የአርሲ ዞን ያለውን እምቅ የስፖርት አቅም ለመጠቀም ከትምህርት ቤቶች ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁማል። ዞኑ በስፖርቱ ዘርፍ ተተኪዎችን ለማፍራትና ውጤታማ ለመሆን ከትምህርት ቢሮ ጋር በትብብር እንደሚሰራም አስታውቋል።
አርሲ ዞን በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላት ስፍራ ነች። በተለይ በአትሌቲክስ ከኢትዮጵያም አልፎ በዓለም መድረክ አስገራሚ ገድሎችን በመፈጸም ታሪክን የከተቡ አትሌቶች መነሻ መሆንዋ ይታወቃል። እነዚህ አትሌቶች ዞኗን እንደ መነሻ እንዲሁም በቆጂንና አሰላን እንደመንደርደርያ በመጠቀም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ዝናን እንድትጎናጸፍ አድርገዋል።
ዞኑ በአንድ የስፖርት ዘርፍ ብቻ ጎልቶ የወጣው ስሙን በሌሎች ስፖርቶችም ለመድገም በትምህርት ቤት ደረጃ ለመስራት ቆርጦ ተነስቷል። የአርሲ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ስፖርቱን ወደ ትምህርት ቤቶች በማውረድ ከዞኑ ትምህርት ቢሮ ጋር መስማማቱን ገልጿል። ቢሮው በትምህርት ቤት ደረጃ እስከ አሁን እንዳልተሰራበትና ከተያዘው ዓመት ጀምሮም ሊሰራበት እንደተዘጋጀ ነው የገለፀው።
ቢሮው ከአትሌቲክሱ በተጨማሪ በሁሉም ስፖርት ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም ትምህርት ቤት ላይ ትኩረት በመስጠት ታዳጊዎችን ለማፍራት በመተባበር ለመስራት ዝግጁቱን ጨርሶ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ያስታወቀ ሲሆን፣ ከወረዳ እስከ ዞን ድረስ ለስፖርቱ ጠቃሚ ስራዎችን እያከናወነም ይገኛል።። በትምህርት ቤት ደረጃ ሊሰራባቸው ከታሰቡ የስፖርት ዘርፎች ውስጥ አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ ቴኳንዶ፣ ቴኒስ፣ ቅርጫት ኳስና ሌሎች የስፖርት አይነቶች ይገኙበታል። ዞኑ ከውሃ ዋናና ሜዳ ቴኒስ በስተቀር አብዛኛውን የስፖርት እንቅስቃሴ አቅፎ እንደሚገኝም አስታውቋል።
የአርሲ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ሽፈራው ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ የአርሲ ዞን የአትሌቲክስ መፍለቂያ ብቻ ተደርጋ ብትታሰብም በሌሎች በርካታ የስፖርት አይነቶች ትልቅ አቅም አላት። በተለይም እግር ኳስ የተሻሉ ስፖርተኞችን ከስፍራው መውጣት እንደሚቻል የገለፁት አቶ ጌቱ፣ አርሲ እንደ ባህሏ የሚቆጠረው የአትሌቲክስ ስፖርት ቀድሞ የነበረው ውጤታማነት እየቀነሰ ቢሆንም መፍትሔ ሊሆን የሚችለው በትምህርት ቤት የሚገኘውን እምቅ አቅም ተጠቅሞ ሲሰራና ትክክለኛ ተተኪን ማግኘት ሲቻል መሆኑን አስረድተዋል።
ዞኑ በዘንድሮ ዓመት 40 ወጣቶችን ወደ ጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ በቆጂ አትሌቲክስና ቦሬ ማሰልጠኛ ማዕከል ገብተው እንዲሰለጥኑ ማድረጉን አቶ ጌቱ ተናግረዋል። ይህን ለመጨመርና ብቃት ያላቸውን ስፖርተኞች ለማፍራት ከፕሮጀክቶች በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ትክክለኛ ቦታ እንደሆኑም አብራርተዋል።
ክለብ አለመኖሩ አርሲን ዞን ስፖርት እንደጎዳው የገለጹት ኃለፊው፣ ‹‹የኛ ልጆች ተስፈኛ ተብሎ ለብቻ ይያዛሉ ክለብ ውስጥ አይገቡም ስለዚህ ሲወዳደሩ ከኛ ጋር ተመልሰው ይወዳደራሉ፣ በዚህም አርሲ ወደኋላ ይቀራል እኛ ደግሞ ቀጥረን የምናስቀምጥበት ብር የለንም፣ ስለዚህ ክለብ እንደ አርሲ መመስረት አለበት የሚል አላማ አለን›› ሲሉም ተናግረዋል። በዚህም መሠረት ፕሮፖዛል ተሰርቶ ማለቁንና የዞኑ ምክር ቤት ውሳኔ ሲሰጥበት ክለቡን ወደመመስረት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
እንደዞኑ በፌደራል መንግስትና በክልሉ የሚደገፉ ሁለት ሁለት ፕሮጀክቶችና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቀሟት የሚደገፉ ሌሎች ፕሮጀክቶች እንዳሉ አቶ ጌቱ ይናገራሉ። በእግር ኳሱም ጥሩ እንቅስቃሴ መኖሩን የሚጠቁሙ ነገሮች እንዳሉ የገለጹት አቶ ጌቱ፣ ከዞኑ ወደ ኦሮሚያ ሊግ ያደጉ ክለቦች ስምንት መሆናቸውንም ገልፀዋል። በዞኑ ስፖርት ትልቁ ችግር የበጀት ችግር ሲሆን ክለቦቹ የሚደገፉት በከተማ በመሆኑ ምንያክል ርቀትን ይዞ ይጓዛሉ የሚልም ስጋት እንዳለም አክለዋል።
ከትምህርት ቤት ጀምሮ መስራቱ የተሻለ ቢሆንም በአትሌቲክስና በእግር ኳሱ ክለብ መቋቋም እንደሚኖርበት የገለፁት አቶ ጌቱ፣ ክለብ ካልተቋቋመ ከስር ጀምሮ መስራቱ ዋጋ እንደማይኖረውና ህዝቡም ይህን ከግምት በማስገባት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል። አክለውም ‹‹እኔ ባለሙያም አመራርም ነኝ፣ እዚ ቦታ ላልቆይ እችላለው ነገር ግን ማንም ቢመጣ ክለብ እስካልተቋቋመ ድረስ በአትሌቲክሱ አመርቂ ውጤት ለማምጣት ያስቸግራል›› ብለዋል።
ዞኑ ለጊዜው በአትሌቲክስ የውጤት ማጣት በመኖሩ ክለብ የማቋቋሙን እቅድ ለአትሌቲክሱ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ነው። አትሌቲክስ ብዙ በጀት አለመጠየቁና ከሱ ከሚገኝ ገቢ እግር ኳሱን መደገፍ የሚቻል በመሆኑ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደታሰበ ታውቋል።
የታሰበው የክለብ ምስረታ እንዲሳካ ለአርሲ ዩኒቨርሲቲም ፕሮፖዛል ቀርቦ ጉድለቱ ተለይቶ የባለሙያ ስልጠናዎች መሰጠታቸው ተጠቁሟል። በተጨማሪም አርሲን ዞን እንዴት ወደፊት ማስኬድና በትብብር መስራት እንደሚቻል በመነጋገር በመስራት ላይ መሆናቸውን ኃላፊው አስረድተዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም