በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ስር ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል የተመሰረተው እኤአ በ2008 ነበር። በቤጂንግ ኦሊምፒክ ሁለቱ የምንጊዜም የረጅም ርቀት ድንቅ አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማስመዝገባቸውን ተከትሎ እነሱ በፈለቁበት አካባቢ ይበልጥ ተተኪዎችን ለማፍራት የወጣቶች ማሰልጠኛ ማዕከሉ በጥሩነሽ ዲባባ ስም ተቋቁማል።
ማሰልጠኛ ማዕከሉ በወቅቱ ከ200 በላይ ሰልጣኞችን በመመልመል ወደ ስራ የገባ ሲሆን፤ ለአራት ዓመት ሳይንሳዊና ዘመናዊ ስልጠናዎችን በመስጠት በተለያዩ ስፖርቶች ብቁ አድርጎ ያስመርቃል። ማዕከሉ ስልጠናውን መስጠት ከጀመረበት ወቅት አንስቶም ለአስራ አንድና አስራ ሁለት ዞሮች ሰልጣኞችን ማስመረቅ ችሏል።
በአሁኑ ወቅት ማሰልጠኛ ማዕከሉ 179 ወንድና 131 ሴት በድምሩ ለ310 ሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል። ከነዚህ ሰልጣኞች መካከል 101 አዲስና 270 ነባር ሰልጣኞችን በመያዝ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ዓመት ስልጠናዎችን ይሰጣል።
የማሰልጠኛ ማዕከሉ የትምህርት ስልጠናና ውድድር ምክትል ዳይሬክተር ተወካይ አቶ መሳይ ጉልላት፣ ማዕከሉ አገር አቀፍ እንደመሆኑ የምልመላ ሂደቱም ሁሉን አቀፍና ችሎታን መሰረት ያደረገ መሆኑን ይናገራሉ። በአገሪቱ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ምልመላ በማካሄድም ነው ለወጣቶች ስልጠናው የሚሰጠው። ምልመላው የሰላም ስጋት በነበረባቸው እንደ ትግራይ ክልል ካሉት አከባቢዎች በስተቀር በሁሉም አካባዎች ሲደረግ ቆይታል። ለዚህም ማዕከሉ ‹‹ችሎታን(ታለንትን) መፈልግ እንጂ በራሱ ይምጣ›› የሚል እምነት ስለሌለው በተለያየ አካባቢ እየተጋዘ እንደሚመለምል አቶ መሳይ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በአስር የስፖርት አይነቶች ስልጠና ይሰጣል። ጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል ደግሞ በሶስት የስፖርት ዘርፎች ላይ ብቻ ትኩረቱን አድርጎ ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን አቶ መሳይ ይናገራሉ። እነዚህም አትሌቲክስ፣ እግር ኳስና ፓራሊምፒክ ናቸው።
እንደ አቶ መሳይ ገለፃ፣ ማሰልጣኛ ማዕከሉ ስልጠና መስጠት ከጀመረበት ወቅት አንስቶ በርካታ አትሌቶችን ለክለቦችና ለአገር ማበርከት ችላል። በዚህም ከማዕከሉ ኢትዮጵያን በአለም መድረኮች በመወክል ሜዳሊያ ማስመዝገብ የቻሉት በርካታ አትሌቶች ማፍራት ችላል። ከነዚህም መካከል ለሜቻ ግርማ አንዱ ሲሆን አትሌቱ በሁለት የዓለም ቻምፒዮናና በአንድ ኦሊምፒክ የ3 ሺ መሰናክል ውድድር በታሪክ ሶስት የብር ሜዳለያን ማስመዝገብ ችሏል። ሌሎች የማሰልጠኛው ውጤቶች ጌትነት ዋለ፣ሳሙኤል ፍሬው፣ ሳሙኤል ዱጉናና አዲሱ ይሁኔ በዋናነት የሚጠቀሱ ውጤታማ አትሌቶች ናቸው።
ይህ ማሰልጠኛ ማዕከል ከሌሎች የሚለየውም አንድ ነገር አለ። ይህም በርካታ አትሌቶችን ባልተለመዱ የአትሌቲክስ ዘርፎች በማሰልጠን ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያደርገው ጥረት ነው። እነዚህ የአትሌቲክስ ዘርፎች በኢትዮጵያ ብዙም ትኩረት ያልተሰጣቸው የአጭር ርቀትና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ሲሆኑ፣ በነዚሁ ውድድሮች ውጤታማ አትሌቶችን ለማፍራት ከመሰረቱ ጀምሮ ስልጠና በመስጠት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴም እየታየ እንደሚገኝ አቶ መሳይ ጠቁመዋል። ለዚህም በቅርቡ በተካሄደው 11ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና የማዕከሉ ተሳትፎ አበረታች ውጤትና ጥሩ እንቅስቃሴን በማድረግ በወንዶች አንደኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ አቶ መሳይ አንዱ ምሳሌ እንደሚሆን ያብራራሉ። በዚህም ተተኪ ስፖርተኞችን በትክክለኛ እድሜያቸው ተሳትፈው ተስፋ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚቻል ማዕከሉ ማሳየቱን ያነሳሉ።
ማዕከሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ለሚያደርጋቸው አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ውድድሮች ከመቶ የሚበልጡ አትሌቶችን ማስመረጥ መቻሉን እንደ አንድ ስኬት የጠቆሙት አቶ መሳይ፣ ሰልጣኞችን በተለያየ እድሜ እርከን መልምሎ ወደ ስልጠና የሚያስገባ ሲሆን በዚህም እድሜያቸው አስራ ሰባትና ከዚያ በታች የሆኑ አትሌቶችን ለአራት ዓመታት ተገቢውን ስልጠና ከሰጠ በኋላ እንደሚያስመርቅ ያብራራሉ።
ማዕከሉ በተለይም በአጭር ርቀትና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ላይ በአህጉር ደረጃ ያለውን ሰፊ ርቀት ለማጥበብ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። በዚህም መሰረት በአህጉር አቀፍ ከሃያ ዓመት በታች ውድድር ላይ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ጭምር ማጠናቀቅ የቻሉ አትሌቶችን ማፍራቱ እንደ ጥሩ ጅምር ሊጠቀስ እንደሚችል ያምናሉ።
ማዕከሉ ለዚህ አበረታች ውጤት የበቃበትን ምክንያት አቶ መሳይ ሲያስረዱ፣ በነዚህ ውስን ውድድሮች ላይ ትኩረት አድርጎ ከመስራት ባለፈ እምቅ አቅም ባለባቸው ስፍራዎች ላይ በትኩረት በመሰራቱ እንደሆነ አስረድቷል።
በተረፈ ቴክኒክ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት በመቻሉ ውጤታማ መሆን እንደተቻለ ያስረዱ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በሜዳ ተግባርም ይሁን አጭር ርቀት ከሌሎች አገራት አንፃር ያለውን ክፍተት ለማጥበብ በደንብ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። “ይህንን ስናደርግ ስራው ድካም ይኖረዋል። ግን ትኩረት በመስጠት መሰራት ስላለበት ያንን እናደርጋለን” ሲሉም አክለዋል።
“እኛ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንሰራለን፣ ነገር ግን ከኛ ጋር የዛሬ ስድስትና ሰባት ዓመት የወጡ ልጆች ክለቦች መልሰው ሲያሳትፏቸው አይተናል፣ ይሄ ነገር ለማንም የማይጠቅምና ወጣቱንና ታዳጊውን ወደላይ እንዲመጣ አያደርግም›› ያሉት አቶ መሳይ የማሰልጠኛ ማዕከሉ አንዱ ፈተና አትሌቶቹ በተለያዩ ውድድሮች ከእድሜ ከሚበልጣቸው ስፖርተኞች ጋር ለመፎካከር መገደዳቸው መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህ ረገድ በቅርቡ በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና ፌዴሬሽኑ በእድሜ ተገቢነት ዙሪያ የወሰደው እርምጃ አበረታች እንደሆነና መቀጠል እንደሚገባው ገልፀዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም