በ2023 የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን የመጀመሪያ ውድድሩን በአውስትራሊያዋ ባትረስት ከተማ ባለፈው ቅዳሜ አከናውኖ ከትናንት በስቲያ ሌሊት ወደ አገሩ ተመልሷል። ትናንት ለአትሌቶቾች በተከናወነው የአቀባበልና የሽልማት መርሃ ግብር ላይም በእንባ የታጀበ የልዩ ሽልማት መድረክ በስካይ ላይት ሆቴል ተከናውኗል። በስፖርታዊ የውድድር መድረኮች ያልተጠበቁ ሽንፈቶችና አሳዛኝ ሁኔታዎች መፈጠራቸው የተለመደ ነው። ኢትዮጵያ ከዓለም አገራት ሁለተኛውን ደረጃ ይዛ ባጠናቀቀችበት የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና ላይ የተከሰተው መሰል ሁኔታም የስፖርት ቤተሰቡ መነጋገሪያና ትኩረት ሆኖ ነበር።
በዚህ ቻምፒዮና እጅግ ተጠባቂ ከሆኑ አትሌቶች መካከል አንዷ በአዋቂ ሴቶች የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ላይ ተሳታፊ የሆነችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ ነበረች። ለተሰንበት የውድድሩን የአሸናፊነት መስመር ልታልፍ ጥቂት ሜትሮች ሲቀራት በድንገት በገጠማት ጉዳት እግሯን ለማዘዝ ተስኗት የድል ሪቫኑን ቀድማ መበጠስ ተስኗት ነበር። በዚህ ጊዜ የአሸናፊነቱን ክብር ልትቀዳጅ ጥቂት ሲቀራት የወደቀችውን ለተሰንበትን አሰልጣኟ ኃይለ ኢያሱ ወደ ውድድር ሜዳው በመግባት እንድትነሳ በመርዳት የውድድሩን ፍጻሜ መስመር እንድታልፍ ቢያደርጋትም አትሌቷ ከውድድር ውጪ ሆናለች።
ለተሰንበት በውድድሩ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ቢገጥማትም አንገቷን ሊያስደፋት እንደማይገባ ትናንት ቡድኑ በተሸለመበት ወቅት ተገልጧል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በሙሉም በእንባ ታጅበው ድጋፋቸውን ለለተሰንበት ገልጸውላታል። በመርሃ ግብሩ ታዳሚያን በጭብጨባ ታጅቦ በተካሄደው በዚህ ስነስርዓት ላይ አትሌቷ ሽልማቷን የተቀበለችው እያነባች ነበር።
ይህንን ተከትሎ ንግግር ያደረገችው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ከራሷ ተሞክሮ በመነሳትም ምክሯን ለግሳታለች። በዚህ የውድድር መድረክ ሶስት ወርቅ ሜዳሊያዎችን ያጠለቀችው አንጋፋዋ አትሌት ደራርቱ ‹‹በአትላንታ ኦሊምፒክ አሸንፋለሁ ብዬ ነበር የሄድኩት ነገር ግን አልሆነም፤ በቀጣይ ኦሊምፒክ ግን ወርቅ ማግኘት ችያለሁ። አንቺም በቀጣይ ወርቁን ታመጪዋለሽ። ከዚህ ቀደም በርካታ ውጤቶችን ያስመዘገበሽ አትሌት ብትሆኚም አሁንም ገና ብዙ ይቀርሻል። ከዝግጅት ጀምሮ እስከ ውድድር ድረስ ለፍታችኋል ከአሰልጣኞቻቹ ጋር በመሆን ትልቅ ነገር ሰርታችኋል፤ ለዚህም እናመሰግናለን›› ብላለች። ልዩ ሽልማቱን በሚመለከትም፤ ለተሰንበት ውድድሩን ለማሸነፍ ጥቂት ሲቀራት ባትወድቅ ኖሮ የወርቅ ሜዳሊያው ይመጣ ነበር፤ ስለዚህ ወርቁ እንደመጣ ተቆጥሮ ልዩ ሽልማቱ ሊሰጣት ይገባል በሚል ለወሰነው ስራ አስፈጻሚም ፕሬዚዳንቷ ምስጋናዋን ገልጻለች።
በግልና በቡድን 2 የወርቅ፣ 6 የብር እና 2 የነሃስ በጥቅሉ በ10 ሜዳሊያ ኬንያን ተከትሎ ውድድሩን በሁለተኛነት ለፈጸመው ቡድን የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶለታል። በዚህም የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት 45ሺ ብር ስታገኝ፤ የብር ሜዳሊያ ያጠለቁ 30ሺ፣ የነሃስ 15ሺ፣ ዲፕሎማ 10ሺ እንዲሁም ተሳትፎ ያደረጉ 10ሺ ብር ተሸላሚዎች ሆነዋል። ቡድኑ ከዚህም በላይ ውጤት እንደሚያስመዘግብ የተጠበቀ ቢሆንም ውድድሩ የተካሄደበት አውስትራሊያ ከርቀቱም ባለፈ በወቅቱ የነበረው ሙቀት እንዲሁም ከዚህ ቀደም ያልተለመዱ ሰው ሰራሽ መሰናክሎች አስቸጋሪ እንደነበሩም በቡድኑ አባላት ተገልጸዋል።
የብሄራዊ ቡድኑ የቴክኒክ ባለሙያ የነበሩት አቶ አስፋው ዳኜ፤ ውድድሩ ዳገታማ በሆነ ቦታ የተካሄደ፣ የሩጫው መነሻ ዳገት መጨረሻው ደግሞ ቁልቁለት የሆነ፣ ሰው ሰራሽ መሰናክሎቹ እስከ 60 ሳንቲ ሜትር የሚደርሱና አስቸጋሪ እንደነበሩ አብራርተዋል። ውድድሩ ጠንካራ ከመሆኑም በላይ ፈታኝ የሆኑ ተፎካካሪዎች ቢኖሩም፤ ቡድኑ ይህን ውጤት አስመዝግቦ መመለሱንም ጠቅሰዋል። የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የውድድሩ የቡድን መሪ የነበሩት ወይዘሮ ሳራ ሃሰን በበኩላቸው፤ ውድድሩ በተካሄደበት ወቅት በስፍራው የነበረው የአየር ሁኔታ ባልተጠበቀ መልኩ ከባድ ሙቀት እንደገጠማቸው አስታውሰዋል። ከጉዞው ጀምሮ ከባድ በነበረው ውድድር የቡድኑ አባላት በአብሮነት መስራታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ያደረጋቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
በአትሌቶች አቀባበል ስነስርዓቱ ላይ የታደሙት በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ ይህ ውጤት የሚያኩራራ ሳይሆን በቀጣይ ለሚካሄዱ ውድድሮች ትምህርት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። አትሌት ለተሰንበት ግደይንም ላደረገችው ጥረት አበረታተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም