በአውሮፓውያኑ በ1963፣ 32 ነፃ መንግሥታት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ያቋቋሙ ሲሆን፤ የድርጅት ራዕይ የነበረው አህጉሪቱ እየገጠሟት የነበሩትን ተግዳሮቶች እንዲሁም የቅኝ ግዛት እና የዘር መድልዎ ማስወገድ ነበር። በአውሮፓውያኑ በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ የአህጉሪቱ መሪዎች እየተለወጠ ባለው ዓለም አዳዲስ ተግዳሮቶችን ለመወጣት የድርጅቱን ራዕይ ማስተካከል አስፈላጊ መሆኑን ተወያይተዋል።
በዚህም የአፍሪካ ህብረት በአውሮፓውያኑ 2002 የአባላቱን ቁጥር 45 በማድረግ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ተክቶ፤ ስያሜውን ወደ አፍሪካ ህብረት ሲቀይር በደቡብ አፍሪካ ዳርባን የአፍሪካ ህብረት መሪዎች እና መንግሥታት የመጀመሪያ ጉባዔ ሲያደርጉ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህል እና በሌሎች ዘርፎች የአፍሪካን ማህበረሰብ ችግሮች ለመፍታት እንደ ዓላማ በመያዝ ተነስቷል፡፡ አሁን ላይ የአባል ሀገራቱ ቁጥር ከሃምሳ አራት በላይ ሆኗል፡፡
የአፍሪካ ህብረት በ54 አባል ሀገራት መካከል ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት መፍጠር፤ ልማትን ማሳደግ፣ ድህነትን ማጥፋት ወይም መቀነስ እና አፍሪካን ወደ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ማምጣት ግቡ ነበር። ለዚህም እንዲረደው በአውሮፓውያኑ 2013 የ2063 አጀንዳ ቀርጾ አህጉራዊ አንድነት ለመመስረት የሚያስችሉ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን መርሐ ግብሮች ለይቶ አስቀምጧል።
የአፍሪካ ህብረት አፍሪካን በዓለም አቀፍ መድረክ የበይ ተመልካች እንዳትሆን ከማድረግ በተጨማሪ ሁሉን አቀፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ አህጉራዊ ውህደት፣ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እና ሰላም እና ደህንነት መረጋገጥ ቅድሚያ ትኩረቱ ነው። በአውሮፓውያኑ ግንቦት ወር 2013 የአፍሪካ ህብረት ምስረታ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ባከበረበት ወቅት የአፍሪካ መሪዎችና መንግሥታት አፍሪካ በራሷ ዜጎች የምትመራ የተቀናጀ፣ የበለፀገች እና ሰላም የሰፈነባት አፍሪካን ራዕይ ለማሳካት እና በዓለም አቀፍ መድረክ የምትወከል አህጉር መፍጠር ግብ አድርገው አስቀምጠዋል፡፡ ይህንን ራዕይ ከአውሮፓውያኑ 2013 እስከ 2063 በአምሳ ዓመታት ውስጥ ለማሳካት ውሳኔ ላይ ደርሰው ነበር። ሌላው የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት፣ ማዕከላዊ ባንክ እና የገንዘብ ፈንድ እንዲሁም በያዝነው የአውሮፓውያኑ 2023 የአፍሪካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ በአንድ ገንዘብ ለማቋቋም ሰፊ እቅድ ነበራቸው፤ ዕቅዱ እንደልተሳካ ዛሬ ላይ መመልከት ይቻላል።
ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የታሰበውን ያህል ውጤት አላሳየም፣ በሚል በብዙዎች የሚተቸውና “ጥርስ የሌለው አንበሳ” በመባልም የሚታወቀው የአፍሪካ ህብረት አህጉሪቱን የተኩስ ድምጽ የማይሰማባት እና ከግጭት የጸዳች አደርጋታለሁ ቢልም የጥይት ድምጾች እንደተበራከቱ እስከ ዛሬ አሉ፡፡
መቀመጫውን ኖርዌይ ያደረገው የዓለም ሰላም ጥናት ተቋም መረጃ እንደሚያመለክተው፤ እንደ አውሮፓውያኑ በ2005 በአህጉረ አፍሪካ በስድስት ሀገራት ሰባት ግጭቶች የነበሩ ሲሆን፤ ይህ ቁጥር እያደገ እንጂ መቀነስን አላሳየም።፡ አፍሪካ ከግጭት እና ጦርነት ተለቃ አልታመለከትናትም፡፡ በተጨማሪም ወታደራዊ የመንግስት ግልበጣ ተበራክቶ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ቅንጦት ሆኖ ዛሬም ድረስ ዘልቋል።
የአፍሪካ ህብረት የብልጽግና እድል ከመፈጠሩ በፊት ግጭቶች መፈታት አለባቸው ብሎ በማመኑ፤ እነዚህን እና መሳል ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲረዳ ህብረቱ በአውሮፓውያኑ 2004 የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት አቋቁሟል፡፡ ይህ ምክር ቤት በግጭቶች ውስጥ ጣልቃ በመግባት ግጭቶችን መፍታት ተግባሩ ነው፡፡ ይህም የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተልዕኮ ማለትም የዘር ማጥፋት እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መከላከል ሲከሰቱ እንደ ሁኔታው ወታደራዊ ኃይሎችን በማሰማራት ግጭቶችን መፍታት እና ሰላም የማስከበር ተልዕኮዎችን መወጣት ኃላፊነቱ ነበር።
በዚህም እስካሁን የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል በቡሩንዲ፣ ሱዳን ዳርፉር ግዛት እና ሌሎችም ሀገራት ላይ አገልግሏል፤ ከአውሮፓውያኑ መጋቢት 2007 ጀምሮ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት ጦር በሶማሊያ ተሰማርቶ ይገኛል። በሌላ በኩል ህብረቱ በአውሮፓውያኑ 2010 ፈጣን ምላሽ ሰጪ ወታደሮች ተጠባባቂ ኃይል እንዲኖር አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አህጉሪቱ ከዓመታዊ በጀቷ 15 በመቶ የሚሆነውን ለጦር መሳሪያ ግዢ ይውላል። በሌላ በኩል አህጉሪቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ በልቶ ለማደር የምግብ እርዳታ ይጠብቃል፡፡ የምግብ ዋስትናና ስርዓተ ምግብ ካነሳን፣ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የሚኖሩ ከሁለት መቶ ሚሊየን በላይ ዜጎች የምግብ እርዳታ የሚሹ ናቸው፡፡
ለአህጉሪቱ የከፋ የምግብ እጥረት ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥና የኢኮኖሚ ችግር በተጨማሪ ምክንያትነት ቢጠቀሱም፣ ግጭት ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ የታጠቁ ኃይሎች እንደ አሸን መበራከት፣ ሙስና ሌሎችም ምክንያቶች ተደማምረው አፍሪካ ሰቅዞ ከያዛት ድህንነት እና ኋላ ቀርነት ፈቀቅ እንዳትል አድርጎታል፡፡
በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ብትሆንም ይህን ፀጋዋን ተጠቅማ መለወጥ እንዳትችል ሀብቷን መበዝበዝ እና መቀራመት በሚፈልጉ የተለያዩ ኃይሎች አህጉሪቱ ከግጭት ነፃ እንዳትሆን በተሰራው እና እስከ ዛሬም በዘለቀው ሴራ በድህንነት ውስጥ እየዳከረች ዛሬ ደርሳለች፡፡
በሌላ ጎኑ የአፍሪካ ህብረት ሁለንተናዊ እና ቀጣይነት ያለው የልማት ግቡን ለማሳካት ያለመ እና የመላው አፍሪካ የአንድነት፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን፣ የነፃነት፣ የእድገት እና የጋራ ብልፅግናን በፓን አፍሪካኒዝም መርህ ለማረጋገጥ የአፍሪካ ህብረት አዲስ አጋርነት ለአፍሪካ ልማት (ኔፓድ) አቋቁሞ በዚህም ድህነትን መቀነስ እና ልማትን በአፍሪካ ለማረጋገጥ ወጥኖ ቢንቀሳቀስም ውጤታማ ሲሆን እየተመለከትን አይደለም፡፡ እነዚህን ጉልህ ችግሮች መፍታት ዛሬም የአህጉሪቱ መሪዎች የቤት ስራ ሆኗል፡፡
ህብረቱ ዘንድሮ ለህብረቱ ማቋቋሚያ ጉልህ ሚና በነበራት ኢትዮጵያ (አዲስ አበባ) ሰላሳ ስድስተኛውን የመሪዎች ጉባኤ አካሄዷል። በአህጉሪቱ ነጻ የንግድ ቀጣና መፍጠር፣ ሰላምን ማስፈን፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ህብረቱ ከተወያየባቸው አጀንዳዎች መካከል ቢሆንም፤ በውይይታቸው የደረሱባቸውን የውሳኔ ሀሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ከፍ ያለ ቁርጠኝነት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም እራሳቸውን በሁለንተናዊ መንገድ ዝግጁ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
የቀደምት አፍሪካ መሪዎችን ራዕይ አሁን ያሉት ልጆቻቸው ከግብ ማድረስ እና ዓላማቸው የነበረውን ሰላም የሰፈነባት፣ የበለፀገች፣ ጠንካራ እና አንድነቷ የተረጋገጠ አፍሪካን እውን ለማድረግ አሁን ያሉት የአህጉሪቱ መሪዎች ከፍ ያለ ኃላፊነት አለባቸው፤ ለዚህም በንቃት ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም