እንደ መግቢያ
እማማ ባዩሽ ቅጣው ይባላሉ።በ90ዎቹ የዕድሜ ክልል ይገኛሉ። ከእርጅና ብዛት የተነሳ ብዙ ነገሮችን የዘነጉ ይመስላሉ። መመረቅ ደስ ይላቸዋል። በየመሃሉ እግዚአብሄር ይስጣችሁ ይላሉ። በእርጅና ብዛት ሙጭሙጭ ባሉ ዓይኖቻቸው እንባቸው ቁርርር ብሎ በጉንጫቸው ላይ ይወርዳል። በውስጣቸው ያለውን ኀዘን መቆጣጠር የሚችሉ አይመስልም።አጠገባቸው ሆኖ የሚያናግራቸውን ሰው ድምፅ እንጂ መልኩን ብዙም አይለዩም።
ተናግረው የማይጨረሱት ብሶት አለባቸው። ዓለም ጨክናባቸዋለች። ወንድሞቻቸውም ሆኑ እህታቸው በሕይወት የሉም። ኑሮም አልሞላላቸውም፤ በልጆቻቸውም አላለፈላቸውም። ኑሮ እንዲህ የጭ ካኔ በትሩን አሳርፎባቸው፣ ቀና እንዳይሉ ደጋግሞ ደቁሷቸው፣ በዘመድ አዝማድ ጠያቂ ናፍቋቸው ህይወታቸውን ቢያከብድባቸውም በፈጣሪ ተስፋ የቆረጡ አይመስሉም።
ደብረብርሃን ከተማ ተገኝቻለሁ። ቀበሌ 02 አካባቢ በአንዲት ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ነኝ። የእማማ ባዩሽ የክፉ ቀን ደራሼ የሚሉትን ዳንኤል ተስፋዬ የተባለን ወጣት ይዤ ነበር ከስፍራው የደረስኩት።
ሰፈሩ የተጎሳቆለ ነው። እርጅና በኃይለኛው የተጫጫናቸው ቤቶች ይበዛሉ። ጣሪያቸው ዝጓል፤ ወገባቸው ዘሟል። በአኗኗራቸው አንደኛው ከሌላኛው ብዙም የተሻለ ሰው እንደማይኖር መንደሩ በራሱ ያሳብቃል። ከጭቃ የተሰሩት ቤቶች አፍ አውጥተው ባይናገሩም ብስክስክ ያለ ጣሪያቸው፣ ፍርስርስ ያለው መደባቸው፣ የዘመመው ግድግዳቸውና ወደ ውስጥ ይሁን ወደ ውጭ ለመክፈት አቅጣጫቸው የማይለዩ በሮች እማኝ ሳያስፈልግ ሁሉንም ነገር ይናገራሉ።
አድማሱ ደግሞ በዚህ ሰፈር ከሚገኙ ደሳሳ ጎጆዎች መካከል በአንዱ ውስጥ የሚኖሩት የአቅመ ደካማዋ አዛውንት እማማ ባዩሽ ልጅ ነው። ቡና ሊያፈላ ደፋ ቀና እያለ ነበር። እርሱ ዕድሜውን በትክክል ባይነገርንም ጎረቤቶቹ ከ40 እስከ 45 ዓመት እንደሚሆነው ይገምታሉ። እናቱም የራሳቸውን ዕድሜያቸውን በወጉ አያውቁትም። ግን ከጠላት ወረራ በፊት መወለዳቸውን ያውቃሉ።
ጤናን ፍለጋ
እማማ ባዩሽ ደብረብርሃን ከተማን አልተወለዱ ባትም፤ የእንጀራ ገመድም አልጎተተቻቸውም። ነገር ግን ልጃቸው አድማሱ በልጅነቱ በጠና ታሞ በደብረብርሃን አካባቢ ከሚገኝ ፀበል ለማስጠመቅ ይዘውት መጥተው በዚያው ከረሙ። ግን ልጃቸው ከችግሩ ማገገም አልቻለም። እርሳቸውም ወደት ውልድ ቀያቸው አልተመለሱም። እማማ ባዩሽ ይጨነቁ የተባለ ልጃቸውን ከክርስትና አባቱ ዘንድ አስቀምጠውት ነበር አድማሱ የተባለውን ታማሚ ልጃቸውን ወደ ፀበል ይዘውት የሄዱት። እርሳቸው ስለይጨነቁ ሲያስቡ፤ ልጃቸውም ስለእናቱ ማሰቡ አልቀረም።
ይጨነቁ እናትና ወንድሙ ከአጠገቡ ሲጠፉበት በጭንቀት ውስጥ ማቋል። እነርሱን ጥሎ ብቻው እንደምን ይኖር፤ እንደምን ውሎ ይደር? ምድር ጨነቀችው፤ ወዲህ ደግሞ በአደራ ከተቀመጠበት ክርስትና አባቱ ቤት ብዙም ደስተኛ አልሆነም። በአንድ በኩል ናፍቆቱ በሌላኛው ጎኑ ደግሞ ብሶቱ አላስቀምጥ አለው። የኋላ ኋላ እናትና ወንድሙን መፈለግ እንዳለበት ወሰነ። እናም ወደ ደብረብርሃን በጎች እየነዱ የሚሸጡ ነጋዴዎች አገኘ። እነሱንተከትሎ ደብረ ብርሃን ደረሰ። እናትና ወንዱሙንም አገኘ፤ በዚያውም መኖር ጀመሩ።
በስቃይ የተገፉ 90 ዓመታት
እማማ ባዩሽን አቅም እያላቸው አንድ ጋን ሊጥ በአንድ ብር ሙሉ ቀን ሲያስጋግሯቸው ይውላሉ። እንጀራውን በቁጥር ባያውቁትም ግን ለሙሉ ቀን ሥራቸው ነበር አንድ ብር የሚከፈላቸው። ተከስተ ከሚባል ወፍጮ ቤት ዱቄት ያፍሱ ነበር። ከዚህም ሌላ ብዙ ሥራዎችን እየሰሩ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሯቸውን ገፍተዋል። ብቻ በየአምባው እየዞሩ ከኑሮ ጋር የሞት ሽረት ትግል ገጥመዋል። በዚህ ዕድሜያቸውም ትውልድ ፈጅ የሆኑ ጦርነቶችን ተመልክተዋል። «በተፈሪ የለም ፍርፋሪ» እየተባለ ሲተረትና ከጃነሆይ በኋላ ደርግ መተካቱንም በሚገባ ያስታወሳሉ። ኢህአዴግንም ጠንቅቀው ያውቃሉ። ነገ ስለሚሆነውም ደግሞ አብዝተው ይጨነቃሉ።
«ኑሮ እንዴት ነው እማማ?» በማለት ጠየኳ ቸው መቼስ መጠየቅ አይገድ። ‹‹ኑሮማ ይኸው እንደምታየው ነው ልጄ። ፃድቃን ይረዱናል። ሲርበን አብልተው፤ ሲጠማን አጠጥተው ከዛሬ ደርሰናል» አሉ በተሰበረ ቅስም፤ በሰለለ አንደበት። ልጃቸው አድማሱ ብር ቢሰጠውም ምን ከምን እንደሚያቀናጅ አያውቅም። የቱን ገዝቶ የትኛውን እንደሚተወው በቅጡ አያገናዝብም።
ግን ደግሞ ጎረቤቶቻቸውን ያመሰግናሉ። ካለቻቸው ላይ አካፍለው ያቃምሷቸዋል፤ ልብስ ያጥቡላቸዋል። ዳንኤል ተስፋዬ የሚባለው ልጅ ደግሞ ይበልጥ አዛኛቸው ነው። ልብስ ያመጣላቸዋል። ዳንኤል እማማ ባዩሽን ጨምሮ ደብረብርሃን ውስጥ 170 የሚጠጉ ሰዎችን ከለጋሽ አካላት እየለመነ የተገኘውን ሁሉ ያደርስላቸዋል። እማማ ባዩሽ የሚሰጣቸውን ብቻ ሳይሆን የሚጠይቃቸውን ሰው ሁሉ ይናፍቃሉ። የሰዎችን ድምጽ ሲሰሙ ተስፋቸው ይለመልማል።
የልጅ ናፍቆት
እማማ ብዙ ተስፋ የሚያደርጉት ነገር አላቸው። የመጀመሪያ ልጃቸው ይጨነቁ በዘመነ ደርግ ወደ ውትድርና ጥሏቸው ሄዶ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። ያኔ ከውትድርና ሳይተዋወቅ ወንድሜ እና እናቴ ናፈቁኝ ብሎ ከበግ ነጂዎች ጋር እርሳቸውን ፍለጋ ረጅም መንገድ ኳትኖ ያገኛቸው ልጃቸው ተመልሶ የሚፈልጋቸው ይመስላቸዋል።
ይጨነቁ መቶ አለቃ ማዕረግ ላይ እንደደረሰ ሰምተው ነበር። ዛሬ ቢያንስ በማዕረጉ ከፍ ያለ ቦታ ይደርሳል፤ ሁሉ ነገሩ የተሟላ መልካም ትዳር እንደሚኖረው ይገምታሉ። አንድ ቀን ከልጆቹ ጋር መጥቶ እኔም አያት ሆኜ እርሱም በሕወይት ኑሮ አገኘዋለሁ ብለው ያስባሉ። ምኞታቸው ሰምሮ ረጅም ዓመት መኖር ይፈልጋሉ። አድማሱ አንድ ቀን ጤናውን አግኝቶ እርሳቸውን እንደሚንከባከባቸውም ተስፋ ያደርጋሉ።
እማማ ባዩሽ ይጨነቁ መንገሻ የተባለው ልጃቸው አስተዋይ እንደሆነ ይናገራሉ። በቀበሌው ብዙ ሰው ያውቀዋል። ውትድርና ሳይሄድ ከአካባቢው ተመርጦ ስጋጃ ይሰራ እንደነበርም ይናገራሉ። ይጨነቁ ቀላ ያለ ጥርሰ ፍንጭት ነው። አንድ ቀን ይህ ልጃቸው እንደሚመጣ አሊያም ያለበትን ቦታ የሚጠቁማቸው ሰው እንደሚከሰት ተስፋ ያደርጋሉ።
ልጃቸው በዘመነ ደርግ ወደ ብሄራዊ ውትድርን ቢሄድም ዛሬም ድረስ ከዛሬ ነገ ይመጣል ብለው እየጠበቁት ነው።‹‹በአንድ ወቅት ብላቴ ከሚባል ሥፍራ ነበር። ደርግ ሊወድቅ ሲል አንድ ጋንታ ጦር እንደከዳ ሰምቻለሁ። ልጄም በዚሁ ወቅት ወደ ኤርትራ ሳይሄድ አይቀርም›› ይላሉ። ሞቶ ይሆናል የሚለውን ተስፋ አስቆራጭ ወሬ ለአእምሯቸው ፈጽሞ ሹክ ማለት አይፈልጉም። ድንገት ድምጹ ለየት ያለ ሰው ሲመጣ ልጃቸው የመጣ እየመሰላቸው የልባቸው ትርታ ይጨምራል። ልጃቸው በዓይነ ህሊናቸው ድቅን ይላል። «የይጨነቁ እናት» ሲሏቸው ልባቸው ድንገት ወደ ሌላ ዓለም ዘው ብሎ ይሄዳል። ስለልጃቸው እየተጨነቁ በትዝታ ምናብ ይወጣሉ ይወርዳሉ። የልጃቸውን ስም ሲጠራ ልባቸው ባር ባር እንደሚለው ይናገራሉ። ይጨነቁን የማያውቁ ደግሞ የአድማሱ እናት እያሉ ሲጠሯቸው ደስ ይላቸዋል።
ለልጄ የማወርሰው ቁልፌን
ብቻ ነው
እማማ ባዩሽ በራቸውን ክርችም አድርገው የሚቆልፉበት ቁልፉ ጓጉንቸር ይባላል። ከእርሳቸው ጋር 50 ዓመታት እንዳሳለፈ ይናገራሉ። በረጅም ጨርቅ ከአንገታቸው ላይ ነው የሚያንጠለጥሉት። ለልጃቸውም ሆነ ለእርሳቸው መጦሪያ ጥሪት አላስቀመጡም። የሚላስ የሚቀመሰውን ሁሉ የሚያገኙት በቸር ሰዎች መልካም ፍቃድ ላይ የተመሰረተ ነው። ታዲያ ለአድማሱ የሚያወርሱት አንድ ነገር አላቸው። ይህም ለዘመናት ሳይከዳ አብሯቸው ለ50 ዓመታት የኖረውን ‹‹ጓጉንቸር›› የተሰኘውን ቁልፍ ነው። አንገታቸውን ደፍተው፤ እጃቸውን አጣጥፈው ከጉልበታቸው ላይ አድርገው «ከዚህ ውጭ የማወርሰው ሌላማ ምን አለኝ?» ሲሉ በትካዜ ይናገራሉ።
«መልካም ሰዎች ሲገኙ ዓለም መልካም ይሆናል» ይላሉ እማማ ባዩሽ። ቤተክርስቲያን ለመሄድ ይናፍቃሉ። ግን ዓይናቸው ደክሟል፤ ጉልበታቸው ዝሏል። የሚመራቸው ሰው የለም። በአቅራቢያቸው ቤተክርስቲያን ቢኖርም ብቻቸውን መሄድ አይችሉም። በትራንስፖርት ለመሄድ ቢያስቡም ‹‹ባጃጅ›› ወደ ሰፈራቸው አይገባም፤ ባጃጅ ቢገኝም የሚጠይቁት ገንዘብ አቅማቸው እንዴት ፈቅዶ? እናም እንዲሁ ከቤት ሆነው ይፀልያሉ። ከምንም በላይ ‹‹አምላኬ የአገሬን ጉዳይ አደራውን›› ይላሉ። ኀዘንም ደስታም በአገር ነው። እንኳንስ ሰው አራዊቱ ሁሉ ካለ ሰላም ዋጋ የለውም ይላሉ። እማማ ባዩሽ።
ጎረቤቶቻቸውም እንደዛው እጅ አጠር ናቸው። ግን ኢትዮጵያዊነት የመረዳዳት ባህል ያስገድዳቸዋል፤ ህሊናቸው ይወቅሳቸዋል። ያገኙትን ነገር ለእማማ ያካፍላሉ። አንድ ዳቦ ካገኙ ለሁለት ይካፈላሉ። ኑሮ ክፋቱ ሁላችንን እጅ አነስ አደረገን የሚሉት እማማ ባዩሽ አንዳንድ ልባቸው የራራ ሰዎች ቤታቸውን አፈላልገው ይጠይቋቸዋል። ቡና ሲገኝ ቆልተው ለአድማሱ ይሰጡታል። አድማሱም እንደምንም ብሎ አፍልቶ ያጠጣቸዋል።
አስፋልት የሚፈራው አድማሱ
አድማሱ በሕይወት ዘመኑ ብቻውን ከቤታቸው በ50 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን አስፋልት ተሻግሮ አያውቅም። ትንሽ ግጭትም ካየ ይፈራል፣ ይጨነቃል፤ ህመሙ ይነሳበታል። ምንም ዓይነት ድምፅ መስማት አይፈልግም። ፀጥታ ይመቸዋል። ስለመብላትና መጠ ጣት ብዙም አይጨነቅም።
እኔም አድማሱን ለማናገር ሞከርኩ። ነገር ግን ትንሽ ትንሽ ሃሳቡን ከመግለፅ በዘለለ በአግባቡ አይናገርም። ወደ ከተማ እንውጣ ስለው «አልወጣም» አለኝ። ለምን አልኩት። ‹‹እዛ ጥሩ አይደለም!›› ከማለት ውጭ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ሊሰጠኝ አልፈቀደም። ና! እንሂድ ብዬ ስንነሳ በፍጥነት ዘሎ ወደ ጓዳ ገባ። አድማሱ ዕድሜ ዘመኑን አደባባይ ፈርቶ፤ ከጓዳ ተደብቆ ለመኖር ተገዷል። ጉረቤቶቹ ሲጠፉ አድማሱን ይከፋዋል። የእርሱ ተስፋ ጠዋትና ማታ እነርሱን ማየቱ ብቻ ነው። አድማሱ ከመደበኛው የሰው ልጆች አኗኗር ተነጥሎ ዕድሜውን ይቆጥራል።
ግን ማን ያውቃል? አንድ ቀን ችግሩን ተረድቶ የሚያግዘው ቢያገኝ አደባባይ ይናፍቅ ይሆናል። አንድ ቀን እንደ ዕድሜ እኩዮቹ ከተማውን ብቻ ሳይሆን ከከተማው ርቆ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ይቃኝ ይሆናል። ማን ያውቃል አንድ ቀን የእናቱ ምኞት ሰምሮ ጤናውን አግኝቶ፤ የእናቱ ጧሪ ቀባሪ ይሆናል። ምናልባትም እናቱ ያዘጋጁለትን ‹‹ጓጉንቸር›› የተባለውን የቤት ቁልፍ ብቻ ሳይሆን፤ ጤናው ተሻሽሎ እንደ እናቱ ጠንካራ ሆኖ ብዙ ኃላፊነቶችን ይውርስ ይሆናል። «ዓለም ዘወርዋራ ለአንዱ ቀኝ ለአንዱ ግራ» ማለት ይህ አይደለምን? እማማ ባዩሽና ልጃቸውን ለመርዳት የምትፈልጉ ካላችሁ በዝግጅት ክፍላችን አድራሻ ታገኟቸዋላችሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር