(የመጨረሻ ክፍል )
የተለያዩ ቆየት ያሉ የጥናትና የምርምር ወረቀቶች አገራችን ኢትዮጵያ በመስኖ መልማት የሚችል 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ሲኖራት ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ መሬት የሚገኘው በዓባይ ተፋሰስ ነው። የሚያስቆጨው እስካሁን የለማው ከ6 በመቶ አለመብለጡ ነው። ኢትዮጵያ እስካሁን ያለማችው 250ሺህ ሄክታር መሬት ሲሆን ከዚህ ውስጥ የዓባይ ተፋሰስ ድርሻ ከ20ሺህ ሄክታር አይበልጥም። የአገራችን ግብርና የዝናብ ጥገኛ ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውሃ ማማ በመባል ብትታወቅም በየአመቱ ሊባል በሚችል ሁኔታ በድርቅ እየተጠቃች ነው። በየአስር አመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ በበልግና በመኸር በአመት ሁለት ጊዜ ሲጎበኘን እየተመለከትን ነው። ይህ ያልተስተካከለና የሚቆራረጥ ዝናብ የሚያስከትለው ድርቅ ሚሊዮኖች ለምግብ እጥረት እንዲዳረጉ ምክንያት እየሆነ ነው።
በውል እንደሚታወቀው አገራችን ከግብፅም ሆነ ከሱዳን ጋር የዓባይን ወንዝ በጋራ መጠቀም የሚያስችል ስምምነት የላትም። ሆኖም ለናይል ወንዝ 86 በመቶውን ውሃ የምታበረክተው ኢትዮጵያ በ1929ኙም ሆነ በ1959ኙ የቅኝ ገዢ ስምምነት እንደማትገዛ በየአጋጣሚው ከማሳወቅ ባሻገር እውን ሳይሆን ቢቀርም ከ1950ዎቹ ጀምሮ የኃይል ማመንጫና የመስኖ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። እኤአ ከ1958 እስከ 1963 ድረስ አሜሪካ እንዲህ እንደ ዛሬው የግብፅ ጥቅም አስከባሪ ሳትሆን የዓባይን ወንዝ ለማልማት በሚደረጉ ጥረቶች ግንባር ቀደም ተዋናይ ነበረች። ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅ የለም እንዲሉ። የዛሬውን ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ 33 የመስኖና የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን አጥንታ እንዲለሙ ምክረ ሀሳብ አቅርባ ነበር። ከእነዚህ ጥናቶች ሥራ ላይ የዋለው እኤአ በ1972 ዓ.ም የተገነባውና 128 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው የፊንጫ የውሃ ኃይል ቀዳሚ ነው ማለት ይቻላል።
ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ድርቅ በሌላ በኩል ፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገት እንደ ውጋት ቀስፈው ይዘዋታል። ከዚህ ውጋት ተንፈስ ለማለት የውሃ ሀብቷን አልምታ መጠቀም አለባት። የመስኖ መሠረተ ልማትን በማስፋት እያደገ የመጣውን የምግብ ፍላጎቷን በማሟላት ሕዝቧን ከተመፅዋችነት ማላቀቅ ይጠበቅባታል። ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ሽግግር እና በኩራዝ ጭስ ለሚጨናበሰው ከ60 ሚሊዮን ለሚበልጠው ሕዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይልና መብራት ለማቅረብ እንደ ዓባይ ያሉ አመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞቿን ገድባ መጠቀም የሞት ሽረት ትንቅንቅ እየሆነ መጥቷል። ከዚህ ከፍ ሲልም ኢትዮጵያ ለተፋሰሱ አገራት የኃይል አማራጭ የመሆን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋ አላት።
ይሁንና እስከቅርብ አመታት ድረስ በድህነቷ እንዲሁም ከዓለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድርና ድጋፍ ለማግኘት የምታደርገው ጥረት በግብፅ የተቀናጀ ስውርና ይፋ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ የተነሳ እቅዷ ሁሉ ይጨናገፍባት ስለነበር ግዙፍ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችንና ታላላቅ የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታዎችን ማካሄድ ስላልቻለች በከፋ ድህነት በመማቀቅ ላይ ትገኛለች።
የሚያሳዝነው ለኢትዮጵያ ሲሆን የሚታጠፈው የዓለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እጅ ለግብፅ ሲሆን ግን ያለስስት ይዘረጋል። ለጋስ ይሆናል። ግብፅ ይህን በመጠቀም ኢኮኖሚዋን ማሳደግ ችላለች። የአገር ውስጥ ጥቅል ምርቷ 235 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ፤ የዜጎቿ የነፍስ ወከፍ ገቢ 2ሺህ 440 ዶላር ደርሷል። የኢትዮጵያ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት 111.27 ቢሊዮን ሲሆን የነፍስ ወከፍ ገቢዋ ደግሞ 951 ዶላር ነው። ከዚህ የድህነት አረንቋ ወጥቶ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የተፈጥሮ ሀብቷን በተለይ የውሃ ሀብቷን በአግባቡ ማልማት ይኖርባታል።
ኢትዮጵያ እኤአ በ2025 ዓ.ም ከግብፅ በላይ የሕዝብ ብዛት ይኖራታል ተብሎ ተተንብዮአል። በዘወርዋራ ምግብና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስፈልገው ሕዝብ ቁጥር አሁን ካለው ይጨምራል ማለት ነው። ከግብፅ በላይ የውሃ ሀብቷን ለመስኖና ለኃይል ማመንጫ መጠቀም ይኖርባታል ማለት ነው። በግዛቷ ስር ያለ የውሃ ሀብቷን መጠቀም ደግሞ ሉዓላዊ መብቷ ነው። ሆኖም የፋይናንስ እጥረትና የቴክኖሎጂ ውስንነት ዘረፉን ለማልማት የተያዘውን እቅድ ፈታኝ ቢያደርገውም ተጨማሪ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችንና የመስኖ አውታሮችን መገንባት ቅድሚያ የተሰጠወው ተግባር ሆኖ ይቀጥላል። ቁልፉ የእድገትና የልማት ግብ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሁለንተናዊ መልኩ ድህነትን መቅረፍ ነውና። በ2003 ዓ.ም ከሱዳን ድንበር 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ግንባታው የተጀመረውና ለኃይል ማመንጫነት የሚውለውና 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ የሚይዘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እድገትንና ልማትን በማፋጠን ዜጎችን ከድህነት የማላቀቅ ራእይ ሰንቋል። ግድቡ በቀን 6ሺህ ሜጋ ዋት፣ በአመት 15ሺህ 130 ጊጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው።
በዚህም የአገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትን በማርካት ለምሥራቅ አፍሪካ በተለይ ለራስጌ ተፋሰስ አገራትም የማቅረብ እቅድ አለው። ግድቡ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘውን የንጹህ ኃይል ተደራሽነት ያሳድጋል። የዓለም ባንክ ጥናት እንደሚያመለክተው ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የንጹህ ኃይል ሽፋን ከ15 በመቶ በታች ሲሆን፣ የአገራችን 3 ነጥብ 5 በመቶ፣ የሱዳን 41 ነጥብ 3 በመቶ ፣ የግብፅ 97 ነጥብ 6 በመቶ ነው ። ከሰሀራ በታች ያሉ አገራት የኤሌክትሪክ ሽፋን 24 በመቶ ፤ የኢትዮጵያ ከ45 በመቶ ያልበለጠ ፣ የሱዳን ከ57 በመቶ ያልበለጠ ሲሆን የግብፅ ሽፋን ግን 100 በመቶ ደርሷል። በናይል ውሃ አጠቃቀም ላይ ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን በመጥቀስ ብቸኛ ባለመብትና ተጠቃሚ እኔነኝ በማለት የያዘችው ግትር አቋም፤ የራስጌ አገራት በዓለምአቀፍ ሕግ የተረጋገጠላቸውን ውሃውን በፍትሐዊነት የመጠቀም ተፈጥሮአዊ መብት የሚጥስ ስለሆነ በንግግርና በውይይት ካልተፈታ ለግጭት ሊዳርግ ይችላል ተብሎ እየተፈራ ነው።
የዓባይ ወንዝ እርዝመት 6650 ኪሎ ሜትር ይጠጋል። የተጠቃሚው ሕዝብ ቁጥር አንድ ላይ ቢደመር ወደ አምስት መቶ ሚሊዮን ይደርሳል። ኢትዮጵያ እና ግብፅን በዲፕሎማሲው መስክ በተደጋጋሚ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲገናኙ እና እንዲነጋገሩ አድርጓል። ሆኖም ግብፅ የምታቀርበው ሀሳብ ሰጥቶ ለመቀበል ዝግጁ አለመሆኗን በተደጋጋሚ አሳይቷል። ግብፅ የህዳሴው ግድብ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ በየዓመቱ ይልቀቅ በሚል ያቀረበችው ሐሳብ በአብነት ይወሳል። የኢትዮጵያ የውሃ መስኖና ኢነርጂ የቀድሞ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂኒየር ስለሺ በቀለ ተቀባይነት የሌለው ጥያቄ መሆኑን በጊዜው ምላሽ ሰጥተዋል። የናይል ወንዝ ለኢትዮጵያ፤ ግብጽ እና ሱዳን የመኖር እና ያለመኖር ጥያቄ እንደሆነ በበርካታ ታዛቢዎች ይነገራል። ሦስቱ አገራት ተገናኝተው ፍትሐዊ አጠቃቀም ላይ ቁጭ ብለው መነጋገር ይጠበቅባቸዋል። ሱዳን በዚያ ሰሞን ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ያረጋገጠች ሲሆን ግብጽ ግን በእምቢተኝነቷ ገፍታበታለች።
ግብጽ ባለፉት 3 ዓመታት በኢትዮጵያ ከባዱ የክረምት ወቅት ሲጀምር እየጠበቀች ተፅዕኖ ማሳደር ይችላሉ በምትላቸው አገራትና ተቋማት በኩል በውሃ አጠቃቀሙ ዙሪያ አሳሪ ስምምት እንዲደረግ ግፊት ስታደርግ ቆይታለች። ግብጽና ሱዳን፣ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት አትችልም የሚል ተቃውሞና ማስፈራሪያቸውን ቢገፉበትም ኢትዮጵያ 3ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት አጠናቃለች። በግድቡ የተወዛገቡት ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን ተከታታይ ድርድርና ውይይት ሲያካሂዱ ቢቆዩም እስከአሁን ይህ ነው ከሚባል ስምምነት ላይ አልደረሱም።
ሱዳንና ግብፅ ሦስቱ አገራት በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ በሚያደርጉት ድርድር ከአፍሪካ ህብረት ውጪ ሌሎች አገራትና ዓለምአቀፋዊ ተቋማት እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ሲወተውቱ የቆዩ ሲሆን ኢትዮጵያ ግን በአደራዳሪነት ከአፍሪካ ህብረት ውጪ ማንንም እንደማትቀበል እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ግን ሊኖሩ እንደሚችሉ ስትገልጽ ቆይታለች በዚህም በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነትና በዓለምአቀፍ ማህበረሰብ ታዛቢነት ሲካሄድ የከረመው ድርድር ተጨባጭ ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችል ቀርቷል። ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ድርድር ሰበብ የዓባይን ወንዝ ተጠቃሚነቷን የሚገድብ ስምምነት እንደማትቀበል በተደጋጋሚ ገልጻለች ይለናል የአዲስ አድማስ ጋዜጣ።
ኢትዮጵያ በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም የመጀመሪያ የግድቡን ሙሌት በማካሄዷ ሳቢያም የትራምፕ አስተዳደር ለአገሪቱ ከሚሰጠው እርዳታ ላይ ቅነሳ እንደሚያደርግ በማስታወቅ አገሪቱ ከአሜሪካ ታገኝ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ማስቀረቱ አይዘነጋም። በዚያው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የተካሄደውን 2ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ተከትሎ ግብጽና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ለተከሰተው አለመግባባት በተመሳሳይ ጉዳይ ቀደም ሲል ባልታየ ሁኔታ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ አቅርበው፤ ምክር ቤቱ ሐምሌ 2013 ዓ.ም በጉዳዩ ላይ ለመምክር ተሰበስቦ ነበር። ኢትዮጵያም በህዳሴው ግድብ ጉዳይ የፀጥታው ምክር ቤት መወያየቱን እንደማትቀበለው በማስታወቅ ጉዳዩ ቀደም ሲል በተያዘበት የአፍሪካ ህብረት በኩል መቋጫ እንዲያገኝ ጠይቃለች። ይህ ጥያቄዋ ተቀባይነትን አግኝቶ ምክር ቤቱ ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት በኩል ሊታይ ይገባል የሚል ውሳኔ ማሳለፉ አይረሳም። ሆኖም ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው ግብጽ ይሄን ሀሳብ ለመቀበል ዝግጁ አልሆነችም።
እንደ ማጠቃለያ
ለናይል ወንዝ 86 በመቶ ውሃ የምትገብረው ኢትዮጵያ ፍትሐዊ በሆነ አግባብ ውሃውን የመጠቀም መብቷ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ይሁንና ግጭትንና አለመግባባትን ለመፍታት ሰባቱ የራስጌ የተፋሰስ አገራት የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አዳዲስ ውሎች ሊተኩ እንደሚገባ የሚጠይቀውና በ2002 ዓ.ም የተፈረመውን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት Cooperation Frame Work Agreement (CFA ) ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል። ስምምነቱን የተፈራረሙ አገራት ብሩንዲ፣ ኬንያ ፣ ኡጋንዳ ፣ ኢትዮጵያ ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ሲሆኑ የትብብር ማዕቀፉ የናይል ን ወንዝ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መጠቀምን የሚያረጋግጥና ዋስትና የሚሰጥ ቋሚ ኮሚሽን እንዲቋቋም የሚጠይቅም ነው። ዳሩ ግን ሱዳንና ግብፅ ይህን የትብብር ማዕቀፍ ለመፈረም ፈቃደኛ ባይሆኑም በ2007 ዓ.ም በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተፈረመውን የመርሆዎች መግለጫ (Declaration of Principles) ፈርመዋል።
በዚህ ስምምነት ሱዳንና ግብፅ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን የተቀበሉ ሲሆን ኢትዮጵያም ግድቡ በግርጌ ተፋሰስ አገራት ማለትም በግብፅና በሱዳን ሊያሳድረው የሚችል ተፅዕኖ ወይም ጉዳት ካለ ጥናት እንዲደረግ ተስማምታለች። በዚህ ስምምነት ላይ ተከታታይ ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን ተስፋም ተጥሎባቸው ነበር። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትብብር አብነት የሚሆንና የራስጌ አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ስለሆነ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል። ግብፅም በግድቡ ውሃ አሞላል ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ጀምራ ወደነበረው ድርድር ብትመለስ አገራቱን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል መግባባት መድረስ ይችላል።
አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ፈጣሪ ይጠብቅ !
ሻሎም !
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም