የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን አዲሱን የውድድር ዓመት በሃገር አቋራጭ ውድድር ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ በድል ጀምሯል፡፡ በዕፅዋት የተከፋፈሉ መተላለፊያዎች፣ ረግረጋማ፣ ዳገታማ፣ ቁልቁለታማ፣ አቧራማ፣ ሜዳማ ስፍራዎች እንዲሁም በሰው ሠራሽ መሰናክሎች ፈታኝ በሆነው ሀገር አቋራጭ ውድድር የአትሌቶች ጽናት በእጅጉ ይፈተናል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው ሻምፒዮና ግን በግል 1 የወርቅ፣ 3 የብር እና 1 የነሃስ ሜዳሊያ እንዲሁም በድብልቅ ሪሌ 1 የብር ሜዳሊያ አስመዝግበዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሚታወቁበት የቡድን ሥራም 1 የወርቅ እና 3 የብር ሜዳሊያዎች የተገኙ ሲሆን፤ በዚህ ውድድር በጥቅሉ 10 ሜዳሊያዎችን ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ይኸውም ኢትዮጵያ በውድድሩ ከተካፈሉ የዓለም ሃገራት በወርቅ ሜዳሊያ ቁጥር ብቻ ተበልጣ ሁለተኛ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል፡፡ ዩጋንዳ፣ አሜሪካ እና አውስትራሊያ ደግሞ ተከታዮቹ ሃገራት ሆነዋል፡፡
የ44ኛው የዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሳትፎውን የጀመረው በብር ሜዳሊያ ነው፡፡ ንጋት ላይ በተጀመረው የድብልቅ ሪሌ 8 ኪሎ ሜትር ውድድር ተሳታፊ የነበሩት አዳነ ካህሳይ፣ ጌትነት ዋለ፣ ሐዊ አበራ እና ብርቄ አበራ ተካፋይ ነበሩ፡፡ በውጤቱም ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በኬንያ ተቀድመው አዘጋጇን አውስትራሊያን በማስከተል ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የብር ሜዳሊያውን ማጥለቅ ችለዋል፡፡
በቀጣይ በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ውድድር ኢትዮጵያ ሁለት ሜዳሊያዎችን ማስቆጠር ችላለች፡፡ በዚህ ውድድር አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያውን ያጠለቀችው አትሌት ሠናይት ጌታቸው ስትሆን የገባችበት ሰዓትም 20፡53 ሆኖ ተመዝግቦላታል፡ ሌላኛዋ አትሌት መዲና ኢሳ ደግሞ ከሰባት ሰከንዶች መዘግየት በኋላ ኬንያዊያን አትሌቶችን በማስከተል ሁለተኛ ሆና መግባት ችላለች፡፡ ከውድድሩ በኋላም አሸናፊዋ አትሌት ሠናይት ‹‹ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመሆን በጥሩ የቡድን ስሜት ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል። ይህንኑ በውድድሩ ላይ በመተግበራችንም አሸናፊ ልሆን ችያለሁ›› ስትል ምስጋናዋን አብረዋት ለሮጡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሰጥታለች፡፡ የ17 ዓመቷ ወጣት አትሌት በጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሃገር አቋራጭ ውድድር ሦስተኛ በመሆን ነበር ሩጫዋን የፈጸመችው፡፡
ከ20 ዓመት በታች የወንዶች ውድድርም በግል ሁለተኛው የነሐስ ሜዳሊያ ተመዝግቧል፡፡ በውድድሩ ኢትዮጵያውያኑ ወጣት አትሌቶች አስደናቂ የቡድን ሥራ በመሥራት ለኬንያ እና ኡጋንዳ አትሌቶች ፈተና መሆናቸው አልቀረም፡፡ ይሁንና ኬንያውያኑ (እስማኤል ኪፕኪሩይ እና ሬይኖልድ ቺሩዮት) አጨራረስ ላይ ባሳዩት ብቃት አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የድል ባለቤት ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያዊው አትሌት ቦኪ ዲሪባ የነሐስ ሜዳሊያ ሊሆን ችሏል፡፡ አሸናፊ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የቆየው ቦኪ ከአሸናፊው አትሌት በሁለት ሰከንዶች ብቻ ተበልጦ 24 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ የሆነ ሰዓት ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡ በቡድን ደግሞ የብር ሜዳሊያ ተገኝቷል፡፡
የምስራቅ አፍሪካውያን ውድድር ይመስል በነበረው የአዋቂ ሴቶች የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ከመነሻው አንስቶ ፉክክሩ በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ዩጋንዳ፣ እና ኬንያ አትሌቶች መካከል ነበር ጠንካራ ፉክክር ሲታይ የቆየው። በዚህ ውድድር ለአሸናፊነት እጅግ ተጠባቂ የነበረችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ ቀድሞ ከወጣው የምሥራቅ አፍሪካዊያን ቡድን መጨረሻ ሆና በእርጋታ ስትከተላቸው መቆየቷን ተከትሎ ውድድሩ በቀጥታ በሚያስተላልፉት ባለሙያዎች ጭምር በራስ ከመተማመን ስሜት የመነጨ ስለመሆኑ በአድናቆት ሲነገርላት ቆይቷል፡፡ ርቀቱ ከተጋመሰ በኋላ ግን እንደተጠበቀው ለተሰንበት ከቡድን አጋሯ ጽጌ ገብረሰላማ ጋር በመሆን ወደፊት በመውጣትና ከኬንያውያን ተቀናቃኞቿንም በማስከተል የአሸናፊነት መስመሩ ጋር ለመድረስ ጥቂት እርምጃዎች ሲቀሯት ያልተጠበቀ ሁኔታ አጋጠማት፡፡ ብርቱዋ አትሌት አሸናፊነቷን ባረጋገጠችበት ቅጽበት ቁርጭምጭሚቷ አካባቢ በደረሰባት የእግር መታጠፍ የመውደቅ አደጋ ስለደረሰባት አራተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የግድ ሆኗል።
በዚህም መሠረት የአዋቂ ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር ሩጫ አሸናፊ ኬንያዊቷ ባትሪስ ቺቤት ልትሆን ችላለች። ለነሐስ ስትጠበቅ የቆየችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጽጌ ገብረሰላማ ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያውን ስታጠልቅ፣ ኬንያዊቷ አግነስ ጂቤት ደግሞ ተከትላት ገብታለች፡፡ ልብ ሰባሪ በሆነው አሳዛኝ ገጠመኝ በመድረኩ ሦስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያጣችው ለተሰንበት ግደይ በሰከንዶች እድሜ በመዘግየቷ የዲፕሎማ ተሸላሚ ሆናለች፡፡
በመጨረሻ በተካሄደው የአዋቂ ወንዶች 10 ኪሎ ሜትር ውድድር ደግሞ ኡጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞ ቀዳሚው አትሌት ሲሆን፤ በሪሁ አረጋዊ አራተኛውን የብር ሜዳሊያ ለሃገሩ ማስገኘት ችሏል፡፡ የ5ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የዓለም ክብረወሰን (12፡49) ባለቤቱ አትሌት ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ሰዓት 29 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ ሆኗል፡፡ ይኸውም ከአሸናፊው አትሌት በዘጠኝ ደቂቃ ብቻ የዘገየ ነው፡፡ እአአ 2019 ላይ በዴንማርክ አህሩስ በተካሄደው ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያው ባለቤት የነበረው ኡጋንዳዊው አትሌት ጆሽዋ ቺፕቴጊ ደግሞ በዚህ ውድድር ሦስተኛ በመሆን የነሐስ ሜዳሊያውን ወስዷል፡፡ በሁለቱም ጾታዎች የአዋቂ ዘርፍ የቡድን ብር ሜዳሊያም ተመዝግቧል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም