የአፍሪካ ህብረት መመስረት ዘመናትን በባርነት ቀንበርና በድህነት ላሳለፉት የአፍሪካ ሀገራት የነጻነትንና የእድገትን ጭላንጭል የከፈተ ነው። ምንም እንኳን ህብረቱ ከተመሰረተበት አላማና ሊሰራ ከሚገባው አንጻር ሲመዘን በርካታ የቤት ስራዎች የሚቀሩት ቢሆንም የአውሮፓውያንን ተጽእኖ ከመቋቋም ጀምሮ በፖለቲካውም በኢኮኖሚውም መስክ የተመዘገቡት ውጤቶች አበረታች ነበሩ።
ይህም ሆኖ ዛሬም ድረስ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት እምቅ የተፈጥሮ ሀብታቸውን ተሸክመው በርካታ አምራች ወጣቶችን ይዘው ውስብስብ በሆኑ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ተጠላልፈው ይገኛሉ። ይህም ህብረቱ በቀጣይ እነዚህን ችግሮች ለዘለቄታው ለመፍታት ብዙ ስራዎች መስራት እንዲጠበቅበት አድርገውታል።
የአፍሪካ ሀገራት አሁን ላሉበት ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች የውጪ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት ዋነኛ ችግር ነው። ችግሩ ከሁሉም በላይ ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ አንድነታቸውን አጠንክረው እንዳይጓዙ አድርጓቸዋል። ህብረቱም የታሰበው ያህል ውጤታማ ሆኖ ለአህጉሪቱ ህዝቦች የተሻለ እድል መፍጠር አልቻለም።
ህብረቱ ከግማሽ ምእተ አመት በላይ በዘለቀ ጉዞው የሰራቸው በርካታ ተግባራት ቢኖሩም ፣ በተለይም የአህጉሪቱን ህዝቦች በኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዘርፎች በማስተሳሰር፤ በአለም አቀፍ መድረኮች ተሰሚነታቸውን ለማሳደግ ገና ብዙ መስራት ይኖርበታል፡፡ በዚህ በኩል ያጋጠሙት ሆነ እያጋጠሙት ያሉ ተግዳሮቶች በቀጣይም ፈተና እንደሚሆኑበት፤ ለዚህ ደግሞ በአህጉሪቱ ሀገራት መካከል ሊኖር የሚገባውን የእርስ በእርስ ግንኙነት መጠናከር ፤ ይህንንም ከግብ ለማድረስ ህብረቱ ጠንካራና ተከታታይነት ያለው ስራ መስራት ይጠበቅበታል ።
አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት በእርስ በእርስ ግጭቶች ውስጥ አመታት እያስቆጠሩ ይገኛሉ። በዚህም ህዝቦቻቸው እየከፈሉት ያለው ዋጋ ከፍ ያለና ነገዎቻቸውን በተስፋ እንዳይጠብቁ ፈተና ጭምር ሆኖባቸዋል። ለዚህም ሁነኛ ማሳያ ልትሆን የምትችለውን የቅርብ ጎረቤታችን ሱማሊያን እንመልከት። በሀገሪቱ አመታት ያስቆጠረ የእርስ በእርስ ግጭት አለ ፤ ግጭቱ ሀገሪቱን የአሸባሪ መፈንጫ አድርጓል ፤ የችግሩ ጦስ ለጎረቤት ሀገራትም ተርፏል።
የደቡብ ሱዳን ጉዳይም ከዚሁ የራቀ አይደለም። በእነዚህ ሀገራት ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከአፍሪካ ሀገራት ሰላም እንዲያስከብሩ የተላኩ ወታደሮች ዛሬም ድረስ ለአመታት እዛው ከትመው ይገኛሉ። ከችግሮቹ በስተጀርባ ጠንካራና ስውር የውጪ ጣልቃ ገብነት ያለበት በመሆኑ መቼ እንደሚፈታ እንኳን ለመገመት አስቸጋሪ ሆኗል።
በተቃራኒው ህብረቱ አቅሙን አጎልብቶ እየሰራባቸው የሚገኙ ስራዎች መኖራቸው ደግሞ ትልቅ ተስፋ ሰጪ እውነታ ነው። ለዚህ በቅርቡ በሀገራችን ተከስቶ የነበረውን ችግር ለመቅረፍ የተደረገው ጥረትና የተገኘው ውጤት ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
ከአመት በፊት ነገሮች በተጋጋሉበትና በሀገሪቱ ውጥረት በነገሰበት ወቅት የድርድር ሃሳብም ሆነ የድርድሩ ሂደት በአሜሪካና በአውሮፓውያን መካሄድ አለበት የሚለው እሳቤ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ብቻ ሳይሆን ስኬታማ እንዲሆን ብቸኛ መንገድም ተደርጎ ተወስዶ ነበር።
ከእልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ በኋላ ይህን እሳቤ ወደጎን በመተው ወደ አፍሪካ ህብረት የተሄደበት መንገድና የተገኘው ውጤት አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ የመፍታት አቅም እንዳላት በተጨባጭ ያሳየ ነበር። ተሞክሮው በእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ለሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ተስፋ ሰጭ እንደሚሆን ይታመናል ።
በርግጥ አፍሪካውያን የውጪ ጣልቃ ገብነትን አሸንፈው በራሳቸው ፈቃድ ችግሮቻቸውን ለመፍታት የሚያደርጓቸው ጥረቶች በብዙ ተግዳሮቶች የሚፈተኑ ናቸው፡፡ ይህንን ፈተና አሸንፈው ለመሻገር አንድነታቸውን በማጠናከር፣ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማሳደግ፣ በዚህም በአለም አቀፍ ደረጃ ድምጻቸው እንዲሰማ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ የህብረቱ አስተዋጽኦ ከፍያለ እንደሚሆን ይታመናል።
የአህጉሪቱ ሀገራት ጠንካራ ኢኮኖሚ ገንብቶ ቢያንስ በምግብ እህል ራሳቸውን መቻል እራሳቸውን ሆነው ለመገኘት ወሳኝ ነው። ያላቸውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፤ ሊሰራ የሚችል የወጣት ጉልበት በማቀናጀት ሊንቀሳቀሱና ከተያዙበት የድህነት ወጥመድ ሊወጡ ይገባል። ይህም በመካከላቸው ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ትርጉም በሚኖረው መንገድ በማሳደግ የጋራ ተጠቃሚነትን መፍጠር ይቻላል።
ይህ እውነታ ዛሬም በድንበር ከተሞች አካባቢ ብቻ ተወስኖ የሚገኘውን የአፍሪካ ሀገራት በየንግዱ ግንኙነት በማሳደግ ጠንካራ የንግድ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል ነው። ለዚህ ደግሞ ሀገራትን በሚያስተሳስሩ መሰረተ ልማቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ወሳኝ ነው። ህብረቱ በዚህ ረገድ ምን ያህል ሊጓዝ እንደሚገባ ማሰቡ አይከብድም።
የአፍሪካ ሀገራት መንግስታትና ህዝቦች ዐይንና ጆሮ / የቅርብ ሩቅ አድርጎ ያስቀመጣቸው በየሀገራቱ መካከል ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የላላና የየሀገራቱ መንግስታት ድጋፍ የሌለበት መሆኑ ነው። በመሰረቱ በአሁኑ ወቅት ያለው የአፍሪካ ሀገራት የድንበር ወሰን ሀገራቱን ለግጭት የሚዳርግ አውሮፓውያን በቅኝ ግዛት ዘመን የተሰራ አርቴፊሻል አከላለል ነው።
ይህ አርቴፊሻል የድንበር ወሰን አከላል ወደነበረበት ይመለስ ለማለት ሳይሆን የአፍሪካ ሀገራት በፖለቲካውና በኢኮኖሚው መስክ ተቀራርበው ሊሰሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር መልካም መደላድልን መፍጠር ያስችላል ለማለት ያክል ነው።
ህብረቱ በአጎራባች ሀገራት መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ማጠናከርና በንግድ ማስተሳሰር የሚችልበት ሁኔታ ከተፈጠረ በአንድ የገንዘብ ኖት መጠቀም ሳያስፈልግ በሀገራቱ መካከል የሚኖረውን ግንኙነት ማጠናከር ይቻላል።
ለምሳሌ የምስራቅ አፍሪካን ሀገራት ብንወስድ በየድንበሮቻቸው አካባቢ የሚገኙ ህዝቦች በአብዛኛው ተመሳሳይ ቋንቋ የሚጠቀሙና ተመሳሳይ ማንነት ያላቸው ናቸው። ይህም በንግድ ልውውጥ ረገድ የምርት ፍላጎትና አቅርቦት ከሞላ ጎደል ተቀራራቢና ተመሳሳይ ስለሚሆን የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያስገኝ ይሆናል።
ህብረቱ ሆነ የአህጉሪቱ መሪዎች የአህጉሪቱን ህዝቦች ወደተሻለ ሕይወት ማሻገር በሚያስችሉ የጋራ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ የጋራ ራእይ ሊኖራቸው ፤ ለራእዩም ስኬት ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል። ከህብረቱ ጉባኤ የሚጠበቀውም ይኸው ነው።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን የካቲት 12 ቀን 2015 ዓ.ም