋፋት፣ ባክቴሪያዎች፣ ትላትሎች፣ ተሣቢና ተራማጅ እንስሳት፣ በውሃ ውስጥ የሚገኙ ፍጥረታትን ጨምሮ የሁሉም ህይወት ያላቸው አካላት ስብስብን ያካተተ የወል መጠሪያ ነው።
ብዝሃ ህይወት ለዘላቂ የህይወት ቀጣይነት ብቸኛው መሰረት ነው። የእዚህ ህይወታዊ ሀብት ስርጭት በዓለም ዙሪያ ተመሣሣይ እንዳልሆነ የሚታወቅ ሲሆን በብዝሀ ህይወት ሀብታቸው ከታወቁት ውስን አገራት መካከል አንዷ አገራችን ኢትዮጵያ ናት። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው የብዝሃ ህይወት ሀብት የመመናመን አደጋ የተጋረጠበት በመሆኑ አብዛኛዎቹ የአገሪቱ ክፍል የብዝሀ ህይወት ሀብት ጥበቃ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገባ የተለዩ የዓለማችን አካባቢዎች አንዷ እንደሆነች የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታል።
አገራችን በሰብል ጄኔቲክ ሀብት ከ12 አገሮች አንዷ ስትሆን፤ በደን ብዝሀ ህይወት ሃብቷ ደግሞ ከ25 አገሮች አንዷ በመሆን ትመደባለች። ኢትዮጵያ ውስጥ በመጀመርያ ተገኝተው የመጀመሪያው የጀኔቲክ ማእከል ካደርግዋት የሰብል ምግብ እፅዋት ዝሪያዎች ውስጥ ጤፍ፣ ኑግ ሰናፍጭ፣ እንስሳትና ቡና ሲሆኑ፤ ከሌላ አገር ገብተው 2ኛ የጀኔቲክ ማእከል ያደረግዋት የምግብ ሰብሎች ደግሞ ዳጉሳ፣ ምስር ፣ ተልባ፣ ገብስ እና ስንዴ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ደቂቀ አካላት የምንላቸው ምንድን ናቸው?
ዶክተር መለሰ፡– ደቂቀ አካላት (ማይክሮ ኦርጋኒዝምስ/ማይክሮብስ) አጉልቶ በሚያሳይ መነጽር ካልሆነ በዓይን የማይታዩ የፍጥረት አካላት ናቸው። እነዚህ አካላት ቫይረስ፣ ባክቴሪያ፣ ፈንገስ፣ ማይክሮ አልጌና ፕሮቶዝዋ ይባላሉ። ከሃይማኖታዊ ውጭ በሳይንሳዊ መንገድ ካየን ዓለም ገና ስትፈጠር የነበሩ የመጀመርያው ፍጥረታት ደቂቀ አካላት ናቸው። ይህም በመሆኑ ኦክስጅንና ፎቶሲንተሲስን ለዓለም አበርክተዋል። እንዲሁም ካርቦንዳይ ኦክሳይድን የሚያመጡ ናቸው። እንዳው በአጠቃላይ ለቀጣዩም የፍጥረት ዓይነት መነሻ የሆኑ ነገሮችን ያመቻቹ፣ ለእንስሳትም ሆነ ለሰው የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ያለስስት በመስጠት ሕይወት እንድትቀጥል የሚያደርጉ
ናቸው። እኛ የምንመገበውን ምግብ ጥርሳችን በግርድፉ ከፈጨው በኋላ ወደ አንጀታችን ይገባል። አንጀታችን ውስጥ በግርድፉ የገባውን እህል አድቅቀውና አዋህደው እንዲሠራጭ የሚያደርጉት ደግሞ ሆዳችን ውስጥ ያሉት ደቂቀ አካላት (ማይክሮ ኦርጋኒዝምስ) ናቸው።
በምግባችን እርሾን ይሠራሉ። እንጀራ ቢጋገር፣ ዳቦ ቢደፋ፣ ጠላ ቢጠመቅ ወተት ቢረጋ ዝርያቸው ይለያይ እንጂ ይህን የሚያደርጉት ደቂቀ አካላት ናቸው። ስለዚህ ከእኛ ጋር ይኖራሉ፣ እኛን ያግዛሉ። ከዚህም ሌላ ከአፈር ውስጥ ያለውን ንጥረ ነገር እየሰባበሩና እየመጠኑ በመስጠት እፀዋት እንዲያድጉ እንዲሁም እንስሳት ሆድ አንጀት ውስጥ ያለውን የሚበላ ነገር እንዲብላላ በማድረግ ረገድም ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። እነዚህ ደቂቀ አካላት ከተፈጠሩ ከሁለት ቢሊዮን ዓመታት በኋላ ሌሎች ሕይወት ያላቸው እንደመጡ ሳይንስ ያስረዳል።
ደቂቅ አካላት ቁጥራቸውን መግለፅ ይከብዳል። በአንድ ትንሽ የሻይ ማንኪያ አፈር ውስጥ እስከ ሁለት ቢሊዮን የሚሆኑ ደቂቅ አካላት እንደሚኖሩ ይገመታል። ከእነዚህም ውስጥ 0 ነጥብ 01 በመቶ ያህሉ የሚታወቁ ሲሆን፣ ከሚታወቁም መካከል በሽታ አምጪ በመባል የተሰየሙት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። ገና ከጅምሩ ግን አፈጣጠራቸው ሲታይ በሽታ አምጪ አልነበሩም። በሽታ አምጪ ሊሆኑ የቻሉት የሚኖሩበት አካባቢ በሰው ሲዛባ ወይም ሲጠቃ ነው። በዚህ ጊዜ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለመፈለግ ሲሉ ወደ ሰው ይሄዳሉ። ከዚህም ያረፉበትን ሰው ሊጎዱ ይችላሉ። አሁን የመጣው ኮሮናም የዚህ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። እነርሱ ግን አይሞቱም፤ ሕይወት ይቀጥላል።
ደቂቀ አካላት የሚኖሩት በሁለት መንገድ ነው። ይህም ከአካባቢው ጋር ይላመዳሉ ወይም የአካባቢውን ሥነ ምኅዳር ለእነርሱ በሚስማማ መልኩ ይለውጣሉ። በአጠቃላይ ባዮሎጂካል ኢሞርታል (ለዘላለም የሚኖሩት) ከሚባሉት የፍጥረት ዝርያዎች መካከል አንዱ ደቂቅ አካላት ናቸው።
ለምሳሌ ያህል አንበሳ የሚኖረው ሰንበሌጥ፣ ጫካና ሌሎች እንስሳት ባሉባቸው አካባቢ ነው። ይህ ዓይነቱ አካባቢ በሰው ሲነካበት ወይም ሲራቆትበት ሥነ ምኅዳሩ ይናጋበታል፣ ይበላሽበታል። በዚህም የተነሳ ወደ ሰው መጠጋቱና መተናኮሉ አይቀሬ ነው። ከዚህም አኳያ ደቂቅ አካላት አካባቢያቸው ሲናጋ ወይም ኢኮ-ሲስተማቸው ሲዛባ ወደ ሰው በቀላሉ ይተላለፍና ይላመዳሉ። ሰውነታችን ደግሞ ከእነሱ ጋር ትውውቅ ስላልነበረውና ያንን የመከላከል አቅም ስላላዘጋጀ የመጀመርያው ጥቃት ሞት ነው። በሂደት ውስጥ ግን ሰውነታችን ያንን የመከላከል ብቃት ይጨምራል። ይኼም በኮሮና ቫይረስ የታየ ነው።
መታሰብ ያለበት አንዱ ትልቅ ነገር ቢኖር የትኛውም የፍጥረት አካል የሚኖረው በመስተጋብር፣ በመረዳዳትና በመተሳሰር ነው። የተፈጥሮ ሕግም የሚለው ይህንኑ ነው። ሰው ግን በተፈጥሮ ሲኖር ራሱን የበላይ አድርጎ ይቆጥራል። በዚህም የተነሳ ተፈጥሮን እንደፈለገው ለማድረግ ይንቀሳቀሳል። በዚህ እንቅስቃሴ ተፈጥሮን እያሳሳ ይሄዳል። የአንድ በዓይን የማይታይ ትንሽ የሕይወት አካል መበላሸት ብዙ ችግሮችን ያስከትላል።
የደቂቀ አካላት መኖሪያ የትም ነው። አይኖሩበትም የተባለ ቦታ የለም። ሰው በማይኖርበት ቦታ ሁሉ ይኖራሉ። አካባቢን ያሳመሩም እነሱ ናቸው። እንዲያውም የምድር ኢንጅነሮች ይባላሉ። ደኑ ለልማት ሲውል በተጠናና በተጠበቀ መንገድ መሆን አለበት። መነካትና ዝም ተብሎ መጨፍጨፍ የለበትም። እርሻ ላይ ያሉ የአዝዕርት ዝርያዎች እኛ ዘንድ አሉ። ለምን ቢባል በአንድ ወቅት እንዳይጠፉ ነው። የእንስሳት ዝርያዎች አርሶ አደሩ በአግባቡ እንዲጠብቅ እናስተምራለን። የእንስሳት ዘረ መልን እናቀርባለን።
የተፈጥሮ አካባቢ ከሰው ንክኪ ነፃ እንዲሆን እንሠራለን። የአካባቢ መጠበቅ ደግሞ በዓይን የማይታዩ ደቂቅ አካላት የተጠበቁ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ከዚህም ሌላ በኢንስቲትዩቱ ለዚህ ሲባል በተዘጋጀ ቀዝቃዛ ክፍል ውስጥ ደቂቀ አካላትን እናስቀምጣለን። በሽታ አምጭ ናቸው የተባሉ ደቂቀ አካላትም ጥቅም ስላላቸው እንይዛቸዋለን። ጥቅማቸውም ለፈውስ የሚሆን መድኃኒት ከነሱ ማምረት መቻሉ ነው።
እነዚህን ለማንበርና ለመለየት ባክቴሪያ ላይ የሠራ፣ ስለቫይረስ የተማረ፣ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ ደረጃ ፈንገስና ማይክሮ አግሪ ላይ የተማረ ባለሙያና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል። እነዚህን የተዘረዘሩት ባለሙያዎችና ቴክኖሎጂዎችን ኢንስቲትዩቱ በተፈለገው መልኩ አላሟላም። ይህም የሆነበት ምክንያት ለኢንስቲትዩቱ እንደ አገር የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የእንስሳት ዝርያዎች እንዳይጠፉ ምን ምን ስራዎች ይሰራሉ?
ዶክተር መለሰ፡- እንስሳቶች እንዳይጠፉ የማንበር ሥራዎች ይሰራሉ። የእንስሳቱ ጥበቃ የሚከናወነው በሁለት መልክ ነው። ይህም አንደኛ በኢ ዘቦታ በሚባለው መንገድ ነው። ይህ ኢዘቦታ የሚባለው የማንበር መንገድ ዝርያቸው የተመናመኑትን የወንድ አባላዘር በመሰብሰብ በጂን ባንክ በማስቀመጥ እንደ አስፈላጊነቱ የማሰራጨት እና ዝርያ እንዳይጠፋ የማድረግ ተግባር ነው። በዘቦታ የሚባለው የማንበር መንገድ ደግሞ ዝርያው በማህበረስቡ እጅ ሆኖ ከተፈጥሮ አካባቢያቸው ሳይወጡ እዛው ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለማድረግ ነው።
ይህም ማለት አገር በቀል ዝርያዎች ሆነው ከእነሱ መካከል ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት የሚሰጡትን በመምረጥ የማዳቀል ሥራ ነው። ለምሳሌ ከወተት ምርት አንፃር፤ ከስጋ ምርት አንፃር፤ የተሻለ ዝርያ ያላቸውን በማዳቀል እና አገሪቱ ባላት የጀነቲክ ሀብት በዘላቂነት የምትጠቀምበትና ህብረተሰቡም በተወሰነ አቅም ብዙ ምርት የሚያገኝበትን አካሄድ ለማስቀጠል የተለያዩ ምርምሮች ብሎም በተግባር የሚከናወኑ ሥራዎች ይሰራሉ።
የተሻሉ ምርቶችን ለማግኘት ከመስክ ጀምሮ በላብራቶሪ የተደገፉ የምርምር ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። በሁሉም የእንስሳት ዘርፍ ምርምር የሚያደርጉ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ፒ ኤች ዲ ዲግሪ ደረጃ ድረስ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ተመራማሪዎች በያዘ የተለያዩ የምርምር ሥራዎች ይሰራሉ።
የዝርያ መጥፋት ስጋት ያለባቸው እንስሳት ማለትም የመጥፋት አደጋ ያንዣበበባቸው ናቸው ሲባል፤ ቁጥራቸው በዓለም አቀፉ እስታንዳርድ ከ250 በታች ሲሆን ነው። የእንስሳቱ ቁጥር እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርስ ዝርያውን መመለስ አዳጋች እንዲሆን ያደርገዋል።
በአገራችንም ይህ ስጋት ያንዣበበባቸው ሁለት ዝርያዎቸ አሉ። የሸኮ ዳልጋ ከበትና የቁንዱዶ ፈረስ ዝርያዎች ቁጥራቸው እጅግ ዝቅ ብሎ ነበር። የቁንድዶ ፈረስ በ2006 ዓ.ም ቁጥራቸው ስድስት ነበር። ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን በተሰራው ስራ ቁጥራቸው ወደ 31 ከፍ ብሏል። እነዚህ የቁንዱዶ ፈረስ ዝርያዎች የፈረስ አይነት ሆነው በዱር የሚኖሩ የፈረስ ዝርያዎች ሲሆኑ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ተመናምነው ነበር። ምንም እንኳን አሁን ቁጥራቸው የማንሰራራት ሁኔታ ላይ ቢሆንም ከመጥፋት አደጋ ሰጋት እንዲወጡ እየተሠራ ነው።
ለእዚህም በአካባቢው የሚገኘው የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ፤ የኦሮሚያ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፤ የአካባቢው ማህበረሰብ እና ኢንስቲትዩቱ በጋራ በመሆን ዝርያው ከአደጋ ስጋት ነፃ እንዲሆን እየተሰራ ነው።
ሌላው የመጥፋት ስጋት ያንዣበበባቸው የሸኮ ዳልጋ ከብት የሚባሉት ዝርያዎች ናቸው። መገኛቸው በደቡብ ክልል ሆኖ ልዩ የሚያደርጋቸው አገሪቱ ካላት 28 የቀንድ ከብት ዝርያዎች በፀፀ ዝንብ ምክንያት የሚመጣውን ፀፀ በሽታ መቋቋም የሚችሉና በቀላሉ በበሽታው በመጠቃት የማይሞቱ ናቸው። እነዚህ ዝርያዎችም ቁጥራቸው ወርዶ የነበረ ሲሆን፤ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማደራጀት የእዚህን ዝርያ ኮርማ እንዲጠቀሙ በማድረግ ዝርያው ከስጋት እንዲወጣ ብሎም እንዲያገግም ተሰርቷል።
ከዚህም በተጨማሪ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ዝርያቸውን የማብዛት ስራ እየተሰራባቸው ያሉ የቦረና፤ የሸኮ፤ ቤጋይት፤ ፎገራ፤ ቤጋሪያ ዳልጋ ከብቶችን ሲሆን፤ ይህ የቦረና ዳልጋ ከብት ቀደም ሲል የመጥፋት ሰጋት ነበረበት። አሁን በተከሰተው የድርቅ አደጋ ምክንያት ዝርያው የመመናመን ሁኔታ ታይቶበታል። ቦረና አካባቢ ያለው ይህ ዝርያ እንዳይጠፋ ተቋሙ ወደ አንድ ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ በማድረግ መኖ የማቅረብ ሥራ ሰርቷል።
በሥራ ክፍሉ ዝርያ የማሻሻል ስራ ይሰራል ሲባል የውጭ ዝርያዎቸን እያመጡ ማዳቀል ሳይሆን በአገር ውስጥ የተሻለ ምርት የሚሰጡትን በመለየት በማዳቀል የእነሱን ዝርያ የማብዛት ስራ እየተሰራ ነው። ከውጭ ከሚመጡት በተሻለ የአካባቢውን ችግር መቋቋም የሚችሉ በመሆናቸው ቅድሚያ ተሰጥቶ ይሰራል።
የኢትየጵያ የዱር እንስሳት ላይ የሚሰሩ ጥናቶች በጣም ውስን ከመሆናቸው የተነሳ የሚገኙ ውጤቶችም ተመሳሳይ የሆነ ቁጥሮች ናቸው። ለምሳሌ የውሃ ውስጥ አካላት በጣም በርካታ ዝርያዎች ቢኖሩም በአገሪቱ ተጠንቶ ቁጥሩ ሊታወቅ የቻለው ግን የአሳ ዝርያ ብቻ ነው። በአገራችን የሚገኙ የአሳ ዝርያዎችም ወደ 200 ዝርያ የሚጠጉ መሆናቸው በጥናት ተለይቷል።
በዘርፉ በቂ ባለሙያ አለመኖሩ ስራው በስፋት እንዳይሰራ ያደረገው መሆኑን ገልፀው፤ ወደፊት ባለሙያው ሲፈጠር በጥናት ሊለይ ይችላል በማለት ዝርያዎች እንዳይጠፉ ለማድረግ የመሰብሰብ ስራ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በአጠቃላይ የተፈጥሮ ገፀ በረከት እንዳይጠፋ የመባዛት፤ ዝርያውን የመሰብሰብ፤ የመመራመር ስራን በመስራት ከምድረ ገፅ የሚጠፉ ሀብቶቻችንን የመጠበቅ ስራ የብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት እየሰራ ነው። ማህበረሰቡ ግን ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ እንዳይጋረጥባቸው በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡ ብዝሃ ህይወትን ማንበር ስንል ምን ማለታችን ነው?
ዶክተር መለሰ፡- ምድር ተፈጥሯዋን ጠብቃ ትኖር ዘንድ የብዝሃ ህይወት ሀብትን ለይቶ መንከባከብ ተገቢ ነው። የብዝሃ ህይወት ሀብቶችን መጠበቅና መንከባከብ ሲባል ግን ዘሩን ሰብስቦ ከማንበር በዘለለ ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ሀብቶች አካባቢያዊ ስነ ምህዳር እንደጠበቀ ለማቆየት የግድ የስርዓት ምህዳር መስተጋብር መጠበቅ ይኖርበታል።
የብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ሀብት የመጠበቅ የመንከባከበና ጥቅም ላይ እንዲውል የማድረግ ኃላፊነት ይዞ የሚንቀሳቀስ፤ ብዝሀ ህይወት ላይም ጥናትና ምርምር የሚያካሂድ ተቋም ነው። ተቋሙ መጀመሪያ ሲቋቋም የግብርና ሰብሎችን መሰረት አድርጎ የተቋቋመ ነበር። በሂደት ግን እየተደራጀ እየተሻሻለ መዋቅራዊ ለውጥ እያደረገ ከግብርና ሰብሎች ውጪ ያሉ ሰብሎችን በተለይ ደግሞ የዓለም አቀፉ የብዝሀ ህይወት ስምምነት በ1991 በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከፀደቀ በኋላ ሁሉንም የብዝሃ ህይወት ሀብቶችን ማለትም የእንስሳትና የዕፅዋት አጠቃላይ የደቂቀ አካላት ምርምርና ጥበቃ ሥራዎች ሲሰራ ኖሯል።
ብዝሃ ህይወትን እንጠብቅ ሲባል የምንጠብቀው ለምንድ ነው? በመጠበቃችን የተነሳ ከመክሰር የምናድነው ዋጋስ ስንት ነው? ቢጠፉስ ምን ይጎዳሉ? የሚሉት ለመለየት ሰዎች ተፈጥሮን ዘላቂነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲያከናወኑት በማድረግ የተፈጥሮ ሀብትን በዘቦታ ማለትም ባሉበት የተፈጥሮ ሰነምህዳርና በኢ ዘቦታ ደግሞ በጀነቲክ ማቆያ የማንበር ተግባራትን ያከናውናሉ።
አዲስ ዘመን፡- ዶክተር ቀሪ ዘመናቸውን ምን በመስራት ቢያሳልፉ ደስ ይላቸዋል የሚል ጥያቄ ላነሳ ወደድኩ መልሶ ምን ይሆን?
ዶክተር መለሰ፡- ቀሪ ዘመኔን በጀመርኩት የማስተማር ስራ፤ የተለያዩ ምርምሮችም ፋብሪካ ገብተው ተጨባጭ ወጤት በማምጣት የአገር ኢኮኖሚ የሚያድግበትን ሰራ ለመስራትና የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራ ላይ ብሰማራ ደሰ ይለኛል።
አዲሰ ዘመን፡- ውድ ጊዜዎን ሰውተው ጠቃሚ ሀሳብ ስላካፈሉን እናመሰግናለን።
ዶክተር መለሰ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን የካቲት 18 ቀን 2015 ዓ.ም