ምንም ሳንፈራገጥ፣ እንዳለ ስንፈታው “ታረቀን” ማለት “ይቅር በለን” ማለት ነው። “ይቅር በለን” ማለት ደግሞ “አጥፍተናል፣ በምንም ይሁን በምን ብቻ “ጨቅይተናል”፣ “ቆሽሸናል” . . . (ሌላውን አንባቢ ሊያክልበት ይችላል) ማለት ነውና ይሄንን ይዘን ወደ ፊት እንቀጥል።
ከሁሉም በፊት “መጀመሪያ ቃል ነበር፤ …” እንዲል መጽሐፉ መጀመሪያ “እርቅ” የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፅንሰ-ሀሳብ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። “እርቅ” ከእግዚአብሔር የራቀን መመለሻ መሆኑንም እንደዛው። (ለበለጠ ግንዛቤና አስተውሎት ሐዋርያው ጳውሎስ 1፣ 21-22፤ ሮም 5፣10፤ 2. ቆሮንቶስ 5፣18-19፤ ቆላስይስ 1፣ 19-20 እና ሌሎችንም መመልከት ይቻላል።)
እዚህ ላይ በተለያዩ ቦታዎች፣ ታክሲ ውስጥ ጭምር ብዙ ጊዜ አጋጥሞኝ በጥሞና ካዳመጥኳቸው ዜማና መንፈሳዊ መዝሙሮች መካከል የሚፍታህ ሁሴን “ታረቀን፣ ታረቀን አላህ … ታረቀን አላህ …” የሚለው መንዙማ ቀዳሚው ነው። የሊቀ መዘምራን ይልማ ኃይሉ “ክርስቶስ ታረቀን” ዲቪዲም ከዚሁ ጋር በአቻነት የሚጠቀስ ነው።
(ይሄ ሁሉ ምንድ ነው? “ታረቀን …”፣ “ታረቀን …” የሚል ምስኪን ካለ እሱ ያለው እዚህ አገር አይደለምና ገጣሚው “… እሱን ዝለለው” እንዳለው፣ ዘለነዋል።)
ለዚህ ጽሑፍ ሲባል፣ ጉዳዩ የቋንቋ (ሊንጉዊስቲክስ) መሆኑን በልባችን ይዘን፤ የስያሜ ጉዳይ እንደሆነም በአእምሯችን መዝግበን፤ በ“አላህ” ቦታ ”እግዚአብሔር”ን በተለዋዋጭነት ተክተን ሁላችንም፣ ባንድ ላይ “ታረቀን ታረቀን … አምላክ ታረቀን …” እንል ዘንድ ሁኔታዎች ብቻ ሳይሆኑ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ታስገድዳለች።
ሁሉም፣ አላህ ባዮቹም ሆኑ እግዚአብሔር ወይም ኢየሱስ ባዮቹ (ሁሉም የአዳምና ሄዋን ዘር መሆናቸውን በሚገባ ያውቁታል) ባንድ ላይ “ታረቀን … እግዚአብሔር/ አምላክ/ አላህ/ እየሱስ ታረቀን …” ካላሉ ሁሉም ልክ አይመጣምና በሁኔታዎች ላይ መቆዘምን፤ በነበረውና እየሆነ ባለው ላይ መብሰክሰክን ግድ ይላል ማለት ነው።
በእርግጥ ጉዳዩ ቀላል አይመስል ይሆናል። ግን ደግሞ እጅግም ከባድ አይደለም። ከባድ ነው የሚል ካለ ወደ ወሎ – ገራዶም ይሁን ደሴ፤ ቃሉም ይሁን ወረኢሉ፤ ካስፈለገም ወልዲያ፣ ኮምቦልቻ … ሄድ ብሎ አስፈላጊውን ትምህርት ቀስሞ መመለስና አምላክ እና እግዚአብሔርን ስፍራ እያለዋወጠ መጠቀም ይችላል። “ወደ ወሎ ብቅ ብዬስ?” የሚል ካለ መልሱ “ደሴ ቄስ መሀመድ አሉልህ” ይሆናልና እዳው ገብስ ነው። ምንጭ የሚፈልግ ካለ ደግሞ ወደ ስንዱ አበበ “ሃሎ” የማለት፣ ወይም በማህበራዊ ድረ-ገጽዋ “ቴክስት” የማድረግ መብቱ የተጠበቀ ነው። (ወይንም (ምን ላይ ነበር? ከሳቸው ጋር ያደረገችውን (ቃለ-መጠይቅ?) የጻፈችው?)፣ ፈልጎ ማንበብ።)
ሊቀ መዘምራን ይልማ ኃይሉ ከላይ በጠቀስንለት ተወዳጅ ዲቪዲው “ክርስቶስ ታረቀን፣ ይቅር ይበለን” እንዳለው ሁሉ፤ መቼም እዚህ ላይ “ታረቀን” ስንል ምን ማለታችን እንደ ሆነ፣ አምላካችን ሆይ፣ አስቀይመንሀል፣ ከትእዛዝህ ውጪ ሄደናል፤ አንተ የማትፈልገውን፣ የማትሻውን አድርገናል፤ ከሰው ልጅ፣ ከአዳም ዘር … የማይጠበቅ ሀጢያት ፈፅመናል፣ ወንድም በወንድሙ ላይ አይነሳ ያልከውን ጥሰናል፤ ጓደኛህን እንደ ራስህ ውደድ የሚለውን ትእዛዝህን ሁሉ በነጭ ሰርዘናል፤ ታላላቆችህን አክብር ያልከን ቢሆንም እኛ ግን በተቃራኒው ሆነን ተገኝተናል፤ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሄር ቤት መሆኗን ገና በጠዋት ብትነግረንም እኛ ግን ዶጋ አመድ አድርገን አስቀይመንሀል … ማለታችን እንደ ሆነ እማያቅ ካለ “አውቆ የተኛ …” ነውና እሰጥ አገባ ውስጥ አንገባም።
እዚህ ላይ የኢትዮጵያዊያንንና የአምላክን የቀረበ ግንኙነትና ከፈጣሪ ይቅርታ መሻትን፣ ይታረቀን ዘንድ ተማፅኖን በተመለከተ፣ የሪፖርተሩ ዘውዳለም ደምሴ ከዘንድሮው የገና በአል ጋር አያይዘው በ“የሳምንቱ ገጠመኝ” አምድ ስር ባሰፈሩት ጽሁፍ የሚከተለውንም አስፍረው ነበር፤
አንዲት እናት ከገበያ መልስ፣ ‹‹አምላኬ እባክህን ይቅር ብለኸን ታረቀን…›› እያሉ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ መንገድ ላይ አገኘኋቸው። ‹‹እናቴ አምላክዎን እያነጋገሩ ያሉት ምን ገጥመዎት ነው?›› በማለት ቀረብ አልኳቸው። በቀኝ እጃቸው የያዙትን ዘንቢል እያመለከቱኝ፣ ‹‹ይኼ ዘንቢል ዕድሜ ልኩን የኖረው ከእኔ ጋር ነው። ድሮ በደጉ ዘመን በ20 ብር ይሞላ የነበረ ዘንቢል አሁን በ1ሺህ 500 ብር የያዘውን ተመልከት። አንዲት ዶሮ፣ ቅመማ ቅመምና የወይራ እንጨት ብቻ ነው። እነዚህ ደግሞ ሩብ የሚሆነውን የዘንቢል አካል አልሞሉትም። እሱ ባለቤቱ ዘንድሮ ካልታረቀን በቀር ከዚህ እሳት ከሆነ ኑሮ ማንም አያስጥለን…›› እያሉ መንገዳቸውን ቀጠሉ።
ነበር ያለው። እንደ’ኚህ እናት ድምዳሜ የኑሮ ውድነቱ መንስኤ እኛ የሰራነው ፈጣሪን ያስቀየመ ጥፋት ነው ማለት ነው። አሁን እየሆነ ላለውስ፣ በሰራነው ጥፋት እየተቀጣን ላለመሆኑ ምን ማስረጃ አለ? የለም። በመሆኑም “ይቅር በለን”፤ “ታረቀን” ማለቱ ነው የሚያዋጣው፤ ታረቀን።
ቱርኮች ሰሞኑን የደረሰባቸውን የተፈጥሮ አደጋ (ርእደ ምድር) ተከትሎ እያሉት ያሉትም ይህንኑ ነውና “ታረቀን”፤ “ምህረትህን አውርድልን” ማለት አጥፊ ባለበት ቦታ ሁሉ አለ ማለት ነውና “ታረቀን” ማለት ብርቅ አይደለም።
በላይኛው ያላበቃው የሪፖርተሩ ጸሐፊ የእናቶችን (በተራዛሚው የኢትዮጵያዊያንን) እና የአምላክን የጠበቀ ግንኙነትና ትስስር እንደሚከተለው አስነብቦናል፤
እናቴ ፈጣሪ ነፍሷን በአፀደ ገነት ያሳርፈውና በ1977 ዓ.ም በአንዱ ቀን መርካቶ ውላ ስትመጣ ለመቀበል እኔና ወንድሜ አውቶቡስ ፌርማታ ስንጠብቃት ሳለ፣ የተሳፈረችበት የአንበሳ አውቶቡስ ደርሶ ሰዎችን ሲያራግፍ በሁለት ወጣቶች ዕርዳታ አንዳች የሚያህለው ዘንቢሏ ሲወርድ ተሯሩጠን ተቀበልናት። እኔና ወንድሜ መርካቶ ስለነበረው ውሎዋ እየጠየቅን ያንን በሸቀጦች የተሞላ ዘንቢል ተሸክመን ወደ ቤት ስናመራ፣ ‹‹ልጆቼ ድሮ በአሥር ብር ይሞላ የነበረ ዘንቢሌ ይኸው እንደምታዩት ሰላሳ ብር ፈጀ … ለማንኛውም እሱ አምላካችን ይታረቀን እንጂ የወደፊቱ ነገር ያስፈራል …›› ያለችን ፈፅሞ አይረሳኝም። ያንን አንዳች የሚያህል የሰሌን ዘንቢል ዛሬ በሰላሳ ሺህ ብር ለመሙላት የሚቻል አይመስለኝም።
አዎ፣ አበሻና እግዚአብሔር ቀረቤታቸው እዚህ ድረስ፤ ይሄንን ያህል ነው። (እዚህ ላይ ይህንን የጠበቀ ትስስር ለመበጠስ እየተደረገ ያለውን ያልተቋረጠ ርብርብ ልብ ይሏል)። በመግቢያችን ስር እንደገለፅነው፣ በየሃይማኖቱ ሁሉም ይኸው መሆኑንም ልብ ማለት፤ መገንዘብ ያስፈልጋል።
በመሰረቱ፣ የአንድ አገር ፈተና፣ መከራ፣ አበሳና ሰቆቃ የሚበዛው “የግለሰብ፣ የማኅበረሰብ እና የሀገር መከራ የሚፀናው በየደረጃው፤ ማለትም በግለሰብ፣ በማኅበረሰብ እና በአገር ደረጃ የመንግሥት ሥርዓትን በሚመሩ፣ ሃይማኖትን በሚያስተምሩ፣ ባህልን በሚያስጠብቁ (አሁን ደግሞ “የማህበረሰብ አንቂ” ተብዬዎች አሉ) ሰዎች ደረጃ ሁሉ ጥመት፣ ክፋት፣ ኃጢአት፣ ርኵሰት እየበዛ በተቃራኒው ደግሞ ርቱዕነት፣ መልካምነት፣ ቅድስና፣ እምነት ሲያንስ ነው።” የሚል ነገር (የት እንደ ሆነ እንጃ እንጂ) ማንበቤን አስታውሳለሁ። ለዚህም ይመስላል የሙዚቃው አለም ንጉስ ጥላሁን ገሠሠ “መከራ ይምከረው . . .”፣ “ብድሩ ይድረሰው . . .” ሲል አስቀድሞ ያዜመው። እኛም የጋሽ ጥላሁንን ያህል ባንጨክንም ለሁሉም “የስራውን ይስጠው” ሳንል ማለፍ ግን ለጉዳዩ ደንታቢስ መሆንን ያመለክታልና ያስወቅሳል።
“ታረቀን” ከመደበኛው አነጋገር ባለፈም በተረትና ምሳሌ (ምሳሌያዊ አነጋገሮች)፣ በፈሊጥ እና ሌሎችም ውስጥ እየገባ ሰብአዊ፣ ማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ሲሰጥ ኖሯል።
”የኢትዮጵያ ፍልስፍና የሚገኘው በስነቃልና ቅኔዎቿ ውስጥ ነው።” የሚለውን ይዘን፤ “ምሣሌያዊ አነጋገሮቻችን ስለ እርቅ (መታረቅ) ምን ይላሉ?” ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ የትየለሌ ሲሆን፤ በወካይነት የሚከተሉትን ማየት ይቻላል፤
ነገር በእርቅ መንገድ በድርቅ፤ ነገር በእርቅ ወይፈንን በድርቅ፤ አሳው እንዳይሞት ውሀው እንዳይደርቅ አድርጎ ነው እርቅ፤ አይን አይፈስ እርቅ አይፈርስ፤ እርቅ ቢፈርስ ካስታራቂው ድረስ፤ እርቅ አፍራሽ፣ ቤተክርስትያን ተኳሽ፤ እርቅ ከወርቅ ዛላ ከምርቅ፤ እርቅ የሰው ደም ያደርቅ፤ …እና ሌሎችም።
ድሮ ድሮ የነበረው “ክፉ ሰው” ነበር፤ ቢበዛ “ክፉ ሰዎች”። ዛሬ ግን ጉዳዩ ከጣራ በላይ ሆኖ “የክፋት ቡድኖች” እንደ አሸን የፈሉበትና ለእነዚሁ ቡድኖች ያልተቋረጠ፣ ስውርና ግልፅ የሆነ ሁለገብ ድጋፍ የሚሰጡ አካላት የተፈለፈሉበት ዘመን ሆኖት እርፍ ብሏል።
ርእሳችንን “ታረቀን።” ብለን ስንነሳ ጉዳዩ በርካታ ጉዳዮችን በጉያው እንደያዘ ሳንገነዘበው ጠፍቶን አይደለም። ርእሰ ጉዳዩን ይዘን ወደ አደባባይ የመጣነው በፖለቲካው ተውኔትና መድረኩ አብዝቶ ከሚዘወተረው “እርቅ” (reconciliation) እስከ ጥልቅና ረቂቅ እስከሆነው እምነት (ማመን) ድረስ እንደሚዘልቅ ተረድተን ነው።
በታላቁ መጽሐፍ እንደተገለፀው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፣ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም” (ዮሐ. 5፡24) በማለት ማመን የሕይወት መንገድ እንደ መሆኑ መጠን እርቅንና ይቅርታን ከላይኛው መንግሥት ለማግኘት በእሱ፣ በሰማያዊው መንግሥት ማመን የግድ እንደ ሆነው ሁሉ እርስ በእርስ መተማመንም የግድ ይሆናል ማለት ነው።
ወደ ምድራዊው አለም ስንመጣ ነገሮች ሁሉ መበላሸት ከጀመሩ ዘመናት መቆጠራቸውን የሚያስገነዝቡን መረጃና ማስረጃዎችን እናገኛለን። ከእነዚህ ማስረጃዎችና መረጃዎች አንዱ የሆነው እንደሚነግረን ከሆነ፣ የአሁኑ ዘመን የአለማችን ፖለቲካ ግራ የገባው ነው፤ የሚሉት – ማስረጃዎቹም፣ መረጃዎቹም ናቸው። እንደነዚሁ ወገኖች አባባል ይህ ራሱ ራሱን በቻለ ሁኔታ “ታረቀን” የሚያስብል ነው። (እዚህ ስለ መሪ፣ ተመሪና አመራር ከተነሳ አይቀር የትእዛዙ ካሳን “ቅን መሪ” (2012 ዓ.ም) ማንበብ ጠቃሚ መሆኑን ይህ ጽሑፍ ሊጠቁም ይፈልጋል።)
አንዳንድ ሀገራት በውስን ዘመን ሕዝብና ሀገራቸውን ከነበሩበት አረንቋ አውጥተው ሁለት እና ሶስት እርምጃ ወደ ፊት ሲያስኬዱ እየተመለከትን ሲሆን፤ ለዚህም 14ኛውን የአምስት አመት የልማት ፕሮግራሟን እያከናወነች የምትገኘውና ከ1978 እስከ 2014 ድረስ ባሉት አመታት ብቻ 250 ሚሊዮን የደሀውን ህዝብ ቁጥር ወደ 70 ሚሊዮን ያወረደችው ታላቋ ቻይና ትጠቀሳለች። (እዚህ ጋ ጉዳዩን የምር እናድርገውና እንነጋገር።)
በ2021 በቀረበው የአለም አቀፍ መዛኞች ጥናት ይህች ታላቅ አገር 770 ሚሊዮን ዜጎቿን ከከፋ ድህነት በማውጣት ታሪክ አስመዝግባለች (ካስፈለገ፣ “In 2021, the government declared the success of its mission: lifting 770 million of its citizens out of poverty. Considering the speed and the population, China’s progress is unprecedented.” (ኦክቶበር 7 2022) የሚለውን ፈልጎ ማጣጣም ነው)።
በርካታ ሀገራትም ጉድ ከማለት አልፈው ምርጫቸውን “የቻይና ሞዴል”ን መከተል በማድረግ ላይ ናቸው። አንዳንድ ሀገራት ግን ሀገራቸውን ወደ እንጦሮጦስ ለመላክ እያደረጉት ያለው ጥረትና ትጋት ሲታይ ይህንን የቻይና ስኬት እንኳን ሊከተሉት የሰሙት ሁሉ አይመስሉም። አንዱ የ“ታረቀን።” አላማ እንግዲህ ፈጣሪ ከእርስ በእርስ ቁርቋሶ ወጥተን ከ“ሕዝበኝነት” ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ከሌላት፣ እንደ ቻይና ሕዝባችንን ካለበት ሁለንተናዊ ስቃይ እናወጣው ዘንድ መማፀን ነውና ደጋግመን “ታረቀን።” ማለቱ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ (“የህልውና”ም ልንለው እንችላለን) ይሆናል ማለት ነው።
ገጣሚው “ምናልባት ቢያስፏጨው …” እንዳለው፣ ምናልባት የሚነሽጠው ካለ ወደ ታላቋ ቻይና እንመለስ። (በቻይና ፋንታ ካልተገነጠልኩ ብሎ 30 አመታትን ጦርነት ውስጥ የኖረውና በተገነጠለ በሁለት አመቱ ተመልሶ ወደ እርስ በርስ ጦርነት የገባውን ደቡብ ሱዳን እዚህ እንዳንጠቅሰው እሱ ራሱ “ታረቀን” ማለት ከሚገባቸው ወገኖች ተርታ መሰለፍ ያለበት በመሆኑ እንደሆነ ልብ ይባልልን ዘንድ ያስፈልጋል።)
ይህንን የቻይናን ጉዳይ ከአርአያነቱ አኳያ ትንሽ ሰፋና ገፋ አድርገን ስንመረምረው፣ የኮሚኒስት ፓርቲው አባላት ህዝባቸውን ከከፋ ድህነት (absolute poverty) ለማውጣት ሲያደርጉ በነበረው ርብርብ ምክንያት 1ሺህ 800 አባላቱ የህይወት መስዋእትነት ከፍለዋል (በእውነት ያስቀናል፤ የበለጠ የሚያስቀናው ደግሞ የአንዳንድ ሀገራት ፓርቲ አባላት ህይወታቸውን አሳልፈው የሚሰጡት ለምን እንደሆነ ሲታሰብ ነው።) እዚህ ጋ “ጉድ በል ጎንደር” እንዳላልን ግን ሊታወቅ ይገባል።
በተለይ ከ1950ዎቹ እስከ 1970ዎቹ አጋማሽ ድረስ በከፋ ድህነትና ረሀብ ትታወቅ የነበረችው፣ ከአጠቃላይ የአለም ህዝብ 18 ነጥብ 47% የሚኖርባት ቻይና በወቅቱ በነበሩት መሪ (Xi) አመራርና አገሪቱ በምትከተለው ድህነት ተኮር ስትራቴጂ በ2012 ብቻ በከተሞች በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ይኖሩ ከነበሩት መካከል 100 ሚሊዮኖችን ከድህነት ለማውጣት ችላለች። ይህም “የተሟላ ድል” ብቻ ሳይሆን ድህነትን በማስወገድ በኩል ቻይና ለአለም ያበረከተችው አስተዋፅኦ ተደርጎ ተወስዶላት (“complete victory,” a “miracle for humankind,” and China’s great contribution to the world. ተብሎላት ማለት ነው) አድናቆትን አትርፎላታል (የሚያስፏጨው ካለ ይህም ያስፏጫል)። እወቅ ያለው በ40 ቀን፤ አትወቅ ያለው በ40 አመት … ይሏል ይህ ነውና፤ አሁንም (የሚቀና ካለ) የቻይናው ስኬት ያስቀናል። በተለይ ሕዝባዊ ኃላፊነትን ወስዶ አመራር ላይ የተቀመጠን አካል ቅናቱ ምላጭ ያስውጣል። ግን ምን ያደርጋል፣ አለመታደል ሆኖ የአብዛኞቹ ሀገራት አመራሮች ለቅናት የታደሉ አይደሉምና ይህ ራሱ ለ“ታረቀን” አንዱ ምክንያት መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ታረቀን!!!
ቸር እንሰንብት።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም