ከባድ ውጣ ውረዶችና መሰናክሎች እንዲሁም ፈታኝ በሆነ የውድድር ቦታ አትሌቶች የሚፈተኑበት የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና ነገ በአውስትራሊያ ባትረስት ከተማ ይካሄዳል። በአዋቂ ወንድና ሴት፣ በወጣት ወንድና ሴት እንዲሁም በድብልቅ ሪሌ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ከ48 አገራት የተውጣጡ 453 አትሌቶች የአገራቸውን ስም ለማስጠራት ለሚደረገው ፉክክር ተዘጋጅተዋል።
በዚህ ውድድር በግልም ሆነ በቡድን የበላይነት ከሚጠበቁ ጠንካራ ቡድኖች መካከል የኢትዮጵያ የአገር አቋራጭ ቻምፒዮና ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን አጠናቆ የውድድሩን መጀመር ብቻ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ በውድድሩ ታሪክ 35 ጊዜ ተሳትፋ ባስመዘገበቻቸው ሜዳሊያዎች ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትቀመጣለች። ይህን ስኬት ለማስጠበቅም በነገው ቻምፒዮና የሚሳተፈው ቡድን በጥሩ አቋም ላይ እንደሚገኝ የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ተናግረዋል።
በአዋቂ ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር ተወዳዳሪ የሆነችው አትሌት ሃዊ ፈይሳ፤ በግልም ሆነ በቡድን የነበራቸው ዝግጅት ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል መሆኑን ለአዲስ ዘመን ገልፃለች። ሃዊ ከአራት ዓመታት በፊት በተካሄደው ቻምፒዮና በቡድን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው የአዋቂ ምድብ 10ኪሎ ሜትር ሩጫ ላይ ተሳታፊ ነበረች። በአገር አቋራጭ ውድድር ልምድ ያላት ሃዊ፤ ለአንድ ወር ያህል በዘለቀው ዝግጅትም በቡድን አባላቱ መካከል የአንድነትና አብሮ የመስራት ስሜት የጎለበተ በመሆኑ ዘንድሮ ከዚህ ከቀደም ከተካሄዱ የአገር አቋራጭ ቻምፒዮናዎች የተሻለ ውጤት ሊመዘገብ ይችላል የሚል ተስፋ አላት። በተለይ በባትረስት ያለው ወቅታዊ የአየር ሁኔታ አሁን በኢትዮጵያ ካለው ጋር የሚቀራረብ በመሆኑ እንዲሁም የአየር ሁኔታውን ያማከለ ዝግጅት በተለያዩ ስፍራዎች በመደረጉ የነገው ውድድር ብዙም አዳጋች እንደማይሆን ጠቁማለች።
በዩጋንዳ ካምፓላ እአአ በ2017 በተካሄደው የአገር አቋራጭ ቻምፒዮና በወጣቶች ዘርፍ የተሳተፈው፤ ከአራት ዓመት በፊትም በ2019 በአህሩስ በአዋቂ ዘርፍ በግሉ ዲፕሎማ በቡድን የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘው የኦሊምፒክ ቻምፒዮኑ አትሌት ሰለሞን ባለረጋ በነገው ውድድርም ተካፋይ ነው። ቡድኑ ጥሪ ከተደረገለት አንስቶ ተሰባስቦ በአንድነት ስሜት ወደ ዝግጅት ለመግባት ጊዜ እንዳልወሰደበት የገለጸው ሰለሞን፣ ከሌሎች ቡድኖች በተሻለ ጥሩ መቀራረብና አንድነት የነበረው ቡድን በመሆኑ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል። በአዋቂ ዘርፍ ተሰላፊ ከነበሩት አትሌቶች መካከል ታደሰ ወርቁ በገጠመው ጉዳት ምክንያት ከውድድር ውጪ ቢሆንም በዝግጅቱ ልክ ክፍተት እንዳይፈጠር ለማድረግ የተቀሩት አትሌቶች ጥረት ያደርጋሉ። ሰለሞን በቡድንም ሆነ በግል እንደ አገር የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣትና አገሩን እንደከዚህ ቀደሞቹ ሁሉ በድል ለማስጠራት ጥረት እንደሚያደርግም አስተያየቱን ሰጥቷል።
ቡድኑ ለአንድ ወር ያህል ሲያካሂድ የቆየው ጠንካራ ዝግጅት ወደማጠናቀቂያው ሲደርስ ጥቂት እክሎች ገጥመውት ነበር። ይኸውም የወጣት ቡድኑ አባላት የሆኑ 8 አትሌቶችን (2ተጠባባቂ) ጨምሮ 1 አሰልጣኝ 5 የተለያዩ ባለሙያዎች በጥቅሉ 14 የልዑካን ቪዛ ተከልክለው ነበር። በዚህ የተነሳ ቡድኑ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ቢደርስም በ11ኛው ሰዓት ችግሩ በመቀረፉ ቡድኑ ተጠቃሎ ወደ አውስትራሊያ መጓዝ ችሏል። በመድረኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ የሚያደርገውና የወጣት ወንዶች 8ኪሎ ሜትር ቡድን አባል የሆነው አትሌት አቤል በቀለ፤ ብሔራዊ ቡድኑ ጥሩ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ በመሆኑ ውጤት የማስመዝገብ ተስፋ እንዳለው ይጠቁማል። አትሌቲክስ አገር ከፍ ብላ የምትታይበት መድረክ እንደመሆኑ ይህንን ለማሳካት ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን ጥረት እንደሚያደርግም አክሏል።
በአምስቱ የውድድር ዘርፎች የሚካፈሉትን ቡድኖች ሲያዘጋጁ ከቆዩት አሰልጣኞች መካከል አንዱ ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ ነው። 4 ኦሊምፒኮች፣ 7የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች እንዲሁም 4 የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮናዎች ላይ በአሰልጣኝነት ብሔራዊ ቡድንን በመምራት ሰፊ ልምድ አካብቷል። ይሁንና በዚህ ሁሉ ዓመታት እንደዚህ የተናበበና የተግባባ ቡድን አለመመልከቱን ይጠቅሳል። ለአንድ ወር በዘለቀው ዝግጅት ከፌዴሬሽኑ አመራች አንስቶ እስከ ቴክኒክ እና ሌሎች ሙያተኞች ድረስ በየዕለቱ የቡድኑን ሁኔታ በመከታተል ከጎኑ ቆይተዋል። አሰልጣኞችም በባትረስት የሚኖረውን ወቅታዊ የአየር ሁኔታ በመለየት እንዲሁም እቅድ በማውጣት ጠንካራ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል። በመሆኑም ከዚህ በኋላ የሚቀረው ይህ ዝግጅት በተግባር የሚታይበት ውድድር መሆኑንም ይገልጻል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 10 ቀን 2015 ዓ.ም