የአፍሪካ ህብረት አፍሪካ አንድነት ድርጅት ተብሎ ቀድሞ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የአህጉሪቱ ህዝቦችን ተጠቃሚ ያደረጉ ሰፊ ስራዎችን ሰርቷል፤ እየሰራም ነው። ይህም ሆኖ ግን አህጉሪቱ ካሉባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አንጻር ገና ብዙ መስራት እንዳለበት ምሁራን እና ያልተሰሩ የቤት ስራዎቹ ምስክሮች ናቸው፡፡
ከዚህም ባለፈ ከግማሽ ክፍለ ዘመን ቆይታ በኋላ ተልዕኮውን አድሶ በ1993 ዓ.ም ግንቦት ላይ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት የሚል ስያም ያገኘው የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት የስያሜ እንጂ ብዙም የመዋቅር ማሻሻያ አላደረገም በሚል በርካቶችም ይወቅሱታል፡፡
በርግጥ አፍሪካ ብዙ ነገዎቹዋን ብሩህ ሊያደርጉ ይችላሉ የተባሉ ብዙ አጀንዳዎች ያሏት አህጉር ነች፡፡ ለማሳያ ያክል አጀንዳ 2063 በሚል በግዙፉ የወጠነችው እንይ፡፡ ይህ ውጥን ‹‹ሁሉን አቀፍ በሆነ ዕድገትና ዘላቂ ልማት የበለጸገች አፍሪካን መፍጠር፣ በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤዎችና በአፍሪካ ሕዳሴ ራዕይ አማካኝነት የተሳሰረ እና ፖለቲካዊ አንድነት ያለው አህጉር እውን ማድረግ፣ አፍሪካን መልካም አስተዳደር የሰፈነበት፣ የሰብዓዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት የሚከበርበት፣ ፍትሕ የነገሰበትና ዴሞክራሲያዊ አህጉር ማድረግ›› የሚል እሳቤ ያዘለ ነው።
‹‹ሰላሙንና አንድነቱን የጠበቀ አፍሪካን መፍጠር፣ ጠንካራ የባህል ማንነት፣ የጋራ ቅርስና እሴቶች ያሉት እንዲሁም ጠንካራ ማህበረሰባዊ የሞራል መሰረት የፈጠረ አፍሪካን ማየት፣ የአፍሪካ ልማት ዜጎችን ማዕከል ያደረገ የአፍሪካን ሕዝብ በተለይም የወጣቶችና ሴቶችን አቅም የሚጠቀምና ለሕጻናት ክብካቤ ትኩረትን የሰጠ እንዲሆን ማድረግ፤ ጠንካራ፣ አንድነቱን የጠበቀ፣ የማይበገርና በዓለም መድረክ ተጽዕኖ ፈጣሪና አጋር የሆነ አፍሪካን መፍጠር›› የሚሉት ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው
ምንም እንኳ እነዚህ ግዙፍ አጀንዳዎችን ይዞ ብትነሳም አሁንም በዓለም ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎዎች ውስጥ ከበይ ተመልካችነት እልፍ ያለ ድርሻ የላትም፡፡ በየቀኑ ለተራቡ ወገኖች ዕርዳታ ከመለመንና የድረሱልኝ ጥሪ ከማቅረብ የዘለለ ውሃ የሚቋጥር አህጉራዊ ለውጥ እምብዛም አይታይም፡፡
አጀንዳ 2063 ላይ የአፍሪካ ህብረት በየአመቱ ስብሰባውን ሲያካሂድ ውይይት ይረግበታል። ተፈጻሚ ለማድረግም እንደሚተጉ የየአገራቱ መሪዎች አሊያም ደግሞ ተወካዮች ደጋግመው ቃል ይገባሉ፡፡ ዳሩ ግን በተግባር ገና መሬት አልወረደም፡፡
በአጀንዳ 2063 አንዱና መሰረታዊ ጉዳይ ተብሎ የተቀመጠው ሌላው ጉዳይ በአፍሪካ ምድር የጥይት ደምፅ የማይሰማባትና ዴሞክራሲ ያበበባት አህጉር መመስረትና ማየት የሚል ነው፡፡ ይህ ሃሳብ መልካም ሆኖ ሳለ መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ከተፃፈው ጋር ከቶውምንም የማይገናኝ ነው፡፡
ይህ ትርክት ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ በዚያው ልክ በርካታ ፖለቲካዊ ምርጫዎች ተደርገዋል፡፡ ዳሩ ግን አብዛኞቹ ምርጫዎች ያለ ጥይት ደምጽ አልተጠናቀቁም ወይንም ምርጫዎቹ ሙሉ ለሙሉ በሰላማዊ መንገድ አልተቋጩም፡፡ ጎረቤት አገራትን ማንሳት ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ በኬኒያ በተደጋጋሚ ደም መፋሰሶች ነበሩ፡፡ በሞቃዲሾ ምርጫን ማሰብ ቅንጦት ሲሆን የታሰቡትም በቦንብና ከባድ መሳሪያ እርሙታ የታጀቡ ነበሩ፡፡
ጎረቤት አገር ደቡብ ሱዳንም ከዴሞክራሲ ጋር የተኳረፈች አገር መስላለች፡፡ እንኳንስ ምርጫ ቀርቶ ዜጎች በሰላም በአገራቸው ለመኖራቸውም እንጥፍጣፊ ዕድል እስከማጣት ደርሰዋል፡፡
ሱዳን የተመለከትን እንደሆነ ከዋና ከተማዋ ካርቱም እስከ ጠረፍ ድረስ በንቃቃት ውስጥ እንደምትሽሎከለክ ዓይጥ ሆናለች- ላለፉት አምስት ዓመታት ገደማ፡፡ በወታደራዊ እና ሲቪል መንግስት መካከል ባለው ሽኩቻ ለከፋ ችግር ተዳርጋለች፡፡ ደም መፋሰሱ ሆነ ስደቱ አሁን አስከፊ ገጽታ ሆኖ ተጋርጦባታል፡፡
በመላ አገሪቱ የሚቀጣጠለው አመፅ ልክ እንደ አውሎ ንፋስ እያናወጣት ነው፡፡ ለሳምንታት ጋብ የሚለው የህዝብ ቁጣ አንዳችም መስመር ሳይዝ በድጋሚ እንደ ጉሽ ጠላ ኩፍፍፍ… ብሎ መልሶ እያናወጣት ይኸው ዛሬ ደርሳለች፡፡ አሸማጋዮች ኸረ ባካችሁን ቢሏቸውም ሰሚ ጆሮ ከጠፋ ሰነባብቷል፡፡ በኢትዮጵያም ተስፋ ሰጭ ተሞክሮ ቢኖርም ለውጡን ተከትሎ በተፈጠሩ ችግሮች አገርና ህዝብ ዋጋ ከፍለዋል።
እንግዲህ የምሥራቅ አፍሪካ አገራትን ለአብነት አነሳን እንጂ የአፍሪካ ነገር በደምሳሳው ‹‹ተከድኖ ይብሰል›› ነው፡፡ የአፍሪካ የተለያዩ ቀጣናዎች ከጦርነትና ግጭቶች እስከ መፈንቅለ መንግሥት ያሉ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮችን እያስተናገዱ ዛሬም አሉ፡፡ በየዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባም ይህንን ጉዳይ በእጅጉ አሳሳቢ ስለመሆኑ ይመክርበታል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግብጽ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ማሊ፣ ጊኒ ማዳጋስካር፣ ኮትዲቯር፣ ቶጎ፣ ጊኒ፣ ሱዳን፣ ዚምባብዌ ውስጥ ተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግስት የተካሄደባቸው አገራት ናቸው፡፡ ህብረቱ ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ 200 የሚደርሱ መፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች መኖራቸውንም ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
በእነዚህ ሙከራዎች ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መሰረታዊ የሚባሉ መብቶቻቸውን የተነፈጉ ሲሆን፤ የዴሞክራሱ ጭላንጭሎችም በራቸው ተከረችሞ ስለመዘጋቱ በግልጽ የታየበት ነው፡፡
በየቀጣናው የግጭት ድግሶች፤ የጦር ጉሰማዎችና እልቂቶች በየቀኑ ይሰማሉ፤ የሚሊዮኖች ሕይወት ይቀጠፋል፤ በቢሊዮን የሚቆጠር ንብረት በየዓመቱ ይወድማል። ሽብር እና አሸባሪ በየማዕዘናቱ እንደ አሸን እየፈሉ ነው።
ስደት፣ ሞት፣ ስቃይ፣ ርሃብማ እርዛት የአህጉሪቱ ብቸኛ መለያ እስከመሆን ደርሷል። በዚህ ሁሉ መሃል ግን የኅብረቱ ሚና እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፣ በዚህም የተነሳ ይህ ድርጅት ወይንም ህብረት ‹‹ጥርስ አልባ አንበሳ›› ሆኗል በሚል ወቀሳ ይቀርብበታል፡፡
አፍሪካ እንዲህ ናት፡፡ ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው እውነታ ግን ሌላ ነው፡፡ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ የአፍሪካ ህብረት መዋጮ ሙሉ ለሙሉ በራስ አቅም መሸፈን አለመቻሉ ነው። ጥቂት የማይባሉ አገራት ደግሞ የአባልነት መዋጮ መክፈል ባለመቻላቸው ከአባልነት እንደሚሰረዙ ጭምር ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲደርሳቸው ይሰማል፤ የአደባባይ ሚስጥርም ከሆነ ሰነባብቷል፡፡
የሪፖርተር ጋዜጣ በ2014 የአፍሪካ ህብረትን በተመለከተ ባስነበበው ሰፊ መጣጥፍ ውስጥ ‹‹እ.ኤ.አ. በ2020 የአፍሪካ ኅብረት በጀት 647 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 157 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሥራ ማስኬጃ፣ 216 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ለፕሮግራም ወጪዎች፣ እንዲሁም 273 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ለሠላም ድጋፍ ዘመቻዎች ድጋፍ የተመደበ ነው፡፡
ከጠቅላላው በጀት በአባል አገሮች የሚሸፈነው 38 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ 61 በመቶ ደግሞ ከአጋሮች ይገኛል ተብሎ የተቀመረ ነው። ከዚህ ባለፈም ሁሉም አባላት በታማኝነት የሚጠበቅባቸውን መዋጮ አያደርጉም፡፡›› የሚል ነበር፡፡
እንግዲህ የአፍሪካ ህብረት በጀት በቂ፣ አስተማማኝና ተገማች ምንጭ ሊኖረው እንደሚገባና ይኼም ልማቱንና የትስስር ግቦቹን ለማሳካት ወሳኝ እንደሆነ ዕሙን እንደሆነ የኅብረቱ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ ኅብረቱ በፋይናንስ ረገድ ያሉበት ችግሮች የገቢዎች ኢ-ተገማችነትና ተለዋዋጭነት፣ በውጭ አጋሮች ላይ የተመረኮዘ መሆን፣ በጥቂት አባል አገሮች መዋጮ ላይ ጥገኛ መሆን፣ ለሚወጣው ገንዘብ ዋጋ መስጠትና ቁጥጥር፣ እንዲሁም በየጊዜው የሚያድግ በጀት ናቸው፡፡
ይህም አፍሪካ ከሃሳብ የዘለለ የሐሳቡን ግብ መምታት እውን ለማድረግ የፋይናንስ ምንጭ ራሳቸው አለመሆናቸው ትልቁ ፈተና ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ አጀንዳ 2063 እንደምን ማሳካት ይቻል ይሆን?
ሲጠቃለል፤ የአፍሪካ ህብረት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የሚኖሩባቸውን 55 አባል አገሮችን የሚወክል ተቋም ነው፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ያለው ተደማጭነትም የሚወክለውን ህዝብ ያህል አይደለም። የሥም እንጂ የተግባር ህብረት ይጎድለዋል፡፡
ከሌሎች አቻ ህብረቶች ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ነገሩ ከዚህ የበለጠ አነጋጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ የአውሮፓ ህብረትን ብናነሳ በቆዳ ስፋት፣ ሃብት ሆነ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ አኳያ ከአፍሪካ ጋር አቻ ሊሆን ቀርቶ በብዙ ማይል ልዩነት ያለው ነው፡፡ ይሁንና ግን የአፍሪካ ህብረትን በገንዘብ ቀጥታ ከሚደጉሙት መካከል በቀዳሚነት የሚነሳ ነው፡፡
የአፍሪካ ህብረት ከስያሜው የዘለለ በተግባር ብዙ ያልተራመደ አዛውንት ተቋም ነው፡፡ ሥምና ግብሩ አልተመጣጠኑለትም፡፡ በመሆኑም ህብረቱ በሰፈው ከልቡ አቅዶ ሊሰራ ይገባል፡፡ አጀንዳ 2063 ሆነ ሌሎች እቅዶችም ቁጥር ብቻ እንዳይሆኑ መንቃትና መሥራት ይጠበቅባታል፡፡
የአፍሪካ ብሩህ ነገዎች ከሁሉም በላይ የአህጉሪቱን መሪዎች ከፍያለ ቁርጠኝነት የሚጠይቁ ናቸው። ከአቋም መግለጫዎች ወጥተው በተጨባጭ ማድረግ የሚችሉትን በማድረግ በአህጉሪቱ ህዝቦች ታማኝነትን ማትረፍ ይጠበቅባቸዋል።
አፍሪካ ከጥገኝት የወጣ እሳቤ ባለቤት መሆን በምጣኔ ሃብት መመንደግ አለባት፡፡ በፖለቲካው መርቀቅ ይጠበቅባታል፡፡ የአፍሪካ ህብረት መጠንከር ፤ በዓለም መድረክ ምላሽ ለማግኘት የአገራቱ አንድነት መሬት መያዝ አለበት፡፡
‹‹የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች በተናጠል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተመጣጣኝ ውክልና እናግኝ›› የሚለው ድምጻቸውም ተሰሚነት የሚያገኘው በአንድነት መቆም ሲችሉና ህብረታቸውን በሚገባ ሲጠናከር ነው፡፡
በአጠቃላይ የአፍሪካ ህብረት ከውልደቱ ጀምሮ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ብዙ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስራዎችን መስራት ቢችልም፤ ከ1993 ዓ.ም በኋላ በወረቀት ያሰፈራቸውን ውጥኖቹን በስኬት ለማጠናቀቅ የሄደበት ርቀት ብዙ የሚቀረው ነው።
ዶክተር ጀኔኑስ
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም