አንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት ሊኖረው የሚችለው ብቁ የሰው ኃይል ሲኖረው እንደሆነ ይታመናል። ብቁ የሰው ኃይል ለማግኘት ደግሞ ትምህርት ግንባር ቀደሙ መሣሪያ ነው። ትምህርትን በተሻለ ጥራት መስጠት ሲቻል፤ የአገሪቱን ራዕይ በቀላሉ ለማሳካት አያዳግትም። በጥራት የተማረ የሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂውም የተሻለ ሐሳብ በማመንጨቱ ረገድ ሚናው ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም።
ኢትዮጵያም ጥራት ያለው የተማረ የሰው ኃይል ከማብቃት አኳያ በዚህ ዓመት የጀመረችው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በጥንቃቄ መፈተን አንደኛው እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ፈተና የመጣው የተማሪዎች ውጤት ከሚጠበቀው በላይ አስደንጋጭ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህንን ዝቅተኛ ውጤት በመቀልበስ የተሻለ ነጥብ ማስመዝገብ የሚቻለው እንዴት ነው? ለትምህርት ጥራት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ ረገድ መንግስትን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላትስ ምን ይጠበቃል? በሚሉና በሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ዙሪያ በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት አመራርና አስተዳደር መምህርና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የቀድሞ የመምህራን፣ የሱፐርቫይዘሮችና የርዕሳነ መምህራን ክፍል ዳይሬክተር ከነበሩት ከዶክተር አማኑኤል ኤሮሞ ጋር አዲስ ዘመን ቃለ ምልልስ አድርጎ ተከታዩን ጽሑፍ አጠናቅሯል።
አዲስ ዘመን፡- የትምህርት ጥራት ሲባል ምን ማለት ነው? ከሚለው ጥያቄ ቃለ ምልልሳችንን ብንጀምርስ?
ዶክተር አማኑኤል፡- የትምህርት ጥራት ቀጥተኛ የሆነ ትርጉም ባይኖረውም በተለያየ መንገድ ሊገለጽ ይችላል። ከዚህም አንዱ በትምህርት ስርዓት ውስጥ የሚገለጸው ነው፤ በተመሳሳይ በምርት ብሎም በአገልግሎት ይገለጻል። ለምሳሌ ጥራት ሲባል የላቀ አገልግሎት ወይም ልሕቀት እንደማለት ነው። ልህቀት ሲባል ደግሞ በየጊዜው የሚሻሻልና የሚስተካከል ነገር ነው።
በትምህርት ስርዓት ውስጥ የላቀ አገልግሎት ማለት የላቀ የተማሪዎች ውጤት ብለን እናስቀምጣለን። የላቀ የተማሪዎች ውጤት ሲባል ደግሞ መገለጫው በየደረጃው ባሉ ክፍሎች ላይ ሲሆን፤ ይኸውም ስታንዳርዱን ጠብቀው የሚዘጋጁ እንደ ስድስተኛ፣ ስምንተኛና 12ኛ ክፍሎች ላይ የሚዘጋጁ ፈተናዎች ልህቀትን ያመለክታሉ። ተማሪዎች በየደረጃው የሚጠበቅባቸውን ትምህርት አጠናቅቀው ምን ያህል ያሉበት ደረጃ ላይ እንደደረሱ የሚያሳይ ነው። ይህ ከተማሪዎች ውጤት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው ነው።
ከዚህም አልፎ ጥራት ልክ እንደገንዘብ ሁሉ ዋጋ አለው። በትምህርት ስርዓታችን ውስጥ ብዙ የሆነና ከፍተኛ የሰው ኃይል፣ የቁሳቁስና የፋይናንስ ወጪዎች አሉ። እነዚያ ወጪዎች በሙሉ ተሰልተው ጥራት ካላመጡ ብክነት ነው። እንግዲህ በትምህርት ስርዓታችን ውስጥ ጥራት ስንል ከብክነት ነጻ የሆነ ነው። ለምሳሌ የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ውጤት ስንመለከት 97 በመቶ አካባቢ ያላለፉ ናቸው፤ በዚህ ውጤት መሠረት ጥራት የለም የሚያሰኝ ነው። ስለዚህ እዚህ ላይ የታየው ብክነት ነው።
ሌላው ጥራት ሲባል ቀጣይነት ያለው ማሻሻል ነው። ጥራት በሌላ አገላለጽ ደግሞ መሰረታዊ ለውጥ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ጥራት ማለት የላቀ አገልግሎት መስጠት እንደማለት በመሆኑ የደንበኛ እርካታን የሚያመጣ ነው። ለምሳሌ ደንበኛው ከሚጠብቀው በላይ እንዲረካ ማድረግ ነው። ነገር ግን ከዚህ አኳያ ሲታይ በጥራት በኩል ውጤት ማስገኘት አልተቻለም።
አዲስ ዘመን፡- በአገራችን በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተሰጠ ያለው የትምህርት አሰጣጥ አግባብነትን እንዴት ይገመግሙታል?
ዶክተር አማኑኤል፡- ጥራት ማለት ስህተትን ለይቶ ማውጣት ማለት አይደለም። የትምህርት ጥራት ማምጣት ማለት ስህተት ከመፈጸሙ በፊት መከላከል ማለት ነው። ስህተት ከመፈጸሙ በፊት መለየት ማለት እንደትምህርት ስርዓት የሚጀምረው የት ላይ ነው? ቢባል ከቅድመ መደበኛ ነው። የትምህርት ስርዓት መሰረት ቅድመ መደበኛ ነው ሲባል፤ ቅድመ መደበኛ ላይ አንድ የአምስት ዓመት ህጻን አዕምሮው 95 በመቶ ይሰራል ተብሎ ይታሰባል። መሰራት ያለበት ቅድመ መደበኛ ላይ ነው። እዛ ላይ ግን አልተሰራም። ቅድመ መደበኛ ላይ ይቅርና አንደኛ ደረጃ ላይም አልተሰራም፤ ለምሳሌ በአንደኛ ደረጃ ከአንድ እስከ አራተኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች በነጻ ዝውውር ማለፍ አለባቸው በሚል ሲያልፉ እንደነበር የሚታወቅ ነው።
ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ስናይ ስምንተኛ ክፍል ላይ በጣር ያለፉ ናቸው\ ስምንተኛ ክፍል አብዛኛው ያለፈው ከ50 በታች የሆነ ውጤት አምጥቶ ነው። በዚህ አይነት ሁኔታ እስከ 12ኛ ክፍል መጥቶ 12ኛን ክፍል ተፈተን ተባለ፤ 12ኛ ክፍልን ሲፈተን በቅርቡ ይፋ የሆነ ውጤት ተመዘገበ።
ስለዚህ የትምህርት ጥራት ማለት ለምሳሌ አንድ ሰው ስንዴ መዝራት ፈልጎ ከጎተራ ሲያወጣ ምርቱን ከእነ እንክርዳዱና ከሌሎች ቆሻሻዎች ሳይለይ ወስዶ ዘራው። ከዘራ በኋላ ምንም አይነት እንክብካቤ ባለማድረጉ ስንዴው ከነአረሙ በቀለ። ያንኑ ከነአረሙ የበቀለውን ስንዴ አጭዶ ከመረ። የከመረውንም ወቅቶ ሲያየው እንክርዳዱ ከስንዴው ጋር እኩል ሆነ። የእኛም የትምህርት ስርዓት የሆነው እንደዚሁ ነው።
ገና ከመነሻው ላይ አልለየነውም፤ ይዘነው መጣን። 12ኛ ክፍል ደርሶ ውጤቱን ስናይ ግን ያገኘነው የወደቀ ውጤት ነው። ስለዚህ የትምህርት ጥራት እንዲኖር ከተፈለገ መሰራት ያለበት ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ነው። ይህ በየደረጃው መስተካከል የነበረበት ነው።
አዲስ ዘመን፡- የመጣውን የሶስት በመቶ ዝቅተኛ ውጤት ለመቀልበስ ምን መደረግ አለበት ?
ዶክተር አማኑኤል፡– ዝቅ ያለውን ውጤት ለመቀልበስ መከተል ያለብን የተለያየ አቅጣጫ ነው። አንደኛ ትምህርት ቤቶቻችን ምን ይመስላሉ? ብለን ልናያቸው ይገባል። ከዚህ አንጻር ትምህርት ቤቶቻችንን ስናይ አንድም ተማሪ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶች አሉ። ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የተወሰኑ ማለትም ከአስር በታች ተማሪዎችን ያሳለፉ ትምህርት ቤቶች አሉ። ሶስተኛው ደግሞ የተሻለ የተማሪ ቁጥር ያሳለፉ ትምህርት ቤቶች አሉ።
ምንም ተማሪ ያላሳለፈው ትምርት ቤት መርከቡ ተንሳፏል ማለት ሳይሆን ሰምጧል ነው። ይህን መርከብ ከተቀበረበት ማውጣት የምንችለው እንዴት ነው? ሌላው ደግሞ ሶስትና አራት ተማሪዎችን ብቻ ያሳለፉ ትምርት ቤቶች መርከቡ ተንሳፏል እንጂ እየሄደ ነው ማለት አንችልም፤ ባለበት የቆመ ነው። ሌላው የተሻለ የተማሪ ቁጥር ማሳለፍ የቻለ ትምህርት ቤት አለ፤ እርሱ የሚታገል ትምህርት ቤት ነው።
የተሻለ ቁጥር ያሳለፉ ትምህርት ቤቶችን ለሌሎቹ ሞዴል እንዲሆኑ በማድረግ ተሞክሯቸውን የሚያካፍሉበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል። ዝቅተኛ ቢሆኑም በተወሰነ ደረጃ እየታገሉ ያሉ ትምህርት ቤቶችን ደግሞ በተሻለ ሁኔታ ማብቃትን ይጠይቃል። ምንም ተማሪ ባለማሳለፋቸው የሰመጡ ትምህርት ቤቶች ግን ከፍተኛ ቀዶ ህክምና ያስፈልጋቸዋል። የሰው ልጅ ኩላሊት አልሰራ ካለ ወይ ማከም አሊያም በቀዶ ህክምና ማውጣት የግድ ይላል። እነዚህ የሰመጡ ትምህርት ቤቶችም ቀዶ ህክምና ያስፈልጋቸዋል። ቀዶ ህክምና ደግሞ የሚጀምረው ከአመራሩ፣ ከመምህሩ፣ ከተማሪው፣ ከወላጁ እንዲሁም ከሌላውም ኅብረተሰብ ነው።
አንድም ተማሪ ማሳለፍ ያልቻሉት አንድ ሺ 162 ትምህርት ቤቶች ናቸው። እነዚህን ትምህርት ቤቶች ቀደም ሲል በሚደረገው አይነት በተመሳሳይ አመራር እና በተመሳሳይ አካሄድ እንዲሄዱ ማድረግ አይገባም። ምክንያቱም ልዩ ክትትል የሚያስፈልጋቸው ናቸው። በእኛ በትምህርት ስርዓት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የሚያሳዩት፤ ትምህርት ቤት ማንን ይመስላል ሲባል የትምህርት ቤቱን ርዕሰ መምህር ነው። ስለዚህም የእነዚህ አንድም ተማሪ ማሳለፍ የተሳናቸው ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን መፈተሽ አለባቸው፤ መጠየቅም አለባቸው።
የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሲጠየቅ ተማሪውም ወላጅም እንዲሁም የየራሳቸውን ስራ መስራት ይጀምራሉ። ለመጠየቃቸው ምክንያቱ በርዕሰ መምህርነት የሚመሩት ትምህርት ቤት ሰምጧል፤ ስለዚህ ተቸግረው ወይም አማራጭ በማጣት ካልሆነ በስተቀር ወደሰመጡት ትምህርት ቤቶች ወላጆች ልጆቻቸውን መላክ እንደማይፈልጉ እርግጠኛ ነኝ። ህልውናውን ባጣ ትምህርት ቤት ውስጥ ወላጅ ልጁን በመላክ እንዲማር አይፈልግም።
ስለዚህ በቀጣይ የትምህርት ስርዓቱ እንዲስተካከል ከተፈለገ ትምህርት ቤቶች ከላይ እስከ ታች በትኩረት ሊሰራባቸው ይገባል። ሌላው በየትኛው የትምህርት ስርዓት ዓለም አቀፍ ጥራት የሚያሳየው በመጀመሪያ በጥራት ትልቅ ሚና የሚጫወተው ተጠያቂው መሪው ነው። መሪ ሲባል የትምህርት ቤት መሪ ብቻ አይደለም። የቀበሌ፣ የወረዳ፣ የዞን ወይም የክልል መሪ ብቻ ሳይሆን የአገር መሪም የትምህርት ጥራት ጉዳይ አጀንዳው መሆን አለበት።
ለምሳሌ በአሜሪካ የአገሪቱ ፕሬዚዳን የነበሩት ሬገን በ1983 የአገራቸው የትምህርት ጥራት ሲወድቅ አገር አደጋ ላይ ነው (Nation at risk) የሚል አዋጅ አወጡ። በወቅቱ ራሽያ ወደህዋ ስትመጥቅ አሜሪካ ወደኋላ ቀርታ ነበር። በዚያን ወቅት 700 ገጽ ያለው አዋጅ ወጣ። በዛ አዋጅ መሰረት የአገሪቱ ትምህርት ሊስተካከል ችሏል።
ሁለተኛ ቡሽ በ2000 (No childe left behind) ማንኛውም ተማሪ በትምህርት ወደኋላ አይቀርም ብለው አዋጅ አወጡ። በዛ አዋጅ የትምህርት ጥራት ተስተካክሏል። በተመሳሳይ ኦባማ በ2009 ላይ (Every Student Succeeds) ሁሉም ተማሪ ውጤታማ ይሆናል ሲሉ ሕግ አወጡ። በዚህም ሕግ አስተካክለዋል። አመራሮቹ በየዘመናቸው ያንን በማድረጋቸው በዓለም ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ አገር ሆነው እየኖሩ ነው። ስለዚህ የትምህርት ጥራት ጉዳይ የዜጎች ጉዳይ ነው። አንድ አገር የሚመራ መሪ ስለዜጎቹ ትኩረት ማድረግ አለበት። ወደእኛ አገር ስንመጣ ግን የትምህርት ጥራትን አጀንዳው አድርጎ የሰራው የትኛው መንግስት ነው? የሚለው ብዙ ያነጋግራል።
ዳግማዊ አጼ ሚኒልክ ዘመናዊ ትምህርትን አስተዋውቀው ሊሆን ይችላል። ጥያቄው ግን ከዛ በኋላ ምን ተሰርቷል ነው። ስለዚህ አሁን መሆን ያለበት የትምህርት ጥራት ሲጓደል ተጠያቂ የሚያደርግ ሕግ መውጣት አለበት። ተጠያቂ የሚያደርግ ሕግ በሌለበት አዲስ ነገር ማምጣት አይቻልም። አንድም ተማሪ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶችን ተጠያቂ ማድረግ ይቻል የነበረው ሕግ መኖር ሲችል ነው። ስለሆነም አጀንዳችን ከላይ እስከታች መሆን አለበት። የትምህርት ቤቱ አመራር ተማሪውም መምህሩም መማር ማስተማሩ የሚካሄደው እርሱ ባለበት ስለሆነ ተጠያቂ መሆን አለበት።
ሌላው ደግሞ ዋናው የትምህርት ትልቁ ስራ ክፍል ውስጥ ያለው ነው። በክፍል ውስጥ ሶስት አካላት አሉ። አንዱ ስርዓተ ትምህርቱ ነው፤ ሁለተኛው መምህሩ ሲሆን፣ ሶስተኛው ተማሪው ነው። እነዚህ ሶስቱ አካላት ላይ በሚገባ መሰራት አለበት። ለምሳሌ ከመምህሩ ዘንድ የሙያ ስነምግባር፣ ብቃት ብሎም ተነሳሽነት ስለመኖሩ መምህሩን ብንፈትሽ የሚገኘው ውጤት ከባድ ነው። ምክንያቱም መምህሩ በስራው እርካታ የለውም፤ እያስተማረ ልቡ ያለው ሌላ ዘንድ ነው። ግን ደግሞ ከመቶ 35 ያህሉ የተማሪው ውጤታማነት ያለው መምህሩ ዘንድ ነው። ተማሪው 40 በመቶ የሚያዝ ሲሆን፣ የተማሪ ውጤት መምጣት አለበት ከተባለ በእነዚህ ሁለቱ አካላት ላይ መሰራት አለበት። ስርዓተ ትምህር ተገቢነት ከተነሳ፤ የስርዓተ ትምህርቱ ተገቢነት ላይ ደግሞ ችግር የለውም።
የተማሪው ችግር ምንድን ነው? ቢባል ተማሪው ራሱ አንደኛ ለመማር ዝግጁ ነው ወይ? የሚለው መጤን ያለበት ነው። በክፍል ውስጥ ባለው የመማር ማስተማር ሒደት ውስጥ እውን ተሳታፊ ነው የሚለው ተመሳሳይ ጥያቄ ነው። ተማሪ ለመማር ዝግጁ ካልሆነና ተነሳሽነት ከሌለው ብሎም በመማር ማስተማሩ ሒደት ላይ ካልተሳተፈ ባልሰማ ምጣድ እንጀራ እንደመጋገር ማለት ነው። ስለዚህ ተማሪው ላይ መሰራት አለበት። ለምሳሌ በሌላ አገር ተማሪ የሚማረው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝና በኮምፒውተር በመደገፍም ጭምር ነው።
ሌላው ደግሞ ተማሪ ልጁን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ መከታተል ያለበት ወላጅ ነው። ይሁንና ይህንን ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጣም። ወላጅ ከራሱ ኑሮ አልፎ የልጁን ኃላፊነት ከመውሰድ አኳያ ችግር አለ። ለምሳሌ የግል ትምህርት ቤት ብንመለከት ወላጅ ገንዘብ ስለሚያወጣ ይከታተላል። ወላጅ ስለልጁ መከታተልና ከትምህርት ቤት ጋር ተባባሪ መሆን አለበት።
ከዚህ ሌላ በቤተ መጽሐፍ እና በቤተ ሙከራ ያለው ሁኔታ ተማሪውን የሚስብ መሆን አለበት። በአጠቃላይ ትምህርት ቤቱ ተማሪውን የሚስብ መሆን ይጠበቅበታል። ይህን ለማድረግ ደግሞ በየደረጃው ያሉ አካላት ኃላፊነት አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- ትምህርት ቤቶችን ተጠያቂ ሊያደርግ የሚችል ሕግ የለም ሲሉ ጠቅሰዋልና በስትራቴጂዎችና በፖሊሲዎች ዙሪያ እየተካሔደ ያለው ነገር ምን ይመስላል?
ዶክተር አማኑኤል፡- እኔ የትምህርት ሕግ ረቂቁን አይቸዋለሁ። የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲም በአዲስ የመጣበት ሁኔታ አለ። ይሁንና አሁንም በሰፊው ማወያየትን ይጠይቃል። የትምህርት ሕጉም ጸድቋል እየተባለ ነው፤ ይሁንና ተጠያቂነትን ያሰፈነ አይደለም። ስለዚህ መፈተሽ ያለበት ነገር ነው። በዚህ ጉዳይ ክልሎችም ትኩረት አድርገው መስራት አለባቸው። የፌዴራሉን መንግስት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በየክልሉ ያሉት ትምህርት ቤቶች የእውቀት ማዕከል መሆን አለባቸው። ክልሎች በራሳቸው አውድ የትምህርት ጥራትን አጀንዳ ማድረግ አለባቸው። ከዚህ ውጪ ከማዕከላዊ መንግስት በሚወርደው ጉዳይ ብቻ መወሰን የለባቸውም። ሌላው ቀርቶ ትምህርት ቤቶች አስቀድመው ከተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት በመጠበቅ ውጥናቸውን ማሻሻልና ማስተካከል አለባቸው። የትምህርት ቤቶችም የስራ ባህል መለወጥ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ዘንድሮ ሶስት በመቶ የሆነው የተማሪዎች ፈተና ውጤት በእርግጥ ጥራት ያለው ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር አማኑኤል፡- አንድ ነገር ልብ ልንል ይገባል፤ የመጨረሻው የትምህርት ግቡ ምንድን ነው የሚለው? የትምህርት ግቡ ብቁ፣ ተወዳዳሪ እንዲሁም መልካም ስነ ምግባር ያለው ተማሪ ማፍራት ነው። ይህ ዘንድሮ የመጣው ሶስት ነጥብ አምስት በመቶ ጥራት አይደለም። ጥራት የሚባለው አንድ ሰው ዝቅተኛውን ስታንዳርድ አሟላ ማለት በመሰረቱ ጥራት አይደለም። ሶስት ነጥብ አምስት በመቶ የተባለው ሃምሳና ከሀሃምሳ በላይ ያመጣው ተቆጥሮ ነው። በመሆኑም 50 ቀርቶ 75 ማምጣት ጥራት አይደለም። እንዲያውም በእኛ አገር የሚታቀደው ጥራት ማለት 85 በመቶ እና ከዛ በላይ ያመጣ ነው። ስለዚህ በዘንድሮው ውጤት 85 በመቶ እና ከዛ በላይ ያመጡ ተማሪዎች አንድ በመቶ እንኳ የማይሞሉ ናቸው። ከዚህ የተነሳ ጥራት ሙሉ ለሙሉ የለም። የጥራት ስሙ እንጂ ተግባሩ የለም ለማለት ያስደፍራል።
ስለዚህ ጥራት እንዲመጣ መሰራት ያለበት ቀድሞውኑ ሲሆን፣ በየትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ታቅዶ መሆን አለበት። እቅዳቸው ተለጣጭ ግብ ማስቀመጥ መሆን አለበት። ለምሳሌ ሲታቀድ በጥቂቱ መሆን የለበትም። ሁሉም ተማሪ ያልፋል የሚል መሆን አለበት። የማንም ልጅ እንዲወድቅ መታቀድ የለበትም። በሚታቀደው እቅድ ደግሞ ተማሪው፣ መምህሩ ብሎም ወላጅ መስማማት አለበት። አሁን የመጣው ውጤት ግን ጥራት አይደለም። የትምህርት ጥራት ሽታው ራሱ እንኳ አለ ማለት ይከብዳል። ስለዚህ መንግስት ትምህርት ቤት ላይ እና ትምህርት ስርዓት ላይ ሪፎርም ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህ ካልሆነ አሁን ባለው ሁኔታ ቀደም ሲል በምናደርገው በአጫጭር ስልጠና እንዲሁም አጫጭር መመሪያዎችንና ደንቦችን አውጥተን በመወርወር የትምህርት ጥራትን ማምጣት አንችልም። የትምህርት ስርዓቱ ሪፎርም መደረግ አለበት። የመምህሩም የርዕሰ መምህሩም ስታንዳርድ መፈተሽ አለበት። ስርዓቱ ባለበት ቆሟል። የትምህርት ስርዓቱ መስራት ስላቆመ እንደገና መስራት እንዲችል መፈተሽ የግድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለትምህርት ጥራቱ መጓደል አንዱ የመምህሩ የገቢ ሁኔታ ዝቅተኛ መሆን ነው የሚሉ አሉና እርስዎ ይህን እንዴት ያዩታል?
ዶክተር አማኑኤል፡– በየትኛውም አገራት የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት ለመምህሩ ተወዳዳሪ የሆነ ደመወዝ ያስፈልጋቸዋል። አገሪቱ አሁን ባላት አቅም ይህን ታደርጋለች አታደርግም ወደሚለው ስንመጣ መክፈል ባትችል እንኳ ከመምህሩ ጋር መደራደር መቻል አለባት እላለሁ። ለመምህሩ እውቅና መሰጠት አለበት። የመምህሩን ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት የሚጨምር ነገር ካለ መምህሩ ሰርቶ ለውጥ ያመጣል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ ከመምህሩ ጋር መተማመን ላይ መድረስ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ነጻና ገለልተኛ ሆነው እየሰሩ ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር አማኑኤል፡- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነጻ ናቸው፤ ገለልተኛ ናቸው? የሚባለው ነገር አጠያያቂ ነው። ከዚህ መረዳት የሚቻለው የከፍተኛ ትምህርት አመራሩ ዩኒቨርሲቲው ካለበት አካባቢ የተገኘ ሰው ነው። እውቀት ደግሞ ዓለም አቀፍ ነው። እነዚህም አመራሮች የመደባቸው ማን ነው? ብንል የሚታወቅ ነውና ነጻና ገለልተኛ ናቸው መባባሉ በጣም አስቸጋሪ ነው። የትምህርት ተቋማት መሆን ያለባቸው ግን ነጻና ገለልተኛ ነው።
እውቀት ዓለም አቀፍ ነው፤ በዓለም ላይ ያሉ ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች ነጻና ገለልተኛ ናቸው። የሚያስታዳድሩትም ራሳቸውን በራሳቸው ነው። ከዚህ የተነሳ የእውቀት ማዕከል ናቸው። እኛ ማፍራት የምንፈልገው ምሩቅ ችግር ፈቺ፣ አዲስ አሰራር አመንጪ እንዲሁም በአግባቡ የሚያስብ ዜጋን ነው። ከዚህ አንጻር ተቋማቱ ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታን መፍጠር አስፈላጊ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየአካባቢዎቻቸው ያሉትን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እየደገፉና እያበቁ የሚሄዱበትን ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ የመሄዱ ጉዳይ አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዘንድሮ የመጣውን ዝቅተኛ ውጤት ተከትሎ ‹‹በልጄ ለምን ይጀመራል›› የሚሉ ወላጆችም አሉና እነዚህን አካላት ምን ይላሉ?
ዶክተር አማኑኤል፡- የትምህርት ጉዳይ የዜጎች ጉዳይ ነው፤ ዜጋ ስንል ደግሞ ሕዝብ ነው። መንግስት ደግሞ ጥራቱን የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት። በዩናይትድ ኔሽን ሂዩማን ራይትስ ላይ መንግስታት ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ይህ ነጥብ ኢትዮጵያም የተቀበለችው ዓለም አቀፍ ስምምነት ነው። በአገራችንም የትምህርት ጉዳይ የመንግስት ጉዳይ በመሆኑ መንግስት ኃላፊነት አለበት።
ትምህርትን ተደራሽም ፍትሐዊም ማድረግ እንችላለን። ትምህርትን በብቃት ማድረስ ብሎም ተገቢም ማድረግ እንችላለን። ይህ ሁሉ ግን ጥራት ከሌለው ከንቱ ነው። ስለዚህ ጥራት ያለው ትምህርት ለማዳረስ ደግሞ መንግስት ኃላፊነት አለበት። ስለዚህ ወላጅ፣ ኅብረተሰቡ፣ ባለሀብቱም ሆኑ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ‹‹ልጆቻችን የተመዘኑበት መንገድ አግባብ አይደለም›› ብለው ጥያቄ የሚያነሱ ቢሆን ተገቢ ጥያቄ አይደለም። ለአብነት ቀላል ምሳሌ ልጥቀስ፤ አንድ ሰው አየር መንገድ ቀርቦ አውሮፕላን ለመሳፈር ቢሄድ ተቋሙ እፈትሻለሁ ቢልና ተሳፋሪው ፈቃደኛ አይደለሁም አለ እንደማለት ነው። ልክ ለአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎችም ሆነ ለተቋሙ ደህንነት ሲባል መፈተሽ ግድ እንደሆነ ሁሉ መንግስትም በትምህርት ጥራት ላይ ያለውን ስጋት ለማስወገድ ለብዙ ዓመታት ያስተማራቸውን ተማሪዎች ሊመዝን የግድ ነው።
መመዘኑ መንግስት የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስወቅሰው መሆን የለበትም። ይህ በቀጣይም ሊሰራበት የተገባው ጉዳይ ነው። ይልቁኑ በ12ኛ ክፍል ላይ ብቻ ሳይሆን ወደፊት በ6ኛ፣ በ8ኛ፣ በ10ኛ እና በየደረጃው ባሉ ክፍሎች ላይ የትምህርት ጥራት መፈተሽ አለበት። ተፈትሾ በተገኘ ግብረ መልስ መስተካከል አለበት። ይህ ሳይሆን ቀርቶ እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ ‹ኮርጀህ እለፍ› ማለት አንደኛ እና ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸውን ሙሰኞች እንደማፍራት ይቆጠራል። ስለዚህ የተማሪዎችን ውጤት መንግስት በእውቀትና ክህሎት ተንተርሶ መፈተሽ መጀመሩ መንግስትን የሚያስመሰግን ስራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በጥራት ተፈትነው አልፈዋል የተባሉት አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች በጥራት በማስተማሩ በኩል የዩኒቨርሲቲ መምህራንስ ምን ያህል ብቁ ናቸው ይላሉ?
ዶክተር አማኑኤል፡- አብዛኛውን ጊዜ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት የሚወሰነው በተማሪዎችም ፍላጎት ላይ ነው። ተማሪ የመረጠው የትምርት መስክ (ፊልድ) ወሳኝነት አለው። ሌላው ደግሞ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህሩ ተማሪዎችን የእሱን እውቀት ብቻ የሚያጎርስበት ስፍራ አይደለም። ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የገባ ተማሪ ከመምህሩ ውጪ የራሱ ልፋትና ትጋት በእጅጉ ይጠበቅበታል። መምህሩ አመቻች ነው። ስለዚህ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ራሳቸውን በሚጠበቅባቸው ልክ ማዘጋጀት የግድ ይላቸዋል እንጂ ከመምህሩ በሚሰጣቸው ብቻ ውጤታማ ይሆናሉ ተብሎ አይታሰብም።
በዩኒቨርሲቲዎቻችን የምናፈራቸው ተማሪዎች በአገራችን ብቻ ተወስነው የሚቀሩ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነት ያላቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል። ተማሪዎቹ አዳዲስ ሐሳቦችን ማመንጨት የሚችሉ መሆን አለባቸው።
በዚህ አግባብ በጥራት አለፉ ለተባሉ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ቀላል ቦታ ነው ብዬ አልገምትም። ምክንያቱም ከ700፤ 350 ይዞ የገባ ተማሪ የማብቃቱ ስራ በዩኒቨርሲቲው ላይ የተጣለ ቢሆንም ሌሎችም ባለድርሻዎች ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል። መምህሩን የበኩልን ለመወጣት ብዙ ሚና ይጫወታል ብለን እናስባለን። የተማሪውም ቁጥር አነስተኛ ስለሚሆን ጥራት ያላቸውን ተማሪዎች ለማፍራት ግን ምቹ ሁኔታ ይገኛል የሚል ሐሳብ አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን።
ዶክተር አማኑኤል፡- እኔም ስለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም