አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል በግምት በስልሳዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አንድ አዛውንት ማኪያቷቸውን አዘው በረንዳው ላይ ቁጭ ብለዋል። ሽበት ጣል ጣል ባደረገበት አፍሮ ጸጉራቸው ላይ ኮፍያ ደፍተውበታል። በነጭ ሸሚዝ ላይ ከረባታቸውን አስረው፣ ጥቁር ካቦርታቸውን ደርበው ከግራጫ ካኪ ሱሪያቸው ጋር ሲታዩ ዘናጭ ስለመሆናቸው አያጠራጥርም። ወንበር ስቤ አጠገባቸው ቁጭ አልኩ። ሰውዬው እንደ አለባበሳቸውም ንግግራቸው የሚጣፍጥና ጨዋታ አዋቂ ናቸው።
ቁጭ ብለን ስንጨዋወት ድንገት አንዲት ወጣት ሴት እርቃኗን ለመሆን እሩብ ጉዳይ የሆነ አጭር ስስ ጉርድ ቀሚስ፣ እንብርቷን ከሚያሳይ አጭር ቲሸርት ጋር ለብሳ በታኮ ጫማዋ መሬቱን እየደቃች ስትገባ ድንገት አይናችንን ሳበችው፡፡ ወደ ውስጥ ከገባች በኋላ.. ወደኔ ዞር አሉና “አዬ ይሄ ትውልድ..በቃ ፋሽኑ እንዲህ ሆነ” ብለው ዝም አሉ። እኔም በከፈቱልኝ ቀዳዳ ሰተት ብዬ ገባሁና ፋሽን ድሮና ዘንድሮ ምን መልክ አለው ስል ላወጋቸው ወደዱኩኝ። “የፊት ጥርሴ አለመውለቁን እንዳታይ ጊዜ መቼም ጥሎ የሚነጉድ ባዳ ነውና እኔም በወጣትነቴ አራዳ ነበርኩኝ” አሉ ገና ጨዋታዬን ስጀምር።
እንዲያው ፋሽን በናንተ ጊዜ እንዴት ነበር?
“በእኛ ጊዜማ ከስር ቦላሌ ሱሩያችንን ታጥቀን፣ በሸሚዙ ላይ የሳሪያን ኮቷን ጣል አድርገን፣ አፍሮ ጸጉራችንን በጠር በጠር እናደርጋትና በከተማው ላይ ጎምለል እያልን በኩራት ነበር የምንሄደው። ግርማ ሞገሱም የተለየ ነበር። ሴቷም ብትሆን በረዥም ሽንሽን ቀሚሷ በእጆቿ አምባሮቹን ደርድራ፣ ከጆሮዋ ሎቲዋን አንጠልጥላ፣ ሽር እያለች ስትሄድ ውበቷን እያደነቀ ከዓይን ያውጣሽ የሚል እንጂ እንደ ዘንድሮው እንዲህ ማንነትን የሚያስገምት አለባበስ ከየት መጥቶ” አሉ ከፊታቸው ላይ ትዝታ እየተነበበ።
ሁለተኛውን ጥያቄ አስከተልኩኝ፤ አራዳነት በእናንተ ጊዜ እንዴት ነበር የሚገለጸው? “አራዳነት ማለትማ የራስህና የሀገርህ በሆነ ፋሽን እራስህን መስልህ ሌሎችም አንተን እንዲመስሉ ማድረግ እንጂ ያልሆንከውን ሆነህ መገኘት አይደለም። ከባሕልና ሥርዓት ውጭ የሆነ አራዳነት ትርፉ የሰው ዓይን ውስጥ መግባት ብቻ ነው።”
ፋሽን ጠቃሚነቱ ወይም ጎጂነቱ ለሁሉም በእኩል ይገለጻል? ለምሳሌ ያህል ስለፋሽን ምንነት የማይረዱ ታዳጊ ወጣቶች ጭምር በዚህ ነገር ተጠምደው ይገኛሉ ይህንን እንዴት ይመለከቱታል?
“ልጆች በባሕሪያቸው በሌላ ያዩትን ሁሉ ለመሆን ይፈልጋሉ። ጥሩነቱም ሆነ መጥፎነቱ አይታያቸውም። ለዚህ ጉዳይ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉም ወላጆቻቸውን ከአቅማቸው በላይ ያስጨንቋቸዋል። የፋሽንን ምንነት በቅጡ ስለማያውቁት ዓይኖቻቸው ያረፈበት ነገር ሁሉ ልባቸውም ይወደዋል። የእነርሱ ዓለምም እሱ ብቻ መስሎ ይታያቸዋል። በልጆች ላይ ሲሆን ከጥቅሙ ይልቅ ጎጂነቱ ያመዝናል።
ምናልባት ይሄ የቴክኖሎጂውና ዘመናዊነቱ የፈጠረው ነገር ነው ብለው ያስባሉ? ቀጣዩ ጥያቄ ነበር፤ “ቴክኖሎጂው ጥሩ ነገር ሆኖ ሳለ በሌላ በኩል ደግሞ ትውልዱ ማንነቱን እያስረሳውም ነው። አሁን አሁን ጫማ ለማሰር እንኳን ኢንተርኔት ነው የሚያዩት። ፋሽን ወይም ዘመናዊነት በራሱ መጥፎ አይደለም፣ ችግሩ ፋሽንን የምናሳይበት መንገድ ነው። እሳት ያበስላልም ያቃጥላልም። ሁሉም ነገር እንደ አያያዙ ይወሰናል። ፋሽን የሕይወታችን የመጀመሪያ ዓላማ አድርገን ልንቆጥረው አይገባም።”
በእናንተ ትውልድ የሚነቀፍና ነገር ግን በዚህኛው ትውልድ እንደ ፋሽን ከሚታዩ ነገሮች ምን አስተዋሉ?
“ትላንትና አዲስ ሱሪ ገዝተው ዛሬ ጉልበቱን እየቆራረጡ ይቦጫጭቁታል። መጀመሪያ አካባቢ አጥተው ወይ ተቸግረው ይመስለኝ ነበር። የኋላ ኋላ ነገሩ ሲገባኝ ለካስ ፋሽን መሆኑ ነው። በዚያ ላይ ደግሞ ለውሻም የማይሆን ሰንሰለት ከአንገታቸው ላይ ተሸክመው፣ ሱሪውም ከታች እየወረደባቸው እንደ እብድ በአንድ እጅ አንጠልጥለውት ሲሄዱ እመለከታለሁ። ሴቷም ከለበሰችው ቀሚስ እጥረት የተነሳ ስልኳ እንኳን ጎንበስ ብላ ለማንሳት ጭንቅ ይሆንባታል። ፋሽን እኮ ነፃነትን፣ ውበትን፣ ግርማ ሞገስን የሚሰጥና የሚያኮራ እንጂ እንደዚህ መላ ቅጣ አሳጥቶ የሚያሳብድ አይደለም። ወንዱ ከወንድነት፣ ሴቷም ከሴትነት ተራ ወጥታ ስመለከት ብዙ ነገሮች እንዳልገባን እገነዘባለሁ። ያገኘነውን ሁሉ መከተል የለብንም እንዲህ ካደረግን የሌላውን እየሰረቅን የራሳችንንም እናጣለን።”
ከአለባበስና የጸጉር ፋሽኖች ባሻገር ሙዚቃና ዳንሱ እንዲሁም የመዝናኛ ስፍራዎችም ጭምር አብረው የሚነሱና በየዘመናቱም ከፋሽኑ ዓለም ጋር ተጣምረው የሚሄዱ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ነገሮችስ ከዛሬው ጋር እንዴት ያዩታል የናንተ ዘመን ትዝታስ እንዴት ያስታውሱታል ስል ጠየኳቸው።
“ በእኛ ዘመን እንደ አሁኑ የትየለሌ ፋሽኖች ያልበዙበት ሰዓት ነበር። ከምንም በላይ ግን የእኛ ዘመን ትልቁ ፋሽን ሙዚቃው ነበር። ሁሉም ሙዚቃ ይወዳል። ከአልባሳቱ ይልቅ የምናተኩረውም በሙዚቃው ውስጥ የሚኖረንን ተዝናኖት ነው። ከአመሻሹ ላይ ባሉን ፋሽኖች በተቻለን መጠን ቆንጆ ሆነን እንወጣና ከጓደኞቻችን ጋር ለአምስት ለስድስት ሆነን ከውቤ በረሃ አሊያም ከንፋስ ስልክ እንሄዳለን።
እዚያ ታዲያ ሙዚቃው ሁሉ ቻቺና ቡጊ ነው። ሀገራዊ ዳንስና ጭፈራው ሁሉ ፍቅርና ደስታ ነበር የሚዘራብን። ስለገንዘብ አንጨነቅም። የአንዱ ለሌላውም ጭምር ይተርፋል። ጥቂት ገንዘብ ይዘን ለምኑም ሳናስብ በጋራ እስኪበቃን ተዝናንተን እንወጣለን። አሁንማ ለመዝናናት ወጥተህ እንኳን ስለ ገንዘብ እያሰብክ ከምኑም ሳትሆን እቤትህ ትመለሳለህ። ሁሉም ነገር ተቀይሯል። አለባበሱ ፈረንጂኛ፣ ሙዚቃው ፈረንጂኛ፣ ዳንሱም ተቀይሮ ከማንነት የወጣ ሆኗል።”
ትውልዱ የራሱና የሀገሩን ባሕልና ፋሽን ተከታይ እንዲሆን ምን መደረግ አለበት?
“ እርግጥ ነው በዚህ ዘመን ልጃችን የሚለብሰውን እኛ ላንመርጥ እንችላለን። ነገር ግን ምርጫው ያማረና ባሕሉን የሚመስል እንዲሆን አስቀድመን ልናስተምረው ይገባል። የትኛውም ሃይማኖትና እምነት ከማኅበረሰብ ያፈነገጠን ፋሽን አይቀበልምና ከማንም በላይ እነርሱ ቢመክሩ ተሰሚነታቸው ከፍ ያለ ነው።” በማለት የመጨረሻውን ምክረ ሀሳባቸውን አስቀመጡ።
አዲስ ዘመን የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም