የኢትዮጵያ የሚትዎሮሎጂ ዕይታዎች በፈረንጆቹ አቆጣጠር፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ ሚሲዮናዊያን እንደተጀመረ ይነገራል:: ይህን እንደመነሻ እርሾ በመጠቀም ሌሎች አማራጮችን መመልከት ተጀመረ:: የተወሰኑ ማዕከላትም እስከ 1890ዎቹ ድረስ መረጃ ነበራቸው:: በ1951 ግን የሚትዎሮሎጂ አገልግሎት በሲቪል አቬዬሽን ባለስልጣን ውስጥ ለሙከራ ተጀመረ:: በሂደትም ብዙ መረጃዎችን እና ልምዶችን ማግኘት ተቻለ::
እውቀት እና ግንዛቤው እያደገ በመምጣቱ በ1971 በተጀመረበት ሲቪል አቬዬሽን ሥር እንዲተዳደር ሆኖ ተቋቋመ:: በ1980 ብሔራዊ ሚትዎሮሎጂ ኤጀንሲ በሚል ሥያሜ ራሱን ችሎ በአዋጅ 201 መሰረት ተቋም ሆነ:: ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን ያማከለ መረጃ በስፋት ማሰራጨት ጀመረ:: በ2021 ደግሞ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በሚል በአዋጅ 1263/2021 ተቋቋመ::
ዘመናትን በመሻገር ዕለታዊውን የአየር ሁኔታ ከመተንበይ አንሥቶ እስከ ረጅም ጊዜ የአየር ጠባይ ትንበያ ድረስ በመተንተንና በመገምገም፤ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉትን ተጽዕኖዎች በመከታተልና አስቀድሞ በመተንበይ የደንበኞችንና የባለ ድርሻ አካላትን ፍላጎት ለማርካት በትጋት በመሥራት ላይ የሚገኝ ተቋም ነው – የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት።
ኢትዮጵያ በዓመት ውስጥ በተጽዕኗቸው የተለዩትን ሦስት ወቅቶች በሚያስተናግድ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የአየር ጠባይ ውስጥ መሆኗ ይታወቃል:: እነዚህ ወቅቶች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባላቸው አንድምታ የተለዩ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የተለያዩ ተጽዕኖዎች ያሏቸው በመሆኑ የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንሳዊ ዘዴዎችን በመከተልና የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችና ግብዓቶችን በመጠቀም በተለያዩ የጊዜ ቀመር የተለዩ የአየር ሁኔታና ጠባይ ትንበያዎችን በማዘጋጀት፤ ከተጠቃሚዎች ጋር በመመካከር የመገናኛ ብዙኃን እና ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም ለተጠቃሚዎች የሚያሰራጭ መሆኑም ይታወቃል::
በዛሬው ዕትማችን የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለዓመታት ያለፈባቸውን ተግባራትና እያስገኛቸው የሚገኙ ውጤቶችን፤ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ያለውን ተናብቦ የመስራት ሂደት፤ በቴክኖሎጂ የደረሰበትን ደረጃ እና በቀጣይ ሊያሳካቸው የሚያስባቸውን እቅዶች አንስተን ከዋና ዳይሬክተሩ አቶ ፈጠነ ተሾመ ጋር ቆይታ አድርገናል::
አዲስ ዘመን፡- በጋውን አስመልክቶ የሰጣችሁት ትንቢያ እና ያለፉት ስድስት ወራት ሂደቶች ምን ያክል ተጣጥመዋል?
አቶ ፈጠነ፡- ኢንስቲትዩታችን በዘንድሮው የበጋ ወቅት ትንበያው ሊፈጠር የሚችለውን የዓየር ሁኔታ በጊዜና በቦታ ያለውን ስርጭትና ተጽዕኖን በተመለከተ በመስከረም 2015 ዓ.ም የወቅት ትንበያ ሰጥቶ ነበር። በተጨማሪም በየጊዜው የወቅት አጋማሽ፣ ወርኃዊና የአሥር ቀናትን፣ የሦስት ቀናትንና ዕለታዊ የአየር ሁኔታና ጠባይ ትንበያ መስጠቱ ይታወቃል:: አሁን ወደ ኋላ ተመልሰን ኢንስቲትዩቱ የሰጠውን የበጋ ትንበያና በተጨባጭ የነበረውን የአየር ሁኔታ ስንገመግም ከሞላ ጎደል የተጣጣሙ ሆነው አግኝተናቸዋል። ይህም ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በተለይም ለግብርናው ዘርፍ የበኩላችንን አስተዋጽዖ እንድናደርግ፤ ተጠቃሚዎችና ባለ ድርሻ አካላትም መረጃዎቻችንን በይበልጥ እንዲጠቀሙ አስችሏል:: በቀጣይም የምንሰጣቸው ትንቢያዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- በዚህ የበልግ ወቅት የአየር ትንቢያ ምን ያመለክታል?
አቶ ፈጠነ፡- የበልግ 2015 ዓ.ም ትንበያ እንደሚያሳየው መጪው በልግ አሁን በትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት እና የህንድ ውቅያኖስ መደበኛ የባህር ወለል ሙቀት መጠን መደበኛ ሆኖ እንደሚቆይ የሚያመለክት በመሆኑ የወቅቱ ዝናብ አጀማመር ሊዘገይ እንደሚችልና በአወጣጥ ረገድ ግን ጊዜውን የጠበቀ እንደሚሆን ይጠበቃል::
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢንስቲትዩታችን ከሚሰጠው አጠቃላይ የበልግ ትንበያ በተጨማሪ በመጪው በልግ በሀገራችን የተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ የሚችሉትን የአየር ሁኔታ ገጽታዎችን አስቀድሞ በመተንበይ የቅድመ – ማስጠንቀቂያ እና የትንበያ መግለጫዎች ይሰጣል:: በመሆኑም ሕብረተሰቡ ይህንኑ መረጃ እንዲጠቀምና የሚሰጡትን የቅድመ-ማስጠንቀቂያ መግለጫዎችን በቅርበት መከታተል አለበት::
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ የምትሰጡት ትንቢያ እና እውነታው የተራራቀ ነው የሚል ትችት ይቀርባል:: በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ፈጠነ፡- ትንቢያዎች በአንድ ጊዜ ብቻ ተሰጥተው የሚጠናቀቁ አይደሉም:: በየጊዜው መረጃዎች የሚታዩና የሚተነተኑ ናቸው:: የአየር ጸባይ በባህሪው የሚቀያየርና ትንተናዎችን የሚፈልግ ነው:: ይህ በአንድ ጊዜ ስራ ብቻ ተሰርቶ የሚቀመጥና በአንድ ጊዜ በቂ አይደለም::
ስለዚህ የአየር ትንበያ መረጃዎች ከእውነታው ጋር የተራራቁ ናቸው የሚለው አግባብ አይደለም:: የምንሰጣቸው ትንበያዎች የሚጠበቀውን ውጤት እየሰጡ ነው:: ለአብነት እኛ በዘንድሮው የበጋ ወቅት ትንበያው ሊፈጠር የሚችለውን የዓየር ሁኔታ፣ በጊዜና በቦታ ያለውን ስርጭትና ተጽዕኖን በተመለከተ በመስከረም ወር (2015 ዓ.ም) የወቅት ትንበያ ሰጥተን ነበር። አሁን ላይ ሁኔታውን ስንገመግመው ያገኘነው ውጤት ትንቢያችንና መሬት ላይ ያለው እውነታ የተጣጣሙ ናቸው:: ቀደም ሲል ስንሰጣቸው የነበሩት መረጃዎችም በተመሳሳይ የተጣጣሙ ነበሩ:: በየጊዜው አዳዲስ ቴክሎጂዎችን እየተጠቀምን በመሆኑ የመረጃው ጥራት በዚያው ልክ እያደገ መጥቷል::
አዲስ ዘመን፡- በምትሰጡት የአየር ሁኔታ ትንበያ የትኞቹ ዘርፎች የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ?
አቶ ፈጠነ፡– እኛ በምንሰጠው መረጃ የተለያዩ፣ በርካታ ዘርፎች ተጠቃሚ ናቸው:: በግብርናው ዘርፍ ብንሄድ ከሚኒስቴሩ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አካላት እየሰሩ ያሉት በትንቢያው መሠረት ነው:: ከአውሮፕላን በረራ ጋር በተያያዘ ሰፋፊ መረጃዎችን እንሰጣለን:: ይህም በጣም በስኬታማ መንገድ የሚነሳ ነው:: በጤና ዘርፍም የሚሰጠው ፋይዳ እጅግ ሰፊ ነው:: ከውሃ ሃብት መንከባከብም ሆነ መጠቀም ጋርም በእጅጉ የሚጠቅም መረጃ የሚገኘው ከዚሁ ትንበያ በመነሳት ነው:: ጎርፍ እና መሰል አደጋዎችን በመከላከል ረገድም የምንሰጣቸው ትንበያዎች ፋይዳቸው የጎላ ነው::
በአየር ጸባይ ትንበያ የማይጠቀም አካል የለም:: ለዚህም በየጊዜው መረጃዎችን ተደራሽ እያደረግን ነው:: ይህ ትንቢያ አንዱን ለብቻ ነጥሎ የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ አይደለም:: አንዱ ከሌላው ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ሁሉም ተጠቃሚ ነው:: እኛም የምንሰጠው መረጃ ሁሉም ተቋማትና አካባቢዎች እንደየነባራዊ ሁኔታዎች እንዲጠቀሙበት ነው::
አዲስ ዘመን፡- የአየር ትንበያን ከመተንተንና ከማወቅ አኳያ ዘመናዊ ራዳሮች ያስፈልጋሉ:: በዚህ ረገድ ምን ተሠርቷል?
አቶ ፈጠነ:- በመላ ሀገሪቱ ያለውን የአየር ሁኔታ ለመከታተል የሚረዱ 12 ዘመናዊ ራዳሮች የሚያስፈልጉ መሆኑ በጥናት ተለይቷል:: በሚቀጥሉት 10 ዓመታት የሚከናወኑ፣ የሚትዎሮሎጂ ምልከታና ትንቢያን የሚሰጡ ራዳሮች በመተከል ላይ ናቸው:: እነዚህ ትንበያዎችን ከማጠናከር አንፃር ለግብርና፣ ውሃ፣ ጤና እና ሌሎች ዘርፎችንም ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች እየተከወኑ ናቸው:: በእነዚህ ዓመታት ውስጥም የአየር ሁኔታን ለመከታተል የሚረዱ ራዳሮችን ከአንድ ወደ ስምንት ለማሳደግ መንግስት በትኩረት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ ከተለያዩ ለጋሽ ሀገራት ጋርም ስምምነት ተደርጎ ሦስት የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር ለመትከል በሂደት ላይ ነን::
ቀደም ሲል በባህር ዳር፣ ሻውራ ከተተከለው ራዳር በተጨማሪ የማዕከላዊ ኢትዮጵያን የአየር ሁኔታ ለመከታተል በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ እነዋሪ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ደግሞ አላባ ቁልቶ፤ እንዲሁም በምዕራብ ኢትዮጵያ ኢሉ አባቦራ፣ በኮ የሚባል ተራራ ላይ ተከላ የማከናወን ተግባራት በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ ናቸው:: እነዚህ ራዳሮች እስከ 250 ኪሎ ሜትር ድረስ መረጃ ይሰበስባሉ:: እነዚህ መረጃዎች ከተሰበሰቡና ከተተነተኑ በኋላ የሚኖራቸው ትልቅ ፋይዳ ከፍተኛ ሲሆን፤ ራዳሮቹ ሲተከሉ የኢትዮጵያን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ መሠረት ባደረገ መልኩ መሆኑንም ማወቅ ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- ራዳሮቹ መረጃ ለመሰብሰብ ብቻ የሚፈይዱ ናቸው?
አቶ ፈጠነ፡– እነዚህ ራዳሮች ወደ ሀገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት “ምን ጥቅም ይሰጣሉ?” የሚለውን
በባለሙያዎች አስጠንተናል:: ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ራዳሮች ደመና ለማበልፀግ በሚደረገው ጥረት ትልቅ ፋይዳ ይኖራቸዋል:: አስር የደመና ዓይነቶች አሉ:: እነዚህ ራዳሮች ደግሞ በተለይም ዝናብ ሰጪ የሆነውን ቁልል ደመና በመለየት ትልቅ አገልግሎት የሚሰጡ ይሆናል:: ይህም ኢትዮጵያን ደመናን በማበልጸግ እና አስፈላጊውን የኬሚካል ርጭት ለማድረግ ዝናብ ለማዝነብ ያስችላታል::
ደመናን ለማበልፀግ የተሞከረው ባህር ዳር ሻውራ ላይ ብቻ በነበረው ራዳር ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን በእነዋሪ፣ ምዕራብ ወለጋ እና ደቡብ ኢትዮጵያ የሚተከሉት ራዳሮች ለዝናብ ማበልጸግ እና አየር ሁኔታን ለመተንተንና ለመከታተል ትልቅ ፋይዳ ይኖራቸዋል:: እነዚህ አራት ራዳሮችም እያንዳንዳቸው እስከ 100 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው ናቸው።
እነዚህ ራዳሮች ዝናብ ሰጪ ዳመናን በተመለከቱ ጊዜ 20 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አስፈላጊውን ሂደት (ፕሮሰስ) በማለፍ ደመና ማበልጸግ የሚቻልበትን ሂደት ያከናውናሉ:: ስራው፣ የመንግስት ትኩረት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከሌሎች አካላትም ሃብት በማፈላለግ የተከናወነ ነው:: በመሰረቱ መጀመሪያ እነዚህ ራዳሮች ሲተከሉ ዝናብን ማበልፀግ ታሳቢ በማድረግ አልነበረም:: ዋና ዓላማው የአየር ሁኔታ ማወቅን የተመለከተ ነበር:: ነገር ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አነሳሽነትና ድጋፍ “ደመና ማበልፀግ” የሚለውን ሐሳብ በሰፊው አካተን ወደ ተግባር ገባን፤ አሁን እየሰራንበት እንገኛለን::
አዲስ ዘመን፡- ቴክኖሎጂን መጠቀም እንዳለ ሆኖ የሚስጥራዊነታቸው ጉዳይ እንዴት ይታያል?
አቶ ፈጠነ፡- ምስጢራዊነታቸውን በተመለከተ ሁሉም ቴክኖሎጂዎች የየራሳቸው ምስጢር ቁጥር አላቸው:: በዚህ ረገድ እዚህ ሲመጡ የሚስተካከሉ ነገሮች አይኖሩም ማለት አይደለም:: የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም ይቻላል:: ነገር ግን መታወቅ ያለበት ጉዳይ የሳተላይት መረጃ ብዙም የተደበቀ ነገር የሌለው መሆኑ ነው:: እኛ ለዚህ ጉዳይ የምንጠቀመው ከፊላንድ የተገዛ ነው:: በዓለም ላይም በዋናነት አቅራቢዎች እነሱ ናቸው::
እኛም በቴክኖሎጂ ላይ ያለንን ግንዛቤ አሳድገን ለሀገር ጥቅም ብቻ እንዲውል ማድረግ ይጠበቅብናል:: ግን ምንም እንከን የለውም ማለት አይደለም:: የሚትዎሮሎጂ መረጃን በተመለከተ ደግሞ ኢትዮጵያ ያላትን ሃብትና በዓመት ምን ያክል ዝናብ ታገኛለች? ምን ያጋጥማታል? በሚሉትና ሌሎችም ላይ መረጃ ለመሰብሰብ ብዙ የሚደበቅ ነገር የለም::
ኢትዮጵያ የዓለም ሚትዎሮሎጂ ድርጅት አባል ነች:: በአባልነቷ የተለያዩ መረጃዎችን የሚሰጡ ሳተላይቶች ታገኛለች:: ሌሎች የዓለም ሚትዎሮሎጂ ድርጅት ተቋማትም የሚሰጡትን መረጃ እንጠቀማለን:: የሚትዎሮሎጂ መረጃ በአንድ ሀገር ውስጥ ብቻ የተገደበ፤ የተወሰነም አይደለም:: አንድ ሀገር የሚከሰተው ክስተት ለሌላው ሀገር መረጃ በመሆኑ ከዚህ አንጸር ዓለም አቀፍ መረጃ ልውውጥ ያስፈልጋል:: በመሆኑም ዝግ ያልሆነ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት አለ:: በመሆኑም በሚትዎሮሎጂ ላይ ያሉ መረጃዎች ያን ያክል ምስጢራዊነታቸው መጠበቁ ጠቃሚ ላይሆን ይችላል::
አዲስ ዘመን፡- ከሀገሪቱ ቆዳ ስፋት አኳያ አሁን ያለው የሚትዎሮሎጂ መረጃ ሽፋን በቂ ነው?
አቶ ፈጠነ፡- ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ ሀገር በመሆኗ የሚትዎሮሎጂ መረጃ ሽፋንን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው:: የሀገሪቱን ሚትዎሮሎጂ ሽፋን ለማሳደግ መረጃ የሚሰበሰብባቸውን ጣቢያዎችን የማደራጀት አጠቃላይ የጣቢያ ኔትወርክ በማሳደግ ረገድም በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ:: በአሁኑ ወቅት የሚትዎሮሎጂ መረጃ የሚሰበሰበው በሰው ኃይል ነው:: ሌላኛው በአውቶማቲክ የሚሰበሰብ ነው:: ከአየር፣ ከአውሮፕላን ላይም መረጃ ይሰበሰባል:: በተጨማሪም የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር ጭምር የሚትዎሮሎጂ መረጃ እየሰበሰበ ነው:: በዚህ ደረጃ ስንት ያስፈልጋናል የሚለውን ለይተን አስቀምጠናል:: ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚትዎሮሎጂ መረጃ በመሰብሰብ ረገድ ሰፊ ሥራ መሠራት አለበት:: ለዚህም 12 ጣቢያዎች ያስፈልጋሉ:: እነዚህ ጣቢያዎችም በተሟላ ደረጃ ወደ ሥራ ሲገቡ ሽፋኑም ሆነ ጥራቱ በዚያው ልክ ያድጋል::
አዲስ ዘመን፡- በአደጉት ሀገራት የበረራ ሥራ በቀጥታ የሚትዎሮሎጂ መረጃ እየታገዘ ነው:: ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ምን ደረጃ ላይ ትገኛለች?
አቶ ፈጠነ፡- ከአየር ሁኔታ እና ጸባይ ጋር በተያያዘ ከትራንስፖርት ዘርፍ፣ በተለይም በምድር፣ በባህር ብሎም በአየር ላይ የሚንቀሳቀሱ የሚትዎሮሎጂ መረጃን በሰፊው ይጠቀማሉ:: ከእኛ አንፃር የምንሰጠው የአቬዬሽን መረጃዎችን ነው :: ከዚህ አኳያ አውሮፕላን ሲነሳ መነሻ ትንበያ እንሰጣለን:: በዚህ ምክረ ሐሳብ ከመንደርደሪያ ይነሳሉ:: ሁለተኛው በበረራ ውስጥ ያለው መረጃም ይሰጣል:: ሦስተኛ በረራ መዳረሻ ላይ መረጃዎች ይሰጣሉ:: ስለዚህ የአየር ጸባይ ጥሩ ካልሆነ በረራ ላይ ማስተካከያ ይደረጋል:: በበረራ ውስጥ የሚኖረው ደግሞ በሲቭል አቬዬሽን በኩል በአየር መቆጣጠሪያ መረጃ ይሰጣል::
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ምን ያክል ተደራሽ ሆነናል?
አቶ ፈጠነ፡- የተለያዩ ጣቢያዎች አሉን:: መረጃ በመሰብሰብ ረገድ አንደኛ፤ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ተብለው የተከፈሉ አሉ:: በሰው መረጃ የሚሰበሰብባቸው አሉ:: ይህ በመላ ሀገሪቱ 1ሺ 300 ጣቢያዎች አሉን:: አውቶማቲክ የአየር ሁኔታ ጣቢዎችም አሉን:: ይህ በ15 ደቂቃ ልዩነት ከየትኛውም የሀገሪቱ ጫፍ የአየር ሁኔታን ወደ ሰርቨሩ ይልክልናል:: ይህም በመላ ሀገሪቱ 300 ጣቢያዎች አሉን:: ከዚህ በተጨማሪ የሳተላይት መቀበያ ማዕከላት አለን:: በተለይም ለዕጽዋት ልምላሜ፣ ለግብርናው ዘርፍ እና ለሌላ ግልጋሎትም ይውላሉ:: እነዚህንም በአዲስ አበባ ሁለት በተጨማሪ በ11 አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎቻችን ተክለን እየተጠቀምን ነው::
ብክለትን የሚከታተሉ ሳተላይቶችም እየተተከሉ ነው:: በአሁኑ ወቅት የአየር ብክለት መከታተያ ጣቢያዎችን በአዲስ አበባ፣ አዳማ እና ሃዋሳ፤ የኢንዱስትሪ መንደሮች እና የተሽከርካሪ ፍሰት በሚበዛባቸው አካባቢዎች ተክለን እየተጠቀምን ነው:: በቀጣይም ከራዳሩ ጋር እየተሠራ ባለው ፕሮጀክትም በአዲስ አበባ ውስጥ 10 የአየር ብክለት መከታተያ ጣቢያ ለመትከል ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው::
በአጠቃላይ ዘመናዊ የሆኑ ቴክሎጂዎችን በመጠቀም ሀገሪቱን የሚትዎሮሎጂ መረጃ ሽፋን በማሳደግ እና በቴክሎጂ በማዘመን ላይ እንገኛለን:: የሳተላይትና የጣቢያዎችን መረጃ በማዳቀል በአራት ኪሎ ሜትር ልዩነት መረጃ ለመስጠት የሚያስችል አቅም መገንባት ተችሏል:: እነዚህ መረጃዎችን በአግባቡ ከተጠቀምን ሀገሪቱ የሚትዎሮሎጂ መረጃ ሽፋንም ሆነ ተደራሽነት እያደገ የሚሄድ ይሆናል:: ይህ ዘርፍ እየተጠናከረ ሲሄድ ሌሎች መረጃ የሚፈልጉና በዋናነት በእኛ መረጃ የሚጠቀሙ ዘርፎችም በዚያው ደረጃ ያድጋሉ የሚል እምነት አለን::
አዲስ ዘመን፡- የሚትዎሮሎጂ መረጃ ሽፋንን በጥራትና በብቃት ከማሳደግ አኳያ የመሠረተ ልማት ሥራው ምን ይመስላል?
አቶ ፈጠነ፡- የሚትዎሮሎጂ መረጃን ሽፋን ለማሳደግ መሠረተ ልማቱን ማሳደግ ይገባል:: ይህን ከመስራት አኳያ ደግሞ መንግስት ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል:: በተለይም ደግሞ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ መታጠቅ ተገቢ መሆኑ ታምኖበታል:: ከዚህ አኳያ የተለያዩ አማራጮችን በመመለከት ላይ ነን:: ከዚህም በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም ለመገንባት በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው::
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ እና ቻይና በመቀጠልም የሚትዎሮሎጂ መሰረተ ልማትን ሙሉ ለሙሉ አንድ ላይ የያዘ ህንፃ ግንባታ በመገንባት ላይ ናት:: ይህ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ያሉት ህንጻ በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እየተከናወነ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም የግንባታው ሂደት 73 ከመቶ ደርሷል:: በቴክኖሎጂ ረገድም ዘመናዊ የሆኑና ዘመኑ የደረሰበትን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው::
አዲስ ዘመን፡- ከመሠረተ ልማት ባሻገር መሰረተ ልማቱን መምራትና መቆጣጠር የሚችል የሰው ኃይል ማፍራት ተችሏል?
አቶ ፈጠነ፡- የሚትዎሮሎጂ መረጃ ሽፋን እና ትንቢያን ለማሳደግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መታጠቅ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚያው መጠን ቴክሎጂውን የሚገነዘብ የሰው ኃይል ማፍራት ይገባል:: እኛም ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት በርካታ ሥራዎችን በመስራት ላይ እንገኛለን:: ተቋሙን ለማዘመንና ሥራውን በፍጥነት ለማከናወን ያግዝ ዘንድም ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል ግንባታ ጀምረናል:: ለአብነት በአሁኑ ወቅት 64 ተማሪዎች የማስተርስ፤ አምስት ደግሞ የዶክተሬት ዲግሪያቸውን በመከታተል ላይ ናቸው:: የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው በርካታ ባለሙያዎች በተቋሙ ውስጥ ይገኛሉ:: በየእርከኑና በየደረጃው የሰው ኃይል ለማብቃት በትኩረት እየተሰራ ነው::
መንግስት የኢትዮጵያን የሚትዎሮሎጂ አቅም ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በሰፊው እየተንቀሳቀሰ ነው:: በመሆኑም ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ እና ተቋም ስንገነባ ጎን ለጎንም የሰለጠነ የሰው ኃይል እያፈራን ነው:: በአስር ዓመት ስተራቴጂክ እቅዳችን እንደ ተቋም የተያዘው አቋም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም መረጃዎችን በስፋት ለተጠቃዎች ማድረስ ነው:: ይህን ለማከናወን ደግሞ በዚያው ልክ የዘመነ የሰው ኃይል አስፈላጊ በመሆኑ በዚህ ላይ በስፋት እንሠራበታለን:: ይህ ሥራችን እየተጠናከረ ሲሄድ የሚፈለገውን ውጤት እንደምናመጣ እርግጠኞች ነን::
አዲስ ዘመን፡- ለተቋሙ ሥራ እንቅፋት የሆኑበት ችግሮች አሉ?
አቶ ፈጠነ፡- ከመጀመሪያው የነበሩብን ችግሮች እነዚህን መረጃዎችን ለማዘመን የሚያስችል አቅም መፍጠር አለመቻል ነው:: ይህ ከበጀት ጋር ይያያዛል:: ምቹ የሥራ አካባቢ አለመኖርም አንዱ ነበር:: ሰርቨሮች ሲመጡ ምቹ ማስቀመጫ ሊጠፋ ይችላል:: በቂ የኤሌክትሪክ ኃይልም አልነበረም::
በአሁኑ ወቅት እየተሟሉ ነው:: መንግስት ትኩረት በመስጠቱ ችግሮቹን በማቃለል ላይ ነን:: መሳሪያዎችን ከማዘመን አኳያ አፍሪካ ውስጥ አብዛኞቹ ሀገራት የሌላቸውን ቴክኖሎጂ እና አቅም እኛ እየገነባን ነው:: በሰው ኃይል ግንባታም በሰፊው እየሰራንበት ሲሆን ትልቅ ለውጥ እየተመዘገበ ነው:: የማዕከላትም አቅም እያደገ ነው:: ለሀገሪቱ የሚመጥን መረጃ ለመስጠት በስፋት እየሰራን ነው:: ከጉድለት ባለፈ በርካታ ጠንካራ ጎኖች ስላሉን በአሁኑ ወቅት ከመንግስት አቅም በላይ የሆነ ችግር የለም። የመንግስት ድጋፍም ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ የተጠናከረ ነው:: ችግሮች አሉ ብለን ብናስብ እንኳን በተቋሙ አቅም በፍጥነት መፍትሄ የሚሰጣቸው በመሆናቸው በዚህ ደረጃ ጎልተው የሚነገሩ አይደሉም::
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እያመሰገንኩ ተጨማሪ ሃሳብ፣ መልእክት ካለዎት ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
አቶ ፈጠነ፡– በጣም አመሠግናለሁ:: የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዘመናዊ ቴክሎጂዎችን በመጠቀም በመላ ሀገሪቱ ተደራሽ የሆነ የሚትዎሮሎጂ መረጃ በመስጠት ላይ ይገኛል:: ኢንስቲትዩታችን ዛሬ ከሚሰጠው አጠቃላይ የበልግ ትንበያ በተጨማሪ በመጪው በልግ መካከል በሀገራችን የተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ የሚችሉትን የአየር ሁኔታ ገፅታዎችን አስቀድሞ በመተንበይ የቅድመ-ማስጠንቀቂያ እና የትንበያ መግለጫዎችን የሚሰጥ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ይህንኑ መረጃ ቢጠቀም የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ::
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም