የሆርቲካልቸር ዘርፍ በተፈለገው መጠን እና በጥራት የሚመረት ከሆነ አንደ አገር ለውጭ ገበያ በመቅረብ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ዋንኛ ምርት ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ለዜጎች የሥራ እድልን በመፍጠር ረገድ የሚጫወተው ሚና ላቅ ያለ መሆኑ አያጠያይቅም። በተለይ አትክልትና ፍራፍሬ ለአገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ከማድረጉ በተጨማሪ እንደቤተሰብ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥም ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው። ከዚህ ከሆርቲካልቸር ዘርፍ ጋር በተያያዘ እየተሠራ ያለው ሥራ እና እያስገኘ ያለው ውጤት ምን ይመስላል ሲል አዲስ ዘመን በግብርና ሚኒስቴር የእርሻ ልማትና ሆርቲካልቸር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከሆኑት ዶክተር መለሰ መኮንን ጋር ያካሔደውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ለአበባ፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ ያላት ምቹነት እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር መለሰ:– አገራችን በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ናት። ይህን ስንል ግን እንዲሁ ስለምንወዳት ብቻ ለማለት ሳይሆን እውነት ስለሆነ ነው። ለዚህ ምክንያቱ አንደኛ በሥነ ምሕዳር (በአግሮ ኢኮሎጂው) ብንወስድ ሁሉንም ዓይነት ሥነ ምሕዳር ያላት ሀገር ናት። በጣም ውርጭ ከሚባለው እስከ በረሃማ የአየር ዓይነት በዚህች አገር ላይ አለ። ይህ ማለት ሀገራችን ውስጥ የማይበቅል የሰብል ዓይነት የለም እንደማለት ነው። ምክንያቱም ለሁሉም ዓይነት ሰብል ምቹ ናትና።
ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ ገና በጣም ሰፊ የሆነና ያልታረሰ ለም መሬት ባለቤት ናት። እየተጠቀምን ያለነው በአብዛኛው ደጋማ፣ ወይናደጋ እና በተወሰኑ ቆላማ በሆኑ አካባቢዎች ያለውን መሬት ብቻ ነው። በአብዛኛው እየተጠቀምን ያለነው ሰው የሰፈረበትን አካባቢ ነው። ወረድ ብሎ ለእርሻ ሥራ ምቹ የሆኑ በጣም ሰፋፊ አካባቢዎች ቢኖሩም እሱ ግን ከዓመት ዓመት ሳይታረስ እንዲሁ ጦሙን የሚያድር መሬት ነው።
በሰሜን ምዕራቡም ብንወስድ ሰፊ ያልተነካ መሬት አለ። ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም ወደጋምቤላም መስመር ብንወስድ ሰፊ ያልተነካ መሬት አለን። ኦሮሚያ፣ አፋር እንዲሁም ሶማሌ ላይ ሰፊ ያልተነካና ለም የሆነ መሬት በተመሳሳይ አለን። ለዚህም ነው ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብት የታደለችና ምቹ ናት የምንለው። በውሃ ሀብትም በኩል የገጸ ምድር እንዲሁም የገጸ ምድር ውሃ ከየትኛውም አካባቢ የተሻለ ያለን ነን። ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች አሉን። በበጋውም ሆነ በክረምቱ ወቅት በቂ የሆነ የከርሰ ምድር ውሃ አቅም ያላት አገር ናት። ከዚህ የተነሳ ትንንሽ ጉድጓዶች በመቆፈር ብቻ በመስኖ ማልማት የሚያስችል አቅም አለ።
ለምሳሌ ምሥራቅ አማራን ብንወስድ ከአላማጣ ጀምሮ እስከ ሸዋ ሮቢት ድረስ ያለው አካባቢ 50 ሺ ሔክታር አካባቢ መሬት በከርሰ ምድር ውሃ ብቻ መልማት የሚችል ነው። ጉድጓዶች ተቆፍረው ውሃው ወጥቶ የተወሰኑት እየለሙም ይገኛሉ። ስለዚህ ይህ አቅም አለ። ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ በርካታ ወንዞች ስላሉ መስኖ ላይ መሥራት ብንችል ለሆርቲካልቸር ሰብል መስኖ ልማት እጅግ በጣም ምቹ ነው። ስለዚህም ያልተነካ አቅም አለን ማለት ይቻላል። ትግራይን ብንወስድ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ይህ አቅም አለ። በኦሮሚያ ክልል አሁንም በመልማት ላይ ያለ ምርት አለ። አፋርም ብሎም ሶማሌ እንዲሁ በርካታ ለአዝርዕትም ለጥጥም ለሆርቲካልቸርም ምቹ የሆኑ አካባቢዎች አሉ። ከዚህ ጎን ለጎን እየለሙም ያሉ አካባቢዎች አሉ። ኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ለማምረት የሚያስችል ሰፊ አቅምና ምቹ ሁኔታ ያላት አገር ናት ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- እንደአገር ይህን ያህል ያልታረሰ መሬት እንዲሁም በቂ ውሃ እያለ የተፈለገውን ያህል ማልማት ያልተቻለው ለምንድን ነው?
ዶክተር መሰለ፡- ይህ ሀብት እያለን ማልማት ያልቻልንበት አንዱ ምክንያት እስከ ዛሬ ድረስ ያለን የእርሻ እንቅስቃሴያችን እጅግ ኋላ ቀር በመሆኑ ነው። የተለመደው ከእጅ ወደአፍ ማምረት ነው። አምርቶ ለራስ ከመመገብ ባለፈ ገበያንም ሆነ ሌላውን መሠረት ያደረገ ነገር ላይ ያለንን አቅም አሟጥጦ በመጠቀሙ ረገድ የነበርንበት ሁኔታ እጅግ ኋላቀር ነው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በልምድም በክህሎትም በተለይ ዘመናዊ የሆነ የሆርቲካልቸር ልምዳችን የአጭር ጊዜ ታሪክ ነው። ስለዚህም የእሱ ልምድ አለመኖር ነው።
አሁን አርሶ አደሮቻችን በየጊዜው ልምዱን እያገኙ ሲመጡ በአዝርዕቱ ወይም በሆርቲካቸርና ፍራፍሬ ሰብል እያሰፉ መምጣት ጀምረዋል። በተለይ ደግሞ ከውጭ በተለያዩ ተልዕኮ የሚመጡ አውሮፓውያኑም ሆኑ ሌሎች የውጭ ዜጎች ብዙ በሰፈሩባቸው አካባቢዎች አትክልትና ፍራፍሬ ማልማት ላይ እያስተማሩ ስለሆነ በርካታ ፍራፍሬዎችን በማልማት ረገድ የማይናቅ ሥራ ሠርተዋል፤ ከዚህ አንጻር ሲታይ ለምሳሌ ደቡብ የተሻለ አቅም ያለው ክልል ነው። ኦሮሚያ ደግሞ የተሻለ ልምድ ያለበት ክልል ነው። ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አማራ ክልል ወደማልማቱ ሥራ እየተቀላቀለ ይገኛል።
በሆርቲካልቸርም አርሶ አደሩ ከሚሠራው ውጪ እምብዛም የተሠማራ ባለሀብት አልነበረም። አሁን አሁን ግን የሀገር ውስጥም የውጭም ባለሀብት በአትክልትም ሆነ በፍራፍሬ ላይ ሰፊ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ። ቀደም ብሎ በነበረው ላይ አትክልትና ፍራፍሬ የሚያመርተው አካል ለራሱ ከመጠቀም በዘለለ ለገበያ የማቅረቡ ሁኔታና ገቢ የማግኘቱ ነገር ብዙ አልነበረም።
አሁን ግን ከጊዜ ወደጊዜ አንደኛ ለአገር ውስጥ ገበያም ማቅረብና የተሻለ ጥቅም ማግኘት ተጀምሯል። በተወሰኑ የፍራፍሬና የአትክልት ዓይነቶች ደግሞ ወደውጭ መላክ የተጀመረበት እድል ስላለ በአሁኑ ወቅት እየሰፋ በመምጣት ላይ ይገኛል። መንግሥት ይህን በማየት ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው። ለምሳሌ አግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎችን መውሰድ ይቻላል። ቲማቲም በሰፊው ቢለማ ከፍጆታ አልፎ መቀመጥ አይችልም፤ በቀላሉ መበላሸት የሚችል ምርት ነው። ስለዚህ ቲማቲምን እሴት በመጨመር የሚያመርቱ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች እንዲኖሩ ማድረግ ያስፈልጋል። የሚመረተውን አቮካዶ ሁሉ ለፍጆታችን ተጠቅመን አንችልም፤ የድንች ምርትም ቢሆን በሰፊው ተመርቶ የተወሰነ ጊዜ ተጠቅመን ከዛ በኋላ የመበስበስ እድሉ ከፍተኛ ይሆናል። ስለዚህ አቮካዶንም ሆነ ድንች እሴት የሚጨምር (ፕሮሰስ የሚያደርግ) የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም። ስለዚህ የአትክልትና ፍራፍሬ ዋናው ነገር ድኅረ ምርት አያያዝ ነው ማለት ነው፤ ለምሳሌ ድንችን በጥብስ (ቺፕስ) መልኩ መጠቀም መጀመራችን የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው። በዚህ መልኩ እውቀቱም ክህሎቱም በፊት ያልነበረ ሲሆን፣ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣት ጀምሯል። ምቹ ሁኔታዎች እየታዩ ሲመጡ የአካባቢውን ሀብትና ጸጋ እንዲሁም አቅም በማየት አርሶ አደሩ፣ በልማት የተሠማሩ ተቋማትም ሆኑ ባለሀብቶችም የማልማት ሥራው ላይ በመሳተፋቸውና ሥራውም ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ መልካም ጅማሮ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዘርፉ በተለይ በአበባ ልማት ላይ የሚሠማሩ የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ አገር ኢንቨስተሮች እንዳሉ ይታወቃሉ፤ ምን ያህል ውጤታማ ሆነዋል?
ዶክተር መሰለ፡- በጣም ውጤታማ ሥራ እየሠሩ ናቸው ማለት ይቻላል። ውጤታማ ናቸው ብለን ከምንጠቅሳቸው ውስጥ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በአበባ ልማቱ ላይ እየሠሩ ያለውን ሥራ አንዱ ነው። ሥራው እጅግ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ውጤት ያሳየ ነው። ሰፊ ልማት ማልማት የተቻለ ሲሆን፣ ከዚህም ልማት አገራችን አበባ ወደ ውጭ በመላክ በተሻለ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ እያገኘች መምጣቷ ተጠቃሽ ነው።
እንደሚታወቀው ቀደም ሲል ወደውጭ አገር የምንልከው ቡናን ነው። ለብዙ ዓመታት በቡና ተወስነን ቆይተናል፤ በአሁኑ ወቅት ቡና እንዳለ ሆኖ አበባን ወደውጭ መላክና የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተችሏል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን የአበባ ልማቱ በመምጣቱ ብቻ ከውጭ ምንዛሪ ጎን ለጎን ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል መክፈት ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪ በአበባ ልማት ዕውቀትንና ክህሎትን ማግኘት የተቻለ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ይህ ዓይነቱ ልምድ በሀገራችን አልነበረም። ይህንንም ልማት ለማልማት የውጭ ኢንቨስተሮች ባለሙያዎችን ይጠቀሙ የነበረው ከውጪ አምጥተው ነው። አሁን ከጊዜ ወደጊዜ ግን የዕውቀት ሽግግሩ ኖሮ ብዙዎች የአበባ እርሻዎች በውጭ ይመሩ የነበሩ ዛሬ በእኛ ባለሙያዎች መመራትና የእኛ ባለሙያዎች እየተተኩ መምጣት ተችሏል። በዚህም የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግሩም እየመጣ ይገኛል።
በፍራፍሬም እንደዚሁ የተወሰኑ ለምሳሌ ከአውሮፓ የኔዘርላንድስ የግል ኩባንያዎች እርሻ በመውሰድም የአትክልት ዘር በማምረትም ወደ ውጭ በመላክ ላይ ይገኛሉ። ከዚያም በሀገራችን እየተካሄደ ባለው የአበባ ልማት የውጭ ምንዛሪው ብሎም የቴክኖሎጂ ሽግግሩም የማግኘት እድል ተፈጥሯል። ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በተለይ በፍራፍሬና በአትክልቱ ዘርፍ መሬት እየወሰዱ ኢንቨስት የማድረጉና የመነቃቃቱ ሥራ እየተሠራ ነው። ባለሀብቶቻችን ብሩን ይዘውታል እንጂ ዕውቀት እና ክህሎቱ አልነበራቸውም። አሁን ከጊዜ ወደጊዜ የእኛም ባለሙያዎች ከዩኒቨርስቲ የሚወጡትም ሆኑ ባለሀብቶቻችን ልምድ እያገኙ በመምጣት ላይ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡- የአበባ ልማቱ በሌሎች አገሮች ተፈላጊነቱ እንዴት ይገለጻል? አንዳንድ አካላት በአንዳንድ ባለሀብቶች ግዴለሽነት የተነሳ የአበባ መሬት በኬሚካል እየተበከለ ነው ይላሉ፤ እዚህ ላይ ምን አስተያየት?
ዶክተር መሰለ፡– አንድ ልማት ሲመጣ ጠቀሜታ እንዳለው ሁሉ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ደግሞ የራሱ የሆነ ጉዳት ይኖረዋል። የአበባ ልማት ወደሀገራችን መምጣቱ ሰፊ የገበያ እድል እንዲያገኝ አስችሎታል። የእኛ አበቦች በአውሮፓ ገበያ በቀላሉ መግባት የሚችሉና ተፈላጊ በመሆናቸው የገበያ ችግር የለብንም።
ይህን ልማት በምንሠራበትና በምናስፋፋት ጊዜ ደግሞ አካባቢን የመበከል ሁኔታ እንዳይኖር አንደኛ የሚጠቀሟቸው ኬሚካሎች ከጊዜ ወደጊዜ መሬቱን እንዳይበክሉት የሚከታተል የእኛ የግብርና ኳራንቲ (የግብርና ባለስልጣን) አለ። አሁን በተሻለ መልኩ እያደራጀነው ነው። የሚገቡት ኬሚካሎች ለአካባቢ፣ ለሰው እንዲሁም ለእንስሳት ተጽዕኖ እንዳይኖራቸው ለማድረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል። ሌላው ቀርቶ የአበባ እርሻዎች በሚመሠረቱበት ጊዜ አካባቢን እንዳይበክሉ ማሟላት ያለባቸው ሁኔታዎችና መስፈርቶች አሉ። ይህም ገና ሲሰጣቸው የአካባቢ ተጽዕኖና ግምገማ ተደርጎ ነው። በእርግጥ ይህ ሁሉ ይተገበራል ወይ ብለን ብንጠይቅ የምንሠራ ሰዎች እንደመሆናችን የተወሰኑ ድክመቶች እንዳሉ ማየት ችለናል። ቀደም ብሎ ባሉት ላይ የነበሩ ችግሮች በመቀረፍ ላይ ናቸው። አሁን አዳዲስ እየገቡ ባሉ የአበባ እርሻዎች ላይ እየተሠራ ያለው በተሻለ መጠን ሲሆን፣ በአካባቢው ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ እንዳይኖራቸው ተደርጎ ነው። ይህ የሆነውም ካለፉት እንቅስቃሴያችን የተወሰዱ ተሞክሮዎች በመኖራቸው ነው።
ያለፉትም ቢሆኑ የሚቻለውን የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ እንዲያስተካክሉ ብሎም አካባቢን እንዳይጎዱ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። ከዚህም የተነሳ በአሁኑ ጊዜ ልማቱ የሚገኘው የተሻለ ደረጃ ላይ ነው። ይሁንና የሚቀረን ነገር ስላለ አሁንም ገና ነው። አንድ ጊዜ በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ እንዳያደርሱ ሆነው ተሠርተዋል፤ ተመሥርተዋል ብንልም በየጊዜው ግን ቁጥጥርና ክትትል መደረግ መቻል አለበት። ስህተቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ከስር ከስር ክትትል እየተደረገ መስተካከል አለበት።
አዲስ ዘመን፡- አትክልትና ፍራፍሬም የውጭ ገበያ በማቅረብ ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ ማግኛ መንገድ እንደሆነ ይነገራል፤ ከዚህ ዘርፍ ዋንኞቹ የትኞቹ ናቸው ?
ዶክተር መሰለ፡– አትክልትና ፍራፍሬ ላይ ስንመጣ ለሥርዓተ ምግብ ዋስትና በጣም ጠቃሚ ናቸው። ለሀገር ውስጥ ገበያ ደግሞ በጣም ወሳኝ ናቸው። ከዚህም አልፎ ወደውጭ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሪን የሚያስገኙ ናቸው። በዋናነት ግን ሀገር ውስጥ ላሉ አግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ለግብዓትነት የሚውሉ ናቸው።
ከአትክልት የተወሰኑትን ከፍራፍሬም የተወሰኑትን ለማንሳት ያህል ለምሳሌ የሀገር ውስጥ ገበያን ብሎም ግሽበትን በማረጋጋት በኩል እንዲሁም ለሥርዓተ ምግብ ዋስትናነት ከምንጠቀምበት አንዱ ሽንኩርት ነው፤ ሽንኩርት በጠፋ ቁጥር ምን ያህል ግሽበት ላይ አስተዋፅዖ እንዳለው ይታወቃል። ስለዚህ ሽንኩርት ለሀገር ውስጥ ፍጆታና ለሀገር ውስጥ ገበያ እጅግ ወሳኝ ነው።
ሌላው ውስጥ ፍጆታም ሆነ ለአግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ግብዓት ከሚሆነው አንዱ ቲማቲም ነው። ቲማቲምን በሰፊው ማምረት ብንችል እዚሁ ሀገር ውስጥ በአግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፕሮሰስ ተደርጎ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚቀርብበት እድል አለ። በሦስተኛነት ለመጨመር ያህል ድንችን ማንሳት ይቻላል፤ ድንች ለምግብ ዋስትና፣ ለሥርዓተ ምግብ ዋስትና እንዲሁም ለአግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ በጣም ወሳኝ ነው። ስታርች ከድንች ይሠራል። ድንችን ፕሮሰስ አድርገው ስታርችን ከድንች የሚሠሩ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች አሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በርበሬም አንዱ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ቅመማቅመም ብለን ከምናመርተው ውስጥ ነው። በርበሬ በቅመማቅመምነቱ ለሀገር ውስጥ ገበያ ብሎም ለውጭም ሀገር ገበያ መሆን የሚችል እድል ያለው ምርት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ፍራፍሬ ዘንድ ስንመጣ ሙዝ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ ለመቅረብ ሰፊ አቅም ያለው ምርት ነው። በተመሳሳይ ማንጎም ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ ብሎም ለአግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ መሆን የሚችል አቅም አለው። አሁን ደግሞ በቅርብ በጣም ትልቅ ሥራ እየሠራንበት ያለው አቮካዶ ነው፤ በአቮካዶ በኩል ለሀገር ውስጥ ለአግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ የሚሆኑ የተለያዩ ዝርያዎች አሉን። በተጨማሪም ለውጭ ገበያ ብለን የምናመርታቸው አሉን። ላለፉት ሦስት ዓመታት ዘንድሮን ጨምሮ አቮካዶ ወደውጭ ገበያ በመላክ ላይ እንገኛለን። ከኦሮሚያ፣ ከአማራ አሁን ደግሞ ከደቡብ ክልል እያመረትን ነው። ከዚህ አኳያ አቮካዶ ትልቅ አቅም ያለው ምርት ነው ማለት ይቻላል። በፓፓያ ዙሪያም ትልቅ አቅም ያለን ሲሆን፣ በመመረት ላይ ነው። ይህን ሥራ በኩታ ገጠም በማድረግ በየጊዜው እያሰፋን ችግኞችም እየተዘጋጁ በየዓመቱ ሰፊ የተከላ ሥራ በመካሄድ ላይ ነው። ከዚህ አኳያ ሥራዎችም እየተሠሩ የሚገኙት በልዩ ጥንቃቄ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ አትክልቱም ሆኑ ፍራፍሬዎቹ በጥራት ተመርተው በአስተሻሸጋቸውም የገዥዎቻቸውን ቀልብ ስበው የመቅረባቸው ጉዳይ ላይ ምን ያህል ተመራጭ አድርጓቸዋል? ጥራቱን በማስጠበቁ በኩል ተግዳሮት ካለ ለመፍትሔው ምን እየተሠራ ነው?
ዶክተር መሰለ፡– በአዝርዕትም በአትክልትና ፍራፍሬም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ስናይ የራሳቸው የሆነ ስታንዳርድ አላቸው። በዛ ስታንዳርድ መሠረት ካልሆኑ ከሄዱበት የውጭ አገር ገበያ ወዲያውኑ ይመለሳሉ፤ ከዛ በፊት ግን ወደውጭ ገበያ መጓዝ የሚችሉት እዚህ ጥራታቸው ታይቶና ተፈትሾ የተቀመጠውን ስታንዳርድ ያሟላሉ ተብሎ ሲረጋገጥ ነው። እኛ ባረጋገጥነው ብቻ ስለማይሆን ደግሞ ከዚህ ልከን እዛ በድጋሚ ይፈተሻሉ፤ በፍተሻቸው ወቅት እንከን የሚያገኙባቸው ከሆነ ይመልሱታል፤ መመለሱ ብቻም አይደለም። ለቀጣይ የሚኖረንን የውጭ ገበያ ሰንሰለታችንን የሚያበላሽ ይሆናል፤ ይህም የሚያበላሸው የሀገርን ገጽታ ነው፤ ስለዚህ ለምሳሌ አቮካዶን ወደ ውጭ ገበያ ስንልክ ከእርሻ ጀምሮ የምንከተለው የጥራት ሒደት አለ፤ ከዛፉ ቆርጠን የምናመጣበት የራሱ ቴክኒክ አለው። በዚህ ረገድ ሰፊ ስልጠና ይሰጣል፤ ምርቱን የምንቆርጥበት ሆነ ከዛፉ ቆርጠን የምናጓጉዝበት የራሱ መሣሪያ አለ። ምርቱ ቀዝቃዛ መጋዘን ከገባ በኋላ ደግሞ ምርቱን እንደየመጠኑ መለየት ደግሞ ሌላው ሥራ ነው። በመጠንና በደረጃም የመለየት ሥራ በጥንቃቄ ይካሄዳል። ለእነዚህ የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎች አሉ። ማሽነሪዎቹ ምርቱን በመጠን በጥራት ደረጃ ይለዩታል። ይህ አካሄድ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን የተከተለ ነው።
የሚታሸጉበት እቃ በራሱ የራሱ ስታንዳርድ ያለው ነው። በአብዛኛው ለምርቶቹ የሚሆን ማሸጊያ እቃ እኛ አናመርትም። የሚመጣው ከውጭ ነው። ከካርቱን ጀምሮ የሚመጣው ከኬኒያና ከሌሎች አገሮች ነው። በዚህ መልኩ በቀዝቃዛ መጋዘን ውስጥ ሆኖ በቅብብሎሽ የሚጓጓዘው በቀዝቃዛ ተሸከርካሪ ውስጥ ነው።፡ በመርከብም ሆነ አውሮፕላን ለምርቱ ምቹ በሆነ የቅዝቃዜ ደረጃ ነው። ይህን የሚፈትሹና የሚያረጋግጡ ተቋማት ደግሞ አሉ።
አዲስ ዘመን፡- በሆርቲ ካልቸር ዘርፍ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ በመቶኛ ሲሰላ ምን ያህል ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር መሰለ፡- አጠቃላይ በግብርና ዘርፍ ማየት ከተቻለ በዚህ ዓመት ከ80 በመቶ ያላነሰውን የውጭ ምንዛሪ ድርሻ ያስገኘው ግብርና ነው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት ቡና፣ አበባ እና አትክልትና ፍራፍሬ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በአትክልትና ፍራፍሬ በኩል በሰፋፊ እርሻዎች ላይ በሰፊው እንዲመረት በጠቅላይ ሚኒስትሩም በኩል ፍላጎቱ ከፍያለ ነው፤ ባለሀብቶችም ከዚህ አንጻር ሥራ እንደጀመሩ ይታወቃል፤ ይህ ምን ያህል ተስፋ ሰጪ ነው ተብሎ ይታሰባል?
ዶክተር መሰለ፡- አትክልትና ፍራፍሬ በሀገር ውስጥ ገበያ ለምግብ ዋስትና እና ሥርዓተ ምግብና ዋስትና ካለው አስተዋፅዖ ትልቅ ድርሻ ያለው ነው፤ ከሚፈጥረው የሥራ እድል እንዲሁም ለአግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ከመሆኑ አኳያ አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ነው። ብሎም ለውጭ ገበያ ተመራጭ እንደመሆኑ በአሁኑ ሰዓት የሀገር ውስጥም የውጭም ኢንቨስተሮችን ትኩረት ስቧል። በርካታ ወጣቶች ወደዘርፉ በመግባት ላይ ናቸው። በርካታ ወጣት ባለሀብቶችም ጭምር ዘርፉን በመቀላቀል ላይ ናቸው። ትልልቅ ባለሀብት ናቸው የምንላቸውም በዘርፉ ላይ እየሠሩ ነው።
ለዚህ ማሳያ ሌላ ቦታ መሄድ ሳይስፈልግ እዚሁ ምሥራቅ ሸዋ ላይ መቂ አካባቢን ብቻ ማየቱ በቂ ነው። በጣም በርካታ ወጣት ባለሀብት በዘርፉ ተሰማርቶ አትክልትና ፍራፍሬ እያለማ ይገኛል። ስለዚህ በጣም ተስፋ ሰጪና ሳቢ ዘርፍ ሆኗል። በመሆኑም በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች ቴክኒኩን ጠብቀው በመዘጋጀት ላይ ናቸው። ይህም በኩታ ገጠም እየሰፋ እየተሠራ የሚገኝ ነው። በአነስተኛ አርሶ አደሩም ደረጃ በኢንቬስተር ደረጃ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ባለሀብትም ሰፊ ፍላጎት እንደመኖሩ ሰፊ ሥራዎችም እየተሠሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሆርቲካልቸር ዘርፍ ከሌማት ትሩፋት ፕሮጀክት ጋር ያለው ትስስር እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር መሰለ፡- ከሌማት ትሩፋት ጋር አያይዘሽ ያነሳሽው ጥያቄ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብዬ አስባለሁ። ጥያቄውንም ስላነሳሽልኝ በጣም ደስ ብሎኛል። እንደ ሀገር ስትራቴጂክ ግቦች አሉን። በግብርና ሚኒስቴር አራት መሠረታዊ የሆኑ ግቦች አሉን። የመጀመሪያው ግብ በሀገር ደረጃና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና እና የሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ገቢ ምርትን መተካት እና ለአግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን ምርት በሀገር ውስጥ ማምረት ነው። ለውጭ ገበያ የሚሆኑ ምርቶችን አሊያም ሰብሎችን ማምረትና አይነታቸውንም መጠናቸውንም ማብዛት ነው። አራተኛው ግብና ዋንኛ የሆነው በገጠር ላሉ ወጣቶች እና ሴቶች የሥራ እድል ፈጠራ ነው። እነዚህን ግቦች ለማሳካት የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን አለን፤ በርካታ አቅጣጫዎች አሉን። ከእነዚህም መካከል አንዱ በቅርቡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የተደረገው የሌማት ትሩፋት ነው።
የሌማት ትሩፋት ማለት በአጭሩ በቤተሰብ ደረጃ ብሎም በአገር ደረጃ የምግብና የሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ማለት ነው። የምግብና የሥርዓተ ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ማለት በአንድ ሌማት ወይም በአንድ ማዕድ ላይ በቤተሰብ ደረጃ የምንመገበው ምግብ በዓይነት፣ በመጠንና በይዘት የተመጣጠነ ይሁን ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ፕሮጀክቱን ያስጀመሩት ይህን መነሻ አድርገው ነው። ያ ማለት በአዝርዕት የሚመረቱ ምርቶች ያስፈልጉናል፤ በአትክልት እና ፍራፍሬ የሚመረቱ ምርቶች እንዲሁም በእንስሳት ተዋፅዖዎችም ያስፈልጉናል ማለት ነው። ስለዚህ እንጀራው፣ ዳቦው፣ ሽንኩርቱ፣ ሥጋው፣ ማሩም፣ ወተቱም ሆነ እንቁላሉ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬው ያስፈልገናል።
የዛ የቤተሰብ ማዕድ በዓይነት፣ በመጠን እንዲሁም በይዘት የተሟላ ሆኖ ቤተሰቡን አጥግቦ ለሌላውም የሚተርፍ እንደ ሀገርም ይህን አሟልተን ለውጭ ገበያም እንድንተርፍ ነው። በሚደረገው ሒደት ሰዎች ወተት ላይ፣ እንቁላልና ዶሮ ላይ ወይም ማር ላይ ይመስላቸዋል። እሱ አንዱ ነው እንጂ በአትክልትና ፍራፍሬም በተመሳሳይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት አለበት። በአዝርዕትም በተመሳሳይ ነው፤ እነዚህን ሁሉ ማድረግ ካልቻልን አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ ስለሚሆን የተሟላ ሌማት ወይም የተሟላ ማዕድ አይኖረንም። ስለዚህ ይህን አሟልተን መሥራት መቻል አለብን ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር መለሰ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም