መቼም ብዙዎቻችን ‹‹እንሾሽላ›› ሲባል የምናውቀው ሴቶችና ልጃገረዶች በተለይ የዘመንን መለወጥ ምክንያት በማድረግ ራሳቸውን ለማስዋብ ሲሉ የሚቀቡትን ድንች መሰል ፍሬን ነው። ይሁንና እንሾሽላ (እንሶስላ) በሶዶ ጉራጌ (ክስታኔ) ማህበረሰብ ከመቀባትም በላይ በሠርግ ሰሞን በድምቀት የሚከበር ክዋኔ ነው። በመሠረቱ ይህ ባህላዊ ክዋኔ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሙሽሪት በጫጉላ ጊዜ ሙሽራውን እንዳትቧጭረው ሲባል የሙሽሪት ጥፍር ሙሉ ለሙሉ የሚነቀልበት ሥነ ሥርዓት የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ድርጊቱ ጎጂ መሆኑ በማህበረሰቡ ውስጥ በመታወቁ አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ እንዲቀር ከመደረጉም ባሻገር በዕለቱ የሚከወኑት ባህላዊ ሥርዓቶች በተለይ ጭፈራውና ድግሱ አሁንም ደምቆ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ ይገኛል።
የአካባቢው ተወላጅና የእንሶስላ በዓል ሙዚቃ ተጫዋች የሆኑት አቶ ዱቤ ለማ እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ ሙሽሪት የሠርጓ ቀን አንድ ወር ሲቀረው ንጥር ቅቤ፤ ቅንጬና የተለያዩ ጠጋኝ ምግቦች ይዘጋጃሉ፤ እናቷና ሌሎች ዘመዶች ተሰብስበው የሙሽሪትን ጥፍር ነቀላ ያካሂዳሉ። በወቅቱ ታዲያ የአካባቢው ወጠምሻ ጎረምሶች ተጠርተው ምሽሪትን ጠፍንገው ያስራሉ፤ እናቶች ደግሞ የሙሽሪትን ጥፍር ይነቅላሉ።
ጥፍር ነቀላው ከስሩ የሚከናወን በመሆኑ መድማትና የመሳሰሉ ጉዳቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። በዚህ ወቅት ታዲያ ሙሽሪት ህመሙንም ሆነ የጎረምሶችን እጅ መቋቋም ስለሚያቅታት በከፍተኛ ሁኔታ ትጮኻለች፤ ታለቅሳለች፤ አለፍ ሲልም ራሷን ልትስት ትችላለች። ግን ደግሞ አብዛኞቹ ሙሽሮች ይህ የዚያ ማህበረሰብ የተከበረ ወግና ልምድ በመሆኑ ከፍ ብላ መጮህም ሆነ አሻፈረኝ ብሎ መወራጨት አይደፍሩም። ይህንን ብታደርግ ማህበረሰቡ እንደነውር ስለሚቆጥርባት ነው። በመሆኑም ህመሟንና ስቃይዋን ሳትወድ በግዷ ትውጠዋለች።
ይሁንና ህመሙ ለአንድ ቀን የሚቆይ አይደለም፤ ከእዚያች ዕለት ጀምሮ ጥፍሯ ሙሉ ለሙሉ በመቆረጡ ራሷን ችላ የምትከውናቸውን ነገሮች ማድረግ አትችለም። በዚህም ምክንያት እስከሠርጓ ዕለት ድረስ የምትበላውም ሆነ የምትጠጣው በቤተሰቦቿ ድጋፍ ነው፤ ሌላው ይቅርና በቁስሉ ምክንያት ማከክ እንኳን የሚያቅጣት በመሆኑ ከሚደርስባት አካላዊ ጉዳት ባሻገር በሥነ-ልቦና ትሰበራለች። በሌላ በኩል ቁስሉ ቶሎ ያሽርላት ዘንድ ቤተሰቦቿ ቅቤ አዘጋጅተው ይነክሩላታል፤ እንዳያመረቅዝም ይንከባከቧታል። እንሾሽላም ቀብተው ያስሩላታል።
አቶ ዱቤ እንደሚሉት፤ ሙሽሪት ጥፍሯ ሙሉ ለሙሉ እንዲነቀል የሚደረገው በሠርጓ ዕለት ግንኙነት በሚደረግበት ጊዜ ሙሽራውን እንዳትቧጭረውና እንዳትጎዳው በማሰብ ነው። በተጨማሪም ከሌላው ሰው ለየት ብላ እንድትታይ የሚለውም ሌላው ምክንያት ነው። ይህ ለወንዱ ስሜት ሲባል ብቻ የሚደረገው ባህላዊ ክዋኔ በሴቷ ላይ ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ በቀላሉ የሚታይ ካለመሆኑም በላይ በህመምና በስቃይ የተጀመረው ይህ የሠርግ ሥነሥርዓት ልክ እንደሌላው ሰው ደስታዋን እንዳታጥም ከማድረጉም ባሻገር በትዳሯ ዘመን ሁሉ የበታችነት ስሜት እንዲያድርባት በማድረግ ረገድ የሚኖረው አሉታዊ ሚና ከፍተኛ ነው።
በክስታኔ ማህበረሰብ የሚከወነው ይህ ጥንታዊ ጉጂ ባህላዊ ድርጊት ከጥቅሙ ይልቅ በሴቷ ላይ የሚያመጣው አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት ከፍ ያለ መሆኑን ማህበረሰቡ እየተረዳ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የትኛውም ክስታኔ ቤተሰብ ውስጥ የሙሽሬት ጥፍር ነቀላ አይከናወንም በማለት አቶ ዱቤ ይናገራሉ።
ነገር ግን ከጥፍር ነቀላውና እሾሽላ መቀባቱ በስተቀር ጥንት የሚደረጉ የሠርግ ዝግጅቶችም ሆኑ የጭፈራው ሥነሥርዓት መቀጠሉን ይናገራሉ። ከገጠሩ ማህበረሰብ ባሻገር በከተማ የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ሂደቱን በላቀና በደመቀ ሁኔታ እያከበሩትና ከትውልድ ትውልድም ባህላዊ ይዘቱን እንደጠበቀ እንዲሻገር እያደረጉ መሆኑን ይገልፃሉ። ‹‹ይህ ሥነሥርዓት የሠርጉ ዋዜማ ላይ የሚከናወን በመሆኑ ሠርጉን የበለጠ ለማድመቅና ማራኪ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። በገጠር አሉ የተባሉ ጨፋሪዎችና ዘፋኞች ሠርጉ ቤት መጥተው ያደምቁታል›› ይላሉ። በከተማም እንደእርሳቸው ሁሉ በባንድ ደረጃ ተሰባስበው በየተጠሩበት ቤት እየዞሩ ይህንን ባህላዊ ክዋኔ ይበልጥ የሚያደምቁበት ሁኔታ መኖሩን ነው ያጫወቱን።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ የእንሾሽላ ሥርዓት በሶዶ ክስታኔ ማህበረሰብ ከሠርጉ ዕለት በበለጠ የሚወደድና የሚናፈቀው ባህል ሲሆን የብሔረሰቡን ትክክለኛ ባህላዊ ትውፊት የሚታይበት ልዩ ሥርዓትም ነው። ከሠርጉ ሁለት ቀን ቀደም ብሎ የሚከናወነው ይህ ሥነ-ሥርዓት አሁን ላይ ሴቷም ሆነ ወንዱ ሙሽራ በየቤታቸው የሚያከብሩት ነው። ብዙ ጊዜ ሠርጉ እሁድ ከሆነ አርብ ዕለት ማታ ነው የእንሶስላ ሥርዓት የሚከናወነው።
ከዚያ ቀን ከወር በፊት ጌሾ ተወቅጦ ጠላ ይጠመቃል፤ ስንዴ ተፈትጎ ዳቦ ይጋገራል። በዕለቱ ዘመድ አዝማድ እንዲሁም ወዳጅ ጎረቤት በሙሉ ተሰብስቦ ደስታውን በደመቀ ጭፍራና ምርቃትና ሙገሳን ያዘሉ ዘፈኖች ያደምቁታል። ወንዱ በቤቱ ከሚዜዎቹ ጋር በመሆን ቤተሰብ ዘመድ አዝማድ በተሰበሰበበት ከቃጫ በተሠራ ጅባ መሀል ላይ በነጠላ ተሸፍነው ይቀመጣሉ። በዚህ ጊዜ የእናት የአባት፤ የአክስት የአጎት፤ የወንድምና የእህት እንዲሁም የጎሳ ስም እየጠራ ሙገሳና ምርቃት ይከናወናል።
በዙሪያቸው የከበባቸው ቤተሰብ ዘመድ አዝማድና የአካባቢው ሰው ይጨፍራል። የእንሶስላ ባህሉን የሚገልጽ ዘፈን አለ እሱ ይዘፈናል። ዘፈኑን በማውጣት የሚጀምሩት ወላጅ አባት ቀጥሎ እናት፣ ከዚያም አጎት፣ አክስት እያለ ይቀጥላል። በዘፈኑ ግጥም እህት ወንድም እንዲሁም በሕይወት የሌሉ ዘመዶቹ ሁሉ ይጠራሉ ይወደሳሉ። ጭፈራውም ይሞቃል ይደምቃል። በዚህ ጊዜ ሁሉ ሙሽራው ከሚዜዎቹ ጋር በነጠላ ተሸፍኖ በጅባ ላይ ተቀምጧል። ታድያ በግጥሞቹ መሀል ማልቀስም ይኖራል። በተለይም በሞት የተለዩት ዘመዶቹ በሚጠሩበት ጊዜ ያለቅሳል። እናም ከወላጅ አባት የተጀመረው ባህላዊ ዘፈን ቤተዘመዶቹጋ ደርሶ ሲያበቃ ሙሽራውና ሚዜዎቹ ከሽፍንፍናቸው ወጥተው ይጨፍራሉ።
በዕለቱ ከሠርጉም ከሌሎች በዓላት በተለየ የሚዜሙ ዜማዎች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ዱቤ አመሻሽ ላይ የተጀመረው ጭፈራና ፌሽታ እየተበላ እየተጠጣና በቅብብል እየተዘፈና እየተጨፈረ እስከሚነጋ ድረስ የማያበቃ መሆኑንም ነው የገለፁት። ‹‹በጉራጌ ብሔረሰብ እንሾሽላ ትልቅ ቦታ ያለው ሥነሥርዓት በመሆኑ ዘመድ አዝማድ ይጠራል፤ ለሠርግ የተጠራው ሰው በሙሉ በዚህ ቀን መምጣት ይጠበቅበታል። በአካባቢው ምንአለ? እስኪባል ድረስ የሠርጉን ድባብ የሚደምቀው የእንሶስላ በዓል ላይ ነው›› ሲሉም ይገልፃሉ።
በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጀው ጠላ በዕለቱ በእንግዶች መሰብሰቢያ አዳራሽ መሃል ቦታ ተፈልጎ በተቀመጠው ትልቅ እንስራ ውስጥ ይሞላል ከዚያ እየተቀዳም ለእንግዶችና ለዘመድ አዝማዱ ይሰጣል። ባለሦስት እግር ወንበሮች በአዳራሹ ዳር ዳር ይሰደሩና እንግዶቹ ይቀመጣሉ። የተቀመጠው ሲያጨበጭብ ሌላው ደግሞ እየተነሳ እንስራውን ከቦ ከበሮ ይደልቃል ይጨፍራል።
ለዕለቱ የተዘጋጀው ጠላ በሰው ፊት እየመጣ ወደ እንስራ ሲገለበጥ የሚዘፈነው ባህላዊ ዘፈን፤
‹‹ሞላ አልሞላ፤ ሞላ አልሞላ /2/
ስከሪ አልሞላ፤
ስከሪ አልሞላ /2/ የሚል ይሆናል። ትርጉሙም ‹‹ገንቦው ሞልቶዋል አልሞላም›› ማለት ነው። በዕለተ አርብ የሚከናወነው ይህ የእንሶስላ ባህል በሴቷ ቤትም በተመሳሳይ የሚከበር ሲሆን ሙሽሮቹ ‹‹እንሾሽላ›› እየተባለ እስከሚጨፈር ድረስ ሴቷም ሆነ ወንዱ ሙሽራ ከጓዳቸው አይወጡም፤ ጭፈራው ሲደራ ግን በእልልታና በሆታ ታጅበው በአዳራሹ ከተዘጋጀላቸው ስፍራ ይቀመጣሉ።
በዚህ ጊዜ ታዳሚው ለሙሽሪትና ለሙሽራው ‹‹ እንሾሽላ ያድግልችጎይ የአባአዮ በለ
እንሾሽላ ያድግልችጎይ የእማማ ነው በለ እንሾሽላ ያድጎልችጎይ አንሳቢ ነው በለ….›› በማለት ያዜሙላቸዋል። ይህም ማለት እንሾሽላ ሲታሰርልሽ (ሲታሰርልህ) የአባቴ ነው፤ የእናቴ፤ የወንድሜ የእህቴ የአጎቴ የአክስቴ ነው በዬ (በል) እየተባለ የቤተዘመዱ ሁሉ ስም እየተጠራ ሙገሳና ለዛ ባለው ባህላዊ ዘፈን ጭፈራው ይደራል። በነገራችን ላይ እንዲህ እየተባለ ይዘፈን እንጂ በተለይም በከተማ ነዋሪ በሆኑ የብሔረሰቡ ተወላጆች ዘንድ እንሾሽላ መቀባት ቀርቷል። ከዚያ ይልቅም ዘመን አመጣሽ በሆኑ መዋቢያዎች ነው ሙሽሪት ደምቃ የምትታየው። ያም ቢሆን በነጠላ ተሸፍና ነው በቤተዘመድና በወዳጅ ጎረቤቱ ፊት የምትቀርበው።
በዚህ ባህላዊ ክዋኔ ዘመድ አዝማድ ስሙ እየተጠራ ከመሞጋገስ እና ከመመራረቅ ባለፈ ማህበረሰቡ እርስ በእርስ ያለውን መከባበር ይበልጥ አጉልቶ የሚያሳይ ነው። በተለይ ለሽማግሌዎችና ለእናቶች ምርቃት አዲሱ ትውልድ ዋጋ እንዲሰጥ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ነው አቶ ዱቤ ያጫወቱን። ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ይህንን ባህላዊ ክዋኔ ትውልዱ ለማስጠበቅ የሚያደርገው ጥረት በእጅጉ ሊበረታታ የሚገባ መሆኑን የገለፁት አቶ ዱቤ አሁን ላይ ከብሔረሰቡ ተወላጆች ባሻገር የሌላ ብሔረሰቦች ዘንድም እየታወቀ በመምጣቱ በናፍቆት የሚጠበቅ ቀን መሆኑን አብራርተዋል።
ከፌዴራል እስከ ዞን ድረስ የባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ይህ እሴት ለአገርም የቱሪዝም ምንጭ እንዲሆን ሊሠሩ እንደሚገባ ያሳስባሉ። ከዚህም ባሻገር ማህበረሰቡ በባህላዊ ሥርዓቱ ይከናወን የነበረውን ጎጂ ድርጊት በማስቆም ባህላዊ ክዋኔው ይዘቱን ጠብቆ ከትውልድ ትውልድ እንዲሻገር በማድረግ በኩል ያደረገው አስተዋፅኦ በዘርፉ ምሁራን ጥልቅ ጥናት ሊደረግበትና ለሌሎች ማህበረሰቦችም ተሞክሮውን ማካፈል ጠቃሚ መሆኑን ነው የባህል ተጫዋቹ ያስገነዘቡት።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን የካቲት 10 ቀን 2015 ዓ.ም