በዓለም ከሚታወቁት የስፖርት ጋዜጦች አንዱ፣ “RUNNERS WORLD” ባወጣው መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ በአለም ላይ ከሚካሄዱት ምርጥ የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድሮችን በማዘጋጀት ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ቀዳሚ ሆናለች።
ጋዜጣው ለኢትዮጵያ ይህን ደረጃ የሰጠው “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አለም አቀፍ 10 ኪሎ ሜትር”ን በየአመቱ በታላቅ ድምቀትና ስኬት ማስተናገድ በመቻሏ ነው።
ከኢትዮጵያ በመቀጠል በለንደን የሚካሄደው “ቪታሊቲ” 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድርና የፓሪስ 10 ኪሎ ሜትር ውድድር ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ረነርስ ወርልድ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በርካታ ሰዎች የሚሳተፉበት የአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ ውድድር መሆኑን በማስታወስ ጭምር አሞካሽቶታል።
ይህንንም ተከትሎ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወይዘሮ ዳግማዊት አማረ ደስታቸውን ሲገልፁ” ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ለማዘጋጀት ከሃያ ሁለት አመታት በፊት ጉዞ ስንጀምር የኢትዮጵያን ብርቅዬ አትሌቶች ስኬት የሚያንፀባርቅ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጎዳና ላይ ውድድር እውን ለማድረግ እንደምንፈልግ ገልጸን ነበር፣ ከአለም ምርጥ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድሮች ቀዳሚ መሆን ማለትም ይህ ነው፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአስር ኪሎ ሜትር የአለም ምርጦች ናቸው፣ እኛም አሁን የአለም ምርጡን 10 ኪሎ ሜትር ውድድር አዘጋጆች ነን ብለን በኩራት መናገር እንችላለን” ብለዋል።
ይህ ስኬት የኢትዮጵያ ስኬት መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ዳግማዊት፣ በተለይም ከመጀመሪያ አንስቶ ለውድድሩ ድጋፍ ያደረጉ አትሌቶች የዚህ ስኬት ሚስጥሮች መሆናቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ለተገኘው ስኬት ብዙ ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አክለው መንግስትም ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም “The Challenge Awards ” በተሰኘ መድረክ ላይ በጎዳና ላይ ሩጫ ዝግጅት ዘርፍ በአለም ቀዳሚ ሆኖ በመመረጥ ልዩ ሽልማት መቀበሉ ይታወሳል፡፡
ዘ ቻሌንጅ አዋርድን የሚያዘጋጀው ሌትስ ዱ ዚስ (Let’s Do This) በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው የድረገፅ ምዝገባ አገልግሎት ሲሆን የሽልማቱ አቅራቢ ደግሞ በከፍተኛና ልዩ የአትሌቲከስ ባለሙያዎች የተደራጀው ታዋቂው ራነርስ ዎርልድ መፅሄት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዓለም የሩጫ ስፖርት ኢንዱስትሪ የኦስካርን ያህል ክብርና ግምት የሚሰጠው ሽልማቱ በመላው ዓለም የሚካሄዱ ፈታኝ የስፖርት ውድድሮችን የሚያዘጋጁ፤ ጎን ለጎን የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎችን የሚያከናውኑ ማህበረሰቦችና ግለሰቦችን በልዩ መስፈርቶች አወዳድሮ እውቅና ይሰጥበታል፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ የክብር ሽልማቶችን ከዚህ ቀደምም ማሸነፍ ችሏል። በ2013 የመጀመርያውን “የAIMS Social Award” የማህበረሰብ አዋርድ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የማራቶንና የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር AIMS አባል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኤይምስ AIMS በየዓመቱ የውድድር አዘጋጆች በሚያቀርቡት ማመልከቻ መሰረት ለአባል የማራቶንና የጎዳና ላይ ሩጫ አዘጋጆች በሁለት ዘርፎች አወዳድሮ የሶሻል እና የግሪን አዋርዶችን በማዘጋጀት ይሸልማል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያም ከዓመታት በፊት ዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫ ማህበር በግሪክ አቴንስ ባዘጋጀው የሽልማት ስነስርዓት ላይ የAIMS Social Awardን አሸንፎ ነበር፡፡
ከ22 ዓመት በፊት በ10 ኪሎ ሜትር፤ 10 ሺህ ስዎችን በማሳተፍ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር የጀመረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተወዳዳሪው ቁጥር ከ45 ሺህ ልቋል።
በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ እውቅናና ተሳትፎ ያላቸውን የጎዳና ውድድሮች አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚያሰናዳውን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የመሰረተው ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ነው።
የተለያዩ የዓለማችን ዜጎች ምንም ዓይነት ዕድሜ፣ ጾታና ዘር እንዲሁም ሃይማኖትና የቆዳ ቀለም ሳይገድባቸው በአንድ መድረክ ሮጠው ስሜታቸውን የሚገልጹበት የሚደሰቱበትና ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በወርሐ ኅዳር ይካሄዳል፡፡ ሩጫው የአንድ ቀን ድግስ ሆኖ ነገር ግን ዓመቱን ሙሉ የሚጓጓለትና ዝግጅትም የሚደረግበት ነው፡፡ በዚህ ስኬቱ የተነሳም ዛሬ በአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ ሆኗል፡፡ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ልዩ ጌጥ እንደሆነ የተነገረለትና ኢትዮጵያን የሩጫ ምድር እንደሆነች ያስመሰከረም ሆኗል። ከዚህ ጎን ለጎን በሚያከናውናቸው የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችም ተመስጋኝ ለመሆን በቅቷል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም